Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉበት ሳይታለም የተፈታው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉበት ሳይታለም የተፈታው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

ቀን:

አምላክ የሞት መልአክ የሆነውን አዛኤል ፕሬዚዳንቱን ይዘህልኝ ና ብሎ ወደ ግብፅ ይልከዋል፡፡ መልአኩም ግብፅ ሲደርስ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ታስሮና ተደብድቦ፣ ተሰቃይቶ ይለቀቅና ወደ አምላኩ ይመለሳል፡፡ ይኼንን ያየው አምላክ ‹እኔ እንደላኩህ አልነገርካቸውም አይደል?› ሲል ይጠይቀዋል፡፡

ግብፃውያን ይኼንን ቀልድ የቀለዱት በሆስኒ ሙባረክ የ30 ዓመታት የሥልጣን ዘመናት ነበር፡፡ በፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ወቅት ግን ይኼንን ዓይነት ቀልድ ለመቀለድ ድፍረት ያለው ማንም የለም፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 የካይሮን ታህሪር አደባባይ ባጥለቀለቀው የዓረብ ፀደይ አብዮት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ሲወገዱ፣ ግብፃውያን ከ30 ዓመታት በኋላ የመጀመርያውን ፍትሐዊ ምርጫ እ.ኤ.አ. በ2012 አድርገው የሙስሊም ወንድማማቾችን ወክለው መሐመድ ሙርሲ ሥልጣኑን ጨበጡ፡፡

የሙርሲን ወደ አምባገነናዊ መንግሥትነት የሚደረግ ግስጋሴ ሥጋት ላይ የጣላቸው የጦር ኃይሉ ኃላፊዎችና የግብፅ ሕዝብ እ.ኤ.አ. በ2013 ባደረጉት መፈንቅለ መንግሥት፣ መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን አስወግደው የውትድርና ጄኔራልነታቸውን ትተው የሲቪል ሥልጣን ለመጨበጥ የፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው እ.ኤ.አ. በ2014 ለቀረቡት አብዱልፈታህ አልሲሲ በትረ ሥልጣኑን እንካችሁ አሉዋቸው፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉበት ሳይታለም የተፈታው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

 

ይሁንና አልሲሲ ለመጀመርያ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ የተረከቡት ውጥንቅጡ የወጣ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ነበር፡፡ የግብፅ ብሔራዊ ዕዳ ከ46 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነበር፡፡ የወጣቶች የሥራ አጥነት መጣኔም ከፍተኛ ነበር፡፡

አልሲሲ ምንም እንኳን በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን የአገሪቱ ብሔራዊ ዕዳ ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢያድግም፣ የግብፅን ፓውንድ የመግዛት አቅም በማዳከምና የተጨማሪ እሴት ታክስ በመጣል የመንግሥትን የበጀት ጉድለት ለማስተካከል ጥረት አድርገዋል፡፡

ሆኖም አልሲሲ ጦር ኃይሉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና በእጅጉ በማስፋት የሕፃናት ወተት እስከ ማከፋፈል የደረሰ ተሳትፎ እንዲኖረው መፍቀዳቸው በጣም ያስተቻቸዋል፡፡ ለኢኮኖሚው ዕድገት ምንም አይፈይዱም የተባሉ በሲናይ በረሃ ላይ የሚገነቡት አዲስ ከተማና በስዊዝ ካናል ላይ የሚደረገው አላስፈላጊ ማስፋፊያ፣ ለወጣቱ ሥራ ለመፍጠር ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ገንዘብ የሚባክንባቸው ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ማሳያ ናቸው የሚሉም በርካታ ናቸው፡፡

ግብፅን ቀጥቅጠው ይመራሉ የሚባልላቸው አልሲሲ ለሁለተኛ ጊዜ በሚወዳደሩበት የፕሬዚዳንትነት ምርጫ፣ ከእርሳቸው ጋር ለክርክር መቅረብ ክብራቸውን ይነካል በማለት ከክርክር መድረኩ ከሸሹት ‹ከደጋፊ› ተቃዋሚያቸው ጋር ለምርጫ ፉክክር ቀርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉበት ሳይታለም የተፈታው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

 

ሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ ተጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚዘልቀው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አልሲሲ እንደሚያሸንፉ ጥርጥር የለውም ሲሉ በርካቶች መላምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ይህም ሊሆን የሚችልበት ዋነኛ ምክንያት ፕሬዚዳንቱ ብርቱ ተፎካካሪ እንዳይኖራቸው ቀድመው ግልጽ ባልሆኑ ማስፈራራቶች ጠንካራ ተፎካካሪዎቻቸውን ከፉክክሩ በማስወጣታቸው ምክንያት እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ በስተመጨረሻም እርሳቸውን ለመተቸት ቃል መሰንዘር እንኳን ከማይደፍሩ ተፎካካሪ ጋር ለፕሬዚዳንትነት ውድድር ቀረቡ፡፡

‹‹ይህ የእኔ ጥፋት አይደለም፡፡ በአምላክ ስም እምላለሁ ሰዎች የፈለጉትን እንዲመርጡ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ኖረው ከእነርሱ ጋር ለፉክክር ብቀርብ በተመኘሁ፡፡ ነገር ግን እነርሱ ለዚህ ዝግጁ አይደሉም፡፡ ይኼንን ለማለትም ምንም ማፈር አያስፈልግም፤›› ነበር ያሉት ስለጉዳዩ የተጠየቁት አልሲሲ፡፡

ከግብፃውያን አራት ሰዎች አንዱ ማንበብ ስለማይችል ለምርጫው ውድድር የሚቀርቡ ተፎካካሪዎች ራሳቸውን በምልክት መወከል ግድ ስለሚላቸው፣ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ኮከብን ምልክታቸው አድርገው ሲቀርቡ ተፎካካሪያቸው ሙሳ ሙስጠፋ ሙሳ አውሮፕላን ምልክታቸው አድርገዋል፡፡

የአውሮፕላኑ ምልክትነት ያስገረማቸው ተመልካቾች ‹‹አንድ ድምፅ እንኳን ቢያገኙ ከአገሪቱ በርረው መጥፋት ስለሚኖርባቸው ነው ይኼንን የመረጡት፣›› ሲሉ ተሳልቀውባቸዋል፡፡

ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ምንም ጥርጥር ያልገባቸው አልሲሲ ከምርጫ ፉክክሩ ይልቅ ያሳሰባቸው የመራጮች ቁጥር ነበር፡፡

‹‹ሁሉም ነገር በእጃቸው ሳለ ለምን ሥጋት እንደገባቸው ግራ ያጋባል፤›› ሲሉ ቀድመው ጥር ላይ ከፕሬዚዳንትነት ፉክክሩ ራሳቸውን ያገለሉት መሐመድ አንዋር አል ሳዳት ተችተዋል፡፡

አልሲሲ በሥልጣን ላይ ሆነውም የመጡበትን የጦር ኃይል በጎሪጥ እንደሚመለከቱትና ሥጋት ይሆኑብኛል ያሏቸውን ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች ከሥራ ማሰናበታቸው፣ ያለባቸውን የውስጥ አለመረጋጋት ያመላክታ ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ አልሲሲ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹማቸውን ጥቅምት ላይ፣ ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊያቸውን ደግሞ ጥር ላይ ማባረራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉበት ሳይታለም የተፈታው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

 

ሆኖም ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱ ማሸነፋቸው ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም፣ የሕዝቡን እውነተኛ ድጋፍ የሚያዩት ለምርጫ የሚወጣውን የሕዝብ ቁጥር በማየት ስለሆነ፣ የመራጮች ቁጥር በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ነው የተነገረው፡፡ ከምርጫው የመወዳደሪያ ሜዳው ጠቧል በሚል ምክንያት ራሳቸውን ያገለሉ ተቃዋሚዎች ሕዝቡ ወጥቶ እንዳይመርጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረ በመሆኑና ፕሬዚዳንቱም ሥጋት ስለገባቸው፣ እነዚህን ቀስቃሾች ማስፈራራታቸው የመራጮች ቁጥር ምን ያህል እንዳሳሰባቸው ማሳያ ነው፡፡

በግብፅ ሕገ መንግሥት መሠረት አልሲሲ ይኼንን የምርጫ ዘመናቸውን ሲያጠናቀቁ በድጋሚ መመረጥ አይችሉም፡፡ ሆኖም በደጋፊዎቻቸው የፓርላማ አባላት አማካይነት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች አስደርገው ለተደጋጋሚ፣ ከሆነም እንደ ቻይናው ዢ ጂንፒንግ ዘለዓለማዊ መሪነትን እንዲጎናፀፉ ለማድረግ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

‹‹አልሲሲ ፖለቲካ ይጠላሉ፡፡ በዚህም ምርጫ እያየን ያለነው ይኼንን ነው፣›› ሲሉ አል ሳዳት ይናገራሉ፡፡ ‹‹የሚያሳስበኝ ቀጣይ የሚሆነውን ማየት ነው፡፡ እንደ ቻይና ልንሆን ነው? ያ ነው ጥያቄው፤›› ብለዋል››

በቀጣይ አራት ዓመታት አልሲሲ የሚሠሩዋቸው ምን ሊያመጡ እንደሚችሉ ካሁኑ መተንበይ ባይቻልም ጨቋኝ መሆናቸውን እያዩ፣ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ልሆኑ ድርጅቶችን አግደውና ሚዲያውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር አድርገዋል ተብለው እየተተቹ እንኳን አሜሪካና ሳዑዲ ዓረቢያ ለፕሬዚዳንቱ የልብ ልብ ሰጥተዋቸው ዘለዓለማዊ መሪነትን ሊያልሙ ይችላሉ የሚሉ አልጠፉም፡፡ 

ፕሬዚዳንት አልሲሲ እንደሚያሸንፉበት ሳይታለም የተፈታው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...