Thursday, May 30, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ አንድነት ለምን ያስፈልጋል?

ውድ አንባቢያን ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ ግንኙነት በሚመለከት ሰፋ ያለ ጥናት ሳካሂድ ቆይቻለሁ፡፡ የጥናቱም ውጤት 800 ገጾች ባሉት መጽሐፍ ተጠቃሏል፡፡ ይህን መጽሐፍ በአምስት ሺሕ ቅጂዎች ለማሳተም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያ ደግሞ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፡፡ ስለዚህም በሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ፈቃደኛነት የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝቦች አንድነት በሚመለከት ያደረግሁትን የጥናት ጭማቂ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ወደ ጽሑፉ ከመግባታችን በፊት ግን አንድ ነገር ላውሳ፡፡ ይኸውም በአሁኑ ጊዜ የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሰላማዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነትን በሚመለከት በአውሮፓና በሌሎችም ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እየተነጋገሩበት እንደሆነ ጥናቱን ካጠናቀቁ በኋላ በጉዳዩ ላይ ከሰዎች ጋር ስነጋገር ተገንዝቤያለሁ፡፡ ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚነጋገሩት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ፓርቲዎች፣ ወገኖች፣ ቡድኖች፣ ክፍሎችም ጋር ሆነ ከሚያስቡበት ሰዎች ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌለኝ መሆኑን አስቀድሜ ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

የመጽሐፉ መሠረታዊ ዓላማ

የመጽሐፉ መሠረታዊ ዓላማ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ታሪክ በማውሳት ወደ ቀዳማዊ አንድነታቸው ተመልሰው ጥንታዊ ታሪካቸውን እንዲያድሱ፣ የህዳሴ እንቅስቃሴያችን በፖለቲካ ዕርቅ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች ታሪክ ዕርቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዲገነዘቡ፣ የታሪክ ዕርቅን ተመሥርተው የሚከተሏቸው ሰላማዊ መንገዶች ከሁሉ አስቀድመው ከአመፃ የጸዱ፣ ቀጥሎም ለሽምግልና የተሻሉ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ መሆናቸውን አውቀው በጋራ እንዲንቀሳቀሱ ሐሳብ ለመሰንዘር ነው፡፡ ሰዎች እኔ ማን ነኝ ብለው በመጠየቅ የማንነታቸውን ጥያቄ ራሳቸው እንዲመልሱ አስተያየት ስለመስጠት ነው፡፡ ይኸው የሰላም ፍኖት የኢትዮጵያንና የኤርትራን አንድነት ደረጃ በደረጃ፣ ቀስ በቅስ፣ ሥልትና ሀቅን በተከተለ መንገድ፣ ከጥንት ጀምሮ እንደኖሩትና እንደነበሩት ከሁሉ አስቀድሞ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቦች፣ ኅብረተሰቦች ብሎም ሕዝቦች አንድ እንዲሆኑ፣ አንድ ሆነውም የተሻለ የጋራ ልማትና ብልጽግና እንዲያመጡ፣ በአፍሪካ ቀንድ ስመ ገናና ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመጠቆም ነው፡፡ በመሠረቱ የጸሐፊው ራዕይ በአፍሪካ ቀንድ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ኑሮና በፖለቲካ የተሳሰረ ብሎም የተዋሀደ ማኅበረሰብ ዕውን እንዲሆን ነው፡፡

ይሁንና ሁኔታዎች ከሽምግልና አኳያ ነገሮች በአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን፣ ቢቻል በሁለትና ከሁለት በላይ በሆነ አቅጣጫ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሳንቲም እንኳን በተለያየ አቅጣጫ ለሚመለከተው የተለያየ ስለሚመስል ነው፡፡ ስለሆነም የሰላም ፍኖታችን የሰመረ ይሆን ዘንድ ጉዳዩን በሦስት አቅጣጫዎች ማለትም በጥቅልና ሁለቱን በተናጠል እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

ጥቅል የማንነት ጥያቄ

በመሠረቱ ማንነት ከእናት ማህፀን፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በአካባቢ፣ በቀበሌ በአገር፣ ወዘተ የሚዳብር ሲሆን በአገር ደረጃ የሚገኘው አገራዊ ባህርይ ይባላል፡፡ በአገራዊ ደረጃ ከሚከሰቱት የማንነት መገለጫ ባህሪያት አንዱ ብሔራዊ ኩራት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊ በውጭ ወራሪዎች ስላልተገዛች በውስጥ የበታችነት ስሜት አይንፀባረቅባትም፡፡ ይህ ብሔራዊ ኩራት ለረጅም ጊዜ የሚታይና በመንፈስም የሚተላለፍ በመሆኑ ኢጣሊያውያን የኤርትራ ሕዝብን ነጥለው መግዛት እንዳልቻሉ፣ ባለመቻላቸውም ከተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ጋር ቀላቅለው ለመግዛት ጥረት አድርገው እንደነበረ፣ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ የኤርትራ ክልል ነዋሪዎች ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ሰብዕና እንዳላቸው በማስተማር፣ በአዲሱ ማንነታቸው ለእነሱ እንዲሰግዱ በሌላ መንገድ ጥረት እንዳደረጉ እንረዳለን፡፡

