Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሐሳብ ማጥለያ የት ይገኝ ይሆን?

እነሆ ጉዞ! ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ተሳፍረናል። “እስኪ ሙዚቃውን ቀንሰው ሾፌር። ወገን ተርቦ እኛ ስንጨፍር ትንሽ አይቀፈንም?” ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ራሰ በራ። “መቼ የጭፈራ ዘፈን ከፈትኩ? ትዝታ እኮ ነው፤” ሾፌሩ ይሟገታል። “ረሃብ ላይ ሆነን ረሃብ ማስታወስም ያው ነው። ቀንሰው አሁን!” ተቆጣ ሰውዬው። “እሺ ምን ልክፈት?” ሾፌሩ ጫቱን በጉንጩ ወጥሮ አንገቱን አዙሮ ሙዚቃ ሲያስመርጥ እናስተውላለን። “ጭራሽ እየቃምክ ነው የምትሾፍረው?” ሰውዬው ከንትርክ ሌላ የሚያውቅ አይመስልም። “ምነው የእህሉ አይበቃም? ምርቃናም እንከልከል እንዴ? አልሰማህም አቦ፤” ተራውን ሾፌሩ ያመራል። “ . . . ሂዱና ሰው የሚያሳዩት ላይ ጉልበታችሁን አሳዩ። በገዛ ደማችን ማንም ምንም አያገባውም፤” ሾፌሩ  መከላከያውን ይደረድራል። ወደ ወያላው ዞር ብሎ፣ “አንተ! ይኼው ዛሬ አንድ ሰው ሳትፈትሽ ብታስገባ ወዬውልህ፤” ይለዋል።

ወያላው ታዛዥነቱን ለመግለጽ አጎንብሶ እጅ እየነሳ “ሴቶቹ ግን ከአቅሜ በላይ ናቸው፤” ይላል። “ነገርኩህ! ፍተሻ ለሁላችንም ደኅነነት ነው እያልክ ማሳመን ያንተ ፋንታ ነው። ለነገሩ አንተ መፈተሽ የምትፈልገውን ነገር አውቀዋለሁ። ይኼው ፍተሻን ምክንያት በማድረግ ማንኛውም ዓይነት የፆታዊ ትንኮሳ ተግባር የተፈጸመብሽ ካለሽ ቀጥታ ለእኔ መንገር ነው፤” ብሎ ማሳሳቢያውን እንዳስተላለፈ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ከጎኔ የተሰየመች ቀዘባ፣ “ከነገርንህ በኋላስ?” ብላ ጠየቀችው። “በቃ! በድጋሚ በወጉ እኔ ራሴ እፈትሻችኋለሁ። እንግዲህ ‘ጄት’ የለኝ ይኼን የሚያክል ወጠምሻ በምኔ እደበድበዋለሁ?” ብሏት ሲዞር፣ ከራሰ በራው አጠገብ የተቀመጠች ወይዘሮ በፈረንሣይ ባንዲራ ቀለም የተቀለመ ሻሿን እያስተካከለች፣ “ጄት ስለኖረህና ስላልኖረህ ብለህ ነው የአፀፋ ምላሽ የምትሰጠው። ለሕዝብ ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት ካለህ እንኳን ጄት ዱላና አካፋ ተይዞ ይዘመታል። ልክ እኛ ያኔ በአደዋ እንዳረግነው ማለቴ ነው። ዛሬ ታንክና ጄት ኖሮን ግን ደም ሳናፈስ የወገኖቻቸውን ደም የሚያፈሱ አገሮችን ዜና እናስተጋባለን። ውይ! ኧረ ፈረንሣዊት መሆን አማረኝ፤” ስትል አንዱ፣ “አምሮ አምሮ ይተውሻል፤” አላት። አቤት አንዳንዱን?

