Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የኢትዮጵያዊው ሳተላይት በአፍሪካ ሕዋ ውስጥ

አቶ ኖኅ አዝሚ ሳማራ በሳተላይት ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚሠራና አዝሚ ዩኤስኤ ኤልኤልሲ ኩባንያ መሥራች፣ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን፣ የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ተወልደው ባደጉበት ከተማ አዲስ አበባና ዳሬሰላም ታንዛኒያ ውስጥ ነው፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ እንግሊዝ አገር አቅንተው የመሰናዶ ትምህርታቸውን ተከታተሉ፡፡ አሜሪካ ተሻግረው ፔንሶልቬኒያ በሚገኘው ኢስት ስትራውድስበርግ እና በሎስአንጀለስ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መርሐ ግብሮች የመጀመርያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑትን አቶ ኖህ ሳማራን በኩባንያቸውና ተዛማጅ በሆኑ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳሬሰላም ድረስ ሄደው የተማሩበትን፣ በእንግሊዝ አገር መሰናዶ ትምህርት ቤት የገቡበትንና እዚያው እንግሊዝ አገር ትምህርትዎን መቀጠል ሲችሉ ወደ አሜሪካ የተሻገሩበትን ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ኖኅ፡- ዳሬሰላም የሄድኩበት ምክንያት አዲስ አበባ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አባቴ ዳሬሰላም በሚገኘው በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሊብሬሽን ኮሚቴ ውስጥ ተመድበው እንዲሠሩ በመደረጋቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የጀመርኩትን ትምህርት ካጠናቀቅኩ በኋላ አባቴ ወደሚገኝበት ዳሬሰላም ሄጄ የ11ኛ ክፍል ትምህርቴን ጀመርኩኝ፡፡ የጀመርኩትን ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ ደግሞ ወደ እንግሊዝ በመሄድ (ሳንፎርድ) ትምህርት ቤት ገብቼ የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፡፡ እንግሊዝ አገር ‹‹ኤ› ሌቨል የገባሁበት ምክንያት የዚያች አገር የትምህርት ሥርዓት ሁለት ዓይነት ፕሮግራሞች ስላሉት ነው፡፡ አንደኛው ለኮሌጅ መግቢያ ዝግጁ የሚያደርግ ‹‹ኤ›› ሌቨል ወይም መሰናዶ ትምህርት ሲባል ሁለተኛው ፕሮግራም ደግሞ ለ12ኛ ክፍል መግቢያ የሚያዘጋጀው ‹‹ኦ›› ሌቨል ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሌቨል የሚሰጠውን ትምህርት ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ይፈጃል፡፡ የኮሌጅ መሰናዶን ፕሮግራም ካጠናቀቅኩ በኋላ ወደ አሜሪካ አቀናሁ፡፡ ይህንንም ያደርግኩት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ወንድሜ አሜሪካ ውስጥ ስለሚገኝ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የአሜሪካ የትምህርት ሥርዓት ከእንግሊዝ አገር የተሻለ ነው የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢስት ስትራውድስበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪዎን ከሠሩ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ትምህርትዎን አቋርጠው ነበር፡፡ ምክንያቱን ሊገልጹልኝ ይችላሉ?

