Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀደሙ ቴአትሮች ለዛሬው ተመልካች

የቀደሙ ቴአትሮች ለዛሬው ተመልካች

ቀን:

የዊልያም ሼክስፒር ድርሰት ‹‹ኦቴሎ›› ለዘመናት እንደተወደደ የዘለቀ ቴአትር ከመሆኑ ባሻገር በበርካታ ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለመድረክ የበቃበትን ወቅትም ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ ከቴአትሩ ገጸ ባህርያት አንዱ በሆነው ኢያጎ ድርጊት የተበሳጩ ተመልካቾች ንዴታቸው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ተዋናዩን እስከማጥቃት ደርሰው ነበር፡፡ የኦቴሎና ዴዝዴሞናን ፍቅር መሠረት ያደረጉ ዜማዎች መሠራትም ቴአትሩ ምን ያህል ቦታ እንደተሰጠው አመላካች ሊሆን ይችላል፡፡

ከሦስት አሠርታት በፊት ለመድረክ የበቃውን ‹‹ኦቴሎ›› የማየት ዕድል ያላገኙ ወጣቶች ጥቂት አይደሉም፡፡ የቴአትሩን ጽሑፍ በማንበብ ወይም ቴአትሩን መነሻ አድርገው የተሠሩ ፊልሞችን ብቻ ለተመለከቱ መልካም አጋጣሚ የተፈጠረው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር፡፡ ቴአትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ያዘጋጀው ሁለተኛው ዓመታዊ የቴአትር ፌስቲቫል መክፈቻ ሲሆን፣ አንጋፋ የቴአትር ባለሙያዎች፣ የቴአትር ተማሪዎች እንዲሁም ተመልካቾች ታድመዋል፡፡

በዕለቱ በተቋሙ ፋውንቴን አካባቢ የተዘጋጀው መድረክ በሕዝብ ተከቦ ነበር፡፡ ዛፍ ላይ ተንጠላጥለው የቴአትሩን መጀመር የሚጠብቁም ነበሩ፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ቴአትሩ ተጀመረ፡፡ ዴዝዴሞና እንዴት ጥቁር ታገባለች የሚል ጥያቄ አንግበው ከአባቷ ቤት ደጃፍ ከቆሙት አንዱ ኢያጎ ነበር፡፡ አባቷ በንዴት ተሞልቶ ኦቴሎ ዴዝዴሞና እንድታፈቅረው ያደረገው በመተት ነው ሲል ይከሳል፡፡ ክሱን ያጣጣሉት ዴዝዴሞናና ኦቴሎ በአብሮነታቸው ሲዘልቁ፣ ሁለቱን ለመነጣጠል የሚዶልተው ኢያጎ ደግሞ ሲያሴር እያሳየ ቴአትሩ ይቀጥላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹እስኪ ቴአትር እንይ›› በተሰኘው ፌስቲቫል መክፈቻ ላይ ቴአትሩን ለመመልከት በተቋሙ ፋውንቴን አካባቢ ከተገኙ አንዱ የ27 ዓመቱ ሙሉሰው ፀጋዬ ነበር፡፡ በግል ሥራ የተሰማራው ሙሉሰው፣ የቴአትሩን ዝና ቢሰማም ለመመልከት ዕድሉን አላገኘም፡፡ በእሱ እምነት፣ አንጋፋ ፀሐፌ ተውኔቶች፣ አዘጋጆችና ተዋንያን የተሳተፉባቸው ቀደምት ሥራዎች ፌስቲቫልን በመሰሉ አጋጣሚዎች ለሕዝብ መቅረባቸው መልካም ነው፡፡ ፌስቲቫሉ የቴአትር ባለሙያዎችና ተመልካቾች በአንድነት የታደሙት መሆኑ በመካከላቸው መቀራረብ እንደሚፈጥርም ይናገራል፡፡

የፌስቲቫሉ መክፈቻ እንዲሁም መዝጊያ እንዲሆን ከተመረጠው ‹‹ኦቴሎ›› በተጨማሪ ብዙ ቀደምት ሥራዎች ወደ መድረክ ተመልሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ተጠቃሽ ከሆኑና ተቀንጭበው ከቀረቡ ሥራዎች ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ›› እና ‹‹ያላቻ ጋብቻ›› ይገኙበታል፡፡