ጉዟችን ተጀምሯል። “ጉድ ነው” ይላል መሀል ወንበር ላይ የተሰየመ ወጣት። ተሳፋሪው ባልሰማ ባላየ በየገዛ ሐሳቡ ሰርጥ እየተሽሎከሎከ ጆሮ የሚሰጠው ጠፋ። እንደገና፣ “ጉድ ነው!” ሲል አጠገቡ የተቀመጠች ገራገር፣ “ሌላ ቃል ካልፈጠርን በቀር ጉድ ብሎ ጉድ ማብሰር የማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤” አለችው። ገባው። “እህ ለዚያ ነው ዝምታው? እኔ ደግሞ ዕርሜን ዛሬ ወሬ ቢያምረኝ ምነው ሰው ፊት የነሳኝ ብዬ እኮ አሳስቦኛል። ለማንኛውም ምን እያልኩ ነበር?” አላት መለስ ብሎ። “ገና ምንም ሳትል?” አለችው እየተሽኮረመመች። “ኦ! እንደዚያ ከሆነማ ልበለዋ። ምን ልል ነበር መሰለሽ? አጥፍቶ ጠፊ የሚያቀነባብረው ሞት ይርሳኝና ረስቼው ነበር። አዎ . . . ብለን ብለን በሰው አገር ባንዲራ ደግሞ መጨቃጨቅ ጀመርን አሉ። ምንድነው የሚወራው በሞትሽ?” ብሎ አስደነበራት። “ኧረ ጠላቴ ድብን ይበል። እዛው ሞትህን አትሞትም? ከሞቴ ምን አለህ በሞትሽ የምትለኝ?” አራስ ነበር ሆነችበት።

“ይቅር በይኝ የወንዜ ልጅ! አሟሟታችንን ፈጣሪ ያሳምረውና  ባንዲራው ላይ እናነጣጥር፤” ልጁ ይቅርታው ከልቡ መሆኑን አስተዛዝኖ ለማሳመን ተጣጣረ። “የቱ ባንዲራ?” ጠየቀችው። “ፌስቡክን ያተራመሰው የፈረንሣይ ባንዲራ ነዋ፤” መለሰላት። “በአገርህ፣ በአደግክበት ሠፈር ሰው ሲሞት አይታዘንም?” ከቁጣዋ ቀዝቀዝ ብላለች። “ኧረ ይታዘናል። እንኳን የምንናውቀው በሩቅ ተተክሎ ለምናየው ድንኳን ባርኔጣችን ከፍ ማድረግ ወግ ነው፤” ሲላት ወዲያ ራሰ በራው፣ “ወጉንማ ማን ብሏችሁ? አድርጉት ብትባሉ ግን ለታይታ ካልሆነ አትሞክሩትም” አለ፡፡ “ታዲያ ምን ይደረግ የዓለም የሙቀት መጠን ጨመዴ እኮ? እንኳን በባርኔጣ በጃንጥላም ንዳዱን አልተቋቋምነው፤” ብሎ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ወጣት ይባስ አዘበራርቆት አረፈው። ‘የእኛ አልበቃ ብሎ ደግሞ በሰው አገር ባንዲራ መነታረክ ጀመርን?’ የሚለው ሳይቋጭ ባርኔጣ ደፍተን ጃንጥላ ዘረጋን። ‘ኮሜንት’ ሲበዛ እኮ ድሮም ይኼው ነው!

“አበስኩ ገበርኩ!” ይላሉ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ አዛውንት። ግርማ ሞገሳቸው ልዩ ነው። ፀጉራቸው፣ ሪዛቸውን ጨምሮ ቡፍ ብሎ ቆሟል። “ምነው አባት? ምን ሆኑ?” አጠገባቸው የተቀመጠች አጭር ቀይ ኮረዳ ታጫውታቸዋለች። “የምሆነው እየጨነቀኝ ነው እንጂ ምንም አልሆንኩ እስካሁን!” መለሱላት በእርጋታ። “ማን የሚሆነውን ያውቃል ብለው ነው?” ለማወጣጣት ነው ነገሩ። “እሱን ብዬ እኮ ነው ልጄ ነጋ ጠባ አሟሟቴን አሳምረው የምለው። ሳይሰለቸው ቀረ ብለሽ ነው?” ፍስስ ይላሉ ደርሰው በተመስጦ። “ምነው ካልጠፋ ነገር አሟሟትዎ ያስጨንቀዎታል? ልጆች የሉዎትም? ባለቤትዎስ?” የምትለቃቸው አትመስልም ወጣቷ።

