Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየብዙዎች ፍርሀት

የብዙዎች ፍርሀት

ቀን:

የራስን ቢነዝስ ጀምሮ ራስን የመቅጠር ጉዞ አስቸጋሪ ባይሆን ተቀጣሪነትን አቁሞ የራስን ሥራ መጀመር የብዙዎች ዕርምጃ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ የተሻለ የገንዘብ አቅም ለማግኘት በሚደረግ ጉዞ ውስጥ የሚኖር ፍርሀት በሕይወት ዘመን ሰዎችን ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን የሚናገሩም አሉ፡፡ ብዙዎች የገንዘብ አቅማቸውን ለማጎልበት ምን መሥራት እንደሚፈልጉና እንዳለባቸው ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የመጀመርያዋን ዕርምጃ መውሰድ ፈታኝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ከተቀጣሪነት ራስን ወደ መቅጠር የሚደረገው ሽግግር አደጋ ሊኖረው መቻሉ ነው፡፡  ላይሳካልኝ ይችላል የሚል ፍርኃት ሰዎችን የራስን ሥራ ለመጀመር ከሚያደርጉት ጉዞ ሊያስቀራቸው አይገባም የሚል እምነት ያላቸው የራስን ሥራ መጀመር በተጋነነ መልኩ ከአደጋና ካለመሳካት ጋር መያያዙን ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል የራስን ሥራ ጀምሮ የራስ ቀጣሪ መሆን ምንም ዓይነት የስኬታማነት ማስተማመኛ በሌለበት ዕርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ ከልዩ ጥንካሬ ጋር የሚያያይዙትም አይታጡም፡፡

‹‹አባት እናቶቻችን ቀደም ሲል በደመወዝ ይኖሩ ነበር፡፡ የሚያገኙት ገንዘብ ለሕይወታቸው በቂ ነበር፡፡ የአሁኑ የእኛ ደመወዝ ግን ኑሮን መሸከም አይችልም፡፡ ይህ ተቀጣሪ የመሆንን ዋጋ ዝቅ እያደረገው የመጣ ይመስለኛል፤›› የሚል አስተያየቱን የሚሰነዝረው ከአሥር ዓመት በፊት የራሱን አማካሪ ድርጅት ያቋቋመው አቶ ስንታየሁ ኪዳኔ ነው፡፡

- Advertisement -

የዩኒቨርሲቲ መምህር ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሲቪክ (የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር) መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡ ተቀጣሪ ሆኖ ያገኝ የነበረው ደመወዝ ለኑሮው በቂ ስላልሆነ ብቻም ሳይሆን ትዕዛዝ ተቀባይ ሳይሆን ትዕዛዝ ሰጭ ሆኖ፣ እንደ አቅምና እንደ ፍላጎት የመሥራት ነፃነት በመፈለጉ የራሱን ቢዝነስ እንዲጀምር ያደረጉት ተጨማሪ ነገሮች እንደነበሩ ይገልጻል፡፡

ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በስፋት እንቅስቃሴ የነበረውና ሰዎችን አሳትፎ በነበረው በጎልድ ኩዌስት ኔትወርክ ማርኬቲንግ አቶ ስንታየሁም ገብቶ ነበር፡፡ ከዚያ ተሞክሮ ገንዘብ ባያተርፍም የሥራ ፈጣሪነትን፣ ሰዎች የገንዘብ ነፃነት የሚኖራቸው ተቀጥረው ሳይሆን የራሳቸው ቀጣሪ በመሆን ነው የሚለውን ሐሳብ በማግኘት ለዛሬ የጠቀመውን ትልቅ ነገር ማትረፉን ይናገራል፡፡ ‹‹ያ ልምድ ውስጤ የሆነ ነገር ጭሮ አልፏል፣ ሠርቶ ስለመለወጥ የራስን ሥራ ስለመሥራት፤›› ይላል፡፡

የራስን ሥራ መጀመር ሲታሰብ በቂ መነሻ ገንዘብ ስላለ ብቻም ሳይሆን ስለ ልምድ፣ ማኅበራዊ ካፒታልና እንዲሁም እችላለሁ የሚል በራስ መተማመን መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡

የራሱን አማካሪ ድርጅት እንደከፈተ ወዲያው ማስተማር አላቆመም፡፡ የራሱ ሥራ እስኪጠናከርና መሠረት እስኪይዝ ለተወሰኑ ዓመታት ሁለቱንም ጎን ለጎን አስኪዷል፡፡ በዚህ የጀመርኩት ቢዝነስ መቀጠል ባይችል እንዴት እሆናለሁ? የሚል ሥጋቱን መቅረፍ ችሏል፡፡

