Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየበጎ አድራጎትና ማኅበራት የሚመሩበት አስገዳጅ የሥነ ምግባር ረቂቅ ደንብ ተዘጋጀ

የበጎ አድራጎትና ማኅበራት የሚመሩበት አስገዳጅ የሥነ ምግባር ረቂቅ ደንብ ተዘጋጀ

ቀን:

ቁጥራቸው ከ3,000 በላይ የሚሆኑ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት በፈቃደኝነት ተስማምተው እንደሚያፀድቁት እምነት የተጣለበት አስገዳጅ የሥነ ምግባር ደንብ ረቂቅ፣ ለመፅደቅ ጫፍ ላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡

ማኅበራቱ የሚመሩበትና የተሰማሩበትን የሥራ መስክ በአግባቡ እንደሚሠሩና ግድፈትም ቢፈጽሙም የሚታረሙበት፣ ወይም የሚቀጡበት ማድረግ የሚቻልበት ደንብ በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡

ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና ማኅበራት መድረክና የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶች ልማት ማኅበራት ኅብረት (ሲሲአርዲኤ) በጋራ ኅዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ባዘጋጁት የግማሽ ቀን ውይይት እንዳስታወቁት፣ ለትርፍ የማይሠሩ በጎ አድራጎትና ማኅበራት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ አስቆጥረዋል፡፡ አብዛኛውን ዓመታት በሥራው ላይ ተሰማርተው ቢቆዩም፣ የሚመሩበት የሥነ ምግባር ደንብ አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን በ1991 ዓ.ም. የወጣ የሥነ ምግባር ደንብ ነበር፡፡ ደንቡ በማኅበራቱ ተቀባይነት ካለማግኘቱም በተጨማሪ፣ ተቆጣጣሪ የሆነው ፍትሕ ሚኒስቴርም ደንቡ ስለመኖሩም የሚያውቀው ስላልነበረ፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሚተካ አዲስ የሥነ ምግባር ደንብ ማዘጋጀት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ እንደተዘጋጀ በውይይቱ ተገልጿል፡፡

የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ 621/2001 ከወጣ በኋላ፣ በተለይ 90 በመቶ የሚሆነውን ዕርዳታ ከውጭ የሚያገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚሰማሩበት የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ፣ ሕጉን በጠበቀ መንገድ አፈጻጸማቸውን እንዲያሳምሩ የሚያደርግ የሚመሩበት የሥነ ምግባር ደንብ መዘጋጀት እንዳለበት፣ የሁሉም በጎ አድራጎት ድርጅቶች ፍላጎት እንደነበር የሲሲአርዲኤ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶ/ር መሸሻ ሽዋረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መሸሻ እንደገለጹት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት፣ የሚሠሯቸው ሥራዎች አድራጎት ብቻ ሆነው መቅረት የለባቸውም፡፡ በሥነ ምግባር ላይ የተመሠረተ በጎ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ ሥራቸውም የተሳካ የሚሆነው በሥነ ምግባር የታገዘና ዓላማውን የጠበቀ መሆን ሲችል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በረቂቅ ደረጃ የቀረበው ‹‹የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት የሥነ ምግባር ደንብ›› የተዘጋጀው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰመረ የበጎ አድራጎት ሥራ ትግበራ ካላቸው በተለያዩ አገሮች ያሉ ተመሳሳይ ድርጅቶች፣ የሚመሩበት የሥነ ምግባር ደንብን በመመልከትና አገሮችን ጋብዘው ሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ፣ በተገኘ ግብዓት ጭምር መሆኑን ዶ/ር መሸሻ አስረድተዋል፡፡ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የአፍሪካና የሌሎች አገሮችንም ተሞክሮዎች መውሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሥነ ምግባር ደንቡ በፈቃደኝነት የሚተገበር ቢሆንም አስገዳጅነት እንዳለው የገለጹት ዶ/ር መሸሻ፣ ከተሰማራበት የበጎ አድራጎት ሥራ ውጪ ተሰማርቶ የሚገኝ ድርጅት ከሥራው መታገድን ጨምሮ፣ የሠራቸው አግባብነት የሌላቸው ሥራዎች በተለያዩ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን እንደሚገለጽና እስከ መሰረዝም እንደሚደረስም በደንቡ እንደተካተተ አስረድተዋል፡፡

ደንቡን የሚያስከብርና የሚያስፈጽም ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ እንደሚቋቋም የገለጹት ዶ/ር መሸሻ፣ አምስት አባላት ከድርጅቶቹ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከመንግሥት አካላት፣ ከኅብረተሰቡና ከታዋቂ ሰዎች መሆናቸውንና በየሦስት ዓመቱ እንደሚቀያይሩ ተናግረዋል፡፡  የሕግ ባለሙያ በሆኑት አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል እንደተዘጋጀ የተገለጸው የሥነ ምግባር ደንብ ረቂቅ 45 አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡ ረቂቅ ደንቡ ላይ ውይይት ተደርጎበት እ.ኤ.አ. በ2016 ይፀድቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ዶ/ር መሸሻ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ ሲሆኑ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ፎረም ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሤን ጨምሮ ማኅበራትን የወከሉ በርካታ ሰዎች ውይይቱን ተካፍለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...