Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅብሔራዊ ቴአትር ኢዮቤልዩውን እያከበረ ያለው በ208 ዓ.ም. (፪፻፰) ነው እንዴ?

ብሔራዊ ቴአትር ኢዮቤልዩውን እያከበረ ያለው በ208 ዓ.ም. (፪፻፰) ነው እንዴ?

ቀን:

ስድሳኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን በያዝነው ኅዳር ወር እያከበረ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለክብረ በዓሉ መሪ ቃል ይሆንለት ዘንድ የመረጠው ‹‹የኢትዮጵያውያን ትውፊታዊ ኪነ ጥበብ ሥፍራ!›› የሚል ነው፡፡ ማለፊያ መሪ ቃል ነው፡፡  ለስድስት አሠርታት ከዚሁ ኃይለ ቃል የሚመነጩ በርካታ ተግባራት እንዳከናወነም ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ የዘመናችን የቴአትር ቤቱ ባልደረቦችና አለቆች ከኢትዮጵያውያን ትውፊታዊ ኪነ ጥበባዊ ተግባራት አንዱ ከሆነው አገራዊ ቁጥር (የግእዝ አኃዝ) ጋር ፈጽሞ እንደማይተዋወቁ የሚያሳይ ክሥተትን በበዓላቸው ላይ አንፀባርቀዋል፡፡ ለበዓል ማብሰሪያ ባዘጋጁት ሰሌዳዎች (ፖስተርና ቢልቦርድ) ላይ በግእዝ/ኢትዮጵያ ቁጥር ፳፻፰ (2008) ብለው መጻፍ ሲገባቸው 2008ን እንዲወክልላቸው የጻፉት ፪፻፰ (208) ብለው ነው፡፡ ቁጥራችንን እንዲንከባከብ ትውልዱም እንዲያውቀው ኃላፊነት ያለበት የባህል፣ የቱሪዝምና የቅርስ አካል የሆነው ብሔራዊ ቴአትር ከእንዲህ ዓይነቱ ገደል ላይ መውደቁ ያሳስባል፡፡ ቴአትር ቤቱ የቁጥር ምንጭ ውስጥ ተቀምጦ በምንጭነት የተጠቀመው በአካባቢው በተለጠፈውና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከዘመን መለወጫ ጀምሮ ምርቱን በተሳሳተ የቁጥር ምልክት ሲያስተዋውቅ ከከረመው ‹‹›ዋሊያ ቢራ›› መውሰዱ ነው፡፡ ብሔራዊ ቴአትር ኢዮቤልዩውን እያከበረ ያለው በ208 ዓ.ም. (፪፻፰) ነው እንዴ? ያሰኘን ለዚህ ነው፡፡ የተለጠፈው ሰሌዳ በአስቸኳይ ካልታረመ ወደፊት ጽሑፉን ለሚያዩ ብሔራዊዎች በዓላቸውን ከ1800 ዓመታት በፊት ነው እንዴ ያከበሩት ማለታቸው አይቀርም፡፡

(ሔኖክ መደብር)  

***************

ሁለት ሞት

ስለ ‹‹ወንበር›› ስንጽፍ … ‹‹ሥልጣን›› ነው እያሉ

ስለ ‹‹መንገድ›› ስንጽፍ … ‹‹ስደት›› ነው እያሉ

ስለ ‹‹መጮህ›› ስንጽፍ … ‹‹አመጽ›› ነው እያሉ

ስለ ‹‹መሳቅ›› ስንጽፍ … ‹‹ምጻት›› ነው እያሉ

ቅኔ ሳንናገር ቅኔ እያናገሩ

በብረት ካቴና እኛን አሳሰሩ

መታሰሩ ሳያንስ …

አስበን ያልነውን አስበው ሳይሰሙ

ቃል እየፈጠሩ

ፊደል እየጫሩ

በአቦ ስጡኝ ግምት ያላልነውን ሲሉ

እኛን አስሰቀሉ እኛን አስገደሉ

መገደሉም ሳያንስ መሰቀሉም ሳያንስ

ለወጭ ለወራጁ አጉልተው እንዲታይ

ሀረግ ባበቀለው መቃብራችን ላይ

‹‹በማያገባቸው ገብተው ተቀጠፉ››

የሚል ሞት ለጠፉ

  • ሰለሞን ሳህለ፣ ያማል፣ 2007 ዓ.ም.

