በአዲስ አበባ ሸገር ሮተሪና በህንድ ሮተሪ ክለብ ትብርር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 21 በጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች ከዛሬ ኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀጣይ አሥር ቀናት በዘውዲቱ መታሰቢያ፣ በየካቲት 12 እንዲሁም በደብረ ብርሃን ሆስፒታል እንደሚያገለግሉ ሮተሪ አዲስ አበባ ሸገር ክለብ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በበጎ ፈቃደኝነት ለተጠቀሱት ቀናት በኢትዮጵያ ለማገልገል የመጡት ህንዳውያን ዶክተሮች እንደ እሳት ባሉ ድንገተኛ አደጋ ለደረሰባቸው የፕላስቲክ ሰርጀሪ እንዲሁም የአጥንት፣ የጥርስና የመሀፀን ሕክልምና እንደሚሰጡ ማወቅ ተችሏል፡፡
ሮተሪ አዲስ አበባ ሸገር የላከው መግለጫ እንደሚያሳየው እነዚህ በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች በተጠቀሱት ሆስፒታሎች ከሚሰጡት አገልግሎት በአጠቃላይ ሦስት ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በደብረ ብርሃን ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ለማግኘት የተመዘገቡ 1,000 የሚሆኑ ታካሚዎች ናቸው፡፡
ሮተሪ አዲስ አበባ ሸገር ክለብ የዓለም አቀፉ ሮተሪ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ክለብ ሲሆን፣ እንቅስቃሴ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2015 መጀመርያ ላይ ነው፡፡ አባላቱ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉና ለማኅበረሰብ አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ናቸው፡፡