Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን የጠለፈው ረዳት አብራሪ የአዕምሮ ችግር እንዳለበት ተረጋገጠ

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን የጠለፈው ረዳት አብራሪ የአዕምሮ ችግር እንዳለበት ተረጋገጠ

  ቀን:

  ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ጣሊያን ሮም ከተማ ይበር የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የጠለፈው ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ፣ በስዊዘርላንድ የሕክምና ባለሙያዎች የአዕምሮ ችግር እንዳለበት ተረጋገጠ፡፡

  አቶ ኃይለ መድኅን አውሮፕላኑን ለመጥለፍ ያቀደው ቀደም ብሎ ቢሆንም፣ አውሮፕላኑን በጠለፈበት ወቅት ግን የገዛ ድርጊቱን የሚያመዛዝንበት ሁኔታ ላይ እንዳልነበረና ፍርኃትና ጭንቀት ውስጥ እንደነበር ከስዊዘርላንድ ሚዲያ ዘገባዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

  በዚህ የባለሙያዎች የምርመራ ውጤት ሳቢያ አቶ ኃይለ መድኅን የማገገሚያ ካምፕ ውስጥ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን፣ የአገሪቱ ዋና ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ክሱን ማንሳቱ ታውቋል፡፡

  አቶ ኃይለ መድኅን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ይበር የነበረውን አውሮፕላን በረዳት አብራሪነት ኃላፊነትን የወሰደ ቢሆንም፣ ጣሊያናዊው ዋና አብራሪ ከበረራ ክፍሉ ወደ መፀዳጃ ክፍል በሄዱበት ወቅት የበረራ ክፍሉን በመቆለፍ አውሮፕላኑን መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡

  የበረራ መስመሩንም በመቀየር ወደ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያቀና ሲሆን፣ ለረጅም ደቂቃዎች በጄኔቭ አየር ክልል ላይ በመመላለስ ከጄኔቫ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር ጥገኝነት እንዲሰጠው ድርድር ሲያደርግ እንደነበር በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

  በወቅቱ የአውሮፕላኑ ነዳጅ እያለቀ በመሆኑ በውስጡ የነበሩ 202 መንገደኞችን ሥጋት ላይ ጥሎ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ በጄኔቫ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም አሳርፎ በመስኮት በመውጣት እጁን መስጠቱ አይዘነጋም፡፡

  በዚህ የረዳት አብራሪው ድርጊት የኢትዮጵያ ፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሌለበት ክስ በመመሥረትና ምስክሮችን በማቅረብ፣ የ19 ዓመት ጽኑ እስራት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማስወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img