******************

ለፈገግታ

እመቤቲቱ፡- ማሪያ እንግዶች በሚኖሩበት ጊዜ እፀል እያልኩኝ ብጠራሽ የተሻለ ነው፡፡

ሠራተኛዋ፡- እኔስ ማን ብዬ ልጥራዎት እመቤቴ?

እመቤቲቱ፡- (በቁጣ) ደደብ!

ሠራተኛዋ፡- ይሁና እንግዲህ …

********

‹‹ሜሪ፣ ኮርኒሱ ጋ የሚታየኝ የሸረሪት ድር ከየት የመጣ ነው?››

‹‹እኔ አላወቅሁም፣ እመቤቴ፡፡ ግን እዚህ ቤት ውስጥ ሸረሪት ሳይኖር አይቀርም፡፡››

**************

‹‹ጄን ትላንት የሆነ ሰው በሩ ጋ ሲስምሽ አይቼዋለሁ፡፡ ለመሆኑ ፖስተኛው ነው ወይስ የወተት አድራሹ ልጅ ነው የሳመሽ?››

‹‹ከአራት ሰዓት በፊት ከሆነ የወተት አድራሹ ልጅ መሆን አለበት፡፡››

  • ሰለሞን ሰይፈ፣ የሳቅ ምንጭ፣ 2001

*******************

ሀረር ጌይ በሪያች – በአሚሮቹ ዘመን

በጥንቱ ዘመን ሁሉም የሀረር ጌይ በሮች መዝጊያ ነበራቸው፡፡ በሮቹ ከንጋት እስከ ምሽት ባለው ጊዜ ክፍት ይሆኑና ሕዝብን ያስተናግዳሉ፡፡ በጸሐይ መጥለቂያ ወቅት ክርችም ተደርገው ይዘጋሉ፡፡ በሮቹ ከተዘጉ በኋላ እንዲሁ አይተውም፡፡ ከጥንታዊ የዓረብ ብረት በተሠሩ መቀርቀሪያዎች ይቆለፋሉ፡፡ የበሮቹ መፍቻዎች ደግሞ ከሁለት ሰዎች በስተቀር በማንም እጅ እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡ ታዲያ ሁለቱ ሰዎች ቁልፎቹን የሚይዙት በተለያየ ፈረቃ ነው፡፡

‹‹የሀረር ጌይ በሪያች››ን ጧት እየከፈተ ምሽት ላይ የሚዘጋው ሹም ‹‹ቁልፊ ጎይታ›› ይባላል፡፡ በአማርኛ ‹‹የቁልፉ ጌታ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቁልፊ ጎይታ›› አመሻሹ ላይ በሩን ይቆልፈውና መፍቻውን ለሀረር አሚር ያስረክባል፡፡ አሚርም ቁልፉን ለማንም ሳያስነካ ከራሱ ጋር ያሳድረዋል፡፡ ንጋት ላይ ደግሞ ተረኛው ‹‹ቁልፊ ጎይታ›› መፍቻውን ከአሚሩ ይቀበልና በሮቹን ይከፍታል፡፡ ሆኖም ጸሐይ እስክተጠልቅ ድረስ መፍቻውን ከራሱ ዘንድ ያኖረዋል እንጂ ለአሚር አያስረክብም፡፡ ይህም ምክንያት አለው፡፡

‹‹ጌይ ጁገል›› የተገነባበት ዋነኛ ዓላማ ከተማዋን ከጠላት ጥቃት መታደግ ነው፡፡ ለጥቃት የሚመጣ የዚያ ዘመን ወራሪ ግቡን ለማሳካት የሚችልበት ብቸኛው መንገድ በሮቹ ክፍት በሚሆኑበት ጊዜ አድብቶ ወደ ከተማዋ መግባት ነው (በሌላ በኩል ልሞክር ቢል ግንቡ ይከለክለዋልና)፡፡ የከተማዋ አሚሬታዊ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቱን አደጋ በሩቁ ለማስቀረት ያልተቋረጠ ጥበቃ ማድረግ ነበረበት፡፡

በዚህ መሠረት በከተማዋ አቅራቢያም ሆነ ራቅ ባለ ቦታ አንዳች ዓይነት አስጊ እንቅስቃሴ ከታየ፣ ወይንም ከተማዋን ለመውረር የሚገሰግስ ኃይል እየመጣ ስለመሆኑ ከተጠቆመ ‹‹ቁልፊ ጎይታ›› በሮቹን በቶሎ እንዲዘጋ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ለዚህም ሲባል በቀኑ ፈረቃ የበሮቹ መፍቻዎች ከርሱ ጋር እንዲቆዩ ይደረግ ነበር፡፡

  • አፈንዲ ሙተቂ፣ ሀረር ጌይ፣ 2004 ዓ.ም.

***************

የሀላባ ሴራ በዓል (ሀላቢ ሴሪ ከበጀታ)

የሀላባ ልዩ ወረዳ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግሥት ሥር ከሚገኙ 14 ዞኖች 4 ልዩ ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ በ315 ኪሎ ሜትር ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ሐዋሳ ደግሞ በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

የሀላባ ሴራ በዓል በየዓመቱ በታህሳስ(መንገሳ) ወር ይከበራል፡፡ ይህ ወር የተመረጠበት ዋና ምክንያት የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ ወር በመሆኑ ነው፡፡ መንገሳ(ታህሳስ) ወር አርሶ አደሩ አዝመራውን ሰብስባ የሚያጠናቅቅ፣ ግርዘኞች የግርዘኝነት ሥርዓት ጊዜያቸውን አጠናቀው ከልጅነት ወደ ኃላፊነት ዕድሜ የሚሸጋገሩበት ወቅት ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ የሀላባ ሴራ በዓል የታህሳስ (መንገሳ) ወር ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የገጠር ቀበሌያት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በቡድን ቡድን ተከፋፍሎ የተለያዩ የብሔረሰቡን ባህላዊ ጭፈራዎችን በመጨፈርና ሌሎች ባህላዊ ሥርዓቶችን በመፈፀም ይከበራል፡፡ በቀበሌ ደረጃ የጀመረው የበዓሉ አከባበር አድማሱን በማስፋት አጎራባች የሆኑ ቀበሌያት በአንድ ላይ በመሆን ያከብሩታል፡፡ በመጨረሻም በልዩ ወረዳ የብሔረሰቡ ሕዝብና የብሔረሰቡ ወዳጆች በተገኙበት በተመረጠ ቦታ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡

የሀላባ ሴራ በዓል እንዲከበር በተወሰነበት ቦታ አካባቢ የሚኖር ሕዝብ የበዓሉን ታዳሚዎች ለመቀበልና ለማስተናገድ በየቀበሌው ተደራጅቶ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን በግልና በቡድን ባህላዊ ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት የበዓሉን ተሳታፊዎች ይጋብዛሉ፡፡ በበዓሉ ዝግጅት የሀላባ ብሔረሰብ ልዩ ልዩ ባህላዊ ምግቦች፣ ብሔረሰቡ በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ኑሮው የሚገለገልባቸው የተለያዩ ባህላዊ ቁሳቁሶች ጭምር ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡ በተጨማሪ የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ውድድር የበዓሉ አንኳር ዝግጅቶች ነው፡፡  

  • ቱባ፣ የካቲት 2002   

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