Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአሸባሪዎች የተሳሰሩበት ኃያላን መንግሥታት የተፍረከረኩበት አጀንዳ

አሸባሪዎች የተሳሰሩበት ኃያላን መንግሥታት የተፍረከረኩበት አጀንዳ

ቀን:

‹‹ወደድነውም አልወደድነውም ሽብርተኝነትና የሽብር ጥቃት ለአሜሪካ፣ ለአጋሮቿና ለሌላውም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ችግር ሆኖ ይቀጥላል፤›› በዋሽንግተን የብሔራዊ ደኅንነት ሐሳብ አመንጪ (Think Tank) ዳኔል ዲፔትሪስ

አሸባሪዎችና የሽብር ጥቃታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ፣ ዓይነቱን እየለዋወጠና አድማሱን እያሰፋ መጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2001 አልቃይዳ በአሜሪካ ካደረሰው የሽብር ጥቃት በኋላ፣ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ያገኙትና አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ቡድኖች ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ አፍሪካ ብሎም እስያ የሽብር ጥቃታቸው ዓይነት፣ መጠንና ድግግሞች ይለያይ እንጂ እየተንሰራፉ መጥተዋል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የአልቃይዳ ክንፍ የሆነውና እንደተዳከመ የሚነገርለት አልሸባብ፣ በናይጄሪያ በሺዎች የሚቆጠሩትን የፈጀውና በየጊዜው እየፈጀ የሚገኘው እንዲሁም ለኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) አጋርነቱን የገለጸው ቦኮ ሐራም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚዲያውንና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት የሳበው አይኤስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሽብር ሥጋት ከሆኑ ከርመዋል፡፡

አገሮችም የሽብር ጥቃትን ለመከላከል ፖሊሲና ስትራቴጂ ቢያወጡም፣ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ናቸው የተባሉ አካባቢዎችን በአየርም ሆነ በምድር ቢደበድቡም ማስተንፈስ አልቻሉም፡፡ በተለይ አይኤስ ወደ ሽብር ጥቃቱ ጐራ ከተቀላቀለ ወዲህ ሁኔታዎች ተቀያይረዋል፡፡ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ቡድኑን ለመምታት ጥምረት ፈጥረናል ቢሉም አልተሳካላቸውም፡፡ አይኤስ በስፋት በሚገኝባቸው ኢራቅ እንዲሁም ሶሪያ ውስጥ የአየር ድብደባ ቢያካሂዱም፣ ቡድኑ ስትራቴጂውን ቀይሮ ባገኘው ክፍተት ሁሉ ጥቃቱን ከመፈጸም አልተገታም፡፡ በስፋት ከሰፈረባቸው ኢራቅና ሶሪያ አልፎም አጥፍቶ ጠፊዎችን በማሳተፍ በተለያዩ አገሮች ጥቃቱን እየፈጸመ ይገኛል፡፡

በግብፅ ሲናይ በረሃ የተከሰከሰው የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን ለ224 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት ከሆነ ወር እንኳን አልሞላውም፡፡ ከዚሁ ቀጥሎ ለ43 ሰዎች ሞት ከ200 በላይ ለሚሆኑት ደግሞ መቁሰል ምክንያት የሆነው ጥቃት በቤይሩት የተፈጸመው ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡ የቤይሩቱ ጥቃት በተፈጸመ በቀናት ልዩነት የፈረንሳይዋ ፓሪስ በተለያዩ የሽብር ጥቃቶች ታምሳለች፡፡ ዓርብ ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓሪስ በደረሰ የሽብር ጥቃት 129 ሲሞቱ ከ300 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን፣ በቤይሩት እንዲሁም በፈረንሣይ ለደረሰው የሽብር ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደው አይኤስ ነው፡፡ ቡድኑ በፈረንሣይ በመጠጥና ምግብ ቤት፣ በኮንሰርት አዳራሽ እንዲሁም በስታዲየምና በተለያዩ ስድስት ቦታዎች የደረሰውን ጥቃት መፈጸሙን አሳውቋል፡፡