‹‹ሰዎች የግል ሥራ ሲጀምሩ በዚያ ሥራ እርግጠኛ ለመሆን ሥራው ቢያንስ ለአምስት ዓመታት መዝለቅ አለበት፤›› የሚለው አቶ ስንታየሁ፣ የግል ሥራ በጋራ ሁለት ሦስት ተሆኖ ቢጀመር መልካም እንደሆነም ይናገራል፡፡ ይህን የሚለው አንዱ ቢደክም ሌላኛው ሲበረታ፣ አንዱ ዕውቀት ቢኖረው ሌላኛው ጥሩ የገንዘብ አቅም ይኖረዋል ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው፡፡ በሌላ በኩል በጋራ ቢዝነሶች ብዙ ጊዜ የተወሰነ ደረጃ ላይ አለመስማማት ሲፈጠር ቢታይም ይህ ከሥራው ስኬታማነት የተገናኘ ሳይሆን፣ ሥራው ካስገኘው ውጤት እንዴት ተጠቃሚ እንሁን ከሚል እንደሆነ ማስተዋሉን ይገልጻል፡፡

በብዙ መልኩ የአቶ ስንታየሁን ሐሳብ ትጋራለች፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ትሠራ የነበረው በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ነበር፡፡ ጥሩ ተከፋይና ጥቅማ ጥቅሞችም ነበሯት፡፡ ቢሆንም ግን የራሷን ሐሳቦች ወደ ተግባር ለመቀየር ነፃነት የሚሰጣት የራሷ ተቀጣሪ መሆን እንደሆነ በማመን ሥራዋን ለቃ የራሷን የማማከር ድርጅት ከፈተች፡፡

‹‹መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ መሥራት የገንዘብ ነፃነት ይሰጣል ምቾትም አለው፤›› ብትልም እንደሷ የራሴ የሥራ ሐሳቦች፤ ለማኅበረሰቤም የማበረክተው አለኝ ለሚል ይህን ምቾት ትቶ የራስን ሥራ ለመጀመር የግድ የሚል ኃይል ስለመኖሩ ታምናለች፡፡

እሷ እንደምትገልጸው፣ የራስ ተቀጣሪ ሆኖ በገንዘብ ጥሩ መሆን ከመፈለግ ባሻገር በወቅቱ ትሠራባቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሲታጠፉና የተጠቃሚዎች ተስፋ ሲጨልም መመልከቷም የራሷን ሥራ እንድትሠራ የገፋት ሌላ ነገር ነበር፡፡  የራስን ሐሳብ ወደ ተግባር የመቀየር ፍላጎት፣ በሥራዋ ላይ ትመለከታቸው የነበሩ እንከኖች በአጠቃላይ የነበራት የሥራ እርካታ የውሳኔዋ መሠረቶች ነበሩ፡፡

በጊዜው በአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል የጀመረችውና ዛሬ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ድርጅቷን ማቋቋም ቀላል እንዳልነበር ታስታውሳለች፡፡ መጀመርያ የራሷን ሥራ ጀምራ ነገሮች እንዳሰበችው ባለመሄዳቸው ተመልሳ ተቀጣሪ ሆናም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም የተቀጠረችው በፊት ትሠራ የነበረበት ዓይነት ድርጅት ውስጥ ነበር፡፡ ገንዘብን ጨምሮ ነገሮች የተመቻቹ ነበሩ፡፡ አሁንም ግን ልቧ የራስን ሥራ መሥራት ላይ በመሆኑ በድርጅቱ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት አልቻለችም፡፡ ከቀደመው ተሞክሮዋ በመማር አስቸጋሪ ያለቻቸው ሁኔታዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እንደገና ሥራዋን ጀመረች፡፡

እንደ አቶ ስንታየሁ እሷም ምንም እንኳ የራስን ሥራ የመጀመር ፍላጎት የቱን ያህልም ከፍተኛ ቢሆን ተቀጣሪ ላለመሆን ወስኖ የራስን ሥራ መጀመር ጥንቃቄ የሚሻ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ነገሮች ቀላል አይሆኑም፡፡ ማድረግ የምፈልገው ምንድን ነው? ያለኝ  ገንዘብ፣ ዕውቀት ወይስ ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት? እነዚህንስ እንዴት ኢንቨስት ማድረግ እችላለሁ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፤›› ትላለች፡፡

የራስን ሥራ ለመጀመር ብቻ ከመሆን ይልቅ በጋራ መሆን ጠቃሚነት ላይም በአቶ ስንታየሁ ሐሳብ ትስማማለች፡፡ ነገር ግን አብሮነቱ እንዲሁ ሻይ ላይ በቃል የሚፀና ሳይሆን በጽሑፍ ማን ምን ያበረክታል፣ ከሚገኘው ነገርስ እንዴት ይጠቀማል? የሚሉት በግልጽ መቀመጥ እንዳለባቸው ታሳስባለች፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ ባለመሆኑ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ውድቀትን ሲያስከትሉ እንደሚስተዋል፤ በዚህም ሰዎች የራስን ሥራ ስለመጀመር አይሳካም የሚል ፍርኃት እንደሚያድርባቸው ትናገራለች፡፡

ከገንዘብ ከልምድም አንፃር በሕይወቴ እደርስበታለሁ ካለችው ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደሚያስችላት፤ ከነጭራሹም ያሰበችው ነገር ላይ የሚያደርሳት መስመር ላይ አለመሆኗን ስታረጋግጥ ተቀጣሪነትን ለማቆም እንደወሰነች የነገረችን ወይዘሮ ፍሬሕይወት ከሳዬ፣ ለአምስት ዓመታት በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ጸሐፊ ሆና ሠርታለች፡፡

‹‹በዚያ ሥራ መቆየት ለእኔም ለሥራውም የሚሰጠው የተሻለ ነገር እንደማይኖር ተረዳሁ፤›› የምትለው ወ/ሮ ፍሬሕይወት ውሳኔ ላይ መድረስ ግን በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ የራሱን ሥራ የሚሠራ ጓደኛም ቤተሰብም ስላልነበራት በዙሪያዋ ያሉ በሙሉ ውሳኔዋ አደገኛ እንደሆነ ነግረዋታል፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ስለምትሠራው ነገር በሚገባ አሰበች፡፡ ሲጀመር ነገሮች አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምታለች፡፡ የመጀመርያ ሙከራዋ ባይሳካ ሁለተኛ ዕቅድ አስቀምጣ ወደ ሥራ ገባች፡፡ ‹‹ቀላል አይደለም የሚያስፈራ ነገር አለው፡፡ ተቀጣሪ ሆኖ ረዥም ዓመታትን ከመቁጠር የበለጠ ያስፈራል፣ አደጋ አለው ብዬ ግን አላስብም፤›› ትላለች፡፡

የራሷን ሥራ መሥራት ከጀመረች አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመጀመርያ ሁለት ዓመታት በእግሯ ለመቆም ስትታገል የነበረበት እንደሆነ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ሰዎች የራሳቸው ቀጣሪ እንዲሆኑ የምትመክርበት ደረጃ ላይ መሆኗን ትናገራለች፡፡ የሌሎቹን ሐሳብ በመጋራት ራስን መጀመሪያ ማዳመጥና መሥራት ስለሚፈልጉት ነገር ግልጽ መሆን ወሳኝ ዕርምጃ ነው ትላለች፡፡

የጂኒየስ ኢንተርፕረነርሺፕ ማሠልጠኛና የቢዝነስ ማማከር አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ወሮታው በዛብህ የራስን ሥራ መጀመር ሲታሰብ ግልጽ ዓላማ ማንገብ በጣም አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ሥራ ፈጣሪዎች ትርፍና ኪሳራቸውን የሚያውቁት በወረቀት ላይ ነው፡፡ ብዙዎች ግን መጀመሪያ መሥራት ያለባቸውን ባለመሥራት የሚሞክሩት በሕይወታቸው ነው›› በማለት የመጀመሪያውን እርምጃ ከመውሰድ በፊት ስለማሰብ አስፈላጊነት ይናገራሉ፡፡

ምንም እንኳ የራስን ሥራ የመጀመር ፍላጎት ብዙዎች ጋር ቢኖርም ወስነው የሚራመዱ ጥቂቶች መሆናቸውን፤ ያለመወሰን ዋናው ምክንያት ፍርሀት መሆኑን ዶ/ር ወሮታው ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ፍርሀቱ የሚመጣው ግልጽ ዓላማ ካለመኖር እንዲሁም ነገሮችን ማሳካት የሚቻለው በመውደቅ በመነሳት መንገድ መሆኑን ካለመረዳት ነው፡፡  በመጨረሻም ‹‹ፍርሀት ደጋግሞ የሚገድል ነገር ነው›› ይላሉ፡፡

    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...