ከተለመደው የቴአትር ቅርፅ ወጣ ካሉ ሥራዎች ደግሞ አሳታፊ ተውኔቶቹ ‹‹ኮንደሚኒየም›› እና ‹‹ሸፍጥ›› ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹የሠርጌ ለታ›› የተሰኘው ማይም ድራማ፣ ‹‹ሱሚ›› እና ‹‹ቅፅበት እውነት›› የተባሉ ግለ ተውኔቶች፣ እንዲሁም ‹‹አባቡ›› የተሰኘ የሕፃናት ቴአትር ተካተዋል፡፡

ከኅዳር 3-11፣ 2008 ዓ.ም. ባሉት የፌስቲቫሉ ቀናት ለኢትዮጵያ ቴአትር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ስምንት አንጋፋ ባለሙያዎች ተዘክረዋል፡፡ የባለሙያዎቹን ግላዊ ሕይወትና ሙያዊ አበርክቶ ያሳዩ የጥናት ጽሑፎች ቀርበው፣ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ባለሙያዎቹ አውላቸው ደጀኔ፣ ዶ/ር ፍሊፕ ካፕላን፣ አስናቀች ወርቁ፣ እዩኤል ዮሐንስ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ደበበ እሸቱ፣ ደበበ ሰይፉና መላኩ አሻግሬ ናቸው፡፡

በፌስቲቫሉ ካገኘናቸው አንጋፋ የቴአትር ባለሙያዎች አንዱ አባተ መኩሪያ ነው፡፡ በመጀመሪያው የቴአትር ፌስቲቫል ከተወሱ አንዱ የሆነው አባተ፣ መሰል ፌስቲቫሎች ቀድሞ አለመካሄዳቸውን አስታውሶ የ‹‹እስኪ ቴአትር እንይ›› ተካፋይ መሆኑ እንዳስደሰተው ይናገራል፡፡ በአጋጣሚው የቴአትር ባለሙያዎች፣ ተማሪዎችና ተመልካቾች ትምህርት እንደሚቀስሙበት ያምናል፡፡ ‹‹በባለሙያዎች መካከል ውህደት ይፈጥራል፤ ጥበብን ለሚያደንቅም ምቹ መድረክ ይፈጥራል›› ይላል፡፡

እሱ እንዳለው፣ ፌስቲቫሉ በርካታ ባለሙያዎችን ማሳተፉ ከአወንታዊ ጎኖቹ አንዱ ነው፡፡ ዘመን የማይሽራቸው የኪነ ጥበብ ሥራዎች አበርክተው ያለፉ ባለሙያዎች መዘከራቸውም ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ስለ ሥራዎቻቸው ማውሳትና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ክብር መስጠት ወጣቶችን አስተማሪና አበረታች እንደሆነ ያምናል፡፡ ‹‹በአገራችን የፌስቲቫል ባህል መለመድ አለበት፤›› ይላል፡፡

ሌላዋ አንጋፋ ባለሙያ አልጋነሽም የአባተን ሐሳብ ትጋራለች፡፡ ፌስቲቫሉ ከሚዘክራቸው አንጋፋ ባለሙያዎች አንዷ የሆነችው አስናቀች ወርቁ መታሰቢያ ዕለት በይፋ መጀመሩን ያበሰረችው እሷ ነበረች፡፡ የሙያ አጋሯና ጓደኛዋም የነበረችው አስናቀችን ‹‹ያሳደገችኝ የሙያ እናቴ፣ ጓደኛዬ፣ ሁሉነገሬ ስለሆነችው አስናቀች ለመናገር በመቻሌ ዕድለኛ ነኝ፤ ለሙያው መስዋዕትነት ከፍላ ከትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ የቻለች ነች፤›› በማለት ትገልጻታለች፡፡ የአሁኑ ትውልድ የአስናቀችና ሌሎችም ባለሙያዎችን አስተዋጽኦ መዘከሩ እንዳስደሰታትም ትናገራለች፡፡ አውላቸው ደጀኔና እዩኤል ዮሐንስን የመሰሉ ለሙያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ነገር ግን ስማቸው ያልተጠራ ባለሙያዎች ለመታወሳቸውም ትልቅ ቦታ ትሰጣለች፡፡

