ባለቅኔዋ እማሆይ ገላነሽ
ዕድሜያቸው በግምት 70 ዓመት እንደሚሆናቸው ይናገራሉ፡፡ ሴቶች የእኩልነት መብት ያገኙት አሁን ሳይሆን በዘመነ ክርስቶስ እንደሆነ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡ «ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከከርሰ መቃብር ሞትን ድል ነስቶ መነሳቱ የተናገራቸው ለሴቶች ነው» ይላሉ፡፡ ይህም ከወንድ እኩልነትን ሳይሆን የበላይነታቸውን ያስረዳል የሚሉት እማሆይ ገላነሽ ሐዲስ የቅኔ መምህርት ናቸው፡፡
በ15 ዓመታቸው ቅኔ ማስተማር የጀመሩት እማሆይ ገላነሽ 52 ዓመታት ቅኔ በማስተማር አያሌ ሊቃውንት አፍርተዋል፡፡ እማሆይ ገላነሽ ከ100 እስከ 300 የሚሆኑ ተማሪዎችን ቅኔ ያስቆጠሩበት ጊዜ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ በዚያ ጊዜም ታላቅ ደስታ ያስገኛል፡፡
የዓይናቸውን ብርሃን በልጅነት ጊዜያቸው ያጡት እማሆይ ገላነሽ የፊደልን መልኳን በዓይናቸው አላዩም፡፡ ሆኖም አበጥረው ያውቋታል፡፡ የቅኔ ሊቅነትም እውቀት የቀሰሙት ካባታቸው ከመሪጌታ ሐዲስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
- አዲስ ዘመን፣ መስከረም 13 ቀን 1966 ዓ.ም.