የኤርትራ ሕዝብ በመጀመሪያ በኤርትራ ነፃነት ግንባር፣ ቀጥሎም፣ በጀብሃ፣ ቀጥሎም በኤርትራ ሕዝባዊ ነፃነት ግንባር በጦር መሣሪያ ትግል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሚያዚያ 1983 ዓ.ም. የደርግን ሠራዊት ድል በማድረግ ኤርትራን ከኢትዮጵያ አስተዳደር ለይቷል፡፡ አሠራሩ አከራካሪ (አከራካሪነቱን በዝርዝርና ከዚህ ቀደም ቀርቦ በማያውቅ መረጃ ወደፊት እንመለከታለን) ቢሆንም፣ የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔን የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በጸጋ ተቀብሎታል፡፡ ከሪፈረንደሙ በኋላ በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር በልዩ ልዩ መስኮች ጥረት ማድረጉን ቀጥሎ ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከ1985 እስከ 1988 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በሰሜን ትግራይ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፣ ለብዙ ዓመታት በጦርነት እየታመሰ ፍዳውን ያይ የነበረ ሕዝብ እፎይታ አግኝቶ ነበር፡፡ ከዛላ አንበሳ ወደ ሰነዓፈ፣ ከዓደዋ ወደ አድቀይህ፣ ከሽሬ ወደ ሰራዬ፣ ከሌሎች ሥፍራዎች እየተነሳ ይንቀሳቀስ የነበረው ሕዝብ ጦርነት ያስከተለውን ችግር በአጭር ጊዜ ረሳ፡፡ ተለያይተው የነበሩ ወንድማማቾችና እህትማቾች፣ አባትና ልጆች፣ ባልና ሚስቶች እየተገናኙ ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ለመንግሥታቱም ምሥጋና አቀረቡ፡፡ ድሮውንም የነበረው የጋብቻ ትስስር ቀጠለ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገበያ መጥቶ መነገድም ሆነ ወደ ኤርትራ ድንበር ገበያ ሄዶ ነግዶ መመለስ መዘውተር ጀመረ፡፡ ከጦርነቱ በፊት አንድ የነበረው ሕዝብ ያኔውኑ እንደነበር አንድ ሆነ፡፡ ኤርትራም ለዓለም ገበያ በቡና አቅራቢት ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ምርቶች ግንባር ቀደም አገር የሆነችበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህንንም ወደፊት በስፋት የምንመለከተው ይሆናል፡፡

እስከዚያው ድረስ ግን…. አገር ማለት፣ ታሪክ ማለት፣ ባህል ማለት፣ ማኅበራዊ ሕይወት ማለት ማንነት ነው፡፡ ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› ስንል ‹‹እኔ አገሬ ነኝ፣ እኔ ታሪኬ ነኝ፣ እኔ ባህሌ ነኝ›› እንላለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ፣ ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› ብለን እንጠይቅና ‹‹እኔ የኢትዮጵያ ጥንታዊና ዘመናዊ ኅብረተሰብ ማኅበራዊ ሕይወት ነኝ›› የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ እንግሊዝ አገር ቢቀመጥ፣ ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝ ዜግነት ቢሰጠው ስለእንግሊዝ አገር ማወቁና ለእንግሊዝ ሕገ መንግሥት ማደሩ የማያጠያይቅ ቢሆንም ሰብዕናው  ውስጡ፣ እኔነቱ ግን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለብዙ ዓመታት አሜሪካ የኖሩ፣ ለአሜሪካ የሠሩ፣ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አፍሪካውያን የጥንት ትውልዳቸውን የሚቆጥሩትና ከዚህ ጋር የተያያዘ የሚሠሩት የማንነት ጥያቄ በትውልድም የሚወረስ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

በመሠረቱ አንድ ሰው በማንነቱ ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሌላ ለመሆን ቢፈልግ እንኳን በውስጡ ያለው ማንነቱ ‹‹አለሁ›› ብሎ ሳያውቀው አፈትልኮ ይመሰክርበታል፡፡ ‹‹ላንቺ ይመስልሻል ብቻዬን ሄጃለሁ፣ ዘወር ብለሽ እይኝ ተከትየሻለሁ፤›› እንዲሉ ሌላ የሆንን ቢመስለንም ማንነታችን ይከተለናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ በግል አመለካከታቸው ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ››፣ ‹‹አይደለህም›› ሊባባሉም ይችላሉ፡፡ ሁለቱ በተናጠል ወይም በጋራ ከሌላ ሰው ጋር ሲወያዩ ያ ሌላ ሰው በሁለቱ መካከል በሐሳብ አቀራረብ፣ አገላለጽ፣ በሥነ ባህሪ፣ በእንቅስቃሴ ልዩነት ላያይ ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ጋር አንድ ምዕራብ አፍሪካዊ ወይም ደቡብ አፍሪካዊ ዘግይቶ ቢመጣና ቢቀላቀል ግን የተለየ መሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይታወቃል፡፡  ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሱዳን፣ የግብፅ፣ የጂቡቲ፣ የሶማሊያ ተወላጆች ቢኖሩ የሶማሊያና የጂቡቲዎቹ ሰዎች ከሱዳኖቹና ከግብፆቹ ይበልጥ ተመሳሳይ ባህርይ ይኖራቸዋል፡፡

ዊልያም ጀምስ የተባሉ የሥነ ባህርይ ሊቅ (በ1892) እኔነት ሁለት ደረጃዎች ሲኖሩት አንደኛው ራስን የማወቅ ሒደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ራስን በሒደት ማወቅ ነው፡፡ ራስን ማወቅም ቁሳዊ እኔነት፣ ማኅበራዊ እኔነትና መንፈሳዊ እኔነት እንደሆኑ ዊልያም ጀምስ ይተነትናሉ፡፡ (James, W. Psychology: The briefer course. New York: Henry Holt (1892) ማኅበራዊ እኔነት (ማንነት) ሌሎች ስለእርሱ የሚረዱት ሲሆን፣ ቁሳዊ ማንነት ደግሞ የእኔ ባዩ አካልና የእርሱ ንብረት ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ ማንነት ደግሞ በውስጡ የሚሰማው የእኔነት ስሜቱ ነው፡፡

‹‹እውነተኛ ማንነት በውጭ ከሚንፀባረቀው ጋር ይወዳደራል (ይመሳሰላል) ማለት አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ሮይ ኤፍ ባውመስተር እና ማርክ ሙራቬን ማንነትን ከማኅበራዊ፣ ባህላዊና ከታሪካዊ ዓውድ ጋር ማዋሀድ (ማስማማት) በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት ግለሰብ ሊመርጥ፣ ሊለውጥ፣ እንደሚመቸው አድርጎ ለማሻሻል ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚያ የግለሰብ ማንነት ህልውና እንዲኖረው ታሪክ፣ ባህል፣ ተቀራራቢ ማኅበራዊ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፡፡ (Roy F. Baumeister and Mark Muraven, Journal of Adolescence 1996, 19, 405 – 416) በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህን በሌላ ሁለት ምሳሌዎች እንመልከተው፡፡

