Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለአካል ጉዳተኞች የተዘረጋ እጅ

ለአካል ጉዳተኞች የተዘረጋ እጅ

ቀን:

ለትምህርት ወደ ኩባ እንደሚላኩ ቃል ተገብቶላቸው የትውልድ ቀያቸውን ጋሞ ጎፋ ለቀው አዲስ አበባ የመጡት በ1974 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ የ15 ዓመት ታዳጊ ነበሩ፡፡ ዕድሉ በሚመለከተው የመንግሥት አካለ ድንገት የተሰጣቸው ቢሆንም እንዴትና ለምን ተሰጠኝ ብለው ራሳቸውን አልጠየቁም፡፡ እሳቸውና ሌሎች ጥቂት የማይባሉ የዕድሜ እኩዮቻቸው ወደ ኩባ ለመሄድ አዲስ አበባ አቀኑ፡፡ ከመሄዳቸው በፊት ሊፈጽሙት የሚገባ ግዳጅ መኖሩ ተነገራቸው፡፡

በወቅቱ የቀይ ኮከብ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነበር፡፡ ኩባ ከመሄዳቸው አስቀድሞ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እንዲሳተፉ ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡ ጥያቄውንም ሳያቅማሙ ተቀበሉ፡፡ በየጊዜው ይሰሙት የነበረው ፕሮፖጋንዳና ይመለከቱት የነበረው የጦርነት ፊልም ለውጊያ ዝግጁነት መንፈስ አሳድሮባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በውርሶ ወታደራዊ ሥልጠና ማዕከል ጥቂት ከሠለጠኑ በኋላ ግዳጃቸውን ለመፈጸም ወደ ግንባር  ዘመቱ፡፡

‹‹አራት ዕዞች ነበሩ፡፡ እኔ የነበርኩበት መብረቅ ዕዝ አንዱ ነበር፡፡ ግዳጃችን በጠላት የተያዙ ቦታዎችን ነፃ ማውጣት ነበር፡፡ በውጊያ ላይ ጉዳት የሚደርስብኝ አይመስለኝም ነበር፡፡ ፊልም እየሠራሁ እንዳለሁ ይስማኛል›› በማለት የሚያስታውሱት  የ49 ዓመቱ አቶ ኩማ ምልኪ በሕይወታቸው አስበውት የማያውቁት አደጋ ገጠማቸው፡፡ 1947 ዓ.ም. መጋቢት 28 ሌሊት 11 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ የመብረቅ ዕዝ በጠላት እጅ የነበረን አንድ ቦታ ካስለቀቀ ከሰዓታት በኋላ አቅሙን አጠናክሮ የተመለሰው የጠላት ጦር ጥቃት ሰነዘረባቸው፡፡ ጥቃቱ ያልተጠበቀ በመሆኑ ብዙዎቹ የመብረቅ ዕዝ ሰራዊቶች የጥቃቱ ሰለባ ሆኑ፡፡ አቶ ኩማም በዚያው ቅጽበት በደረሰ የቦንብ ጥቃት እግራቸው ተቆረጠ፡፡

በቂ ሕክምና ለማግኘት አልታደሉም፡፡ እንደነገሩ የተደረገላቸው ሕክምናም ቆይቶ ሌላ ችግር አስከተለ፡፡ ቀደም ሲል ከጉልበት በታች የተቆረጠው እግራቸው እንደገና ወደ ላይ ከፍ ተደርጎ እንዲቆረጥም ሆነ፡፡ በሁኔታው ልባቸው የተሰበረው አቶ ኩማ ኩባ እንደማይሄዱ የተገለጠላቸው ያኔ ነበር፡፡ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስም አልሆነላቸውም፡፡ ስለዚህም ራሳቸውን ደብቀው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተው ከጉዳት የተረፉ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ግለሰቦች በሚረዳ በአንድ የውጭ ድርጅት ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ፡፡ በዚህ መልኩ ጥቂት ከቆዩ በኋላ ድርጅቱ የሥራ ጊዜውን ጨርሶ ተዘጋ፡፡

ላለፉት ረዥም ጊዜያት የአካል ጉዳት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ ከጉዳቱ ጋር የሚኖሩ ግለሰቦች የጤና የትምህርት እንዲሁም ሌሎች የመሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡ በተለይም በጦርነት አካላቸውን ያጡ ወታደሮችም የሰው እጅ ለማየት ሲገደዱ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ እንደ አቶ ኩማ የሚጥሩም ያጋጥማሉ፡፡ ቀድሞ የነበሩበት ድርጅት ቢዘጋም ሰርቫይቨር ሪከቨሪና ሪሀብሊቴሽን በተባለ በአካል ጉዳተኞች ላይ በሚሠራ አገር በቀል ድርጅት በማገልግል ላይ ይገኛሉ፡፡ ድርጅቱ ቀደም ሲል የተዘጋውን የውጭ ድርጅት ያገለግሉት የነበሩ አባላት የተመሠረተም ነው፡፡

አቶ በቀለ ጎንፋ የቀድሞ የኃይለሥላሴ ሐረር ጦር ምሩቅና የሰርቫይቨር ሪከቨሪና ሪሃብሊቴሽን መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ አቶ ኩማ ሁሉ አቶ በቀለም እግራቸውን በጦርነት አጥተዋል፡፡ በኢትዮ ሶማሌ ጦርነት ላይ ተዋግተዋል፡፡ ከውትድርናው ዓለም በጉዳት ምክንያት ከተገለሉ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታስቲክስ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም በኃላፊነት አገልግዋል፡፡ ፈንጂና አካል ጉዳት ላይ ይሠራ የነበረ አንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ በኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ድርጀቱ ከተዘጋ በኋላ በሥራ ምክንያት ከተለያዩ የውጪ ድርጅቶች ጋር በፈጠሩት ትውውቅ ድርጅቱ ከተዘጋም በኋላ የአካል ጉዳተኞች መብት አቀንቃኝ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ከኢትዮጵያ በመጋበዝም ስለ አካል ጉዳተኞች መብት ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊትም ሰርቫይቨር ሪከቨሪና ሪሃብሊቴሽን የተሰኘውን አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሠራውን ድርጅት አቋቋሙ፡፡ አቶ ኩማም የዚሁ ድርጅት ተቀጣሪ ሲሆኑ፣ ኃላፊነታቸውም የድርጅቱን እርዳታ ለሚሹ የማማከር አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ እንደ አቶ ኩማ ገለጻ፣ አካል ጉዳተኝነታቸውን አምነው ለመቀበል የሚቸገሩ ብዙ ናቸው፡፡

 ‹‹ባጋጠማቸው የጤና ችግር እግራቸው አልያም እጃቸው የግድ መቆረጥ እንዳለበት ሲነገራቸው ለማቆረጥ ፈቃደኛ የማይሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ አካላቸው ሳይቆረጥ መሞትን ይመርጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሚሰጣቸው የምክር አገልግሎት ብዙዎቹም ሐሳባቸውን ቀይረው ለመዳን ፈቃደኛ ይሆናሉ፤›› ሲሉ ድርጅቱ ከሆስፒታሎች ጋር በጋራ በመሥራት የምክር አገልግሎት በመስጠት የሌሎች ጥቂት የማይባሉ አካል ጉዳተኞችን ሕይወት ለመቀየር እንዳሰቡ ይናገራሉ፡፡

በድርጅቱ አገልግሎት ከሚያገኙ አካል ጉዳተኞች መካከል ከአማራ ክልል ከጎንደር አካባቢ የመጣው የ15 ዓመቱ ታዳጊ አንዱ ነው፡፡ ሕመሙ የጀመረው ጉልበቱ አካባቢ ነበር፡፡ ‹‹ጉልበቴ ላይ ድንገት ተነስቶ አበጠ፡፡ ይቆረጥመኝም ጀመር፡፡ እግሬን ማንቀሳቅም አቃተኝ፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄድኩኝ፡፡ በዚያም እግሬ መቆረጥ እንዳለበት ሲነገረኝ ፈርቼ አይሆንም ብዬም ነበር›› ሲል ድርጅቱ በሰጠው የምክር አገልግሎት በመጨረሻ ሐሳቡን ቀይሮ እግሩ መቆረጡን ከጉልበቱ የጀመረው በሽታም እንዳይስፋፋ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሕክምናውን ቢጨርስም ወደ ጎንደር አልተመለሰም እዚሁ አዲስ አበባ  በወጣቶች ገነት ትምህርት ቤት ይማራል፡፡ በአሁን ሰዓት የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ የትምህርት  ወጪዎቹን የሚሸፍንለት ድርጅቱ  ሲሆን አርቴፊሻል እግርና ክራንችም ተሰጥቶታል፡፡

ድርጅቱ በተለያየ መልኩ የሞራልና የኢኮኖሚ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ልዩ ልዩ ሙያዊ ሥልጠናዎችን በመስጠት ጥቂት የማይባሉ ጉዳተኞች ራሳቸውን እንዲችሉም ድጋፍ አድርጓል፡፡ ካለው ፍላጎት አንፃር በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ሆነው መሥራት ቢፈልጉም አቅማቸው አይፈቅድም፡፡ ተደራሽነታቸው ለተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነው፡፡

‹‹የፈንድ እጥረት ዋነኛው ችግራችን ነው፡፡ እስካሁን የምንሠራውም አንዳንድ ድርጅቶች በሚፈቅዱልን መጠነኛ ፈንድ ነው›› የሚሉት የድርጅቱ መሥራች አቶ በቀለ  አካል ጉዳተኝነት ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ‹‹ለሽልማቱ አልተወዳደርኩኝም፡፡ ከኔ እውቀት ውጪ በተደረገ ግምገማ ነው የተሸለምኩት›› በማለት ሽልማቱ የበለጠ ለመሥራት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...