አቶ ኖኅ፡- በኢስት ስትራውድስበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪዬ ታሪክ፣ እንግሊዝኛ፣ ሳይንስና ባዮሎጂ ሜጀር ነበር፡፡ ታሪክ በጣም ደስ የሚለኝ የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ እንግሊዝኛ ሊትሬቸርና ታሪክ ሕግ ለማጥናት የሚያዘጋጁ መርሐ ግብሮች ናቸው፡፡ ሳይንስ ደግሞ ሕክምና ትምህርትን ለመከታተል ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ለማንኛውም የመጀመርያ ዲግሪዬን ከሠራሁ በኋላ ለአንድ ዓመት ዕረፍት የወሰድኩበት ምክንያት እንግሊዝ አገር ለአንድ ዓመት በቆየሁበት ጊዜ ሩሲያዊው ደራሲ ፊዮዶር ዶስቶይቪስኪ የደረሰውን ‹‹ዘ ብራዘርስ ካራማዞቭ›› የሚባለውን ልብ ወለድ መጻሕፍት አንብቤ ነበር፡፡ የሩሲያ ዛር (ንጉሥ) በሕይወት በነበረበት ዘመን የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጻሕፍ የሩሲያን ባህል ፍንትው አድርጎ የሚያብራራ በመሆኑ በጣም ወደድኩት፡፡ በዚህም የተነሳ መጽሐፉ ውስጥ የማነባቸውን ዋና ካራክተሮችም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በስማቸው አልነበረም የምጠራቸው፡፡ ለሁሉም የሐበሻ ስም ሰጥቼያቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ዲምትሪ›› የሚባለውን ‹‹ደምሴ›› እያልኩኝ ነበር የምጠራቸው፡፡ ይህንንም ያደረግኩበት ምክንያት የሩሲያና የኢትዮጵያ ባህሎች አንድ ዓይነት በመሆናቸው ነው፡፡ በወቅቱ አገሬ በጣም ትናፍቀኝ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ልክ የአገሬን ታሪክና ባህል የማነብ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ይህም ሁኔታ የአገሬን ናፍቆት እንድወጣው አድርጎኛል፡፡ ሁለቱም አገሮች በዘውዳዊ አገዛዝ ሥር መሆናቸውንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆናቸው ያስተሳስራቸዋል፡፡ ደራሲው ስለ ኢትዮጵያ እንጂ ስለ ሩሲያ ካራክተሮች የሚጽፍ አይመስለኝም ነበር፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ አጻጻፉ ከኢትዮጵያ ባህል ጋር የተያያዘ ወይም የተቆራኘ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በዚህም የተነሳ ይህን መሰል ወይም ተመሳሳይ መጽሐፍ ለመጻፍ ከራሴ ጋር ተዋውዬ ነበር፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የአንድ ዓመት ዕረፍት ወሰድኩ፡፡ ነገር ግን ሁሉም እንዳሰብኩት ሆኖ አልተገኘም፡፡ ወይም አልተሳካልኝም፡፡ ስለሆነም ይህንን ሐሳቤን እርግፍ አድርጌ ተውኩትና ወደ ትምህርቴ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ገባሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በጠቀሱት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ምን ዓይነት የትምህርት ፕሮግራም ነበር ያጠኑት?

አቶ ኖኅ፡- በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ዲፓርትመንት ገባሁና ስለ አውሮፓ ሬናይዘንስና ሪፎርሜሽን ማጥናት ጀመርኩ፡፡ ይህንንም ለማጥናት ያነሳሳኝ ሁሉም የአውሮፓ አገሮች በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከጨለማው ዘመን ወደ ሬናይዘንስ ፔሬድ የተሸጋገሩበት ዘመን ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማርቲን ሉተር ሪፎርሜሽን በሚል ፕሮግራም የክርስቲያን ፕሮቴስታንት ሃይማኖትን አስፋፋ፡፡ እኔም በአውሮፓ አገሮች ሬናይዘንስ ዕውን እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ምን እንደሆነና በአፍሪካ ውስጥም ሬናይዘንስ ለምን አይኖርም? የሚል ጥያቄ ይመላለስብኝ ጀመር፡፡ መልሱንም ለማግኘት የአውሮፓ ታሪክ ፕሮግራሞችን ማጥናት ወደድኩ፡፡ አንዳንድ ጓደኞቼ ግን ምን ይፈይድልኛል ብለህ ነው የአውሮፓን ታሪክ የምታጠናው? ከዚህ ሁሉ ይልቅ ስለ አፍሪካ ለምን አታጠናም? እያሉ ይቀልዱብኝ ነበር፡፡ እኔም መልሼ ‹‹አውሮፓውያኖች እየመጡ ባዮሎጂ ኤክስፐርመንት እያጠኗችሁ ነው፡፡ እነሱ ከሚያጠኗችሁ ይልቅ እናንተ እነሱን ዞር ብላችሁ ማጥናት አይሻላችሁም ወይ?›› እያልሁ እሳለቅባቸው ነበር፡፡    

ሪፖርተር፡- የአውሮፓ አገሮችን ታሪክ ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ በምን አቅጣጫ ላይ ነበር ትኩረትዎ ያረፈው?    

አቶ ኖኅ፡- ስለ አውሮፓውያኖች ታሪክ ማወቅ የፈለግኩትን ያህል ከጨበጥኩ በኋላ የሕግ ትምህርት መማር ጀመርኩ፡፡ የተከታተልኩትም ሕግ በፊሎዞፊ፣ በህሊናና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን፣ አንድ ሰው ወንጀል ከፈጸመ በኋላ እንዴት እንደሚዳኝ ወይም ፍትሕን እንዴት ማግኘት ይችላል የሚለው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ቀጥሎም ስለ ‹‹ሳተላይት ቴክኖሎጂ››፣ እና ‹‹ስፔስ ቴክኖሎጂ›› ወይም ‹‹ዘ ሎው ኦፍ አውተር ስፔስ›› ላይ ያተኮረ ሕግ ማጥናት ቀጠልኩ፡፡ በተለይ ሎው ኦፍ አውተር ስፔስ ስማር ስለ ሳተላይቶችም ወይም ስለ ሳተላይት ቴክኖሎጂ በሚገባ ማወቅ ጀመርኩ፡፡ ተማሪ እያለሁም ዘ ሎው ኦፊሲ ኦፍ ሮዝ ፕላት የሚባል አንድ የሕግ ኩባንያ እንደ ጸሐፊ ቀጠረኝ፡፡ ይህም እየተማርኩ ገንዘብ እንዲኖረኝ አድርጎልኛል፡፡ የኩባንያው ስፔሻላይዜሽን ስለ ስፔስ ሕግ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ኩባንያው ከሕዋ ጋር በተያያዘ የሚሠራቸው ሥራዎች ምን ነበሩ?    

አቶ ኖኅ፡- ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ሕዋ ለሚልኩት ሳተላይት ፈቃድ የሚሰጥ ነው፡፡ በአሜሪካ አገር ሕግ መሠረት ሳተላይት ገንብቶ ወደ ሕዋ ለመላክና ሕዋ ውስጥ ኦፕሬት ለማድረግ ሦስት ልዩ ልዩ ፈቃዶች ያስፈልጋሉ፡፡ የመጀመርያው ፈቃድ ሳተላይቱን ለመገንባት ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ሳተላይቱን ወደ ሕዋው ለማምጠቅና ሕዋ ውስጥ ከገባ በኋላ ደግሞ ኦፕሬት ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ከትምህርት ጎን ለጎን አብረውኝ ከሚሠሩ ሰዎች ስለ ሳተላይት ጥቅም ብዙ ነገር ማወቅ ቻልኩ፡፡ በኩባንያው የቆየሁት የጀመርኩትን የሕግ ትምህርት እስካጠናቅቅ ድረስ ነው፡፡ ከጨረስኩ በኋላ ግን ጂኦ ስታር የሚባል አንድ ሌላ ኩባንያ ቀጠረኝ፡፡ ይህኛው ኩባንያ የቀጠረኝ ከኢንተርናሽናል ቴሌኮሙዩኒኬሽን ዩኒየን ለሳተላይቱ የፍሪኩዌንሲ፣ የኮንስትራክሽንና ወደ ሕዋ የማመንጠቅ ፈቃድ እንዳስገኝላት ነው፡፡ የኩባንያው ተግባር እንደ ጂፒኤስ ማለትም የፖዚሽንስ ሰርቪስ ጥቅም የሚሰጥ የሳተላይት ሰርቪስ መሥጠት ነው፡፡ እሱም የሕግ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ‹‹ስታፍ አተርኒ ኤንድ ግሎባል ኮኦርዲኔተር›› ተብዬ ነበር፡፡ ማዕረጉን በጣም ስለወደድኩት ለሚያውቁኝም ሆነ ለማያውቁኝ ሁሉ ማዕረጌ የተጻፈበትን የአድራሻዬን ካርድ ትፈልጋላችሁ? እያልኩ እንደመኩራራት ይቃጣኝ ነበር፡፡ በዚህም ታይትል በመጠቀም ለብዙ አገሮች እየተዘዋወርኩ ሳተላይት ሰርቪስ ፍሪኩዌንሲ እንዲያገኙ በማድረግ በርካታ ሥራዎችን አከናውኜአለሁ፡፡ ጂኦ ስታርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍሪኩዌንሲ እንዲያገኝ አድርጌያለሁ፡፡    

ሪፖርተር፡- ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ሲቸረው፣ እርሶም ደግሞ ምን ያህል ተጠቃሚ ሆነዋል? ወይም የቱን ያህል ታዋቂ የመሆን ዕድል አጋጠመዎት?   

