– በአስገዳጁ መመርያ የ37.8 ቢሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል
የግል ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ በአንድ ዓመት ውስጥ በ27.6 በመቶ በመጨመር 124.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ፡፡
የባንኮቹ የ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግርድፍ መረጃ እንሚጠቁመው፣ በ2007 ዓ.ም. የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 97.24 ቢሊዮን ብር የነበረው የተቀማጭ ገንዘባቸው መጠን፣ በዘንድሮ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የ26.9 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በ2008 ዓ.ም. ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ ባንኮቹ ከደረሱበት ከጠቅላላው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 77.3 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በቁጠባ የተቀመጠ ሲሆን፣ በጊዜ ገደብ የተቀመጠው ደግሞ 12.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ብልጫ ያላቸው ሦስት ባንኮች ደግሞ አዋሽ፣ ዳሸንና ሕብረት ባንኮች ናቸው፡፡
አዋሽ ባንክ አምና በተመሳሳይ ወቅት የነበረውን 15.9 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘቡን መጠን፣ በ2008 ዓ.ም. ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ 19.5 ቢሊዮን ብር ሲያደርስ፣ ዳሸን ባንክ ደግሞ አምና በመጀመሪያው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረውን 17.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በ2008 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ወደ 20.19 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ከሁለቱ ባንኮች ቀጥሎ ተቀማጭ ገንዘቡን በከፍተኛ መጠን ያሳደገው ሕብረት ባንክ ነው፡፡ ሕብረት ባንክ በ2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 9.7 ቢሊዮን ብር የነበረውን ተቀማጭ ገንዘብ በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ 12.3 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ እንደ መረጃው እስከ 2008 ዓ.ም. ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ሁሉም የግል ባንኮች የሰጡት ብድር መጠን ደግሞ 80.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኮች ከሚሰጡት ከእያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ በማስላት ለቦንድ ግዥው እንዲያውሉ በሚያስገድደው መመርያ መሠረት፣ እስካሁን ለቦንድ ግዥው ያዋሉት የገንዘብ መጠን 37.86 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በመረጃው መሠረት መመርያው ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እ.ኤ.አ. እስከ ሴፕቴምበር 2015 ድረስ ለቦንድ ግዥው ከዋለው ከ37.86 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ ዳሸን ባንክ የ6.26 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ በመፈጸም ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ንብ፣ ሕብረት፣ ወጋገንና አዋሽ ባንኮች ደግሞ ከአራት እስከ 4.5 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል፡፡
አነስተኛ የቦንድ ግዥ ከፈጸሙት ውስጥ ደቡብ ግሎባል ባንክ ተጠቃሽ ሲሆን፣ ባንኩ እስካሁን ለቦንድ ግዥው ያዋለው 26.14 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ሌሎቹ ከ370 ሚሊዮን ብር እስከ 3.7 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ የፈጸሙ ናቸው፡፡
አምስት የግል ባንኮች ከአምስት ቢለዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል፡፡ ስድስቱ ደግሞ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ለቦንድ ግዥ ማዋላቸውን መረጃው ያሳያል፡፡
ግርድፍ ሪፖርቱ ሁሉም ባንኮች በአትራፊነት መቀጠላቸውን ያመለክታል፡፡ 17 የግል ባንኮች በጥቅል የነበራቸው ከ11.3 ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ዕድገት አሳይቶ 13.2 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