Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቡድን ሃያ አገሮች በአዲስ አበባ ስምምነት የተደረሰባቸውን ሦስት የዘላቂ ልማት ግቦች እንደሚቀበሉ...

የቡድን ሃያ አገሮች በአዲስ አበባ ስምምነት የተደረሰባቸውን ሦስት የዘላቂ ልማት ግቦች እንደሚቀበሉ ይፋ አደረጉ

ቀን:

የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የዓለም ሃያ አገሮችን በመወከል የተመሠረተው የቡድን ሃያ አገሮች ስብስብ ካለፈው እሑድ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ያካሄደው መደበኛ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ አዲስ አበባ ባስተናገደችው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ወቅት ይፋ ከተደረጉት የድርጊት አጀንዳዎች መካከል ሦስቱን እንደሚቀበል ይፋ አድርጓል፡፡

የቡድን ሃያ አገሮች በቱርክ አንታልያ ከተማ ባደረጉት ጉባዔ ባወጡት መግለጫ መሠረት፣ የአዲስ አበባውን የተግባር አጀንዳ ሰነድ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ሰነዱ ካሰፈራቸው 134 የስምምነት አንቀጾች መካከል በመጪዎቹ 15 ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች መሠረት፣ ድህነትን ከዓለም ለማጥፋት የተደረሰውን ስምምነት እንደሚቀበሉና እንደሚደግፉ ቡድን ሃያዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ ስምምነት የተደረሰበት የተግባር አጀንዳ ሰነድ ረሃብንና በምግብ እጦት ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን ከዓለም ለማጥፋት ያለመ ሲሆን፣ በተለይ ከ800 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚገኝበትን አሳሳቢ የምግብ ዕጦት ችግር ለማቃለል ያለመ ነው፡፡

በቡድን ሃያ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሌላው አንቀጽ ከስደተኛ ሠራተኞች ወደ አገሮቻቸው የሚላከው የውጭ ኃዋላን የሚመለከተው ነው፡፡ በአዲስ አበባው የተግባር አጀንዳ ስምምነት መሠረት በመጪዎቹ 15 ዓመታት ውስጥ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ወደየአገሮቻቸው የሚልኩት የውጭ ኃዋላ ለአገልግሎት የሚከፈልበት ወጪ ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህ ወጪ ከሦስት በመቶና በየኮሪደሩ በሚደረገው ዝውውር ሳቢያ የሚጠየቀው የአገልግሎት ክፍያ ከአምስት በመቶ እንዳይበልጥ ይደረጋል የሚለው አንቀጽ ተካቷል፡፡ ቡድን ሃያዎች በዚህ አንቀጽ ላይ ስምምነታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ወደ በርካታ ታዳጊና ደሃ አገሮች የሚላከው የውጭ ኃዋላ በአማካይ ከ12 እስከ 20 ከመቶ አገልግሎት ክፍያ የሚጠየቅበት መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑን ከእያንዳንዱ አንድ ዶላር ኃዋላ ላይ ከ12 እስከ 20 ከመቶ ለኃዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች ሲከፈል የቆየበት አካሄድ ይለወጣል ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ተደርጎ ከነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተግባር አጀንዳ አንዱ የሆነው ዘላቂ ፋይናንስ ምንጮችን ለማጠናከርና በመንግሥታትና በግል ዘርፍ መካከል የጋራ የፋይናንስ አቅርቦትና መሰል አካሄዶች የተቃኙበት የአዲስ አበባው የተግባር አጀንዳን እንደሚቀበሉ፣ በቱርክ የወቅቱ ፕሬዚዳንትነት የተመሩት የቡድን ሃያ አገሮች ይፋ አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባው ጉባዔ በፋይናንስ ምንጭነት ከተቀመጡት አማራጮች መካከል አበዳሪ ተቋማት ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን ያሉትን የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች የቀረቡበት እንደሆነ አይዘነጋም፡፡

የአዲስ አበባውን የተግባር አጀንዳ ለመጪዎቹ የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያነት የሚያስፈልገው የፋይናንስ መጠን ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ይህንን ያህል ገንዘብ በ15 ዓመታት ውስጥ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል እንቆቅልሽ ይመስላል፡፡ የዘላቂ ልማት ግቦች ከዚህ ቀደም ሲተገበሩ ከቆዩት የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች በተለየ ባደጉም ባላደጉም አገሮች ዘንድ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የቡድን ሃያ አገሮች በቱርክ ያደረጉትን ጉባዔ ሲያጠቃልሉ በኢኮኖሚ መስክ ትኩረት እንደሚያደርጉባቸው ካሳወቋቸው ነጥቦች መካከል፣ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በአባል አገሮች ውስጥ የ2.1 በመቶ ዓመታዊ አኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻል አንዱ ነው፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በአገሮች ውስጥ የሚታዩ የገቢ ልዩነቶችን በማጥበብ እኩልነትን ማስፈን፣ በመረጃ መረብ አማካይነት የሚደረጉ ዝርፊያዎችን መቆጣጠርና የመሳሰሉት ስምምነት ያደረጉባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡

ጉባዔው ሊጀመር አንድ ቀን ሲቀረው በፓሪስ የደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት ላይ ባለዘጠኝ ነጥብ አስቸኳይ መግለጫ ያወጡት ቡድን ሃያዎች፣ አሸባሪዎችን ለመግታት የሚወስዷቸውን ዕርምጃዎችና ትብብሮችን ይፋ አድርገዋል፡፡

የቡድን ሃያ አገሮች ስብስብ እንዲመሠረት የጠነሰሱት የቀድሞው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓውል ማርቲን ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ ማገባደጃ ላይ በዓለም ላይ በተለይም በእስያ አገሮች ዘንድ የደረሰውን ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስና ሌሎችም ምስቅልቅሎች የቡድን ሰባት አገሮች ሊፈቱ ባለመቻላቸው፣ በዓለም ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው ሃያ አገሮች ስብስብ እንዲመሠረት ባደረጉት ጥሪ መሠረት ቡድን ሃያ ተመሥርቷል፡፡ ይሁንና ይህም ቡድን ቢሆን እንደ እ.ኤ.አ. በ2008 የተከሰተውን የዓለም የፋይናንስ ቀውስና በዚያም ሰበብ የደረሰውን የኢኮኖሚ ቀውስ ማስቀረት አልተቻለውም፡፡ ለቀውሱ ሰበብ ያደረጋቸውን እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያሉ ተቋማት ከሥረ መሠረታቸው ለማሻሻል ቢወጥንም እስካሁን ብዙም አልተራመደም፡፡

ቡድን ሃያ የዓለምን 85 በመቶ የተቆጣጠሩና 80 በመቶ የዓለም ንግድን የያዙ አገሮች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ ሁለት ሦስተኛውን የዓለም ሕዝብ የሚወክሉ ግዙፍ አገሮች የሚገኙበት ተቋም ነው፡፡

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ቱርክ አንታልያ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሕክምናው ዘርፍ የባዮ ሜዲካል ምሕንድስና ተደራሽነት

አቶ አሸብር ወርቄ የኢትዮጵያ ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮችና ቴክኖሎጂስቶች ሙያ...

1498ኛው የመውሊድ ክብረ በዓል

ዛሬ ረቡዕ በዓመተ ሒጅራ አቆጣጠር ረቢ-አል-አወል 12ኛው ቀን (የጨረቃ...

ዕልቂት ያስከተለው የሊቢያ ጎርፍና የተገኙት አዲሶቹ ቅርሶች

በሙዓመር ጋዳፊ ዘመን የኑሮ ሁኔታዋ በከፍተኛ ደረጃ ትጠቀስ የነበረችውና...

‹‹ቱሪዝም ለኢኮኖሚያችንም ሆነ ለኅብረተሰባችን ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም››

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዙብራ ፖሎካሽቪሉ...