Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየምን መፍረክረክ ነው?

የምን መፍረክረክ ነው?

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ፌዴራሊዝም በዓለም ላይ በዋናነት ከሚታወቁ ሌሎች ሁለት መንግሥታዊ ቅርፆች አንዱ ነው፡፡ አንድ ወጥ የሆነ መንግሥት (Unitary State) ፌዴራላዊ መንግሥት (Federal State) እና ኮንፌዴሬሽን (Confederal State) የሚባሉት ናቸው፡፡

የርዕሰ ጉዳያችን መነሻና መድረሻ የሆነው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ብዙዎች የመስኩ ምሁራን ሲበይኑት እንዲህ ነው፡፡ ‹‹. . . ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መንግሥታት ወይም የየራሳቸውን መንግሥታዊ አስተዳደር ያላቸው ሕዝቦች፣ ለጋራ ጥቅማቸውና ዕድገታቸው ማዕከል ሆኖ እንዲያስተባብራቸውና እንዲወክላቸው በፈቃደኝነትና በእኩልነት ላይ ተመሥርተው የሚያቋቋሙት ሦስተኛ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ፌዴራላዊ መንግሥት ከትንሹ ቁጥር ስንነሳ የሦስት መንግሥታት ጥምር ነው፤›› ይላሉ፡፡

በዓለም ታሪክ ኅብረተሰቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጓዝ ጥርጊያ መንገዶችን በማመቻቸት ዘመናዊ ሕግ ተቀርፆለት ፌዴራላዊ መንግሥት ለመጀመርያ ጊዜ ብቅ ያለው ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡ በተለይ እንግሊዝ አሜሪካ17ኛው እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን 100 ዓመታት ገደማ ቅኝ ስትገዛ በተጠቀመችበት 13 ቦታ ከፋፍሎ የመግዛት ሥሌት አሜሪካኑ ግንኙነታቸውን ሲያጠናክሩ ቆይተው፣ ከነፃነት በኋላ ... 1776 13ቱም አስተዳደር ተወካዮች በፊላደልፊያ ተሰባስበው ‹‹የተባበሩት የአሜሪካ መንግሥት›› በመመሥረታቸው እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ሒደቱን እንግሊዝ ተቃውማ ለአራት ዓመታት የፈጀ ጦርነት በኅብረቱ ላይ ብታካሂድም፣ የአሜሪካዊያን ፅናትና ጥንካሬ በርትቶ የመጀመርያውን የአሜሪካ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት ... 1781 ለመመሥረት ተችሏል፡፡

ሌላዋ በፌዴራሊዚም የዳበረ ሥርዓት ተጠቃሽ አገር ጀርመን ነች፡፡ ይህች አገር ከተበታተነ የመሳፍንት አገዛዝ ታላቅ ማዕከላዊ መንግሥት የሚያቋቁም ሕገ መንግሥት የተቀረፀላት ... 1871 ነበር፡፡ ከዚህ ዘመን በፊት በአገሪቱ ውስጥ 30 በላይ የየራሳቸውን አስተዳደር ዘርግተው የነበሩ የአካባቢ ንጉሦች ነበሩ፡፡ ፌዴራሊዝሙ ይህንን የተበታተነ አስተዳደራዊ ሥርዓት በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ሥር ጠቀለለው፡፡ ጀርመኖች አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ቢሆኑም በባህል፣ በተለያዩ ዘይቤዎችና ልማዶች የሚለያዩ ማንነቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ባባሪያዎች፣ ሽባበኖች፣ ፍራንኮኖችና ሳክሰኖች፣ ወዘተ. ቢባሉምና ጀርመን እስካሁን ሦስት ጊዜ ሕገ መንግሥቷን ብትቀያይርም፣ ሥርዓቱ እያደገ መሄዱን መረዳት አያዳግትም፡፡

የፌደራሊዝም መንግሥታዊ ሥርዓትን በካናዳና በአውሮፓ አገሮች፣ እንደ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካን በመሰሉ አገሮች ብሎም ህንድና ብራዚልን በመሳሰሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አገሮች ይከተሉታል፡፡ በሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን ብሔር፣ ጎሳና የማንነት ብዙኃነት ያላቸውና ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትን በስፋት የያዙ አገሮች ያልተማከለ አስተዳደርን መከተል አዋጭ እንደሆነ አስመስክረዋል፡፡ 28 የሚደርሱ የዓለም አገሮች እስከ 40 በመቶ ሕዝብ ይዘው ሥርዓቱን ተግባራዊ እያደረጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ለዘመናት ከዘለቀው የአሀዳዊ ፀረ ዴሞክራሲ አገዛዞች በፊትም ሆነ በኋላ የየራሳቸው አስተዳደር፣ ሕዝብና ወሰን ያላቸው ነገሥታትና መሪዎች ያሏቸው ሥፍራዎች ስብስብ ነበረች፡፡

ሌላው ቀርቶ የዘመነ መሳፍንትን የመበላላት ክስተት ብንመረምር አንዱ ሌላውን ለማስገበርና ለመጠቅለል ከፍተኛ ፍልሚያ ተካሂዷል፡፡ አሀዳዊ ሥርዓት 125 ዓመታት ወዲህ ተጠናክሮ የአሁኗን ኢትዮጵያ ቅርፅ አካቶ በአዲስ መልክ ሲዋቀርም፣ በኃይልና በጦር አቅም በመጨፍለቅ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ማንነትንም በማስቀየር ጭምር መሆኑ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትውስታ ነው፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የዘውድ አገዛዝ ዕድሜ ካበቃም በኋላ ኢትዮጵያዊያን ያጋጠማቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊና ጠበቅ ያለ ማዕከላዊ አስተዳደር ስለነበር፣ ስለፌዴራሊዝም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ በዚሁ መዘዝ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በተፈጠረው የብሔርና የመደብ ጭቆና ላይ ተመሥርተው በትጥቅ ትግል ሥርዓቱን የተፋለሙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ በደርግ ዘመን መጨረሻ አካባቢ 17 ያህል ደርሰው እንደነበር ይነገራል፡፡

በአብዛኛው በኢሕአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የተጠናቀቀው የደርግ ሥርዓት መገርሰስም ሆነ የሽግግር መንግሥቱ የፌዴራላዊ ሥርዓትን የመምረጥ ሒደት፣ ከመነሻው በአብዛኛው ወገን ተቀባይነት የተቸረው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ‹‹ለዘመናት ተረስተን ኖርን›› የሚለው የኅብረተሰብ ክፍልና ‹‹የብሔር ጭቆናን›› የፖለቲካዊ ትግሉ ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ የዘለቀው ልሂቅ ለሥርዓቱ ተቀባይነት ጥሯል፡፡ በእርግጥ በአሀዳዊ ሥርዓቱ ውስጥ የተጠቀመውና የሚጠቀም የመሰለው ወገን የሰነዘረው ተቃውሞና ትችትም ቀላል አልነበረም፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በመገንባት ብዙኃኑን ያሳተፈና ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ዴሞክራሲያዊ ሒደት መገንባት አለባት፤›› የሚለው መከራከሪያ ግን በአሁኑ ወቅት ብዙዎችን የፖለቲካ ኃይሎች የሚለያይ አይደለም፡፡ በአፈጻጸሙ ላይ ባሉት ጉድለቶች ከመነጋገርና ፌዴራሊዝምን ከመተቸት ባለፈ ‹‹አሀዳዊ እንሁን›› የሚለው አተካራ ድምፁ ቀንሷል፡፡ ቢያንስ ከምርጫ 97 ወዲህ በምርጫ ክርክር ወቅት የፌዴራል ሥርዓቱ ድክመት ላይ ከሚነሳ ትችት ያለፈ፣ ፌዴራሊዝም አጥፊያችን ነው ብሎ ፊት ለፊት የሞገተ የፖለቲካ ኃይል አልታየም፡፡ አልፎ አልፎ የሚሰማ ድምፅ ቢኖርም የፌዴራል ሥርዓት ምንነትን ካለመረዳት የመነጨ እንደሆነ ይታሰባል፡፡

ከዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም መርህ አንፃር ሥርዓቱ ይበልጥ አሳታፊና የአናሳዎችን ጥቅም የሚያስከብር መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ የፖለቲካ ሥልጣንን በመካፈል እንደ ቋንቋ፣ ታሪክና ባህል ያሉ ማንነቶችን በማጉላት ረገድ ፋይዳው የሚናቅ አይደለም፡፡ ከሁሉ በላይ የልማትና የሀብት ፍትሐዊ ሥርጭትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳው ፌዴራላዊ ሥርዓት መሆኑ ላይ መሟገት ያስቸግራል፡፡ ይህ በብዙዎቹ ባደጉትና በማደግ ላይ ባሉት ፌዴራላዊ ሥርዓት ተከታዮች ዘንድ ሕይወት የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በተናጠል እየወረደበት ያለው ሒስና ትችት ግን አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ እዚህ መድረሱ ይታወቃል፡፡

ሥርዓቱ በተለይ ቋንቋና ብሔር ተኮር መሆኑ፣ ‹‹በአስተዳደር የየራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣንና መዋቅር ያላቸው ክልሎች በጋራ የሰየሙት አንድ ፌዴራላዊ መንግሥት ይኖራቸዋል፤›› ከሚለው ወደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመምጣት እሳቤ ይልቅ፣ መለያየትና ራሱን የቻለ መንግሥት መሆን የሚቋምጥ ‹‹አካል›› እንዲበረክት አድርጓል የሚሉ አሉ፡፡ ገና ሕገ መንግሥቱ የፀደቀ ሰሞን እንግሊዝ አገር የሚታተመው ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት አንድ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር፡፡ ‹‹የፖለቲካ ሥልጣን ከማዕከላዊ መንግሥት በየክልሉና በየጎሳው ለተፈጠሩ ሹማምንት ማከፋፈልና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል የተባለ መፍትሔ በአንድ ወቅት በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ያልነበረው ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉትዘመናዊመሪዎች ግን በአዲስ ፋሽን ተግባራዊ ይሆናል፤›› ብሎ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 39 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ደንግጓል፡፡ ይህ መብት ተፈጻሚ የሚሆንበት የራሱ ቅድመ ሁኔታዎችና ሕዝበ ውሳኔዎች ያሉት ቢሆንም፣ ብዙዎች ‹‹አገሪቱን ለብተና የሚጋብዝና አፍራሽ ነው›› የሚሉት፡፡ ኢሕአዴግና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግን ‹‹የሕዝቦች ዋስትና›› መሆኑን አስረግጠው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ አገሪቱ ከሞላ ጎደል ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ፌዴራላዊ ሥርዓት እያራመደች መጥታ እንኳ፣ አሁን የመገንጠል (በተለይ የማንነት ጥያቄ) የሚያነሱ ብሔሮች ወይም ወኪል ፖለቲከኞች ቁጥር አልቀነሰም፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) 43 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ጎልማሳ ድርጅት ሲሆን፣ አንድ ጊዜ ያዝ ሌላ ጊዜ ለቀቅ እያደረገም ቢሆን ‹‹የኦሮሞ ነፃነት›› ጥያቄን እንዳነገበ ነው፡፡ ጥያቄው በረገበ ጊዜ እንኳን ‹‹ኦሮሞ ለመቶ ዓመታት ያጣውን የሥልጣን ባለቤትነት ያስመልስ›› እያለእውነተኛ ፌዴራሊዝም የለም በማለት ብዙዎችን ከጎኑ ለማሠለፍ ይቀሰቅሳል፡፡

የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ለቋንቋና ለማንነት በሰጠው የተንቦረቀቀ የሥልጣን መለያ ምክንያት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአስተዳደር አመቺነትና የመሠረተ ልማት ሁኔታ እንኳን ታሳቢ ሳይደረግ ሁሉም እንደ ጉንዳን ‹‹ብሔሩን›› እየፈለገ የሚቧደን ሆኗል፡፡ እነሆ 26 ዓመታት በኋላ እንኳን ለሺሕ ዓመታት ከአማራ ጋር የኖረው ቅማንት ‹‹ማንነቴ ሌላ ነው›› በማለት የራሴ ዞን፣ ወረዳ ወይም ክልል ይኑረኝ በማለት ሕዝብ ውሳኔ አካሂዷል፡፡ አወዛጋቢው የጎንደርና የትግራይ የጋራ ቆላማ ድንበር አካባቢ ከጋራና ከኢትዮጵያዊ ሀብትነቱ በላይ ‹‹በማንነት ጥያቄ›› ስም ጠፍንጎ ሰንብቷል፡፡

ይኼ የብሔር ፍጥጫ ሌላም መገለጫ አለው፡፡ ዛሬ ደቡብ በሚባለው ክልል 56 የማያንሱ ብሔረሰቦች እንዳሉ ይነገራል፡፡ አብዛኛዎቹ እነዚህ ሕዝቦች ተቀራራቢና አንድ ቤተሰብ ያለው ቋንቋ አላቸው፡፡ በባህል፣ በወግና በታሪክም የሚቀራረቡ ናቸው፡፡ ይሁንና ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት 16 የማያንሱ የማንነት ጥያቄዎች ተነስተው አጋጭተዋል፣ አከራክረዋል፡፡ ቢያንስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበው ውድቅ ተደርገዋል፡፡

ዛሬ ተራው የሌሎች ብሔረሰቦች ሆኖ ተደጋጋሚ ጥያቄ አለ፡፡ በጋምቤላ ዓመታትን እየተሻገረ ያለው የኑዌርና የአኙዋ ፍጥጫ በመጠፋፋት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን›› እንዲሉ ዓለም ወደ አንድ ትልቅ የጋራ ማኅበረሰብ ለመሰባሰብ ስባትል፣ በእኛ አገር ሁሉም በጎሳ ቆጡ ሥር ተጠልሎ የበለጠ ይናቆር ይዟል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንፃራዊነት ‹‹ብዙኃን›› የሚባለው በርታ ተጭኖናል የሚሉ የጉሙዝ፣ የማኦና የኮሞ ልሂቃን ጥያቄ አለ፡፡ አፋርና ሶማሌም ቢሆን (በተለይ ከኦሮሚያ አጎራባች ወረዳዎች ጋር) ግጭት እየተነሳ የሰው ሕይወት የሚያስጠፋው መሬትና ውኃ ይምሰል እንጂ ‹‹የእኔ ነው›› ባይነት ውጤት ነው፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ በግልጽ እንደታየው ጥያቄው የመብት ገጽታ ያለው ነው፡፡ በዚህ ሰበብ በተነሳ ሁከት የጠፋ ሕይወት፣ የወደመ ንብረትና ሀብት በቀጥታ ያነጣጠረው ግን በክልሉ በሚኖሩና ኢንቨስት ባደረጉ የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይ ነው፡፡ በዚህ መዘዝ ሀብት ያላቸው ቀርቶ ዩኒቨርሲቲን በመሰሉ በክልሉ ያሉ የፌዴራል ተቋማት የሚሠሩ ተቀጣሪዎች ‹‹ጎመን በጤና›› በማለት ክልሉን በፍራቻ እያዩ እንደሆነ ሲነገር ነበር፡፡

እንግዲህ በታሪክ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተዋግተዋል ወይም የጠላትነት ስሜት ከጥንትም ቢሆን ተፈጥሮባቸዋል የሚባሉ (የጣሊያን፣ የግብፅ፣ የቱርክና መሰል አገሮች) ባለሀብቶች በዋና ከተማዋና በአንዳንድ ክልሎች እንደፈለጉ ሲያለሙና ሲኖሩ፣ ‹‹አይዟችሁ›› ከማለት በቀር ይህ ነው የሚባል ችግር ገጥሟቸው አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር ካለ ክልል ውጣ/ግባ መባባል ግን በእጅጉ የሚያሳፍር የጎሳ ፌዴራሊዝም ውጤት መሆኑን አለማመን አውቆ መተኛት ነው፡፡ አስገራሚው ነገር የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ተጠቅሞ ኅብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር የተሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አለማምጣቱ ነው፡፡ ሚዲያው፣ መንግሥትና አንዳንዱ ፖለቲከኛ ‹‹ለአፍ ያህል›› አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል ቢሉም፣ ውጤቱ የተገላቢጦሽ እየመሰለ መምጣቱ ነው፡፡ ለዚህ መገለጫ የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ለመፍትሔው በጋራ ብንነጋገር እሻለሁና ጥቂት ነጥቦችን ልጠቃቅስ፡፡ ከዓመታት በፊት በጋምቤላ ክልል አቦቦ አካባቢ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር ሲጫወት፣ ናይጄሪያን በመደገፍ ስለኢትዮጵያ አያገባኝም በሚሉ ሁከት አስነሽዎች ምክንያት ሕይወት ጠፍቶ ንብረት የወደመው ለምንድነው?