አቶ ኖኅ፡- ጂኦ ስታር እኔን ከመቅጠሩ በፊት ፍሪኩዌንሲ የማግኘቱ አጋጣሚው ሁለት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው የቀጠረኝ፡፡ ሌሎች ኩባንያዎች ጂኦ ስታር ይህን ሥራ ለጀማሪ ሰው መስጠቱ መዳከሙን የሚያሳይ ነው እያሉ ያሙት ነበር፡፡  ነገር ግን ሠራተኞቹን  በማነቃቃት፣ እንደ አንድ ሰው ሆነን ጠንክረን በመሥራት ተዳክሞ የነበረው ኩባንያ ለመጠናከር ቻለ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍሪኩዌንሲ በቃ፡፡ ይህንን የተገነዘቡ ሌሎች ኩባንያዎች ሐሜታቸውን ትተው ለእኔ ከፍተኛ የሆነ አክብሮትና አድናቆት በመስጠት እየመጡ ለምን አንረዳዳም? ለዚህ ኩባንያ እንደሠራህ ሁሉ ለእኛም ለምን አትሠራልንም? ብዙ ገንዘብ እንከፍልሃለን እያሉ ይወተውቱኝ ጀመር፡፡  ጂኦ ስታር ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዲያገኝ የተደረገው በእኔ እንቅስቀሴ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የኩባንያው ባለሙያዎች በአንድ መንፈስና በቡድን ተደራጅተን በመሥራታቸው ነው፡፡ ኩባንያቹ ግን ሁሉንም ሥራ ያከናወንኩት እኔ ብቻ እየመሰልኳቸው መወትወታቸውን ተያያዙት፡፡

አቶ ኖኅ፡- ከዚያም እንደዚህ ዓይነት ጀብዱ መሥራት የምችል ከመሰላችሁ ሁላችሁንም ለምን አልረዳም? አልኩና አምስት ደንበኞችን ይዤ ወደ ማማከር ሥራ ገባሁ፡፡ ሥራውም የስፔስ ፍሪኩዌንሲ ኦሎኬሽን ፈቃድ ማግኘትና፣ እንዲሁም ኢንተርናሽናል ግሎባል ሰርቪስ መስጠት የመሰሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ስለ ፍሪኩዌንሲና ስለ ሳተላይት የሚሠራው አገር ማነው? የሚለውንም አውቅ ነበር፡፡ ኩባንያዎቹ ብዙ ገንዘብ ይከፍሉኝ ነበር፡፡ በዚያ ሥራ ላይ ለሁለት ዓመት ያህል እንደቆየሁ የወርልድ ስፔስ ሐሳብ በአዕምሮዬ መመላለስ ጀመረ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ ሐሳብ የመጣልዎት በምን አጋጣሚ ነው?

አቶ ኖኅ፡- ኩባንያዎቹ በጣም ብዙ ገንዘብ ነበር የሚከፍሉኝ፡፡ ነገር ግን በኮንሰልታንሲ ሥራ መቀጠል አልፈለኩም፡፡ ምክንያቱም ትንሽ ቆይቶ እንደ መሰልቸት ብሎኝ ነበር፡፡ ለእነዚህ ኩባንያዎች እንደዚህ ዓይነት ሥራ እየሠራሁኝ እስከ መቼ እቆያለሁ? የሚል ጥያቄ ተመላለሰብኝ፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ለአፍሪካ ሬናይዘንስ ለማምጣት እንዴት ነው የሚቻለው ብዬ ከሦስት ዓመት በፊት ያነሳሁት ጥያቄ መልሱ ሳልሰጥበት በእንጥልጥል መቅረቱም የኮንሰልታንሲውን ሥራ ትቼ ወደ ወርልድ ስፔስ እንድገባ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የወርልድ ስፔስ ፕሮግራም አፍሪካ ውስጥ በጤናና በትምህርት ዘርፎች ያተኮሩ መረጃዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም ፍሪኩዌንሲ እንደሚያስፈልግ፣ ለጂኦ ስታር በርካታ ፍሪኩዌንሲ እንዳስገኘሁለት ሁሉ ለራሴ አንድ ፍሪኩዌንሲ እንኳን አግኝቼ ያስብኩትን ሥራ ዳር ማድረስ እንደ ምን ይሳነኛል? የሚል ጥያቄ ሁሉ በአዕምሮዬ ይመላለስብኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡-  ይህን ሐሳብዎን ለሰው ያማክሩ ነበር?   

አቶ ኖኅ፡- የያዝኩትን የኮንሰልታንሲ ሥራ ልተው እንደምፈልግ ለባለቤቴ ነግሬያታለሁ፡፡ እሷም ‹የትኛውን ሥራ?› ብላ ጠየቀችኝ ይኼ የሚከፍሉኝ የኮንሰልታንሲ ሥራ ነው ብዬ መለስኩላት ‹ኦ ጥሩ ነው፡፡ ግን በዚህ ምትክ ምን ልተሠራ ነው ያሰብከው?› አለችኝ፡፡ አፍሪካ ላይ ሳተላይት ለማምጠቅ እፈልጋለሁ አልኳት፡፡ ‹ማን? አንተ?› ብላ በድጋሚ ጠየቀቺኝ፡፡ አዎ እኔ ስል መለስኩላት፡፡ ‹ይልቁንስ ቀልዱን ተውና ቁም ነገሩን ንገረኝ፤› አለችኝ፡፡ እውነቴን ነው የኮንሰልታንሲውን ሥራ ትቼ አፍሪካ ላይ ሳተላይት ለማምጠቅ እፈልጋለሁ ብዬ ደገምኩላት፡፡ ‹እንዴ ሳተላይት ከባድ ነገር አይደለም እንዴ? ግለሰብ ማምጠቅ ይችላል እንዴ?› በማለት ጥያቄዋን አራዘመች እኔም፣ አይ ሰው እንኳን አይደለም፡፡ ትልልቅ ኩባንያዎች ናቸው የሚያመነጥቁት፣ ይህም ቢሆን ግን የሚረዱኝ ፈልጌ ከእነሱ ጋር ተባብሬ ሳተላይት ማመንጠቅ እፈልጋለሁ ብዬ መለስኩላት፡፡ ሐሳቤን የማልቀይር መሆኑን ከተረዳች በኋላ ‹በል ቶሎ ብለህ ወደ ፈለግከው ሥራ ግባና በመካከሉ ድንገት ቢሰለችህ ቶሎ ወደ ኮንሰልታንሲ ሥራህ ብትመለስ ጥሩ ይመስለኛል አለችኝ፡፡ እኔም የያዝኩትን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ያዝሚ የኤስኤስ ኤልኤልሲ በሚል መጠርያ የሚታወቅ ወርልድ ስፔስ ኩባንያ በ1982 ዓ.ም. ለማቋቋም ቻልኩ፡፡   

ሪፖርተር፡- ኩባንያውን ለማቋቋምና ቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት የሚስፈልግዎትን ገንዘብ ከየት አገኙ?    