አንደኛው አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሲሆኑ፣ እርሳቸው ኢሕአዴግ ለአገሪቱ የወደፊት የፖለቲካ ሒደት መሠረት ጣይ የሆነውንና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያቅፈውን ጉባዔ ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም. በመጥራት በአፍሪካ አዳራሽ ጉባዔውን ባካሄደበት ጊዜ የጉባዔው ታዛቢ በነበሩበት ጊዜ በአስተርጓሚያቸው አማካይነት አስተያየት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአስተርጓሚያቸው አማካይነት የሚያስተላልፉት መልዕክት የሐሳባቸው ስላላደረሰላቸው ግን በድንገት እንዲህ በል ብለው አስተርጓሚያቸውን ማረም ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በጉባዔው አዳራሽ የነበረውና ጉባዔውን በቴሌቪዥን በቀጥታ ሲከታተል የነበረው ‹‹እንዲያ ነው ፈረንጅ›› አለና ሽሙጥ ነገር ጣል እንዳደረገ ይታወሳል፡፡ ቁም ነገሩ ግን ንግግራቸው ለ30 ዓመታት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመነጠል የመረረ ጦርነት ቢያካሂዱም፣ ከውስጣቸው ኢትዮጵያዊ የሆነ ስሜት አለመጥፋቱን ፍንትው አድርጎ ማሳየቱ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ያህል ተመሳሳይነት ቢኖር የተዘራ ጥላቻ ካለ፣ የእርስ በርስ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ካለ፣ መከዳዳት ካለ፣ ያ ጥላቻ፣ ያ የፈሰሰ ደም፣ ያ ክህደት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሊደበዝዝ ይችላል፡፡ ወይም በአንድ አካባቢ ተወልደው ያደጉ ሦስት አራት (መቶም፣ ሺም ሊሆን ይችላል) ኢትዮጵያውያን አካባቢያቸውን ትተው  ወደ ሦስትና አራት ቦታዎች (አውሮፓ፣ ቻይና፣ አላስካ፣…) ቢሄዱ  ለጊዜው አነጋገራቸው፣ አለባበሳቸው፣ አመጋገባቸው፣ አኗኗራቸው፣ ወዘተ ሊቀይር ይችላል፡፡ ተመልሰው ሲገናኙም ብዙ የተለወጡ ሊመስል ይችላል፡፡ ይህ አዲስ ማንንነት ግን እንደ ጭምብል ቢሆን እንጂ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን የሚያጠፋ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ውጤትን በሚመለከት ሚያዝያ 21 ቀን 1985 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 እስከ 12፡00 ሰዓት ባካሄደው አምስተኛ አሰቸኳይ ሰብሰባው ሰፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ በከፍተኛ ድምፅ ሲያፀድቅ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩትና የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት መሆኑን አጥብቀው የሚያምኑት አቶ መለስ ዜናዊ በሰጡት የግል አስተያየት እንደሚከተለው ተናግረው ነበር፡፡

‹‹እያንዳንዱ የራሱ የሆነ አመለካከት አለው፡፡ እኔ አሁን የምናገረው የራሴን አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም ለመግለጽ የምፈልገው በሪፖርቱ ላይ የሪፈረንደሙ ውጤት የአንድ ፖለቲካ ታሪክ ፍፃሜ ነው ስለመባሉ ነው፡፡ በእርግጥም የአንድ ፖለቲካ ታሪክ ፍፃሜ ነው፡፡ ነገር ግን የታሪክ መጀመሪያም መጨረሻም አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት ታሪክ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ይኖራል…. ከ50 ዓመታት በፊትም፣ በኢጣሊያ ጊዜም፣ በፌደሬሽኑ ወቅትም፣ በዘውዳዊውና በደርግ አገዛዝ ሥርም፣ በሽግግር መንግሥቱ ወቅትም፣ ብዙ የፖለቲካ ክስተቶች ተለዋውጠዋል፡፡ ነገር ግን ከታች ያለው መሠረታዊ የሕዝቦች ግንኙነት ግን አልተለወጠም፡፡ … እርግጥ እነዚህ መሠረታዊ ግንኙነቶች በአንዳንድ የፖለቲካ ፍፃሜ ባህርያቸው ሊቀይሩ ባይችሉም ደግሞ ሊደበዝዙ ወይም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ መሠረታዊ ግንኙነቶች ላይ በየቀኑ ቦምብ በሚወርድበት ወቅት መደብዘዛቸው አይቀርም፡፡ በመጀመርያ የሚታየው፣ በመጀመርያ የሚታሰበው፣ የሚወርደው ቦምብ ነው፡፡ አብሮ የሚፈጠር ቁስል ነው፡፡ ቦምብ የሚበጣጥሰው አካል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የጦርነት ግንኙነት በሚኖርበት ጊዜ ከሥር ያሉት ዘላቂ የሆኑት መሠረታዊ የሆኑ ግንኙነቶች ይዳፈናሉ፡፡ በደም ይሸፈናሉ፡፡ ይህ የደም ደመና በሚለቅበት ጊዜ ከሥር ያሉት ግንኙነቶች የሚገኙት እዚያው ሆነው ነው፡፡ …. አሁን ያለው እውነት ያ በደም ደመና ተሸፍኖ የነበረ፣ ነገር ግን እየተለወጠ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤›› በማለት በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ መካከል የቆየውን የወንድማማችነት መንፈስ ለማጠናከር የሚፈለግ ከሆነ፣ ሕዝበ ውሳኔውን መቀበል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ነበር፡፡ (ይህንንም በሚመለከት ጸሐፊው ሰፋ ያለ ዘገባ ስላለው ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ የሚተነትነው ይሆናል)

ይሁንና ማንነቱ ግን በአገር ብቻ ሳይሆን በቀበሌም ሊወርድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ወሎዬዎች በጥቀሉ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም፣ ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ግዛት ቢሄዱ ከዚያ ግዛት ማኅበረሰብ የተለየ መገለጫ ባህሪ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዱ ሸዌ ወላይታ ሄዶ ‹‹መሂና ተራው የት ነው?›› ብሎ ቢጠይቅ፣ ‹‹አየ ጉድ ማክና እላለሁ ብሎ መሂና ይላል፤›› እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡

ለመሆኑ ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› ብሎ መጠየቅና ራስን ማወቅ ምንድነው? ስለዚህ ጉዳይ በርካታ ሊቃውንት ከጥንት ጀምሮ አስተያየታቸውን፣ ምክራቸውን፣ ፍልስፍናቸውን፣ አመለካከታቸውን ሰጥተውናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ግርሃም ግሪን የተባለው ዕውቅ ደራሲ ሲሆን እርሱም ‹‹የጉዳዩ ማለቂያ›› The End of the Affair በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ፣ ‹‹እኔ የሚያሰኝህን ሁሉ ብትጥል ምን ትሆን ይሆን?›› ማለቱ ይጠቀሳል፡፡ መልሱም ‹ከሁለት ያጣ ጎመን› የሚል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ መንግሥት ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ውጪ የሆነ ሰው ሠራሽ ኤርትራዊነት ቢሰጠው ላይ ላዩን ሊገለጥ በሚችል ባህርይው ሌላ የመሆንን ስሜት ሊያንፀባርቅ ቢሞክር እንጂ፣ በውስጡ የተለየ ኤርትራዊ ሊሆን አይችልም እንደ ማለት ነው፡፡ ወይም በተለምዶ ተዋናይ ቋሚ የሆነ ማንነቱን የማወቅ ችግር አለበት እንደሚባለው ነው፡፡

በእርግጥም አንድ ተዋናይ እንደተላበሰው ገጸ ባህርይ ላዕላዊ ማንነቱ ሊለዋወጥ እንደሚችለው ሁሉ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎችም ያልሆኑትን ልሁን ቢሉ የራሳቸውን ማንነት ሊጠፋባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኤርትራው መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በአመዛኙ የትግራይ (የኢትዮጵያ አካል) በመሆናቸው ‹‹ኤርትራውያን ነን›› በሚሉ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ በጥርጣሬ ዓይን እንደሚታዩት ሁሉ ማለት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ተስፋ ጽዮን መድኃንዬ ‹‹ይኸውና! ኤርትራ ሞተች። ትግል ለአገር ትንሳኤ!!›› በተሰኘው ሥራቸው በተለያዩ ገጾች፣

ዓንደብርሃን ወልደጊዮርጊሰ በቅርቡ ባሳተመው መጽሐፍ ኢሳያስ ሲሰክር፣ ‹‹እኔ በሌለሁበት ዓጋመ እያላችሁ እንደምታሙኝ አውቃለሁ፣ ግን ክንዴን አሳያችኋለሁ። ይችን አገር እንዳመጣኋት ድምጥማጧን አጠፋታለሁ፤›› ብሎ ይዝት እንደነበረ ነግሮናል። ዓንደብርሃን ይህን መረጃ ስላካፈለን ለሥነ ሥርዓቱ እናመሰግነዋለን። ከዚህ በተረፈ ኢሳያስ ርዕሰ ብሔርና መራሔ መንግሥት ተብሎ ኤርትራን አጠፋታለሁ ብሎ በግልጽ ሲናገር እየሰሙ ዓንደብርሃንና ሌሎች የኢሳያስ አገልጋዮች ምን ሲያደርጉ ነበር? የሚል የክስ መልክ ያለው ጥያቄ ማንሳት የግድ ይላል። ይህ ነገር ራሱን የቻለ ጉዳይ ስለሆነ አሁን እንዲሁ በጨረፍታ ብቻ ጠቅሼው ልለፍ። ይህንንና ሌሎች ተዛማጅ አርዕስቶችን ለሌላ አጋጣሚ በግርድፍ ልተዋቸው መርጫለሁ። … የኢሳያስ ንግግር ብቅል ያወጣው የማይጎዳ ትርጉም-የለሽ አባባል ነው በማለት ችላ ተብሎ የሚታለፍ አይሆንም። ኢሳያስ ምንም ቢሰክርም እንደዚህ ዓይነት ንግግር ዝም ብሎ እንደመጣለት ይጥላል ብዬ አላምንም። … ኢሳያስ ይህንን ዓይነት ፉከራ ያሰማው ከነፃነት በኋላ እንደሆነ ብቻ እንጂ በትክክል መቼ እንደሆነ አልተነገረንም። የሆነ ሆኖ መታወቅ ያለበት እውነታ ኢሳያስ ኤርትራን ማጥፋት የጀመረው ድሮ የትግራይ ትውልድ እንዳለው እንኳን የማይታወቅበት በነበረ ጊዜ ነው። ኢሳያስ ለምን አሁን ደርሶ ይህን ቃል ያነሳል? እንዲሁ ዓጋመ ስለተባለ ሊሆን አይችልም፣ ዓጋመ የሚሉት ሰዎች ካሉ ደግሞ ‹‹ዓጋመ›› የሚለው ቃል ያን ያህል ከባድ ስድብ ሆኖ አገርን ያህል ለማጥፋት ምክንያት ሊሆን? የማይመሰል ነገር ነው። … ኢሳያስ ከትግራይ የትውልድ ሐረግ ቢኖረውም ቅሉ በኤርትራ ተወልዶ ያደገ ስለሆነ ኤርትራዊ ዜጋ ነው። ስለዚህም የኢሳያስን ትውልዳዊ ማንነት ማንሳቱ ወይም መተንተኑ አስፈላጊ ባልሆነ ነበር። ነገር ግን ኢሳያስ ራሱ የመረጠው ዓላማና እያራመደው የቆየና አሁንም እየተገበረው ያለው ፀረ አገራዊ ፖሊሲ፣ የትግራይ ትውልደ ሐረጉን እንደ አንድ መሥፈርት ወይም መገለጫ ወስደን ልንጠቅሰው ተገድደናል። ኢሳያስ አፈወርቂ ለራሱ በአመዛኙ ትውልደ ትግራይ ያለው ስለሆነ ወያኔን የሚያነሳሳውን ውስጣዊ ግፊት (ወይም ምኞት) የሚጋራ ነው፤›› በማለት ‹‹ዓጋመ ማለት አነስ ያለ ስድብ›› መሆኑን በሚገልጽ መንገድ ሐሳባቸውን ያሰፈሩትን ለአብነት ብንወስድ፣ ‹‹ሐበሻ ማንነቱን፣ ነብር ዝጉርጉርነቱን አይለቅም›› የሚለውን የሚያመለክት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ተስፋ ጽዮንም የጀበሃን ዓላማ ስለሚያራምዱ ኤርትራዊ ነኝ ባይ ቢሆኑም እንጂ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው በተለያዩ መንገዶች እየዘለቀ የሚያስቸግራቸው ሰው እንደሆኑ ሥራዎቻቸው ይመሰክሩባቸዋል፡፡ የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር ከተጠቀሰው ሥራቸው ለአብነት ያህል እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