“ኧረ ሁሉም አሉ። የሁሉም አጠገቤ መኖር ነው አንድም የሚያሳስበኝ። በዚያ ላይ አንዳንዱ በአሟሟቱ ይበደልና በአቀባበሩ ይካሳል። ለምሳሌ በፓሪስ ይኼው እንደምትሰሚው በአሸባሪዎች ሴራ የሞቱት ሰዎች ምንም እንኳ እንደወጡ በዚያው አፈር ቢለብሱም፣ ይኼው ዓለም በየሰዓቱ በየደቂቃው እያሰባቸው ይውላል። ዓለም ይኼው በባንዲራቸው ምሥሉን እስከ መሸፈን ደርሶ የሐዘናቸው ተካፋይ ሆኗል።  ሲኖሩ ተረስቶ ሲሞቱ መታወስ እጅግ የሚገርመኝ የዓለም ፀባይ ነው ልጄ። አየሽ ብዙ ብዙ አለ የሚያሳስበኝ። ወዲያ ደግሞ ወደ ጋዛ ወደ ፓሊስቲን፣ ወደ አፍጋኒስታን ብትሄጂ በቦምብ ሞትሽ፣ ታመሽ ሞትሽ፣ ሮኬት አገኘሽ ፍንጣሪው ዓይንሽን አጠፋው፣ ካበቃልሽ አበቃልሽ ነው። በበኩሌ ታዲያ በሕይወት ስኖር ለመኖሬ ዕውቅና ባይሰጠኝም ስሞት ቀባሪ ካላሳጣኝ አሟሟቴ ‘ክላሲ’ ባይሆንም እንኳ አስታዋሾቼ ‘ክላሲ’ በሆነ መንገድ ካስታወሱኝ ምን እፈልጋለሁ?” ብለው ፈገግ አሉ። ወይ ሰው! መፈለግም አለመፈለግም በማይቻልበት ሁናቴ ውስጥ የሚገኝበት ቀን እንደሚመጣ እያሰበም የሚፈልገውና የማይፈልገውን ሲመርጥ ይኖራል? “ታዲያ ከሞት በኋላም ምርጫ አማረህ?’’ ሲል የሰማነው ወያላ ስንት ቢያጆ ሸቅሎ ይሆን ከነጋ?