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት የክልሉ ተወላጅ የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞችና የበታች ኃላፊዎች ጭምር ቢሮ እየዘጉ፣ ሁከቱን ከመቃወም ይልቅ ዝም እያሉ ሲያልፉ የነበሩት በምን ይሆን? መንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት ነው›› ቢለውም በየቦታው የሚነሳው የማንነት ጥያቄ፣ በብሔር ስም የይገባናል ጩኸት የምን ውጤት ነው? የአንድነት ወይስ የመነጠል? ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተገንብቷል ከተባለ የኖረውን ቁስል ያውም በተዛባ ፍረጃ እያከከ ከክልሌ ውጣ፣ ወይም እዚህ እንዳትደርስ የሚለው ለምን በዛ? ዕውን አሁን ለትልቁም ሆነ ለትንሹ ባለሀብት የተሟላ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ዋስትናና ልበ ሙሉነት አለ? በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የጋራ ድምፅና እኩልነት የሰፈነበት አወቃቀር ማስፈን ነው ፌዴራሊዝም ማለት፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህን ያሳያልን? ወዘተ. እያሉ ማንሳት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በጎ ጎኖች ተብለው ከሚገለጹት እሴቶች በላይ ብሔር ተኮርና ‹‹ልዩነትን አቀንቃኝነቱ›› አሁን ዋጋ እያስከፈለ ይመስለኛል፡፡ ለአብነት በአንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የተጠቃለሉ ዘጠኝ ክልሎች ቢኖሩም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከአገር አቀፉ ይልቅ የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልና መስመሩም ተደጋግሞ ሲቀነቀን ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፍፁም በትውልዱ ውስጥ አንድነትን ሊፈጥር አይችልም፡፡ ከአገር ይልቅ የማንነቱ ናፍቆት እያዞረ ከሚደፋው ትንንሽ ‹‹ወሬ›› በስተቀር፡፡ ለመሆኑ ዓለም ነጭና ቀይ ነጠብጣብ ያለውን የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ እንጂ የኒውዮርክ ወይም የሎስ አንጀለስን ያውቃልን? አሜሪካዊስ ቢሆን? በሌላ በኩል የአገሪቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት ክልሎችን ሲያደራጅ ግልጽና የማያሻማ መሥፈርት አለመኖሩም እያደር ራስ ምታት እየሆነ ነው፡፡ በግሌ ባላምንበትም በጎሳ ወይም በብሔረሰብ እንደራጅ እንዳይባል ሁሉንም ብሔረሰቦች በክልል ደረጃ ዕውቅና አልሰጠም፡፡ ሁሉንም በዘጠኝ ቋቶች ውስጥ ከቷልና፡፡ ጂኦግራፊያዊ መሥፈርትን ያገናዘበ እንዳይባልም ገብረ ጉራቻ ያለውን የሰላሌ ኦሮሞ ከቦረናው፣ ወይም መተማና ቋራ ጫፍ ያለውን አማራ ከመንዝ ጋር አቆራኝቶታል፡፡ በዚህ ምክንያትም ከአገራዊ መልካም ግንኙነት፣ ለኑሮ ካለ አመቺነትና ቅርበት ይልቅ ትስስሩን በማንነት ላይ ብቻ ጠፍንጎ ያሰረ ትውልድ እየተፈጠረ እንዲመጣ ሆኗል፡፡

አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ውስጥ አልፋና ኦሜጋ ሆነው የተሳሉት ‹‹የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› ግልጽ ያልሆነ ትርጓሜንም ይተቹታል፡፡ / ዘውዱ ውብ እንግዳ የተባሉ ምሁር ‹‹የፌዴራል መንግሥት ታሪካዊ አመጣጥ›› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 260 ላይ እግዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለመረጡዋቸው ስያሜዎች ግልጽ የሆነ ፍቺ ወይም ማብራሪያ አልተሰጣቸውም፡፡ የትኛው ስያሜ በየትኛው ሥር እንደሚካተት የሚያሳይ ዝርዝር ማብራሪያ የለም፡፡ በሌላ አገላለጽብሔረሰብበብሔር ውስጥ ይካተታል? ወይስ በተቃራኒው? ‹ሕዝብስበብሔር ውስጥ ወይስ በተቃራኒው? ይህንን ነጥብ በተመለከተ ትንሽ ፍንጭ የሚሰጠው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ንዑስ ቁጥር 5 ውስጥየጋራ ባህል፣ ሊግባቡ የሚችሉበት የጋራ ቋንቋያላቸው የሚለው ነው፡፡ ይህም ቢሆን ለየትኛው (ለብሔር፣ ለብሔረሰብ ወይም ለሕዝብ) የተሰጠ ስያሜ እንደሆነ ካለመታወቁ ባሻገር አገላለጾቹ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጂኦግራፊያዊ ገጽታዎችን ያጣጣመ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡››

የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መጀመር ኢሕአዴግንና መንግሥትን ያስመሰግን እንደሆነ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሥርዓቱን እንከኖች እየነቀሱ ከፍጥጫና ቀስ በቀስ ከሚደፈርስ አገራዊ የሥጋት ስሜት መውጣት ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡ በቀዳሚነት ፌዴራሊዝም ያለእውነተኛ ዴሞክራሲ አይረጋምና በጥልቅ ይታሰብበት፡፡ በሌላ በኩል ጎሳ ተኮርና ብሔር አቀንቃኝ ፌዴራሊዝም ካለገደብ ሲለጠጥ፣ በሌላው ዓለም ያመጣውን ቀውስ መርምረን እኛ የቆምንበትን መሠረት እንፈትሽ፡፡ ድክመቱን እናርም፣ ጥንካሬውን እናስቀጥል፡፡ ፌዴራሊዝም ግን ያብብ፣ ይጠናከር፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተገንብቷል እያልን መፍረክረክ ግን ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...