አቶ ኖኅ፡- ኩባንያውን እንዳቋቋምኩ በመጀመርያ የገንዘብ ዕገዛ ያደረገልኝ የጃፓን ትልቅ ፋይናንሰሩ ወዳጄ የሆነው ዶ/ር አይቼ አዩካዋ ነው፡፡ ስልክ ደውዬ ላነጋግርህ እፈልጋለሁ አልኩት፡፡ እሱም ወዲያው ትኬት ልኮልኝ ወደ ቶኪዮ አቀናሁ፡፡ እዛም እንደደረስኩ አንድ ጥሩ ሆቴል ውስጥ አሳረፈኝ፡፡ ከባለቤቴ ጋር ያደረኩትን ውይይት ዓይነት ከወዳጄ ጋር ማድረግም ግድ ሆነብኝ፡፡ በውይይታችንም ላይ ሳተላይት ለማምጠቅ እንደምፈልግ አስረዳሁት ‹ሳተላይት ማምጠቅ እፈልጋሁ ነው የምትለኝ?› ሲል ተየቀኝ፡፡ ‹አዎ!›› አልኩት፡፡ ‹ያረፍክበት ሆቴል ያልተስማማህ ወይም ደስ የማይልህ ከሆነ ሌላ ሆቴል አሳርፍሃለሁ፡፡ በዚህም ሆቴል ለሦስትና ለአራት ቀናት ያህል ካረፍክና ትንሽ ከተረጋጋህ በኋላ ወደሚያስደስቱህ ልዩ ልዩ መዝናኛዎች ሄደን አብረን እንዝናናለን፡፡ ከዚህም በኋላ የወጠንከውን ሐሳብ እርግፍ አድርገህ እንደምትተወው እተማመናለሁ አለኝ፡፡ እኔም፣ የለም ዶ/ር አዩካዋ እኔ እዚህ የመጣሁት ሳተላይት ላውንች ለማድረግ ነው በማለት ሐሳቤን አጠናከርኩበት፡፡ ‹ይህንን ለማከናውን ምን አቅደሃል?› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ከአሜሪካ መንግሥት ላይሰንስ ካገኘሁ በኋላ በአፍሪካ ላይ (ኦቨር አፍሪካ) ወይም አፍሪካ ሕዋው ውስጥ ሳተላይት ለማምጠቅ ነው ዕቅዴ አልኩት፡፡ ከሐሳቤ ንቅንቅ እማልል መሆኑን ከተረዳው በኋላ ‹ከሚያስፈልግህ ገንዘብ ውስጥ ግማሹን አሁን የቀረውን ግማሽ ደግሞ ፈቃዱን ስታወጣ እሰጥሃለሁ፤› ብሎ ቃል ገባልኝ፡፡      

ሪፖርተር፡- ፈቃዱን የማግኘቱ ሁኔታ ምን ሆነ?     

አቶ ኖኅ፡- ኩባንያውን ካቋቋምኩ በኋላ ፈቃዱን በ1983 ዓ.ም. ከአሜሪካ መንግሥት አገኘሁ፡፡ በዓመቱ ደግሞ ላይ ግሎባል ስፔሳል ፍሪኩዌንሲ ተሰጠኝ፡፡ ከዚያም ቴክኖሎጂው ተቀነባበረ፡፡ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ደግሞ ለእንቅስቃሴ የሚያስፈልገው በጀት ተሟላ፡፡ በጀቱ ሊሟላ የቻለው ወዳጄ የገባልኝ ቃል ኪዳን ዕውን በማድረጉና ከሌሎችም ጓደኞቼ ያገኘሁትን ገንዘብ በማጠረቃቀም ነው፡፡ በ1988 ዓ.ም. ሁሉም ሳተላይቶች መሥራት ጀመሩ፡፡ በተከታታይ ዓመታትም የሚያስፈልገው ሥራ ሁሉ ተከናውኖ አለቀ፡፡ ከዚያም ለአፍሪካ የተመደበው የመጀመርያው ሳተላይት በ1990 ዓ.ም. ጥቅምት ላይ ወደ ሕዋው ተመነጠቀ፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኒልሰን ማንዴላ ተገኝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፈቃድ ለማግኘት ብዙ አልተንገላቱም? የፍሪኩዌንሲው ጉዳይስ እንዴት ነው ዕውን የሆነው?    

አቶ ኖኅ፡- አልተንገላታሁም፡፡ በጠየቅኩ በ11 ወራት ውስጥ ነው ፈቃዱን ያገኘሁት፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ፈቃድ ሳገኝ የመጀመርያው ሰው አድርጎኛል፡፡ አንዲት ጠባብ ወይም አዲስ አበባን የሚያክል አካባቢን የሚሸፍን የሳተላይት ለማግኘት ቢያንስ ሦስት፣ አራትና አምስት ዓመት ይፈጃል፡፡ ነገር ግን 124 አገሮችን የመሸፈን አቅም ላለው ሳተላይት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈቃድ ማግኘቱ አዲስ ነገር ነበር፡፡  ፍሪኩዌንሲውን ያገኘሁት ትሪማሪዮ በምትባል የስፔን ከተማ ውስጥ በርካታ የዓለም አገሮች በተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ  ተገኝቼ ያቋቋምኩት ኩባንያ ለአፍሪካና ለእስያ የሚሰጠውን ጥቅም በዝርዝር ካስረዳሁ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የአሜሪካ መንግሥት፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች፣ የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባል የነበሩና አሁን ግን ነፃነታቸውን የተቀዳጁ አገሮች ሐሳቤን ክፉኛ ተቃውመው ነበር፡፡ ነገር ግን አፍሪካ፣ የደቡብ አሜሪካና ጥቂት የእስያ አገሮች ድጋፋቸውን ስለቸሩኝ ለጥያቄዬ አዎንታዊ መልስ በመስጠት ስፔሻል ፍሪኩዌንሲ ለማግኘት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከለጋሾች የገንገዘብ ዕርዳታ ሲጠይቁ ምላሻቸው እንዴት ነበር?