አይኤስ ግዛቱን ማስፋፋት የሚፈልገው በመካከለኛው ምሥራቅ ቢሆንም፣ አሁን አካሄዱን ቀይሮ ጥቃቱን በሌሎች አካባቢዎች አድርጓል፡፡ ለዚህም ኃያላን አገሮች አላቸው ከሚባለው የደኅንነት ጥበቃ መረብ የማይተናነስ ስትራቴጂ አለው፡፡ ጠንካራ የደኅንነት ስትራቴጂ ያላትንና በሻርሊ ሂቢዶ ሽሙጥ ካርቱን አዘጋጆች ላይ ከተፈጸመ ግድያ በኋላ ወታደሮቿን በፓሪስ ሳይቀር ማሰማራት በጀመረችው ፈረንሣይ፣ በአውሮፓ ከ61 ዓመታት በኋላ በዓይነቱ ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት በፓሪስ መድረሱም ቡድኑ ከኃያላኑ ስትራቴጂ የቀደመ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ቡድኑ በቱርክ አንካራ በፈጸመው አጥፍቶ መጥፋት 102 ሰዎች ሞተዋል፡፡

አይኤስ አካሄዱን እየለዋወጠ ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ በአውሮፓ ጥቃት ለማድረስ የተደራጀና ጠንካራ ስትራቴጂ ያለው ሲሆን፣ ቡድኑን ለመምታት በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል ግን ማሽመድመድ ተስኖታል፡፡ በተለይ ለቡድኑ መጠናከር ወሳኝ አገር በሆነችው ሶሪያ ጉዳይ፣ አሜሪካና አጋሮቿ ከሩሲያ ጋር የፈጠሩት ልዩነት ለቡድኑ ጥንካሬን ፈጥሮለታል፡፡ አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ አገሮች የተጠናከረ የደኅንነት መረብ፣ የገንዘብና ሌሎች አገሮችን የማስተባበር አቅም ቢኖራቸውም የቡድኑን መረብ መበጣጠስ ተስኗቸዋል፡፡ አይኤስ አባላት ይመለምላል፣ አመለካከት ይቀይራል፣ የገንዘብ አቅም አለው፣ ሥልጠና ይሰጣል፣ የመሣሪያዎችና የፈንጂዎች የተደራጀ ምንጭም አለው፡፡ አባላቱንም አጥፍቶ መጥፋት ድረስ መስዋዕት እንዲሆኑም ያሳምናል፡፡ 

የዚህ ዓይነቱ አካሄድ በ2000ዎቹ ገኖ የነበረው አልቃይዳ ሞዴል ነው፡፡ በኦሳማ ቢን ላደን ይመራ የነበረው አልቃይዳ እንደ አይኤስ አንገት እየቀላ በየድረ ገጹ አይልቀቅ እንጂ፣ በአባላት ምልመላውም ሆነ በጥቃት ስትራቴጂው ከአይኤስ ጋር ይመሳሰላል፡፡ አልቃይዳም ሆነ አይኤስ ዓለምን ወደ ሙስሊሙ ጎራ መቀላቀል የሚፈልጉ ቡድኖች ናቸው፡፡ አልቃይዳ በአሁኑ ጊዜ የአይኤስ ጥላ ያጠላበት ቢሆንም፣ አሻራውን በአይኤስ አሳርፏል፡፡ የውስጥ ለውስጥ ግንኙነት እንዳላቸውም በፈረንሣይ በሻርሊ ሂቢዶ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ወደ አፍሪካ ቀንድ ሲመጣ የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው አልሸባብ ይነሳል፡፡ አልሸባብ ሶማሊያን ማስተዳደር አለብኝ ብሎ የተነሳ የወጣቶች ቡድን ቢሆንም፣ አካሄዱ ከሽብር ቡድን እንዲፈረጅ አድርጐታል፡፡ አልሸባብ በኢትዮጵያ ጥቃት ለመፈጸም አቅዶ ባይሳካለትም፣ በኬንያ ግን ከባድ ጥቃቶችን ፈጽሟል፡፡ በሞምባሳ፣ በጋሪሳ እንዲሁም በናይሮቢ ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል ባደረሰው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ገድሏል፡፡ በኬንያ ለደረሱ የሽብር ጥቃቶች ሁሉ ኃላፊነቱንም ወስዷል፡፡ የኬንያ ወታደሮችና የፀጥታ ኃይሎች አገሪቱን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል እየሠሩ ቢሆንም፣ ከሙስና እንዲሁም ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ቡድኑን መግታት አልቻሉም፡፡ ቡድኑ የአይኤስን ያህል በአፍሪካ ቀንድ ጥቃት እያደረሰ ባይሆንም፣ አለፍ ገደም እያለ መሠረቱን በጣለበት ሶማሊያና በጐረቤት ኬንያ በአጥፍቶ መጥፋትና በተኩስ ልውውጥ ለብዙዎች ሞት ምክንያት፣ ለሶማሊያ ደግሞ አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አልሸባብ እንዳለ ሁሉ፣ በናይጄሪያ ደግሞ ቦኮ ሐራም ተንሰራፍቷል፡፡ ቦኮ ሐራም እንደ አልሸባብ በመዳከም ላይ ያለ አሸባሪ ቡድን አይደለም፡፡