‹‹ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ እንዲያውም ከ40ዎቹ ጀምሮ የኤርትራ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተዛምዶ ነው ሲታይ የነበረው። ባላት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ምክንያት ኤርትራን ለመቆጣጠር ፍላጎትና ምኞት ያላቸው የባዕድ ኃይሎች፣ ኤርትራን በሚመለከት ስትራቴጂያቸውን ሲቀርፁና ሲነድፉ በኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት እንደነበረና ከእነርሱ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና እንደነበረው ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ይህም ማለት ሌላ የተሸፈነ ትርጉም ከሌለ በስተቀር ‹ለ50 ዓመታት ያህል በኢጣሊያና በእንግሊዝ ስትተዳደር ከነበረች በኋላ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሪፈረንደም የተቀላቀለችው፣ አቀላቃዮቹ (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት) ድሮውንም የኢትዮጵያ አካል መሆኗን አውቀው ነው› የሚል አስተሳሰብ በውስጡ አለው፡፡ ፕሮፌሰር ተስፋ ጽዮን ቀጥለውም በሽግግሩ ዘመን የተፈጸመው ሪፈረንደምም፣ ‹‹ባጭሩ ሲታይ፡ … የኤርትራን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ተብሎ በቅንነት የተቀናጀና የተደራጀ አልነበረም፤›› ይላሉ፡፡ (ይህንንም ‹‹ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፤ እንዲሉ›› ጸሐፊው ወደፊት ዝርዝር መረጃዎችን የሚያቀርብ መሆኑን ቃል ይገባል፡፡) እስከዚያው ድረስ ግን በፕሮፌሰሩ እምነት ሁሉም በሻዕብያ ተጀምሮ በሻዕብያ ማለቅ ሳይኖርበት ሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው፡፡

ፕሮፌሰር ተስፋ ጽዮን በተጨማሪም፣ ‹‹ይህን ዕውን ለማድረግ ከኤርትራ ጋር ለመተጋገዝ ጥቅም ያላቸው፣ በተለይም ከጎረቤቶቻችን እነማን ናቸው ብለን መለየት አለብን። ከእነዚህ አጎራባች አገሮች ውስጥ በኤርትራ ላይ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ጥቅም ያላት ሱዳን አይደለችም፡፡ ጂቡቲ አይደለችም፡፡ የመንም አይደለችም። ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሁሉም መስክ ለመዛመድ መሠረታዊ የሆኑ ጥቅሞች አሏት። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ብቻ ናት የባህር በር የሌላት፡፡ በቀይ ባሕር በኩል የምትዋሰነው ደግሞ ከኤርትራ ጋር ብቻ ነው። ስለዚህ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ለሕይወት አስፈላጊ በሆነ ዓይነትና መጠን ጠቃሚ ናት። ይህ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ለትብብር ዝምድና ፅኑ መሠረት ሊሆን ይችላል። ኤርትራም በሁሉ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በመዛመድዋ ለሕይወቷ አስፈላጊ የሆኑ ጥቅሞች እንደምታገኝ መታወቅ አለበት። በዚሁ የጽሑፌ ክፍል ኢትዮጵያ በሚኖራት ጥቅም ላይ ያተኮርኩበት ምክንያት፣ በቀጠናችን ከኤርትራ ጋር ተገቢነት ባለው ጥቅም ላይ የተመሠረተ ዝምድና የምትፈልግ አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን ለማሳየት ነው፡፡››

ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን በተጠቀሰው ሥራ የመጀመሪያ ገጾችም እንዲህ ይሉናል፡፡

‹‹ኤርትራ በደቡብ በኩል የኢትዮጵያ አካል ከሆነችውና ሕዝብዋ ትግርኛ ተናጋሪ ከሆነው የትግራይ ክፍለ ሀገር ጋር የምትዋሰን መሆንዋ፣ አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ትልቅ መሰናክል ነው። የትግራይ ሕዝብ በኤትኒካዊ ማንነቱ፣ በባህልና በሃይማኖት ከደገኛው (ከበሳ) ትግርኛ ተናጋሪ የኤርትራ ሕዝብ ጋር አንድ ነው።›› ቀደም ሲል በተቀመጡት አንቀጾች ምን እንረዳለን ብለን ስንጠይቅ፣ በሰውየው ውስጥ ምንም ያህል የነፃነት ፍላጎት ቢኖርም ኢትዮጵያዊ ሰብዕና እንደሚያይልባቸው ነው፡፡ በዚህ መነጽር ሌሎች ነፃነት ፈላጊ ነን ባይ የኤርትራ ተወላጆችንም ማየት ይቻላል፡፡

በጸሐፊው ግምት ‹‹ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት ኤርትራውያንን ቢጨቁንም፣ የደርግ መንግሥት ደግሞ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ቢያካሂድም፣ እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ ልሆን አልችልም፤›› ብለው ሐምሌ 13 ቀን 1986 ዓ.ም. ያሸለቡትና አስከሬናቸው ከአሜሪካ (ኖርዝ ካሮላይና) መጥቶ ቅድስት ሥላሴ ያረፈው ፕሮፌሰር አብርሃም ደሞዝና ሌሎች ከእርሳቸው ጋር ተመሳሳይ አቋም ያሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር ታላቅ ስለሆነ፣ ክብር ሲሰጣቸውና እንደ አብነት ሊወሰዱ ይገባል፡፡ ሌላው ተጨባጭ ምሳሌ የሚሆኑን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ኢሕአዴግ ሥልጣኑን እንደያዘ፣ ‹‹ኤርትራዊ ስለሆኑ ኢትዮጵያን ለመበቀል ሲሉ ልዩ ልዩ መጥፎ ዕርምጃዎችን ሊወስዱ ይችላሉ›› እየተባሉ በብዙ የግል የፕሬስ ውጤቶች ይወነጀሉ ነበር፡፡ ይልቁንም፣ ‹‹የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው›› የሚለው ጠንካራ አቋማቸው በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥርጣሬ ላይ ጥሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የኤርትራን ነፃነት አንድም ወደው እንዳልተቀበሉት፣ ወይም እርሳቸውና ሌሎች ጥቂት የትግል ጓዶቻቸው ብቻ የሚያውቁት ምክንያት፣ ካለበለዚያም እነሱ በትግል በነበሩበት ጊዜ ለኤርትራ የቅኝ ግዛት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ሌላ አማራጭ እንዳልነበረ በማመን እንደሆነ የሚያመለኩቱ ብዙ ምክንያቶችን፣ መላ ምቶችንም መምታት፣ ከዚህና ከዚህ የተንጠባጠቡ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዱም ከኦሮሞ፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39ኝ እየጠቀሱ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በሶማሌ፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር፣ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ ዞኖች ሲጠይቁ ልዩ ልዩ ሰበቦችንና ምክንያቶችን እየደረደሩ ጥያቄውን ማቀዝቀዛቸውና ‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት የራስን ዕድል በራስ መወሰን ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከመበታተን ትልቅ አገር መሆን ለተፋጠነ ልማት የበለጠ ጠቃሚ ነው፤›› የሚል አመለካከት እንዲሰፍን ጥረት ማድረጋቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሽግግር መንግሥቱ በተመሠረተ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የሽግግር መንግሥቱን የመሠረቱና በተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የነበራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ወደ ልዩ ልዩ አገሮች ኢምባሲዎች እየሄዱ ኢሕአዴግን በሚኮንኑበት ጊዜ፣ ‹‹ስሙ እናንተ ዛሬ የምትለማመጧቸው አገሮች እኮ የእናንተ አገር ከፍተኛ ሥልጣኔ በነበራት ጊዜ በዘላንነት ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ክብራችሁን ጠብቁ፤›› በማለት ከሌሎች ዕርዳታ ለመፈለግ ከሚሯሯጡ በምክር ቤቱ ውስጥ ተቀምጠው ተከራክረው እንዲያሸንፉ መምከራቸውን ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡  በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ግምት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አባባል፣ ሳሙኤል በትለር እንዳለው ማንነታችሁ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ነው ማለታቸው እንደሆነ አያጠያቅም፡፡ ሰውየው ሶማሌዎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚጋሩዋቸውና አንድ የሚያደርጋቸው ማንነታቸው አብረው እንዲቆዩ እንደሚያደርጓቸውም አሳማኝ በሆነ መንገድ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያውያን በጂኦግራፊያዊ አሰፋፈራቸው፣ በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፣ ወዘተ. የተለያዩ ቢሆኑም የጋራ ማንነት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ ግሬይ ፉል የተባሉ የሥነ ባህርይ ሊቅም ይህን በሚመለከት ‹‹የትናንቱ እኔ ከዛሬው እኔ ጋር ሥነ ባህሪያዊ ግንኙነት አላቸው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

የማንነት ምንነትን በተጨባጭ ለማሳየት እንዲቻል ቀደም ሲል የቀረቡት ሐሳቦች በምሳሌነት ቀረቡ እንጂ ከዚህ ሰፋ ባለ መንገድም ማቅረብ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ማንነት በረጅም የታሪክ ሒደት የሚዳብርና ይህም በተለያዩ ባህሎችና አስተሳሰቦች የሚገለጽ መሆኑ ነው፡፡ ጆን ሎክ የተባሉ ታዋቂ እንግሊዛዊ ፈላስፋ ማንነትን ከንቃተ ህሊና ጋር አያይዘው ያቀርቡታል፡፡ ንቃተ ህሊና ደግሞ በደመነፍስ ከሚደረግና  ከሚንፀባረቅ ባህርይ የተለየ ሲሆን በኅብረተሰብ የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ይህም ማለት አዲስ ልምድ፣ አዲስ ባህል፣ አዲስ አመለካከት ንቃተ ህሊናን አያጎለምሰውም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድ በኑክሌር ፊዚክስ የተራቀቀ ኢትዮጵያዊ በውስጡ ‹‹ብቀጥንም ጠጅ ነኝ›› እንዲሉ ኢትዮጵያዊ ኩራት የሚባለው በውስጡ አይኖርም፣ ወይም በኑክሌር ፊዚክስ ዕውቀት ታጥቦ ሄዷል ማለት አይደለም፡፡ የሳይንስ ክህሎቱ፣ የአካሄዱ፣ የአነጋገሩ፣ የአለባበሱ፣ ወዘተ መገለጫዎች ከሌሎች አገሮች ሳይንቲስቶች ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም የሐዘንም ሆነ የደስታ፣ የፍቅር፣ የጥላቻ፣ ስሜቱን የሚገልጥባቸው ባህሪያቱ ከእርሱ ጋር ናቸውና የሚገለጡት እንደ ሳይንሳዊ ትንተና አቀራረብ አይደለም፡፡ የሚገለጡት ‹‹ጅብ እንዳገሩ ይጮሃል›› እንዲሉ በወላጆቻቸው፣ በወገኖቻቸው፣ በአገራቸው መንገድ ነው፡፡ የአንድ ምዕራባዊ ማንነት ራሱን በማስቀደም ወይም ‹‹እኔ ለእኔ›› በሚል ላይ የተመሠረተ ቢሆን የኤርትራውያን ማንነት ግን እንደ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ‹‹እኔ ለቤተሰቤ፣ እኔ ለወገኔ፣ ቤተሰቤም ለእኔ፣ ወገኔም ለእኔ›› በሚል የመደጋገፍ፣ በይሉኝታ፣ በትህትና፣ በመተሳሰብና ለሌላው ቀድሚያ በመስጠት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡

ወደ ሰላማዊ አንድነት መስመር ስንጓዝ የማንነታችንን አስፈላጊት የምናነሳው በማኅበራዊ መስኩ ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ መስኩም አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