‹‹የአንጋፋዎች ታሪክ መወሳቱ ለዚህ ትውልድ ትምህርት ይሰጣል፤ ብናልፍም እንኖራለን እንድል አድርጎኛል፤›› ትላለች፡፡ በ‹‹ኦቴሎ›› ላይ ዴዝዴሞናን ሆነው ከተጫወቱ ተዋንያን አስናቀችና አልጋነሽ ይጠቀሳሉ፡፡ የበርካታ ባለሙያዎችንና ተመልካቾችን ትውስታ የሚቀሰቅሰው ቴአትሩ፣ ዳግም በወጣቶች መሠራቱ እንደሚበረታታም ትገልጻለች፡፡

በመጀመሪያው ፌስቲቫል ስምንት አንጋፋ ባለሙያዎች ተዘክረዋል፣ ዘጠኝ ቴአትሮችም ታይተዋል፡፡ ሁለተኛው ፌስቲቫል የተያየ ዘውግ ያላቸው ቴአትሮችን ያካተተ ሲሆን፣ የኤክስፐርመንታል ቴአትሮች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እሸቱ እንደሚናገረው፣ ኤክስፐርመንታል ቴአትሮች መሥራትን ለማበረታታትና ለተመልካች ለማስለመድም በፌስቲቫሉ ተካተዋል፡፡ ዓለም ላይ የተለያዩ የቴአትር ዘውጎች በሚታዩበት ወቅት በተለመደው መንገድ መገደብ ተገቢ እንዳልሆነና ቴአትር ትምህርት ቤቱም የሚያበረታታው ኤክስፐርመንታል ቴአትሮችን እንደሆነ ይናገራል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ የዚህኛው ፌስቲቫል ዝግጅት የተጀመረው የመጀመሪያው ፌስቲቫል እንደተጠናቀቀ ቢሆንም ሒደቱ ቀላል አልነበረም፡፡ ዋነኛው ችግር ስፖንሰሮች ማግኘት ሲሆን፣ ከጥቂት ተቋሞች በስተቀር ፌስቲቫሉን ለመደገፍ ፈቃደኛ የሆኑ አልተገኙም፡፡ ‹‹ጥበቡ እንዲያድግ ደጋፊ ያስፈልገዋል፤ በየትኛውም አገር በመንግሥት ድጋፍ ብቻ ያደገ ጥበብ የለም፤ የኅበረተሰቡ መረባረብ ያሻል፤›› የሚለው ተስፋዬ፣ ተቋሙ ያለው ሀብት የሰው ኃይል ብቻ መሆኑን ይናገራል፡፡ ውጣ ውረዱ ቢበዛም ከመጀመሪያው ፌስቲቫል የተሻለ መሆኑን ግን ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ቀደምት ቴአትሮች ዳግም መሠራታቸው ለመምህራኑ ለተማሪዎችም ሙያዊ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ቀደምት ቴአትሮች ድጋሚ ሲሠሩ በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ቴአትር ተቀዛቅዟል የሚል ስሜት ለመቀየር እንደሚረዳ ይናገራል፡፡ ‹‹አንጋፋ ሥራዎች የተሻለ ባለሙያና ተመልካች ይፈጥራሉ፤›› ይላል፡፡

የቴአትር ተመልካቾችን ቁጥር መጨመር ከፌስቲቫሉ ዓላማዎች አንዱ ሲሆን፣ ቴአትር ትኩረት እንዲያገኝ ማስቻል፣ በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱ ነገር ግን ሕዝቡ ያላወቃቸው ባለሙያዎችን ማሳወቅም ይጠቅሳሉ፡፡

ተስፋዬ እንደሚለው፣ ተመልካቾችን በማፍራት ረገድ የፌስቲቫሉ ዓላማ ከሞላ ጎደል ተሳክቷል፡፡ ፌስቲቫሉ በቴአትር ዘርፍ ያለው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚጨምርም እምነቱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...