ቡድኑ የአይኤስን ያህል የሚዲያ ሽፋን ባያገኝም፣ በናይጄሪያ በሚፈጽመው የሽብር ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ገድሏል፣ ቤቶችን አቃጥሏል፣ ንብረት አውድሟል፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት የተወሰኑትን አስለቅቄያለሁ ቢልም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴት ተማሪዎችን ጠልፏል፡፡ ለአይኤስም አጋርነቱን ገልጿል፡፡ ቦኮ ሐራም የምዕራባውያን ትምህርት ወይም ሥልጣኔ ከምድረ ናይጄሪያም ሆነ የእስልምና እምነት በሚከተሉ  አገሮች ውስጥ መጥፋት አለበት ብሎ የሚያምን ቡድን ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የናይጄሪያን መንግሥት አይደግፍም፡፡ መቀመጫውን ሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ በማድረግና በናይጄሪያ አጐራባች ቻድና ካሜሩን በመመላለስ ለአገሪቱ ብሎም ለቀጣናው ሥጋት ሆኗል፡፡

በየአገሮቹ መንግሥቶቻቸውን ከመቃወም በመነጨ በሚያደርጉት ሽምቅ ውጊያ ሳቢያ በአሸባሪ ቡድንነት ከተፈረጁት የኮሎምቢያ፣ የማሊ እንዲሁም ሌሎች አገሮች አማፂ ቡድኖች በተለየ ከሃይማኖት አመለካከትና በየትውልድ አገራቸው ሊኖር ከሚገባው አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ቡድኖች፣ ለዓለም ሥጋት መሆን ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ የሚዲያ ዝናን ያተረፈውና በሚገባ ተደራጅቷል የሚባለው አይኤስ እየገነነ፣ ጥቃቱም እየሰፋ መጥቷል፡፡ ቦኮ ሐራም የቡድኑ አጋር ሲሆን፣ አልሸባብ ደግሞ የአልቃኢዳ ክንፍ ነው፡፡ አልቃይዳ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል የሚል ፍንጭም እየታየ ነው፡፡

አሸባሪ ቡድን የተባሉት እርስ በርስ ሲተሳሰሩ፣ ኃያላን መንግሥታት ካላቸው አቅም አንፃር ቡድኖቹን ለመምታት ያላቸው አንድነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ቡድኖቹ አንድ ዓላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ፣ ኃያላን አገሮች በፖለቲካ ልዩነት በመናቆር የየአገሮችን በር ለሽብር ጥቃት ክፍት አድርገዋል፡፡ ሁሉም አገሮች እንደየአቅማቸው የደኅንነት አካላትና ስትራቴጂ ቢኖራቸውም፣ በፈረንሣይ የደረሰው ጥቃት የስለላ ድርጅቱ የቱንም ያህል ቢጠናከር ሰርጐ መግባት እንደሚቻል የታየበት ነው፡፡ አሜሪካ በአፍጋኒስታን በነበራት ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ከዓመታት በፊት እየተጠናከረ የመጣው አልቃይዳ፣ አሜሪካ ከሰብዓዊ መብት ጋር ብታያይዘውም፣ በአሜሪካና በአጋሮቿ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የተነሳሳው በእምነት አመለካከታችን አትድረሱብን፣ በእስላም አገሮች የሸሪአ ሕግ እናሰፍናለን በሚል ነው፡፡ መቀመጫው በሶማሊያ የሆነው አልሸባብ አመለካከትም ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡

ቦኮ ሐራምም ቢሆን በናይጄሪያ ሰሜን ምሥራቅ ባሉ ሕዝቦች ላይ ይፈጸም በነበረ በደልና አድልኦ ምክንያት ሃይማኖትን ግንባር ቀደም አድርጐ የወጣ ቡድን ነው፡፡ አይኤስም የራሱ ግዛት እንደሆኑ በሚጠቅሳቸው የኢራቅና የሶሪያ ክፍሎች የሸሪአ አስተዳደር አስፍኖ መግዛት የሚፈልግ ቡድን ነው፡፡ እነዚህ አሸባሪ ተብለው በተለይ በኃያላን መንግሥታት የተፈረጁ ቡድኖች ቢሆኑም፣ ሽብር ሲባል ከንፁኃኑም ጋር እየተያያዘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ንፁኃኑ ራሳቸው ቡድኑን እንዲቀላቀሉ በር ከፍቷል፡፡ ከዓረብ አገሮች ብቻ ሳይሆን ከምዕራባውያኑም ጭምር ቡድኖቹን እየተቀላቀሉ ነው፡፡ እንደ መፍትሔ የተያዘው ደግሞ በጦርነት መሸናነፍ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ በነበሩ ሒደቶች ኃያላን መንግሥታት በተለይ በአጥፍቶ መጥፋት ከሚሳተፉ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ለድርድር አልቀረቡም፡፡ ይልቁንም ጦርነት እንደ መፍትሔ ተወስዶ በሁለቱም ወገን ሞት እየተመዘገበ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ፍትሕ የለም፡፡ ኃያላኑም ለዓላማቸው፣ አሸባሪ የተባሉትም ለዓላማቸው ይፋለማሉ፡፡ ለዚህም ነው ሐሳብ አመንጪው ዲፔትሪስ ‹‹አሸባሪዎችም ሽብርም የዓለም ሥጋት ሆነው ይቀጥላሉ፤›› ሲል ያሰፈረው፡፡

ኃያላኑ የፈረንሣዩን ጥቃት ተከትሎ እንደ መፍትሔ የያዙት፣ አካሄዱ ላይ ልዩነት ቢኖርም ጦርነትን ነው፡፡ በቱርክ የተሰባሰቡት የቡድን 20 አባላት የፈረንሣይን ጥቃት በማውገዝ ‹‹ትብብራችንን ልናጠናክር ይገባል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንዴ ጥቃቱን በፈረንሣይ ላይ የተቃጣ ጦርነት ሲሉት፣ የአሜሪካው አቻቸው ፕሬዚዳንት ኦባማ ደግሞ ‹‹በንፁኃን ዓለም ላይ የተቃጣ ጥቃት›› ብለውታል፡፡ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ ‹‹ዓለም አቀፍ ጥረት ያስፈልገናል፡፡ ሩሲያ በአይኤስ ላይ የምታካሂደው ድብደባ ትክክለኛነት ሰሞኑን በፓሪስ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ተረጋግጧል፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም መሪዎቹ ይህንን ይበሉ እንጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ የተጠናከሩ አይደሉም፡፡ ፈረንሣይ አሜሪካን በመደገፍ በሶሪያ የአየር ጥቃት ብትፈጽምም፣ ሩሲያ በፊናዋ አል አሳድን ወግና አማፂያንን ብትደበድብም፣ አይኤስ ከአየር ድብደባ ቀጣና ወጣ ብሎ ጥቃቱን በመሀል የአውሮፓ ከተማ አድርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም በቱርክ፣ አሁን በፈረንሣይ የታየው የቡድኑን ሥልት መቀየር የሚያሳይ ነው፡፡ በቱኒዚያ፣ በግብፅ፣ በሊቢያና በየመን እየዘለቀም ለዓለም ዘግናኝ የተባሉ ጥቃቶቹን አስቃኝቷል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን የሽብር ቡድኑ ብቻውን አይደለም፡፡ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ ብሎም ከአውሮፓ በደጋዎችና በአባላት ተሳስሯል፡፡ ቦኮ ሐራም አጋርነቱን ሲገልጽ አልሸባብ ደግሞ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ይኖረዋል የሚባለው የአልቃይዳ ክንፍ ነው፡፡ ኃያላን መንግሥታት ግን ካላቸው አቅም አንፃር ይህ ይጐድላቸዋል፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...