በመጽሐፉ የሚወሱ ዋና ዋና ጉዳዮች

በዚህ የመጽሐፍ ወሰን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች የሚነሱ ሲሆን፣ ከሁሉ አስቀድሞ ኤርትራን የሚጨምረው ታሪካችን በህንድ ውቅያኖስ የነበረንን ጥንታዊ የንግድ መስመርና ከፊንቃውያን፣ ከአሶሪውያን፣ ከባቢሎናውያን፣ ከፐርሺያውያን፣ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች በተለይም ከህንድ፣ ከሲሎንና ከቻይና ጋር የነበረንን የንግድ ግንኙነት እናያለን፡፡

ቀጥሎም ኤርትራን የምትጨምረዋ ኢትዮጵያ የገጠማትን የእርስ በርስ ጦርነትና በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የገጠማትን ውድመት ለማየት እንሞክራለን፡፡ ይህች በምሥራቅ አፍሪካ ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ ገና ጥንታዊ ግዛቷን አንድ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ከጀመረችባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ፣ አውሮፓውያን አፍሪካን ሲከፋፈሉ ኤርትራን የምትጨምረው ኢትዮጵያም የዚህ መጥፎ ታሪክ አጋጣሚ ሰለባ እንደሆነች እናያለን፡፡ ኤርትራ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት በነበረችበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታም በጨረፍታም ቢሆን እንመለከታለን፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ችግር የሚስጥሩ ቁልፍ ያለው የጦር ቃል ኪዳን አገሮች ጣሊያንና ጀርመንን ድል ካደረጉ በኋላ ኤርትራ በሪፈረንደም ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሀድ ከተደረገችበት ሒደት በመሆኑ ይህን የውህደት ሒደት አንድ በአንድ ለመፈተሽ እንሞክራለን፡፡ ለመሆኑ ‹‹የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው?›› ከሚል ድምዳሜ ለምን ተደረሰ? ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ስትዋሀድ በወቅቱ ገኖ የነበረው የአንድነት ኃይል ሌሎችን አፍኖ ነው፣ በማፈኑም አምፀን ለነፃነታችን ለመታገል ተነስተናል ከተባለ ለምን የኤርትራ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ኤሕነግ) ብቻውን የኤርትራን ዕድል ወሳኝ ሆነ? ለምን ሪፈረንደሙን ‹‹ነፃነት›› ወይም ‹‹ባርነት›› በማለት ከመገደብ ‹‹ነፃነት››፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ተዋህዶ መቆየት››፣ ‹‹በፌዴሬሽን›› ወይም ‹‹በኮንፌደሬሽን›› መተሳሰር የሚል አማራጭ አልተሰጠም?  ወይስ ሌላ ከኢትዮጵያውያን የተሰወረ አጀንዳ ነበር? ወይም አለ? ወይስ የለም? ከነበረ ወይም ካለ ኢትዮጵያን ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል?

‹‹የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ አይደለም›› የሚሉትስ ቢሆኑ ኤርትራውያን ወንድሞቻቸው አለን የሚሉትን ችግር የተመለከቱት እንዴት ነው? በውስጣቸው በኃይል ለማንበርከክ ፈለጉ ወይስ በሰላም? በዴሞክራሲና በመቻቻል መንገድ ለመፍታት ፈለጉ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከሁሉ አስቀድሞ የኤርትራን ጥያቄ እንደ ቅኝ ግዛት ከሚቆጥሩት ወገኖች ጋር በመነጋገር መልስ ለማግኘት ቢሞከርም፣ ቀጥተኛ ምላሽ ባለመገኘቱ ምክንያቱን ወደ እውነቱ የተጠጋ መላ በመምታት ግምታዊ መልስ ለመስጠት ተሞከሯል፡፡ በደርግ ሥርዓትና በሽግግሩ መንግሥት ስለነበረው እንቅስቃሴም አንድ በአንድ ተዘርዝሯል፡፡ የኤርትራን ጉዳይ በኃይል አንበርክኮ ለመፍታት የተደረገውንም ጥረት በጨረፍታ ለማየት ይሞክራል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ የነበረውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ከዳሰሰ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ስለተከሰተው ግጭት፣ የግጭቱ መንስዔና ውጤቱን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ፣ ከቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን፣ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ከፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከሌሎችም በርካታ ባለሥልጣናት የተነገረውን ዋቢ በማድረግ ያቀርባል፡፡

በመጨረሻም ለዘመናት አንድ የነበረን ሕዝብ፣ ቤተሰቡ ግማሹ በኢትዮጵያ፣ ግማሹ ደግሞ በኤርትራ ባለበት ሁኔታ ተለያይቶ መኖር ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ካነሳ በኋላ ዛሬ ያለው የጥላቻ ስሜት፣ ዛሬ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ፣ ዛሬ የተከሰተው ሰው ሠራሽ ልዩነት፣ ዛሬ የሚታየው የጦርነት ፍላጎት ሲቆም ሕዝብ ወደ ነበረበት መመለሱ የማይቀር ቢሆንም፣ የፖለቲካ መሪዎች በጀ እስካላሉ ድረስ ሕዝብ የችግሩን ገፈት እየጠጣ መኖረ ስለማይቀር ከወዲሁ ቅን የሽምግልና ሐሳብ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን የዚህ ጽሐፍ አዘጋጅ ያምናል፡፡ ስለሚያምንም በዚህ ረገድ በ1888 ዓ.ም. የተካሄደው የዓደዋ ዘመቻም ሆነ የ1928 ዓ.ም. ወረራ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የማዋሀድ ዕርምጃ የወሰደችው መነጣጠል የማይችለው ሕዝብ መነጠል አቅቷት እንደሆነ በመጥቀስ የጀርመን፣ የየመን፣ የቬትናምና የሌሎችም አገሮች የውህደት ትግል እንደ ምሳሌ ይቀርባል፡፡ በመጨረሻም ቀስ በቀስ፣ ደረጃ በደረጃ፣ መወሰድ ስላለበት ሰላማዊ ዕርምጃ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ሰዎች በተለይም የፖለቲካ ሰዎች የኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ማዋሀድ ጉዳይ ከቶም መስማት ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ በመሠረቱ የራሳቸው የሆነ እውነት አላቸው፡፡ በእርግጥም መገንጠል የሚፈልጉት ኤርትራውያን ዘረኞች፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞች፣ ቅኝ ገዥዋ ኢጣሊያ ያጎናፀፈቻቸው የበላይነት ካባ ደርበው የሚኖሩ እስከሆኑ ድረስ ከእነሱ ጋር ስለአንድነት ከማውራት ከንቱ ነው፡፡ ተገንጥለው በፈለጉት አቅጣጫ ሕይወታቸውን ካልመሩ እነሱም ዕረፍት አይኖራቸውም፡፡ እኛንም ዕረፍት ይነሱናል፡፡

በመሠረቱ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ኤርትራውያን ብቻ አይደሉም፡፡ ምኒልክ የተሰኘው መጽሔት በቅጽ 2 በቁጥር 15 በሐምሌ 1992 ዓ.ም. ዕትም በተለይም ‹‹ትግራይ ከኢትዮጵያ መገንጠል አለባት›› በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ የተባሉ ሰው በዚህ ጽሑፍ ማስፈር በሚከብድ ጽሑፍ፣ ‹‹እጅግ አስከፊ የዘረኝነት በሽታ አለባቸው›› በሚል እንኳን ሊገለጽ የማይችል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ አሁንም በኤርትራ ምድር የጦርነት ከበሮ የሚደልቁና የሚያስፈራሩን ወገኖች አሉን፡፡ እነዚህ ሰዎች ስለጦርነት ሲነግሩን ትንሽ እሳቱን የቀመሱት አይመስሉም፡፡ ዋናው ቁምነገር በዚህም በዚያ ያሉ ክፉዎች ያልፋሉ፡፡ ድሮውንም አንድ የነበረው ሕዝብ በአንድነት ይኖራል፡፡ የታሪክ ዕርቅ ዕውን ሲሆንም ሁሉም ስህተቱን ይረዳል፡፡

ይህን መጽሐፍ ጀምሮ መጨረስ እንዲህ የዋዛ አልነበረም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ኤርትራንና ኢትዮጵያን የሰላማዊ መንገድ የማካሄድ ሐሳብ ለምን ማመንጨት አስፈለገ? የእሷ ጉዳይ የሞተ፣ የተከተተ፣ ያከተመ ነው ከሚሉ ወገኖች አኳያ ሲታይ ነገሩ ቀላል መልስ የለውም፡፡ ይልቁንም ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንዲሉ ሆን ብለው ለጉዳዩ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ያሉትን ኃይሎች ማሳመኑም አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ስሜት በጸሐፊ ዘንድ ያደረው ገና በደርግ ጊዜ ነው፡፡ ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮም ኤርትራ እንዳትገነጠል የብዕር ጦርነት አካሂዷል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የኢትዮጵያንና የኤርትራን አንድነት ለማሳየት ጥረት አድርጓል፡፡ በግሉ ፕሬስ ውጤቶች የተለያዩ የብዕር ስሞችን በመጠቀም የኢትዮጵያና የኤርትራ አንድነት በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ እንዲሞከር ጥረት ማድረጉ አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ የጉራጌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በመወከል የሽግግር መንግሥቱ ተወካይ ሆነው ሲሠሩና ከዚያም በፊት ከሚያውቃቸው ዶ/ር ኃይሌ ወልደ ሚካኤል ጋር በመሆን ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ›› የተሰኘች መጽሔት (ቡክሌት) ማዘጋጀት ጀምሮ ነበር፡፡ በዚች መጽሔት ውስጥም ዶ/ር ኃይሌ ወልደ ሚካኤል ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ አንድነት በውይይት ወይስ በጦርነት›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ሲያዘጋጁ የበኩሉን የማዳበሪያ ሐሳቦች ከመስጠቱም በላይ የአርትኦትና የዲዛይን ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

ከዚያ በኋላ በነበረው ጊዜም የኤርትራንና የኢትዮጵያን አንድነት ሒደት ሲከታተል ስለነበር ከ1985 ጀምሮ እስከ 1988 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ወደ ኤርትራ ድንበሮች በመሄድ ሁኔታዎችን አይቷል፡፡ በዚህም ጊዜ የትግራይም ሆነ የኤርትራ ሕዝብ ጊዜያዊ ጦርነቱን ረስቶ ወደ አንድነት እየመጣ እንደነበር ለመታዘብ ችሏል፡፡ በባድመ ጦርነትም የድንበር ጥያቄ ሳይሆን በኤርትራና በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ኢትዮጵያውያን እንዳልሆኑ እንዲያውቁ፣ በኤርትራ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ኤርትራውያን እንዳልሆኑ አንዲገነዘቡ የተደረገ ጦርነት ነበር የሚል እሳቤ ይዟል፡፡ እሳቤውንም በፕሬስ ውጤቶች ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ይህንንም እሳቤውን አመቺ በሆነ ምዕራፍ በዝርዝር ለማቅረብ ይሞክራል፡፡ ከባድመ ጦርነት በኋላ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረገውን ድርድርም በሚቻል መንገድ ሁሉ ለመከታተል ሞክሯል፡፡ ከዚህም በላይ የሕዝቡን ስሜት ለማጤን ጥረት አድርጓል፡፡ በጸሐፊው እምነት አንድ የነበሩንና የሆኑን ሰዎች አንድ የማድረጉ ጉዳይ የኔ አይደለም ብሎ ቸል ከሚባል ይልቅ፣ ሰላማዊ አንድነቱ መቶ ዓመታትም ይወሰድ ከወዲሁ መጀመር የተሻለ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ባለንበት የታሪክ ዘመን ሆነን የተለያየውን አንድ ሕዝብ ማገናኘት አስፈላጊ መሆኑን አምነን መንቀሳቀስና ከተለያዩ አገሮች የሰላማዊ አንድነት ታሪክ (ለምሳሌ ከቬትናም፣ ከጀርመን፣ ከየመን…) መማር አስፈላጊ መሆኑን ጸሐፊው ስለሚያምን ይህን መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች አንድነት ለምን ያስፈልገናል? ይህን በሚቀጥለው ዕትም እንመለከታለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles