ሥነ ሕይወታዊ ዑደቱ እስኪጠና መድኃኒት እስኪገኝለት ድረስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተዳርሶ ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓ ውስጥ በተለያዩ በሽታዎች ይሞቱ ከነበሩ ሰባት ሰዎች መካከል የአንዱ ሞት ምክንያት እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ በተደረጉ ምርምሮች ስለ በሽታው ፍንጭ የተገኘው ከወደ ጀርመን ነበር፡፡ መጋቢት 15 ቀን 1874 ዓ.ም. ጀርመናዊው ተመራማሪ ዶ/ር ሮበርት ኮች የበሽታው መንስኤ ሳንባን በማጥቃት ሰዎችን ለሞት የሚዳርገው ማይክሮ ባክቴሪየም ቲዩበርክሎስስ የተባለው ተውሳክ መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡ ይህንን ቀን ታሳቢ በማድረግም በየዓመቱ መጋቢት 15 ቀን ዓለም አቀፍ የቲቢ ቀን ሆኖ እንዲሰየም ተደረገ፡፡
ቲቢ የተለያዩ የዓለም አገሮች በተለይም የታዳጊ አገሮች የጤናው ዘርፍ ከባድ ተግዳሮት ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አንድ ሦስተኛው የዓለም ሕዝብ በቲቢ የተጠቃ ነው፡፡ ይሁንና በቲቢ ሕመም የሚሰቃዩት ከተጠቂዎቹ የተወሰኑት ብቻ ናቸው፡፡ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ደካማ የሆነ ሲሆን፣ በተለይም የኤችአይቪ ሕመምተኞች ከሌሎቹ በተለየ ከ26 እስከ 31 በመቶ በቲቢ በሽታ የመሰቃየት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በየዓመቱ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ሲሞቱ፣ አሥር ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ በበሽታው ይጠቃሉ፡፡
የዘላቂ የልማት ግቡ አካል የሆነውን ቲቢን እ.ኤ.አ. በ2030 እንዲያበቃ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በዓለም ጤና ድርጅት አሴምብሊ ይሁንታን ያገኘው ግቡ በበሽታው የሚሞቱትን ሰዎች ቁጥር በ90 በመቶ፣ አዳዲስ የሚያዙን ደግሞ በ80 በመቶ የመቀነስ ዓላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህንን ለማሳካትም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችና ድጋፎች ይደረጋሉ፡፡ በተለይም በየዓመቱ መጋቢት 15 ቀን የበሽታውን ሥርጭት መግታትና መቆጣጠር ላይ ትኩረት ያደረጉ መሪ ቃሎች ተመርጠው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡
‹‹የቲቢን ሥርጭት ለመግታት የአመራሩ ሚና ወሳኝ ነው›› በሚል መሪ ቃል ያለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡ የቲቢ በሽታ በከፍተኛ መጠን ከሚገኝባቸው 30 የዓለም አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የበሽታውን ሥርጭትና የሟቾችን ቁጥር በግማሽ መቀነሷን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያስታወቀው 21ኛው ብሔራዊ የዓለም የቲቢ ቀን በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተከበረበት ወቅት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባደረገችው ርብርብ የማይናቅ ለውጥ ማስመዝገቧን የገለጹት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ወርቁ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ በሽታውን የመከላከያ ስትራቴጂዎች መተግበራቸው ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን በበሽታው የሚያዙና ታመው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡
የበሽታው ተጠቂዎች አስፈላጊውን ሕክምናና መድኃኒቱን በሕክምና ተቋማት ተመላልሰው እንዲወስዱ መደረጉም ለተመዘገበው ውጤት ትልቁን ድርሻ አበርክቷል፡፡ መንግሥትም በሽታውን ከመከላከል አልፎ ወደ ማጥፋት መግባቱን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ የቲቢን ሥርጭት ለመከላከል በሽተኞችን ለይቶ የማከም፣ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን የተናገሩት የአርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ናቸው፡፡ በተሠሩ ሥራዎች የበሽታውን ሥርጭት በ50 በመቶ መቀነስ መቻሉን፣ በ1982 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር 369 ሺሕ የነበረ ሲሆን፣ ቁጥሩ በ2008 ዓ.ም. ወደ 177 ሺሕ ማሽቆልቆሉን፣ እንደዚሁም በየዓመቱ አዲስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ከነበረበት ወደ 192 ሺሕ ዝቅ ማለት መቻሉን ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም. በስድስት ወራት ውስጥ 55,238 ሕሙማንን በመለየት ሕክምና እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም ሕክምናቸውን ተከታትለው የጨረሱ ሕሙማንን ቁጥር 93.4 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ የተመዘገቡት ውጤቶች ከስኬት የሚቆጠሩ ቢሆንም፣ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅና የላቀ ምላሽ የሚጠይቁ ተግዳሮቶች የተደቀኑበት ነው፡፡ በአገሪቱ በየዓመቱ አዲስ በቲቢ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይ ግን አሁንም አሳሳቢ ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ 157,541 ሰዎች በቲቢ በሽታ እንደሚያዙ ይገመታል፡፡ 33 ከመቶ የሚሆኑት የቲቢ ሕሙማን አስፈላጊውን የምርመራና የሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ ራሳቸውን ለሞት፣ በዙሪያቸው የሚገኙትን ደግሞ ለበሽታ ይዳርጋሉ፡፡
ሌላው ተግዳሮት መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ነው፡፡ የተላመደ ቲቢን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ የሚገኙ ሲሆን፣ ለተላመደ ቲቢ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትን ቁጥር 53 ማድረስ መቻሉን ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡ በሕክምና ተቋማቱ እስካሁን 3,889 ሕሙማንን በመለየት ሕክምና እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡
በዚህ መረዳት ያልቻሉ ሕክምናቸው ያልተሳካላቸውን የተላመደ ቲቢ ሕመምተኞችን በመለየት በአዳዲስ የፀረ ቲቢ መድኃኒቶች የሚታከሙበት አሠራርም ተዘርግቷል፡፡ ይህንን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሰባት ተቋማትም ተለይተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም መደበኛውንና መድኃኒት የተላመደውን ቲቢን መለየት የሚችሉ አዲስና ፈጣን የምርመራ ቴክኖሎጂውን በሥራ ላይ ማዋል ተችሏል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2035 ከቲቢ በሽታ ነፃ የሆነችን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የመንግሥት ቁርጠኝነት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በዚህ በ21ኛው የዓለም የቲቢ ቀንን አስመልክቶ የቲቢ ምርምር ጉባዔ ከመጋቢት 12 እስከ 15 ተካሄዷል፡፡ ከዚህ ፕሮግራም ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ መከላከል የክብር አምባሳደር ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የቢሾፍቱ ሆስፒታል መድኃኒቱን የተላመደ ቲቢ ሕክምና ማዕከልን ጎብኝታ ነበር፡፡ ደራርቱ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዩኒቨርሲቲዎች፣ በማረሚያ ተቋማት፣ በስደተኞች ካምፕና በመሳሰሉት ቦታዎች ሰፊ የማስተማር ሥራ መሠራት እንዳለበት ገልጻለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም እ.ኤ.አ. በ2030 ቲቢን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል፡፡