አቶ ኖኅ፡- የማውቃቸውን ሰዎች ሁሉ በአፍሪካ ሕዋ ውስጥ ሳተላይት የማምጠቅ ዕቅድ አለኝና ገንዘብ ዕርዱኝ እያልኩ መወትወቴን አላቋረጥኩም፡፡ አንዳንዶቹ እንደ እብድ ነበር ይቆጥሩኝ ነበር፡፡ እንደውም አንድ ሰውዬ እንዳንተ ዓይነት ሰው ሳተላይት ማምጠቅ አይችልም ብሎኛል፡፡ እኔም ምን ዓይነት ሰው ነው ማምጠቅ የሚችለውን? ብዬ ብጠይቀው ነጭ፣ ሀብታምና መንግሥት የሚያሟሉለት መሆን አለበት ብሎ መለሰልኝ፡፡ እኔም፣ ችግሩ የቀለም ጉዳይ ከሆነ ፊቴን ነጭ ቀለም እቀባለሁ ብዬ ተሳለቅኩበት፡፡   

ሪፖርተር፡- ኩባንያዎ ስንት ሳተላይቶች ነው ያለው? በአፍሪካ ሕዋ ውስጥ ያመጠቁት ሳተላይት ምን ዓይነት መረጃዎችን ነው የሚያሠራጨው? ሥርጭቱ የሚደርሰውስ ለስንት አገሮች ነው?  

አቶ ኖኅ፡- ኩባንያው ያሉት ሳተላይቶች ሦስት ናቸው፡፡ በአፍሪካ ሕዋ ውስጥ የተቀመጠው ሳተላይት ለኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ለደቡብ አፍሪካና ለናይጄሪያ የጤናና የትምህርት መረጃዎችን ያሠራጫል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሳተላይቱ ለእነዚህ መረጃዎች በሚያመች መልኩ እንደገና እየተገነባ (ሪ-ኢንጂነሪንግ) ነው፡፡ ሥራውም በጥሩ ሁኔታ ወደ መጠናቀቁ ገደማ ተቃርቧል፡፡ በዚህም መሠረት ኬንያ ላይ በሙከራ ደረጃ ባሠራጨነው ትምህርት የተማሪዎቹ የትምህር ውጤት ከፍተኛ ደረጃ ተሸሽሏል፡፡ በተጠቀሱት አገሮች ኢንተርኔትና ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች ትምህርትን በየትምህት ቤቶች፣ ዘመናዊ ጤናን በየጤና ኬላው ማሠራጨት እንደሚችል ተረጋግጦ በከፊል ወደ ሥራው ተገብቷል፡፡  በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ መምህራን እንዴት ማስተማር እንደሚችሉ በሳተላይት አማካይነት የአሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠትና ሠልጣኞችም ዕድሉን ላላገኙት ለሌሎች መምህራን ሥልጠና እንዲሰጡ በመድረግ ላይ ያተኮረ የሰው ሀብት ልማትን የማጠናከሩ ሥራ ለማካሄድ አቅደናል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚጀምረው የዚህ ዓይነቱ ሥልጠና እየታየ ለቀሩት የአፍሪካ አገሮች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኩባንያው ትኩረት በሰው ሀብት ልማት ላይ ያተኮረ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ኖኅ፡- አዎ! ለአንድ አገር ዕድገት ብልፅግና የሰው ሀብት ልማት በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ የሰው ሀብት ልማትን ለማጎልበት ደግሞ ዕውቀት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕዝቦች እንዳይቀየሙኝ እንጂ ከዴሞክራሲም በላይ የሚያስፈልገን ዕውቀት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...