 “ምናለበት እንዲህ ራሳችንን ከመቃብር በላይ እንደምናፈቅረው ቢያንስ ‘ይህቺን ታህል’ ሌላውን ብናፈቅር?” ራሰ በራው የአዛውንቱን ጨዋታ ሲያደምጥ ቆይቶ ነው መናገር የጀመረው። “በቃ እስከ መቃብር እየተዋደድን ተያይዘን ማለቅ ሆነ የእኛ ታሪክ?” ማንም አይመልስለትም። ብቻውን ያነበንባል። “ምንድነው ሰውዬው የሚነጫነጭብን? ኮንትራት ይዞናል እንዴ?” ትለኛለች ከጎኔ ሹክክ ብላ። ይኼን ስትል የሰማት ያ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ጠይም ፈርጣማ፣ “ምናልባት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ‘ፌስቡክ’ ሲጠቀም ቆይቶ ይሆናል የተሳፈረው፤” አላትና ሳቀ። “ታዲያ እኛ የእንካ ሰላንትያ ሰሌዳ ነን እንዴ? አንዳች ደህና ነገር አይታየውም?” ብላ አፏን እንደከፈተች አዛውንቱ፣ “ልይስ ቢል ማን ያሳየዋል ልጄ? ጠማማ ነው ብለሽ የተውሽውን እንጨት ‘የቀና ነው’ ብለው ወስደው ማገር አድርገውት ያሳዩሻል። ‘የቀና ነው’ ያልሽውን ደግሞ ጎባጣ ነው ብለው ይተቹብሻል። ከጠማማው ጋር ስትጣመሚ ከቀናው ጋር ስትቃኚ እንዲችው አንቺ ራስሽን ሳትሆኝ ታልፊያለሽ። እህ ታዲያ? ስታስቢው ገና መንገድሽን ሳታጋምሺው አጨራረሱን እያሰብሽ አጀማመርሽን ታበላሺውና ታርፊያለሽ፤” ሲሉዋት ክው አልን። ገና በጅማሬ እንዲህ ከባሰብን መጨረሻችን እንዴት ይሆን ይሆን ጎበዝ?!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወዲያ፣ “እኮ የዓለም መንግሥታት ምን እያሰቡ ይመስላችኋል?” ብሎ ጥያቄ ያነሳል። “ምንስ ቢያስቡ ምን አገባን? እዚህ የጓዳችንን ረሃብና ችግር አንድ ነገር ሳናደርግ ምን ‘ኬላ’ ያሻግረናል?” ትላለች ወዲህ። “እንዴ ዘመኑ እኮ የግሎባላይዜሽን ነው ኬላ አይደለም ህዋም ያሻግራል ጊዜው፤” ይላል ሌላው። “የፍሳሽ ቦይ ተደፍኖ ያቆረውን ውኃ መሻገር ያቃተንን አትርሱን ፕሊስ፤” ትላለች ከወደ ጋቢና። “አሽሟጣጭ ሰውና ጋሬጣ አንድ ናቸው፣ የሚያልፈውን ሁሉ በመቦጨቃቸው፤” ይላል ከወደ ስፒከሩ ከተማ መኮንን። “እኛን ያስቸገረን እኮ ታዲያ የሚያልፈው አይደለም። እኔም አላልፍም እናንተም አታልፉም ብሎ መንገዱን የዘጋው ነው፤” ራሰ በራው ይቀጥላል። “በስንቱ ይሆን ይኼ መንገድ የሚዘጋው?” ትላለች ከአጠገቡ። “የዛሬ ጓደኛ ዋንጫ አገናኘው፣ መለኪያ አገናኘው፣ ሸርተት ሸርተት ይላል መከራ ሲያገኘው፤” ከተማ ቀጥሏል። “እውነት ነው! ይኼው የመከራ ዕለትማ አለሁ ባዩ ሁሉ ቤቱን ዘግቶ ተቀመጠ፤” ወይዘሮዋ አጉል ነገር ጠመዘዘች።

“የምን መከራ ነው የምታወሩት?” ከወደ መጨረሻ ይጠይቃል። “ኧረ ባትሰማ ይሻልሃል። እኛስ ሰምተን ምን ፈየድን? አሥር ሚሊዮን ተራበ፣ 15 ሚሊዮን ደረሰ እያልን መደመር እንማርልሃለን ይኼው፤” ወይዘሮዋ ቀጥላለች። “እስካሁን መደመር አልተማርንም እንዴ?” ነገር ያልገባው ነገር ሊያቦካ ድንጉር ይላል። “እንጃ! እስካሁን መቀነስ ላይ ነበርን። መሸፋፈን ላይ ነበርን። አሁን ግን ይኼው እንደምራለን፤” ይላል መሀል መቀመጫ ላይ ያለው። “ብቻ እነዚህ አይሲስ የሚባሉትን አሸባሪዎች አንድ ነገር ካላደረግናቸው እንጃልን፤” ይላል ደግሞ ከጎኔ። “እኛ ስንት ሆነን ነው እነሱን አንድ የምናደርጋቸው?” ብለው አዛውንቱ ጣልቃ ሲገቡ፣ “እንዴት?” የሚል ጥያቄ ተከተላቸው። “ምን እንዴት አለው? ይኼው እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል እኮ? አንዱ የሚናገረውን ሌላው አይሰማውም። ወዲያ የፈለገውን ሲል ወዲህ የፈለገውን ይቀጥላል። ችግሮቻችን ውስብስብ። ቋንቋችን ውስብስብ፤” ብለው ሳይጨርሱ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ ማስወረድ ጀመረ። “ኧረ መላ መላ . . .” የከተማ እጆች ክራሩን መከርከር ተያይዘውታል። እኛ ግን ወርደናል። ቢሆንም ግን ውስጣችን የሚብሰለሰለው የተለያየ ሐሳብ ወጥሮ ይዞናል፡፡ የሐሳብ ማጥለያ የት ይገኝ ይሆን? መልካም ጉዞ!        

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት