‹‹አውሮፕላናችንን በቦምብ ያጋዩትን ሽብርተኞች እንበቀላቸዋለን››
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ፣ በውስጡ በተጠመደ ፈንጂ ምክንያት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ማክሰኞ ኅዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የሩሲያ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ማረጋገጫ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከግብፅ በመዝናኛ ከተማ ከሻርም አል ሼክ የተነሳው የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን (ሜትሮጄት) የተከሰከሰው የተጠመደበት ቦምብ ፈንድቶ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን በግብፅ ሲናይ ግዛት ውስጥ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን እንዲያጡ የተደረጉ 224 ዜጎችን መንግሥታቸው ይበቀልላቸዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም የአገሪቱ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች አደን እንዲጀምሩ አዘዋል፡፡ ‹‹የትም ቦታ ቢደበቁ እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህች ፕላኔት ውስጥ የገቡበት ገብተን እንቀጣቸዋለን፤›› ሲሉ በኃይለ ቃል ተናግረዋል፡፡ በሩሲያ መንግሥት መረጃ መሠረት አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን ፈንጂ አውሮፕላኑ ውስጥ ተጠምዶ ነበር፡፡ የዚህን የሽብር ተግባር ፈጻሚዎች መበቀል ደግሞ የመጀመሪያው የሩሲያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በምሥሉ ላይ ፕሬዚዳንት ፑቲንና የወደቀው አውሮፕላን ይታያሉ፡፡