Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መልካም ዕድልና ሥጋት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አፍሪካውያን በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ሊባል በሚችል ደረጃ በርከት ብለው ፊርማቸውን ያኖሩበት ትልቅ ሰነድ እንደሆነ የተገለጸለት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ባለፈው ሳምንት በሩዋንዳ ርዕሰ ከተማ ኪጋሊ ላይ ተፈርሟል፡፡

ከ55ቱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 አገሮች ይህንን ስምምነት ፈርመዋል፡፡ በአፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው የተባለውን ይህ ሰነድ ሰፊ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተና አፍሪካ በ2063 ትደርስበታለች ተብሎ በአፍሪካ ኅብረት የተቀረፀው አጀንዳ አንድ አካል ነው፡፡

በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ድጋፍ ያገኘው ይህ ሰነድ ናይጄሪያን ጨምሮ 11 የኅብረቱ አባል አገሮች ያልተስማሙበት ወይም በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ከማኖር የተቆጠቡበት መሆኑ ደግሞ ብዥታ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ነገር ግን ስምምነቱ የብዙኃኑን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በኪጋሊው ስብሰባ ላይ ሰነዱን አስመልክቶ በመሪዎች ደረጃ ከተደረገው ምክክር ባሻገር የየአገሮቹ የንግድ ኅብረተሰቡ ተወካዮችም ሐሳባቸውን እንዲያንፀባርቁ ተደርጓል፡፡ ሰነዱ ሥራ ላይ ሲውል የግል ዘርፉ ሚና ምን መሆን እንደሚገባው የተለያዩ አመለካከቶች የተንፀባረቁ ሲሆን፣ ግልጽ ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችም እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ የተገለጸ ቢሆንም እንደ መልካም ዕድል የሚቆጠር ስለመሆኑ ግን በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡  በኪጋሊው ስብሰባ ላይ ተካፍለው የተመለሱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት መሪዎች እንደሚገልጹት፣ አፍሪካውያኑ ያደረጉት ስምምነት በታሪካቸው በርካታ አገሮች የተስማሙበት ታሪካዊ ሰነድ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ኅብረተሰብ አንፃር ይህ ስምምነት መልካም አጋጣሚዎችንና ሥጋቶችን በተመለከተ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊው በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ስምምነቱን ለአፍሪካውያን እንደ መልካም ዕድል የሚወሰድ ነገር ግን በርካታ ሥጋቶች ያሉት እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ አፍሪካውያን ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር መስማማታቸው ሊያስከትል ይችላል የሚለው ሥጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ለአፍሪካውያንም ሆነ ለኢትዮጵያውያን የንግድ ኅብረተሰብ እንደ ዕድል የመጣ ትልቅ ሰነድ ነው፡፡

ይኼ የአፍሪካውያን የነፃ የንግድ ቀጣና መመሥረት ለአፍሪካውያን የሚፈጥረው ትልቅ ዕድል አለው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የአፍሪካውያንን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ በማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይም በማኑፋክቸሪንግ ደረጃ ትልቅ ሞዴል በሚባል ደረጃ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ አገሪቱ የኢንዱስትሪ ዞኖች በመገንባት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሰጠችው ማበረታቻ ዘርፉ የበለጠ እየጎለበተ እንዲሄድና ከነፃ የንግድ ቀጣናው ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች እየተበራከቱ ከሄዱ ደግሞ ስምምነቱ ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራል ብለው እንደሚያምኑ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

በኪጋሊው ጉባዔ ላይ የተገኙት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ በበኩላቸው፣ ይህ የነፃ የንግድ ቀጣና ሥራ ላይ መዋል ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡

ይህንንም ሲያብራሩ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ፋብሪካ እስካሁን የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ገበያን ግብ አድርጎ ያመርት የነበረውን ምርት፣ ይህ ሰነድ ሥራ ላይ ሲውል ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚገመተውን የአፍሪካ ሕዝብ ታሳቢ በማድረግ ስለሚያመርት ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የታጠረውን ምርት ያለምንም ኢምፖርት ታሪፍ ወደ 55ቱ የአፍሪካ አገሮች እንዲገባ የሚያደርግ ስምምነት ስለሚሆን ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል ይላሉ፡፡ የውጭ ባለሀብቶች በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚሳተፉት የገቡበትን አገር ሕዝብ ቁጥር ከግንዛቤ በማስገባት መሆኑን ያስታወሱት ዋና ጸሐፊው፣ አሁን ግን ወደ የትኛውም የአፍሪካ አገር ሲገባ የ1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ገበያን ግብ በማድረግ በመሆኑ በርካታ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ወደ አፍሪካ እንዲመጡ የሚያስችል ስምምነት ነው ብለዋል፡፡ ይህም የአፍሪካን ኢኮኖሚ በማሳደግ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያም በዚህ ስምምነት ለመጠቀም በርካታ አማራጮች ይኖሯታል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪግ ላይ የሰጠችውን ትኩረት በማጠናከር አፍሪካ ውስጥ ያለውን ገበያ የማስፈት ዕድሏ እንደ መልካም አጋጣሚ መወሰድ እንዳለበት የንግድ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች ጠቁመዋል፡፡

እንደ ንግድ ምክር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ኢትዮጵያ ይህንን ሰነድ የፈረመች በመሆኑ፣ ከሰነዱ ተጠቃሚ ለመሆን በርትታ መሥራት ይገባታል ብለው ያነሱዋቸው ነጥቦች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ሰነዱን የተመለከተ ብሔራዊ ስትራቴጂ ማዘጋጀት አለበት የሚለው ይጠቀሳል፡፡ እንዴት ነው ከዚህ ሰነድ በትክክል መጠቀም የሚቻለው? የሚለውን ነገር በደንብ መተንተን የሚያስችልና የግል ዘርፉ በደንብ እዚህ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ የሚችልበት ስትራቴጂ መሆን እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ስትራቴጂ ጠቃሚ የሚሆነውም የትኞቹ ዘርፎች ናቸው ወደ አፍሪካ ገበያ ገብተው የተሻለ ተወዳዳሪ ሊያደርጉን የሚችሉት? በየትኞቹ ቀድመን እንግባ? እንዴት እንግባ? የሰው ኃይል አሰላለፋችንን እንዴት ማድረግ አለብን? ከዚህ የነፃ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚነት ምን ማድረግ አለብን? የሚሉትን ነገሮች በደንብ በዝርዝር የሚቀምር ሰነድ መሆን እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡ ሰነዱ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ጭምር ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባትና በቅርብ ለመነጋገርም በንግድ ምክር ቤቱ በኩል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ሰነድ ያመጣል ተብሎ የሚታሰበው ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ የተለያዩ ሥጋቶች መቀስቀሱ አልቀረም፡፡ እንደ ንግድ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች ገለጻ አፍሪካውያን ኩባንያዎች ጠንካራ ሆነው ካልወጡ ነፃ የግብይት ቀጣና ስምምነቱን ተጠቅመው የውጭ ኩባንያዎች ገብተው ሸቀጦቻቸውን የማራገፍ ዕድል ሊያገኙ ይችላል፡፡ አገሮቹ ይህንን ሥጋት ለመቀነስ ብርቱ የቤት ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የተለያዩ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ያላቸውን አገሮች በዚህ ሰነድ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲጓዙ ማድረግ በራሱ ፈታኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ተወዳዳሪ የንግድ ኅብረተሰብ መፍጠር እንዴት ይቻላል? የሚለው ጉዳይ እንደ ሥጋት የሚቀመጥ ነው፡፡

ሌላው ኃላፊዎቹ እንደ ሥጋት የገለጹት፣ ስምምነቱ በአስገዳጅነት ያስቀመጠው ጉምሩክን የተመለከተው ነጥብ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ከአንዱ የአፍሪካ አገር ወደ ሌላው የአፍሪካ አገር በሚያስገቡት ምርት ላይ ከተጣሉ ቀረጦች ውስጥ 90 በመቶውን እንዲያነሱ ያስገድዳል፡፡ ይህም አገሮች የሚያገኙትን ቀረጥ 90 በመቶ ይቀንሳል፡፡  የዚህን ያህል ገቢ የሚቀንስ ከሆነ አገሮቹ ከዚህ ገቢ መቅረት ጋር ተያይዞ ራሳቸውን እንዴት ያዘጋጃሉ? የሚለው ሥጋት ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአፍሪካ አገሮች 90 በመቶውን ቀረጥ በማንሳታቸው ምክንያት በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ዶላር ያህል ያጣሉ፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው በሚፈጥራቸው ዕድሎች ራሳቸውን አጠናክረው በቀጣዮቹ ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ውስጥ ጊዜ ያጡትን አራት ቢሊዮን ዶላር አራት እጥፍ ያህል መልሰው ማግኘት እንደሚችሉ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

ይህ እንዴት ይተገበራል የሚለው ራሱን የቻለ ሥጋት ነው፡፡ ሌላው ሥጋት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ያሉበትን ችግሮች በጊዜውና እንደ ዘርፎች ችግሮችና ማነቆዎች መፈታትን ይመለከታል፡፡ የኤሌክትሪ ኃይል፣ የፋይናንስ እጥረትና የመሳሰሉ ችግሮች ተፈትተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ዘርፍ መፈጠር እንዳለበት የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ መንገድ ካልተሠራ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚገቡ የውጭ ኩባንያዎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪካ አገሮችን ሸቀጥ ማራገፊያ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡ በ2063 አፍሪካ ወደ አንድ ገንዘብ አጠቃቀም ለመሄድ እየተንደረደረች ስለሆነ የውስጥ አቅማችንን እያጎለበትን መሄድ ካልቻልን የኪጋሊ ስምምነቱ ጠቀሜታው ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ በሰነዱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ለመሆን እያንዳንዱ አገር የውስጥ የቤት ሥራውን መሥራት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡ እንደ ግሉ ዘርፍ ተወካይነታቸውም ሰነዱን ከአገሪቱ የግል ዘርፍ አንፃር በመቃኘት እንዴት ተጠቃሚ ይሆናል? የሚለውን ሥራ በብርቱ የሚሠራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ነጋዴዎችን ማብቃት አለብን ያሉት አቶ መላኩ፣ ‹‹ነጋዴዎቻችንን ማብቃት ሲባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነታቸው ምን ያህል ነው? የሚያመርቱ ምርት የጥራት ደረጃውን ጠብቆ ተወዳዳሪ ለመሆን እየተሠራበት ነው ወይ? የሚለውን በአግባቡ ማየት ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህንን ሥራ በአግባቡ ካልሠራን ለውጭ ኩባንያዎች ሸቀጥ ማራገፊያ እንዳንሆን ያሠጋል፤›› በማለትም ነጋዴዎችን በማብቃት የሚሠራው ሥራ መፍጠን እንደሚኖርበትም ጠቅሰዋል፡፡

አቅሙ ያልተገነባና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱ ያልተረጋገጠ ምርት የሚያመርት ነጋዴ ይዘን አፍሪካ ነፃ ቀጣና ውስጥ መግባት እንደ አንድ ሥጋት የሚወስድ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የእኛ ሥራ ከመንግሥት ጋር ሆነን የነጋዴዎቻችን አቅም እንዲነገባ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ከሥር ጀምሮ መረጃ በመስጠት የእርስ በርስ ፉክክሩን ትቶ ተወዳዳሪነቱ ዓለም አቀፍ መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ የግድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ንግድ ፕሮፌሽናል ሥራ መሆኑን በማስረዳት የሚመጣውን ጫና አልፎ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ብዙ ጊዜ አብዛኛው ነጋዴ እያተረፈ ያለው እጥረትን መሠረት አድርጎ ነው፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ ከዚህ በኋላ ግን እንዲህ ያሉ አሠራሮች አደጋ እንደሚኖራቸው በማስተማርና የነፃ ገበያ ቀጣና ስምምነቱን አስመልክቶ ንግድ ምክር ቤቱ ንግድ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መሠራት እንዳለበት እንደሚያሳውቅም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ‹‹በምንነድፈው ስትራቴጂ ላይ እንዴት የነጋዴዎቻችንን አቅም ገንብተን እንዴት ማብቃት ይቻላል? የሚለውን በማስቀመጥ ተወዳዳሪ የንግድ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ይሠራል፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ስምምነት አስመልክቶ የንግድ ሚኒስትሩ በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) ለመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ የወጪና ገቢ ንግድን በማሳለጥ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን በማሰብ ስምምነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠር የሚኖረውን ከፍተኛ ሚና የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገው ጉዞ የገበያ ዕድሏን በመላ አፍሪካ ሰፊ ስለሚያደርግ የስምምነቱን ጠቀሜታ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ድርድር ሒደት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መንገድ በደረጃ ወደ ትስስሩ የምትገባበትን አካሄድ በግልጽ ማስቀመጧንም ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ከ15 በመቶ ያልበለጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ ከአራት በመቶ ያልበለጠ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ነፃ የንግድ ቀጣናው በምን መልክ እንደሚቋቋም፣ እንዲሁም የመዋቅሩ ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት ውሳኔ የሚሰጠው በቀጣዩ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ ስምምነት በአግባቡ ተግባራዊ ከተደረገ አፍሪካ 3.2 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ባለቤት ያደርጋታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች