በ1890 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተከፈተው የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት በዘመኑ ‹‹ሰይጣን ቤት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር፡፡ በስክሪኑ የሚታየው ትዕይንት ‹‹የሰይጣን ሥራ ነው›› ያሉ ተመልካቾችም ለዓመታት ወደ ሲኒማ ቤቱ ከመሔድ ተቆጥበዋል፡፡ ከጊዜ በኋላ ሲኒማ ቤቱ ተለመደ፡፡ አገርኛ ፊልሞችም ተበራከቱ፡፡ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሲኒማ ቤት ያገኘችው ከተማ ድሬዳዋ ስትሆን፣ ከጊዜ በኋላ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋና ደሴ የሲኒማ ቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡
ሲኒማ ቤቶች ባሏቸው በሌሏቸውም ከተሞች አዳራሾች፣ የባህል ማዕከሎችና ዩኒቨርሲቲዎችም እንደ አማራጭ ይወሰዳሉ፡፡ ፊልም ሠሪዎችም ፊልማቸው አዲስ አበባ ከታየ በኋላ አልያም በመታየት ላይ እያለ ወደ ክልል ከተሞች በመሔድ አማራጮቹን ይጠቀማሉ፡፡ የየከተሞቹን ነዋሪ በመቀስቀስ፣ አዳራሽና ሌሎችም ግብዓቶችን በማሟላት ከፊልም ሠሪዎቹ ጋር የሚጣመሩ አመቻቾች (ፕሮሞተሮችም) አሉ፡፡ በብዛት በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች ሲታዩ የተወደዱ ፊልሞች ተመርጠው ወደ ክልል ከተሞች ይሔዳሉ፡፡
ፊልሞቻቸውን በግላቸው ወይም ከአመቻቾች ጋር በመተባበር በክልሎች ተገኝተው የሚያሳዩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች የፊልማቸውን ቅጂ ይልካሉ፡፡ ፊልም ለማሳየት የሚያስፈልገውን ወጪ አመቻቾች ሸፍነው ከፊልሙ ባለቤት ጋር 40 በመቶ ለ60 በመቶ ወይም እኩል ትርፍ የሚካፈሉበት አሠራር አለ፡፡ አመቻቾች ለፊልሙ የተወሰነ ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ አሳይተው ትርፉን የሚወስዱበት ሒደት ሌላው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና የመከላከያ ሠራዊት የሚገኝባቸው አካባቢዎችም ከፊልም ሠሪዎች ጋር በመደራደር ፊልም ይታይባቸዋል፡፡
ፊልሞችን በክልል ከተሞች የማሳየት ሒደቱ በውጣ ውረድ የተሞላ ነው፡፡ በፊልም ሠሪዎችና አመቻቾች መሀከል የሚፈጠር እሰጣ ገባ፣ ፊልም የሚታይባቸው አካባቢዎች ምቹ አለመሆንና የፊልሞች ለስርቆት መጋለጥ ከችግሮቹ ጥቂቱ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሳቢያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፊልሞችን በክልል ከተሞች ማሳየት እየተቀዛቀዘ እንደመጣ ይነገራል፡፡ የፊልም ባለሙያዎች በክልል ከተሞች የሚገጥሟቸው ችግሮች ቢዝነሱን እንዳዳከሙት ሲናገሩ፣ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ፊልሞች ጥቂት መሆናቸው ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
አምና በተለያዩ የክልል ከተሞች ከታዩ ፊልሞች አንዱ ‹‹ብላቴና›› ነው፡፡ የፊልሙ ደራሲ፣ አዘጋጅና ፕሮዲውሰር ክንፈ ባንቡ ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውሮ ፊልሙን አሳይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሠራቸው ፊልሞች መካከል ‹‹ያለ ሴት›› እና ‹‹ወደው አይሰርቁ››ን ተዘዋውሮ ቢያሳይም የ‹‹ብላቴና››ን ያህል ስኬታማ እንዳልነበሩ ይናገራል፡፡ ፊልሙ በአዲስ አበባ ሲታይ ዝነኛ በመሆኑ በክልል ከተሞችም በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡
በእሱ እምነት፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአጭር ጊዜ ልዩነት በርካታ ፊልሞች ከመውጣታቸው በላይ ብዙዎቹ ጥራታቸው የወረደ ነው፡፡ ይህም ተመልካቹ አገርኛ ፊልሞችን ለማየት ያለውን መነሳሳት ቀንሶታል፡፡ ቀድሞ በወራት ልዩነት ፊልሞች ሲታዩ፣ እንደየከተማው ነዋሪ ብዛት ቢለያያም በአማካይ እስከ አንድ ሺሕ ተመልካቾች ይገኙ ነበር፡፡
ክንፈ እንደሚለው፣ ፊልም ማሳየት ፈታኝ የሆነባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ባለሙያዎች ጥሩ ምላሽና ጠቀም ያለ ትርፍ የሚያገኙባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡ በአንዳንድ ከተማዎች ‹‹ፕሮሞተር›› ነን በሚል ያላግባብ ፊልም ሠሪዎችን ለመቆጣጠር የሚሞክሩ አሉ፡፡ እነሱ በሚፈልጉት ቦታና ሰዓት ፊልሙ ታይቶ፣ የጠየቁትን ያህል ገንዘብ ካልተከፈላቸው የፊልሙ ባለቤት ላይ አካላዊ ጥቃት እስከማድረስ እንደሚርሱ ይናገራል፡፡
የፊልም ፖስተር የሚገነጥሉ፣ ፊልም የሚታይባቸው አዳራሾች እንዳይከራዩ የሚያደረጉ ገጥመውታል፡፡ ፊልሞች በሚታዩበት አዳራሽ ጣሪያ ድንጋይ በመወርወርና በሌላም መንገድ የሚረብሹ ግለሰቦችም ይጠቀሳሉ፡፡ መሰል ችግሮች በተደጋጋሚ የሚከሰቱባቸው ከተማዎች ሲሄድ የከተማው መስተዳድር እንዲተባበሩት ይጠይቃል፡፡ ሁሌ ባይሆንም ዕርዳታ ያገኘባቸው ጊዜዎች ግን አሉ፡፡
ፊልሞቹ፣ የሚያሳይበት ክልል ቋንቋ ሰብ ታይትል የሌላቸው መሆናቸው ያስቆጣቸው አካባቢዎችንም ያስታውሳል፡፡ ቀላል ችግሮች ወዳሉባቸው አካባቢዎች በድፍረት ቢሔድም፣ አንዳንድ ከተማዎች እጅግ አስቸጋሪ ስለሆኑ ፊልሙን አይወስድም፡፡ ፊልሞችን በክልል ከተሞች ማሳየት ያለውን ውጣ ውረድ በመፍራት በክልል የሚያሳዩ ባለሙያዎች እንደቀነሱም ይገልጻል፡፡
‹‹በጥቂት ሰዎች ምክንያት የከተሞች ገጽታ መበላሸት የለበትም፤ የክልል መስተዳድሮች መፍትሔ ማበጀት አለባቸው፤›› ይላል፡፡ ነገሮች ፈር ሲይዙ የፊልሞች ተደራሽነት ከመጨመሩ ባሻገር ፊልም ሠሪዎችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ያክላል፡፡
የክንፈን ሐሳብ ከሞላ ጐደል የሚጋራው የፕሮዲውሰሮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ቶማስ ጌታቸው ነው፡፡ ‹‹ስርየት››፣ ‹‹ጽኑ ቃል›› እና ‹‹ፔንዱለም›› አዲስ አበባ እየታዩ በክልሎችም አሳይቷል፡፡
ፊልሞችን በክልል ከተሞች ማሳየት ትርፋማ የነበረበት ወቅት ቢኖርም፣ ዛሬ ዛሬ መቀዛቀዙን ይስማማበታል፡፡ በእርግጥ ቀድሞ ከሰፊ ከተሞች በስተቀር ፊልም አዘውትሮ የመመልከት ልማድ ያላቸው ከተሞች ውስን ነበሩ፡፡ አሁን በትንንሽ ከተሞችም ተመልካች ይገኛል፡፡ ቢሆንም የተመልካቾቹ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ፊልም የማሳየት ወጪና ገቢ ስለማይመጣጠን፣ ዛሬም ትኩረት የሚሰጠው ለትልልቅ ከተሞች ነው፡፡
በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥርና የአንድ ፊልም ተወዳጅነት የፊልሙን የቆይታ ጊዜ ይወስናሉ፡፡ ከሦስት ቀን ጀምሮ እስከ ሦስት ሳምንት ፊልሞች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስተው በአራቱም አቅጣጫ ለማሳየት አቅደው ከጥቂት ከተሞች መዝለል ያልቻሉም ፊልሞች አሉ፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ፊልሞችን በክልል ከተሞች የማሳየት ሒደት በተዋቀረ መልኩ መደራጀት አለበት፡፡ ፊልሞች አዲስ አበባ ከታዩ በኋላ ወደ ክልል የሚሔዱበት አሠራር ተለውጦ በመላው ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ጊዜ ማሳየት የሚቻልበት መንገድ መፈጠር እንዳልበት ይናገራል፡፡
ባደጉት አገሮች በተመሳሳይ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ፊልም ይታያል፡፡ ከአገራቸው አልፈው ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ፊልሞችን በመላክ በአንድ ጊዜም ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳን ይሔ ኢትዮጵያ ባለው ቴክኖሎጂና ውስን ሲኒማ ቤቶች ቢከብድም፣ በተቻለው መጠን ፊልሞች በተመሳሳይ ወቅት የሚዳረሱበት መንገድ መቀየስ እንዳለበት ያሳስባል፡፡
በሌላ በኩል አንዴ ደረጃው የወረደ ፊልም የገጠማቸው ተመልካቾች ተስፋ ስለሚቆርጡ፣ በቀጣይ ጥሩ ፊልም ቢቀርብም እንኳን አይመለከቱም፡፡ ስለዚህም ፊልሞች መመረጥ እንዳለባቸውና በየከተማው ደረጃቸውን የጠበቁ ሲኒማ ቤቶች መገንባት የግድ እንደሆነ ይናገራል፡፡
‹‹የተመልካቹን ገቢ ባገናዘበ መልኩ፣ ጥራት ያላቸው ፊልሞች በተመቻቸ ሁኔታ መቅረብ አለባቸው፤›› የሚለው ቶማስ፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ በየክልሉ ያሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም መንግሥት መረባረብ እንዳለባቸው በማሳሰብ ነው፡፡ የፊልሙን ዘርፍ ችግሮች ለመቅረፍም የፊልም ፖሊሲ መጽደቅ ወሳኝ ነው ይላል፡፡
የፊልም ባለሙያዎች ከሚያቀርቡት ቅሬታ አንዱ ከአንድ ከተማ አንሥቶ በተከታታይ ባሉ ከተሞች የሚገኙ ፕሮሞተሮች የሚፈጥሩት ያልተገባ ሰንሰለት ነው፡፡ በአንድ ከተማ ከፊልም ሠሪው ጋር ካልተስማሙ ፊልሙ በዚያ አካባቢ እንዳይታይ ሊያደረጉ ይችላሉ፡፡
ከዛሬ አሥር ዓመት ጀምሮ በጐንደር ከተማ ፊልሞችን የሚያሳየውን የሊንክ አፕ ሕትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ባለቤት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ፣ ፊልም ሠሪዎች ተደራጅተው ከሚሠሩ ፕሮሞተሮች ጋር ቢጣመሩ መፍትሔ እንደሚሆን ይናገራል፡፡
በቅርቡ ያሳየው ‹‹ጥለፈኝ›› እና ‹‹ሼፉ 2››ን ሲሆን፣ ቢዝነሱ መቀዛቀዙን ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጋር ይስማማበታል፡፡ ፊልሞች በተመሳሳይ ጊዜ በአዲስ አበባና በክልሎችም ቢመረቁ በርከት ያለ ተመልካች ያገኛሉ ይላል፡፡ በእሱ እምነት፣ ዋነኛው ችግር ፊልሞች ከሲኒማ ቤት ሳይወርዱ ተሰርቀው በሲዲ መቸብቸባቸው ነው፡፡
እንደ ጐንደር ሲኒማ ቤት ባላቸው ከተሞች የተሻለ አማራጭ ቢኖርም በአዳራሾችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚያዩ ተመልካቾች ቁጥርም ጥቂት አይደለም፡፡ ተሰርቀው በሲዲ ያልወጡ ፊልሞች ሲገኙ የአዳራሽ፣ ስፒከርና ሌሎችም ግብዓቶች ወጪ የሙስጠፋ ራስ ምታት ይሆናሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ከ3 ብር ጀምሮ በአዳራሾች ደግሞ ከ10 – 30 ብር ተከፍሎ ይታያል፡፡
ፊልሞችን ወደ ሰባት ዓመት ያህል ወደ አዳማ በመውሰድ ያሳየው የዋዜማ ትሬዲንግና ኢንተርቴይመንት ባለቤት አቶ ካሊድ ናስር በበኩሉ፣ በዩኒቨርሲቲዎችና የመከላከያ ሠራዊት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉት ተመልካቾች ቁጥር በርካታ በመሆኑ የተሻለ መሥራት ይቻላል ይላል፡፡ ሲኒማ ቤቶች በተለያዩ ከተሞች መከፈታቸው ፊልም ሠሪዎች በቀጥታ ከሲኒማ ቤቶች ጋር እንዲደራደሩ መንገድ ቢፈጥርም፣ የሌሎች አካባቢዎች አሠራር መሻሻል አለበት፡፡
ሥራው ወቅት ተኮር ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ከፈተና በኋላ ያሉ ሳምንታት ተመራጭ ናቸው፡፡ ፊልም ሠሪዎች የሚሔዱባቸው አካባቢዎች የኑሮ ዘይቤም የፊልማቸውን ዕይታ ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ አርሶ አደር አካባቢዎች ምርት የሚሸጡበትን ወቅት (እንደየአካባቢው የጤፍ፣ የድንች፣ የስንዴ፣ የቡናና ሌሎችም ሰብሎች) መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
ፊልሞችን በክልል ከተሞች ማሳየት ለፊልም ስርቆት የሚያጋልጥበት አጋጣሚ እንደሚሰፋ የፊልም ባለሙያ ያሬድ ሹመቴ ይናገራል፡፡ ፊልሞች በዲቪዲ ሲታዩ አንዳንድ የሲዲ ማጫወቻዎች ፊልሙን ይቀዳሉ፡፡ በዚህ መንገድ ያላግባብ ገበያ ላይ የዋሉ ፊልሞችም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሲኒማ ሲባል ከአዲስ አበባ ወጥቶ ተደራሽነቱ መረጋገጥ እንዳለበት የሚናገረው ያሬድ፣ ችግሮች ካልተቀረፉ የተቀዛቀዘው የፊልሞች የክፍል ሀገር ጉዞ የበለጠ መዳከሙ እንደማይቀር ይገልጻል፡፡
ፊልሞችን በቋሚነት የሚያሳዩ አከፋፋዮች ሌላው ሒደቱን ያስተካክላሉ የሚላቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከአዳራሾች ጐን ለጐን እንደ ሜዳ ያሉ ክፍት ቦታዎችን ለፊልም ማሳያነት ማዋል ተደራሽነቱን ያሰፋዋል፡፡ ያሬድ እንደሚለው፣ ፊልሞችን በክልል ማሳየት ተገቢውን መንገድ ቢከተል ፊልም ሠሪዎችን ትርፋማ ያደርጋል፡፡ ፊልሞች በሚገኙበት አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን በቋሚነት ቢታዩም መልካም ነው፡፡
አንዳንድ ፊልም ሠሪዎች ነፃ ገበያ ያለው በክልል ከተሞች እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በተለይም ከአዲስ አበባ ውጪ ያለው የግብር እፎይታ አበረታች እንደሆነና በአዲስ አበባም ቢለመድ መልካም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የሴባስቶፓል ሲኒማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሺነህ ተፈራ በዚህ ሀሳብ ከሚስማሙ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ፊልሞች ያሳየ ሲሆን፣ በርካታ የፊልም ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኘውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ይገልጻል፡፡
የፊልሞችን ተደራሽነት ማስፋት እንዲሁም ፊልም ሠሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው የዘርፉ ችግሮች ሲቀረፉ መሆኑንም ያክላል፡፡ ተመልካቾች የሚወዷቸው ተዋንያንና ፊልም ሠሪዎች የተሳተፉባቸውን ፊልሞች በጉጉት ይጠባበቁ የነበረበትን ጊዜ ጠቅሶ፣ ስሜቱ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻም ይናገራል፡፡