Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ አፈጻጸም በማሳየት ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በስምንት ወራት 42 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው በዓመቱ ከሚጠበቀው 240 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ነው

የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር በስምንት ወራት ውስጥ የተከናወነው የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ አፈጻጸሙን በተመለከተ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከዘርፉ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ በ42.5 ሚሊዮን ዶላር ተወስኖ፣ ከዕቅዱም የ18 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቦበታል፡፡

ሚኒስቴሩ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ በጀት ዓመት ውስጥ ከቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ከ240 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም፣ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ የተገኘው ግን 42.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሆኗል፡፡ 700 ሺሕ ገደማ በግ፣ ፍየል፣ ግመልና የቀንድ ከብቶችን ለመላክ ቢታሰብም፣ ሊላክ የቻለው ግን 219 ሺሕ የሚጠጋ ብዛት ያለው የቁም እንስሳት ሀብት ነው፡፡ ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቆዳና ሌጦ 11 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱም ታውቋል፡፡

በጥር ወር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የሚኒስቴሩ ሪፖርት፣ በመንፈቀ ዓመቱ የ38 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት የተጠናቀቀው የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ዘርፍ የዕቅዱን 17 በመቶ እንዳከናወነ አመላክቶ ነበር፡፡

ሚኒስቴሩ ለፓርላማው ባሰማው ሪፖርት በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ስለመጥቀሱ ተዘግቧል፡፡ ሚኒስትር ፈቃዱ በየነ (ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ሪፖርት ውስጥ ከተጠቀሱት የሚኒስቴሩ ክንውኖች መካከል በስድስት ወራት ውስጥ ከቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ይገኛል የተባለው ገቢና በተግባር በተገኘው መካከል የታየው ሰፊ ልዩነት አንዱ ነው፡፡

በስድስቱ ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ ይቀርባሉ የተባሉት የዳልጋ ከብቶች ብዛት 222,891 ነበሩ፡፡ ይሁንና በጊዜው መላክ የተቻለው ግን 40 ሺሕ የማይሞላ ከመሆኑም ባሻገር፣ ይገኛል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የ133.8 ሚሊዮን ዶላር የገቢ መጠንም እጅጉን ቀንሶ 24 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ አስገኝቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከታቀደው ውስጥ 18 በመቶ እንኳ የማይሞላ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

 በግና ፍየልም ቢሆን፣ የዳልጋ ከብቶቹን ያህል የከፋ አይሁን እንጂ ከታቀደው አኳያ ዝቅተኛ ውጤት አስመዝገበዋል፡፡ በመንፈቀ ዓመቱ ሊላክ የታቀደው የበግና ፍየል ቁጥር ከ300 ሺሕ በላይ ነበር፡፡ በክንውኑ ግን 160,750 በጎችና ፍየሎች ለውጭ ገበያ ቀርበው፣ ከአሥር ሚሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ ያላለ ገቢ አስገኝተዋል፡፡ 40 ሺሕ ገደማ ግመል ለመላክ ታቅዶ 7,671 ግመሎች ብቻ በመላካቸው፣ ከታቀደው 36 ሚሊዮን ዶላር አኳያ ዝቅተኛውን የ3.8 ሚሊዮን ዶላር ብቻ አስገኝተዋል፡፡

በጠቅላላው ከቁም እንስሳት የወጪ ንግድ የተገኘው የስድስት ወራት ገቢ 38 ሚሊዮን ዶላር ላይ ተወነስኗል፡፡ ይሁንና የዳልጋ ከብት፣ በግና ፍየል፣ ግመልና የዶሮ ጫጩቶችን ወደ ውጭ በመላክ ይገኛል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ገቢ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ቢሆንም፣ በአፈጻጸሙ ግን 38 ሚሊዮን ዶላር ላይ ተወስኗል፡፡ ይህ እንግዲህ ከግመል ብቻ እንደሚገኝ ይጠበቅ የነበረ የገቢ መጠን ነው፡፡ ምንም እንኳ ሪፖርቱ ከሥጋ ኤክስፖርት የተገኘውን የወጪ ንግድ ገቢ ባያመላክትም፣ ከ81 ሺሕ ቶን ሥጋና 251 ቶን ተረፈ ሥጋ የምርመራ ሰርቲፊኬት ተሰጥቶት ለውጭ ገበያ መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡

በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየው ችግር የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ነው፡፡ በርካታ የቁም እንስሳት ሀብት በኮንትሮባንድ እየተነዳ የሚወጣው ወደ ሶማሌላንድ ስለመሆኑም በሰፊው ሲገለጽ የከረመ ጉዳይ ነው፡፡ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ በሚጋዘው የቁም ከብት አማካይነት በምሥራቅ አፍሪካ ከቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የቁም እንስሳት ላኪ አገሮች ተርታ መሠለፏም ይታወቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው የአፍሪካ ከፍተኛ የቁም እንስሳት ላኪ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ በ85 ሚሊዮን ዶላር ከአሥር ዋና ዋና አገሮች ውስጥ በሰባተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ ቢያስችላትም፣ እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያና ሶማሌላንድ ያሉት አገሮች ግን የመጀመርያዎቹን ደረጃዎች በመያዝ ይመራሉ፡፡ የሶማሊያን ኢኮኖሚ 40 በመቶ የሚሸፍነው የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ከ380 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኝላታል፡፡ ሱዳን ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጪ ንግድ ገቢ የምታገኘው ከዚሁ ከቁም እንስሳት ሀብት የወጪ ንግድ ስለመሆኑ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

 ኢትዮጵያ በአንፃሩ እንዲህ ካለው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ለመራቋ ምክንያት ሆነው ከሚቀርቡት ውስጥ፣ በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅ ብሎም በአሁኑ ወቅት በሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ የቁም እንስሳት ንግድ የተባባሰ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንደሚታይበት ይገለጻል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ባሻገር የእንስሳት በሽታም የኢትዮጵያን የቁም እንስሳት ንግድ ከሚገዳደሩት ውስጥ በሰፊው ይጠቀሳል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮች የተንሰራፉበትን ይኼንን ዘርፍ ለማሻሻልና ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን በገበያ ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ከወራት በፊት የዓለም ባንክ የ170 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች