Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት የመዘነው ተቋም ከአሥር ዋና አገሮች ሰባተኛዋ ብሏታል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከወራት በፊት በተሰራጩ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ ከዓለም ዋና ዋና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ቀዳሚ የሆነችባቸውን አኃዞች ያጣቀሱ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ሰሞኑን ይፋ የተደረገው አዲስ ሪፖርት ግን ከአፍሪካ አገሮች ሞሮኮን በቀዳሚነት አስቀምጦ ኢትዮጵያ ከአሥር ዋና ዋና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ሰባተኛዋ እንደሆነች አስፍሯል፡፡

ኳንተም ግሎባል ሪሰርች ላብ የተሰኘው አማካሪና የጥናት ኩባንያ ይፋ ባደረገውና ‹‹አፍሪካ ኢንቨስትመንት ኢንዴክስ 2018›› በተሰኘው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት፣ የዚህ ዓመት ዋና ዋና የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገሮች ተብለው ከተለዩት ውስጥ ሞሮኮ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ቦትስዋና፣ ኮት ዲቯር፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ዛምቢያ፣ ኬንያና ሴኔጋል ቅድሚያውን የወሰዱ አሥሩ አገሮች ናቸው፡፡ የኳንተም ግሎባል ሪሰርች ላብ ኩባንያ የአማካሪ ዘርፉን በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት የሚመሩት ምቱሊ ንኩቢ እንደገለጹት፣ ኩባንያው የ54 አፍሪካ አገሮችን የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ ለማሳየት የሚሞክርበትን ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ሪፖርቱ በስድስት ዋና ዋና መመዘኛዎች መሠረት የአገሮችን የውጭ ኢንቨትመንት አቀባበል ደረጃ ያወጣል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ የሥጋት ተጋላጭነት፣ የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታዎች (የዓለም ባንክን የ‹‹ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› ጠቋሚ መለኪያዎች ይጠቀማል)፣ የሥነ ሕዝብ እንዲሁም ሶሻል ካፒታል የተሰኙትን መመዘኛዎች የሚጠቀመው ኳንተም ግሎባል እነዚህን መሥፈርቶች ዋቢ በማድረግ በሚሠራው ትንተና መሠረት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ደረጃ በዚህ ዓመት ሰባተኛ ሆኗል፡፡ ሶሻል ካፒታል ከሚለካባቸው መመዘኛዎች አንዱ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ብዛት እንደሆም ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዕድገት መመዘኛ ኢትዮጵያ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የ8.4 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ቁንጮ ስትሆን፣ አልጄሪያና ሞዛንቢክ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ይከተሏታል፡፡ በገንዘብ አቅርቦት መስፈርት ደግሞ ደቡብ ሱዳን፣ ግብፅና አንጎላ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ በቅደም ተከተላቸው ይዘዋል፡፡

በሥጋት ተጋላጭነት መስፈርት ደግሞ ቦትስዋና ስትመራ ስዋዚላንድና ሞሮኮ ዝቅተኛ የአደጋ ተጋላጭነት በማስመዝገብ ይከተላሉ፡፡ በሥነ ሕዝብ መስፈርት ናይጄሪያ ስትመራ፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ሁለተና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ በሶሻል ካፒታል መመዘኛ ደግሞ ቱኒዚያ 3.4 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን በመያዝ ስትመራ፣ ሲሸልስና ሞሪሺየስ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

.ኤ.አ. በ2016 በአፍሪካ የተመዘገበው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን 59 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ይህ መጠን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣ አኃዝ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ከ54ቱ አገሮች ውስጥ 15ቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመን መሳብ የቻሉ አገሮች ተብለዋል፡፡ በተለይም አንጎላ፣ ግብፅና ናይጄሪያ በውጭ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ ፍላጎት የታየባቸው በመሆን በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ስለመቻላቸው ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ናይጄሪያና አንጎላ ከአሥሩ ዋና ዋና አገሮች ተርታ ውስጥ አልተመደበችም፡፡

ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2016 ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ማስመዝገቧ ቢጠቀስም፣ በደረጃ ግን ሰባተኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በአንፃሩ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ግብፅ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ማስመዝገብ የቻለች ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ግን ወደ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን ማስመዝገቧ ተመልክቷል፡፡

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የተመዘገበው የውጭ ኢንስትመንት መጠን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚያወጣቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአማካይ በየዓመቱ በኢትየጵያ የሚመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንስትመንት መጠን ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡

በኳንተም ግሎባል ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ በሌሎቹ አገሮች የተሻለ አፈጻጸም ከመበለጧ በቀር ይህ ነው የሚባል ችግር አልቀረበባትም፡፡ ኢትዮጵያ በምታስመዘግበው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በተለይም በአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት መስክና በሥነ ሕዝብ መስክ ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ ለውጦች እያሳየች እንደምትገኝ፣ የገንዘብ አቅርቦቷም አወንታዊነት እንደሚታይበት ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የኢኮኖሚ ስፋት አኳያ፣ ከምታሳየው የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በተለይም የመንግሥት የኢንቨስትመንት ድርሻ የኢኮኖሚውን የ40 በመቶ ድርሻ መያዙ፣ እንዲሁም አገሪቱ በየዓመቱ ስታስመዘግብ የቆየችው ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች አገሮች አኳያ ግንባር ቀደም የሚያሰኛት ቢሆንም በሌሎች ሰባተኛ፣ የወለድ ምጣኔ (ከዋጋ ግሽበት ተቀናሽ በተደረገ ስሌት)፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ጉድለትና ሌሎችም ተደማምረው አማካይ የአገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት ላይ ጫና በማሳረፋቸው ከአሥሩ ዋና ዋና አገሮች ሰባተኛ ላይ ሊያስቀምጣት የቻለውን ውጤት አስመዝግባለች፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች