Sunday, April 14, 2024

ብሔራዊ መግባባት እንዴት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. ለአሥራ ሰባት ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ችግር እንደነበረበት፣ ይኼም ችግር የሕዝብን መብት በማክበርና ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ መግለጫው አክሎም በአገሪቱ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ፣ ሁከት የዕለት ተዕለት ክስተት እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በጽሑፍ ካወጣው መግለጫ በተጨማሪ የግንባሩ ብሔራዊ ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት አንድ ላይ ሆነው በሰጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ችግር ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል መንግሥት እስረኞችን እንደሚፈታና በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራውን እስር ቤት ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር መወሰኑን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በሺሕ የሚቆጠሩ እስረኞችን መንግሥት እንደፈታ ይታወሳል፡፡ ከተፈቱ እስረኞች መካከከል ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገኙባቸዋል፡፡

መንግሥት እስረኞችን ለመፍታት በወሰነው ውሳኔ መሠረት በርካቶችን ከእስር በመልቀቁ፣ በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ ብሔራዊ መግባባትን ሊፈጥሩና አገሪቱ ካለችበት ችግር ሊያወጡ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ እንደነበር ሲነገር ተሰምቷል፡፡

መንግሥት በወሰደው ዕርምጃም በርካቶች ሲደሰቱና ይበል የሚሰኝ ዕርምጃ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ችግር መፍታትና መቅረፍ የሚቻለውም እንደዚህ ዓይነት ዕርምጃዎች ሲወሰዱ፣ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ሲያስወግዱ ነው በማለት ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ከኢትዮጵያ አልፎ ትልልቅ የውጭ ሚዲያዎችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች የሚያበረታታ ዕርምጃ እንደሆነ ሲገልጹ ተደምጧል፡፡

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ሳይቀሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ መንግሥታቸው በበጎ ጎኑ እንደሚያየው ጠቁመው ነበር፡፡ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ ያለን ችግር መፍታት የሚቻለው ከአገሪቱ ሕዝብ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት እንጂ በማሰርና በማንገላታት አይደለም፤›› ሲሉም ተደምጠው ነበር፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ከወራት በፊት በሺሕ የሚቆጠሩ እስረኞችን ከእስር መፍታት የሚደነቅና ለአገራዊ መግባባት በር የሚከፍት፣ ብሎም በአገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ዕርምጃ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡

በተመሳሳይ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላብሮቭ የኢትዮጵያ መንግሥት በሺሕ የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታት፣ ለአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ሚናው የጎላ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ጉዳዩ የሚበረታታ መሆኑን፣ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ዕርምጃዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲያሳስቡ ተደምጧል፡፡

መንግሥት እስረኞችን ከመፍታት ባሻገርም በአገሪቱ ሕዝባዊ ውይይት ለማካሄድ እንዳቀደ፣ ለልዩነት ምክንያት የሆኑ አገራዊ ችግሮችን ለማጥበብና ለመፍታት ዝግጁ እንደሆነ ጠቁሞ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ በፊት ከእስር ተፈትተው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ጥቂቶቹን መልሶ በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 12 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል አቶ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ፣ አቶ አንዷለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፣ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቃገኘሁ፣ ወይንሸት ሞላ (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)፣ አቶ ይድነቃቸው አዲስ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አቶ ተፈራ ተስፋዬና አቶ አዲስ ጌታነህ ናቸው፡፡

ግለሰቦቹ  በቁጥጥር ሥር የዋሉት የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወላጅ እናት በመኖሪያ ቤታቸው ባዘጋጁላቸው የምሳ ግብዣ ላይ ተሰብስበው በነበረበት ወቅት መሆኑን ሪፖርተር ለማወቅ ቢችልም፣ የታሰሩበት ምክንያት ግን እስካሁን በውል አልታወቀም፡፡ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉት በኮማንድ ፖስቱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ነገር ግን ኮማንድ ፖስቱ ግለሰቦቹ በምን ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ አልገለጸም፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከታሰሩ ግለሰቦች መካከልም የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመርያ የጣሱ ግለሰቦችና ጥቂት የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸው ነበር፡፡

ምንም እንኳ መንግሥት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ብሎ በርካታ እስረኞችን ከእስር መፍታቱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የተፈቱ ግለሰቦችን እንደገና በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው እየተነገረ ነው፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ መንግሥት አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እስረኞችን እየፈታ ባለበት ወቅት ይኼን መሰል ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ተሰበሰቡ ብሎ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ፍሬ ነገሩ ተሰብስበው ምን ሠሩ ነው? የተሰበሰቡት ለምሳ ግብዣ እንጂ ለሽብር አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

‹‹በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ሲባል መንግሥት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለብኝ ብሎ በወሰነው መሠረት እስረኞችን ለቋል፡፡ ይኼ የሚደነቅ ተግባር ነው፡፡ አሁን ግን ውኃ ቀጠነ ብሎ ግለሰቦችን እየተከታተለ በቁጥጥር ሥር ማዋል ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ይኼን ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ መንግሥት ለራሱም ጉዳት እንዳለው አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡  የአገሪቱን ገጽታ ጥላሸት ከመቀባት ውጪ የሚገኘው ሌላ ጥቅም እንደሌለም አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ግለሰቦች ትኩረት የሚስቡ ናቸው፡፡ እነሱን በቁጥጥር ሥር አዋልክ ማለት የአገሪቱን ገጽታ ጥላሸት ቀባህ ማለት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት በገባው ቃል ኪዳን መሠረት እስረኞችን በመፍታት ሕዝቡ ደስተኛ ሆኗል ይላሉ፡፡

የእነሱ መፈታት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ከማስፋት ባሻገር አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ለመውጣት አንዱ የመፍትሔ ዕርምጃ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፣ መንግሥት አሁንም በሆደ ባሻነት ሰዎችን ማሰር የለበትም ብለዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ለአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የፖለቲካ ፍላጎት እንጂ በግለሰቦች ጥፋት ተጠምዶ መዋል የለበትም፡፡ እነሱን በመምከርና በማስተማር ጥፋት ካለባቸውም እንዲታረሙ ማድረግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በበኩላቸው፣ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን እያሰበና እየወሰደ ባለበት ወቅት፣ የተፈቱና በሕዝቡ ዘንድ ዕውቅና ያገኙ ግለሰቦችን መልሶ በቁጥጥር ሥር ማዋል የለበትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር መንግሥት እየሠራ ባለት ወቅት፣ ዜጎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ይኼ ዓይነቱ ዕርምጃ የሚቆም ከሆነ አሁንም በአገሪቱ ያለውን ቀውስ ለመፍታት አዳጋች ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቀቅ ባወጣው መግለጫ፣ በግንባሩ ብሔራዊ ድርጅቶች ጭምር የጎራ መከፋፈል እንደነበርና ይኼ ደግሞ በመላ አገሪቱ ቀውስ እያስከተለ እንደሆነ ጠቁሞ ነበር፡፡

በአገሪቱ የሚታየውን በጎራ የመከፋፈል ችግር በማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለአገሩና አንድነቱ እንዲያስብና እንዲጨነቅ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንደሚገባ ተንታኞቹ ተናግረዋል፡፡ የብሔር ዝንባሌው እያደገ አገራዊ እሳቤው እየመነመነና እየቀነሰ እንደመጣም አክለው ገልጸዋል፡፡ ይኼን መሰሉን ችግር መፍታትና አገሪቱ ካለችበት ቀውስ ማውጣት የሚቻለው፣ ብሔራዊ መግባባት ሲፈጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት አሁንም በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ሊያዘጋጅ እንዳሰበ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይኼን ዓይነቱ መድረክ ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ቢታሰብም፣ ወደዚህ የውይይት መድረክ ከመሄድ በፊት መንግሥት አሁንም በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡ በዋነኛነት አሁንም በእስር ላይ ያሉ ዜጎችን ከመፍታት ጀምሮ፣ የተፈቱ ግለሰቦችን ዳግመኛ ማስር እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር መሠራት አለበት ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ ሌላው ጉዳይ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ዓለማቸውን ለሕዝቡ የሚያሳውቁበትን መንገድ መፍጠር አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች መፍታት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከቀዬአቸው የተፈናቁሉ ዜጎችን መመለስና በዘላቂነት ጊዜ ሳይሰጠው ማቋቋም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ ልሂቃን ዘንድ የሚታዩ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች የበኩላቸውን አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ይነገራል፡፡ በቤተሰብ ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች መገናኛዎችና በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚደረጉ የሐሳብ መንሸራሸሮች የሚስተዋሉ እሰጥ አገባዎች ለብሔራዊ መግባባት የማይረዱ መሆናቸው በስፋት ይነገራል፡፡ በየጎራው በመቧደን በፌስቡክ የሚታየው መዘላለፍና አላስፈላጊ ንትርክ ከመቸውም ጊዜ በላይ እየተባባሰበት መምጣቱ፣ ፖለቲካውን ተስፋ አስቆራጭ ያደረገባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በአገር ጉዳይ አንድ ዓይነት አቋም ሊኖር ባይችልም፣ ቢያንስ የሚያግባባ የጋራ ነገር መጥፋቱ አሳዛኝ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑ ነገር ግን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንጋፋ ምሁር፣ ብሔራዊ መግባባት ሊኖር የሚችለው በትንሹ ለመነጋገር እንኳን የሚያስችል መቀራረብ ሲኖር ነው ይላሉ፡፡ እሳቸው የወጣትነት ዘመናቸውን ሲያስታውሱ በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ተማሪዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢመጡም፣ በአገር ጉዳይ የጋራ ራዕይ እንደነበራቸው ያስረዳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የመደብ ልዩነት ቢኖር እንኳ፣ ከመሣፍንቱ ወይም ከባላባቱ መደብ በመንሸራተት የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም የሚያራምዱ ነበሩ ሲሉም ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ግን ከማንነት ወጣ ብሎ አገርን ማየት የሚሳናቸው መብዛታቸው አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ለአገር የጋራ ልብ ከሌለ ተስፋችንን እንደተነጠቅን መቁጠር ይኖርብናል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

በመንግሥት ሥራ በኃላፊነት ጭምር ለረዥም ዓመታት መሥራታቸውን የሚናገሩት አቶ ሳህሌ ዓለሙ፣ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚቻለው ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ሲቻል ነው ይላሉ፡፡ ልዩነት ሳይከበርና ሐሳብ በነፃነት ሳይንሸራሸር እንዴት ስለብሔራዊ መግባባት መነጋገር ይቻላል ይላሉ፡፡ ‹‹አሁን እኮ ከልጆች ጋርም በፅሞና መነጋገር እያቃተ ነው፡፡ ወላጅና ቤተሰብ መግባባት ሳይችል እንዴት ሆኖ ነው ፖለቲከኞች የሚግባቡት? እኔ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበኝ የሐሳብ ነፃነት ነው፡፡ አሁን እንደማየው ግን በነፃነት ሐሳብህን ስታቀርብ ውርጅብኝ የሚመጣበህ ከአየቅጣጫው ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከታች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ እንደገና ማኅበረሰባዊ ግንባታ ያስፈልጋል ብለው፣ ይኼንን ሳያሟሉ በባዶ ሜዳ ብሔራዊ መግባባት እያሉ ማላዘን የቁራ ጩኸት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -