Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

“የዕርዳታ አቅርቦቱ እስከ አንድ ዓመት ሊቆይ ይችላል”

አቶ ምትኩ ካሳ፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሥራዎች አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ

ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ይርጋለም ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በይርጋለም ከተማ አጠናቀው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀድሞው ዓለማያ ከአሁኑ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኔዘርላንድ ዋገኒንገን ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሳይንስ ሠርተዋል፡፡ የዛሬ የቆይታ ዓምድ እንግዳችን አቶ ምትኩ ካሳ፡፡ አቶ ምትኩ በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት መምርያ ኃላፊና የክልሉ የምግብ ዋስትና መምርያ ኃላፊ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል፡፡ አቶ ምትኩ ወደ ፌዴራል ተዛውረው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሥራዎች አስተባባሪ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከጥር ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ዘርፍ በዚህ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደሙ እንደመሆኑ፣ በአጠቃላይ እየተደረገ ስላለው ዕርዳታና የተጎጂዎች ሁኔታ አቶ ምትኩን ምሕረት አስቻለውና ታምሩ ጽጌ አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ ሰዎች ብዛትን በሚመለከት የተለያዩ ቁጥሮች እየተጠቀሱ ነው፡፡ በትክክል የተጎጅዎች ቁጥር ስንት ደርሷል?

አቶ ምትኩ፡- በመንግሥት ደረጃ ከለጋሾችም ጋር ያወቅነው 8.2 ሚሊዮን ተጎጂዎች እንዳሉ ነው፡፡ ይኼ ቁጥር አስፈላጊ የሚሆነው ለዕርዳታ የሚቀርበውን ሀብት ለማቀድ እንዲመቸን ነው፡፡ ከታቀደው ውጪ በአንዳንድ ሁኔታዎች ተጨማሪ ነገር ቢመጣ የምናስተናግድበት መንገድ አለ፡፡ ስለዚህ ቁጥሩ ለዕቅድ እንዲያገለግል እንጂ ትልቅ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዕርዳታ የሚያሰባስቡ ተቋማት የቁጥሩን ማደግ በእጅጉ ይፈልጉታል፡፡ ቁጥሩ ሲያድግ ዕርዳታ ከሚያሰባስቡ ሌሎች ተቋማት ጋር መወዳደርና ዕርዳታውንም ማግኘት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቁጥሩን ከፍ አድርጎ መናገር ለእነሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ነው የተለያየና ከፍ ያለ ቁጥር ሲናገሩ የሚስተዋለው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት ግን ቁጥሩን የምንጠቀመው ለቀጣይ ጊዜያትና ወራት ማቅረብ የሚገባንን ዕርዳታ ለማሰባሰብና ለመመደብ እንዲቻል ነው፡፡ የሚቀርበው ዕርዳታ በእህልም ይሁን በዘይት እንዲሁም በአልሚ ምግብና ጥራጥሬ የሚሰላው በሰው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቁጥሩን አሳውቀናል፡፡ ቁጥሩም መወሰድ የሚገባው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ቁጥሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለዋወጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ያወጣነው 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ነበር፡፡ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ደግሞ 8.2 ሚሊዮን ሆነ፡፡ ስለዚህ ቁጥሮችን የምናውቅበት የራሱ አሠራር አለው፡፡ ክልሎች የራሳቸውን ቁጥሮች አስልተው ይልካሉ፡፡ ወደ ፌዴራል ከመጣ በኋላ በብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ አማካኝነት ይፀድቃሉ፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሚሰበስቡት ብሔራዊ ምክር ቤት በኩል ይፀድቅና ከለጋሾች ጋር ሆነን ይፋ እናደርጋለን፡፡ ለጋሾችም ከኛ ጋር ይሠራሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር የተረጂዎችን ቁጥር ለመለየት በምናደርገው ሒደት ሁሉም ይሳተፋሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸው፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የክልል ሴክተር ቢሮዎች በዚህ ይሳተፋሉ፡፡ ስለዚህ እየተናገርነው ያለው አሃዝ በጋራ የፀደቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 15 ሚሊዮን ተጎጂዎች እንዳሉ ገልጾ ሪፖርት አወጥቷል ይባላል፡፡ 15 ሚሊዮን ይሆናል የሚባለው ከኤልኒኖ ክስተት በመነሳት ነው፡፡ ስለኤልኒኖ ክስተት ከዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ተቋማትና እንደዚሁም ከኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚወጡ መረጃዎችና ትንበያዎች የሚያሳዩት በጥቅምት፣ በኅዳርና በታኅሣሥ ወራት ጥንካሬው እየጨመረ ይሄዳል የሚል ነው፡፡ የኤልኒኖ ጥንካሬ እየጨመረ መሄድ የድርቁን ጥንካሬ አብሮ ያሳድገዋል፡፡ “ድርቁ እየጠነከረ ከሄደ እ.ኤ.አ በ2016 ጃንዋሪ ወር የተጎጂዎች ቁጥር 15 ሚሊዮን ሊሆን ይችላል” የሚል ትንበያ ነው፡፡ የትንበያውን ትክክልነት ለማወቅና የተረጂዎችን ቁጥር ለመለየት ከጥቅምት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ 216 ባለሙያዎች ያሉዋቸው 24 ቡድኖች፣ በ134 ተሽከርካሪዎች በስምንት መኸር አብቃይ አርሶ አደሮች አካባቢ ተሰማርተው ነበር፡፡ አሁን በክልል ደረጃ ጨርሰው ወደ ፌዴራል ተመልሰው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ እነሱ የሚያቀርቡት ቁጥር መጀመሪያ በክልሎች እንዲፀድቅ ይደረጋል፡፡ ቀጥሎ በብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ከፀደቀ በኋላ፣ ከለጋሾቹ ጋር በጋራ በመሆን ይፋ ይደረጋል፡፡ ይህ እ.ኤ.አ በ2016 ተግባራዊ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት 15 ሚሊዮን፣ 20 ሚሊዮንና ሌላም የሚለው ልዩነት ምላሽ ያገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ ዕርዳታ በማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰውልናል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛውን ሥራ እየሠራ የሚገኘው መንግሥት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ተሳትፏቸው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ምትኩ፡- የእነሱ ተሳትፎ ቀዝቃዛ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ለምንድነው ቀዝቃዛ የሆነው? የሚለውን ስናይ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ ተጠቃሽ ነው፡፡ የኢራቅ፣ የየመን፣ በተለይ የሶሪያ ስደተኞች በአብዛኛው ወደ አውሮፓ እየገቡ ስላሉ፣ የአውሮፓ አገሮች ለዚህ ቀውስ የሚመድቡት ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ በዚያ ምክንያት ድሮ እንደሚሰጡን እየሰጡን አይደለም፡፡ ያ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ ምግብም ሆነ ምግብ ነክ ባልሆኑ የዕርዳታ አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም ባንክን ጨምሮ እህል እንዲገዛ ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች አሉ፡፡ እርስዎም እነዚህና መሰል ተቋማት የተሻለ ነገር እያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ዕርምጃ አለ?

አቶ ምትኩ፡- እስካሁን ድረስ በተጨባጭ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ መለገስና የተለገሰው ነገር በእጅ መግባት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ቃል የገቡት 163 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የሚፈለገው ግን 596.4 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው ትንሽ ነው፡፡ ከአንድ ሦስተኛ በታች ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን የሚደረገውን ዕርዳታ የተሸከመው መንግሥት መሆኑን ነው፡፡ መንግሥት የያዘው አቋም ለጋሾች ከረዱ እንደ ተጨማሪ እንወስደዋለን የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እነሱን መጠበቅ ሳያስፈልግ በራሳችን እንሠራለን፡፡ ምክንያቱም ዜጎቹ የእኛ ናቸውና፡፡ መንግሥት ደግሞ ዜጋውን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ዕርዳታውን ወደ ተጎጂዎች ለማድረስና እንደ ጉዳቱ መጠን ቅድሚያ መረዳት ያለባቸውን ከመድረስ አኳያ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ ምትኩ፡- ችግር ሆኖብን የነበረው የትራንስፖርት አቅርቦት ነበር፡፡ ምክንያቱም ጨረታ ያወጣነው 4.5 ሚሊዮን ተረጅዎች በነበሩበት ወቅት ነበር፡፡ ኮንትራት የሰጠነው ለስድስት ወራት ነበር፡፡ ምክንያቱም ዕርዳታው ቀጣይነት ስለነበረው፡፡ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ እጥረት አጋጥሞናል፡፡ አሁን የትራንስፖርት አቅርቦቱን አሳድጎ፣ ዕርዳታውን በሚያስፈልገው መጠንና በሚያስፈልገው ጊዜ ማድረስ ስለሆነ፣ ተጨማሪ ጨረታ በማውጣትና አወዳድረን በመጨመር እየሠራን ነው፡፡ አሁን ለ8.2 ሚሊዮን ተረጂዎች ዕርዳታው በሚፈለገው ሁኔታ እየደረሰ ነው፡፡ ስለዚህ አቅርቦትን በሚመለከት የባሰ ችግር ያለባቸው ቦታዎች ላይ ቀድመን እየደረስን ነው፡፡ በእርግጥ የጉዳቱ መጠን አካባቢ ከአካባቢ ይለያል፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹ አካባቢዎች ቅድሚያ እየተሰጣቸው ነው?

አቶ ምትኩ፡- ለምሳሌ አፋር፣ ምሥራቅ አማራ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ አርሲ የመሳሰሉት ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ ዕቅድ አስቀምጠን ጉዳቱ ከፍ ባለበት አካባቢ ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በመጀመሪያ 222 ሺሕ ቶን ስንዴ ገዝቷል፡፡ በሁለተኛው ደግሞ 405 ሺሕ ቶን ስንዴ እንዲገዛ አዟል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ለመግዛት ፍላጎት አለ?

አቶ ምትኩ፡- 222 ሺሕ ቶን ስንዴ እየገባ ነው፡፡ ቀጥሎ 405 ሺሕ ቶን ስንዴ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የመኸር ግምገማ ውጤትን መሠረት አድርገን አስፈላጊ ከሆነ ሦስተኛም ዙር እናዛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ግምት ስላለ፣ ተጨማሪ የማዘዝ ነገር አይኖርም?

አቶ ምትኩ፡- ከአገር ውስጥ በቆሎ እየገዛን ነው፡፡ በቂ የበቆሎ ምርት ስላለ በተለይ አርሶ አደሩን ከማብቃት አንፃር በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዛን ነው፡፡ ስንዴ ከመጠባበቂያ ክምችት እየወሰድን ነው፡፡ ከውጭ ተገዝቶ ሲገባ ወደ ክምችት እንመልሳለን፡፡ ስለዚህ አሁን ያለን 222 ሺሕ ቶንና በቀጣይ የሚመጣው 405 ሺሕ ቶን ስንዴ ብዙ ያስኬደናል፡፡ በመኸር ላይ በሚደረገው ግምገማ የሚገኘውን ውጤት ተከትለን ተጨማሪ ካስፈለገ እናዛለን፡፡ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ፣ አምስት ኪሎ ግራም ጥራጥሬ፣ ግማሽ ሊትር ዘይትና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑት ሕፃናትና ለሚያጠቡ እናቶች 405 ግራም አልሚ ምግብ በቀን ይሰጣል፡፡ በዚህ ልክ ነው የምናሰላው፡፡ በዚህ መሠረት አስልተን፣ የተረጂዎችን ቁጥርና በእጃችን ያለንን ዓይተን የሚያስፈልገን ከሆነ እናዛለን፡፡

ሪፖርተር፡-  ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ እየሠራ የሚገኘው መንግሥት ነው፡፡ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ምን እያደረጉ ነው?

አቶ ምትኩ፡- የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ድርጅት (Organization for the Coordination of Humanitarian Affairs – OCHA) ሥራው ማስተባበር ብቻ ነው፡፡ ሌላ ሥራ የለውም፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ግን ሚና አለው፡፡ ከክልሎችና ከኛም ጋር ይሠራል፡፡ ኦቻ ግን በሌሎቹ ለጋሾች ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ከለጋሾች ከተገኘው 163 ሚሊዮን ዶላር የሱም ድርሻ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ተረጂ ሆኖ የመቀጠል አዝማሚያ እንዳይፈጠር ተጎጂዎችን ጎን ለጎን በተለያየ የሥራ መስክ ለማሰማራት የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ምትኩ፡- ዕርዳታው እንደየጉዳቱ መጠን የሚቆይበት ሁኔታ ይለያያል፡፡ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ የጠፋባቸውና መኸር አብቃይ የሆኑ ቀጣይ ጊዜያትን ነው የሚጠብቁት፡፡ ስለዚህ ዕርዳታው የዘጠኝ ወራት ሊሆን ይችላል፡፡ በልግ አብቃይ የሆኑት ደግሞ በልግ ጥሩ ከሆነ ማለትም ዝናብ ከዘነበና አግባብ ያለው ሥራ ከተሠራ የበልግ ምርት ያገኛሉ፡፡ ዕርዳታም አያስፈልጋቸውም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በአጭር ጊዜ በሦስት ወራት ውስጥ የሚደርሱ የሰብል ዓይነቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ከአካባቢ አካባቢ ስለሚለያይ ከሁለት ወራት እስከ አንድ ዓመት የዕርዳታ አቅርቦቱ ሊቆይ ይችላል፡፡ በቀጣይ ጥሩ የሚሆነው ነገር ከጥር ወር ጀምሮ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ይጀመራል፡፡ በዚህ ፕሮግራም 7.9 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ይካተታሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሥራ ላይ የተሰማሩ አገር በቀል ኩባንያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለአካባቢው ነዋሪዎች የቻሉትን ለመርዳት እየሞከሩ ነው፡፡  የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን በተጠናከረና በአንድ ላይ የማስተባበር ነገር አለ?

አቶ ምትኩ፡- በመሠረቱ በክልሎች ጥሩ ጅማሪ አለ፡፡ ትግራይ አካባቢ ራያ ቢራ ፋብሪካና ሌሎችም ባለሀብቶች ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ በሶማሌ ክልልም ባለሀብቶችን የሚያስተባብረው በክልሉ ያለው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ነው፡፡ ክልሎች አጠናክረው እንዲሄዱ ይፈለጋል፡፡ የድርቁ ጥንካሬ ከ1977 ዓ.ም. ድርቅ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ችግሩ ትንሽ ጠንከር ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የግል ተቋማትንም፣ ለጋሾችንም ይዞ ችግሩን መከላከል አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሩ እየጠነከረና እየገፋ ከመጣ መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጥፎ ወደ ዕርዳታ ሊያስገባ ይችላል፡፡ ድርቅ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡ ማንም የሚያመጣው የሚመልሰው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይኼ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ የሚከሰት አይደለም፡፡ በሌሎችም አገሮች በአሜሪካ፣ በአፍሪካ በተለይ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ድርቅ አለ፡፡ ትልቁ ነገር ምላሽ የምንሰጥበት አግባብ ምንድነው የሚለው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እኛን ከለጋሾች ጋር የሚያላትመን፣ ቁጥር ላይ ከእነሱ የተወሰነ ነገር ስለምንለይ ነው፡፡ መቶ በመቶ እኛ ሸፍነን ቢሆን ኖሮ አሁን እንደተወራው አይዛመትም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ድርቁ የተወሰኑ ዓመታት በመቆየት በተደጋጋሚ የሚከሰት የተለመደ ነገር እየሆነ ነው፡፡ ልዩነቱ ከ30 ዓመታት በፊት ከነበረው የአሁኑ መንግሥት ቶሎ ምላሽ መስጠቱ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢኮኖሚና የመዋቅር ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፣ ለችግሩ ምላሽ የተሰጠበት መንገድ የተከሰተውን ችግር ለመጋፈጥ የሚያስችል ጥሩ ዝግጅት አለ ለማለት ያስችላል?

አቶ ምትኩ፡- በትክክል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች የሚሰጡትን  መግለጫ አስተውላችሁ ከሆነ፣ አንዱ የመንግሥትን አፋጣኝ ምላሽን በሚመለከት ነው፡፡ መንግሥት ማድረግ የሚገባውን አድርጓል፡፡ በጊዜው ሀብት መድቦ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ግን መማር ያለብን ነገር ድርቅ እንደሚመጣ አውቀን በልማት መመለስ አለብን፡፡ በአየር ንብረት ተፅዕኖ ውስጥ የምንኖር በመሆናችን፣ በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ድርቅ ይከሰታል፡፡ ያ በመሆኑም ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ የምንቋቋምበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መሥራት አለብን፡፡ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የከርሰ ምድር ውኃ ስላለ እሱን በመጠቀምና በማልማት ድርቁን መቋቋም ይቻላል፡፡ የውኃ ባንክ ማዘጋጀት ከቻልን ዝናብ ቢጠፋም ድርቅን መቋቋም እንችላለን፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት እንዳለብን አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ አሁንም ለድርቁ ምላሽ እየሰጠን ጎን ለጎን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንገኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱን እየገለጸ ነው፡፡ ግን ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ምትኩ፡- በጥር ወር 2007 ዓ.ም. የተጎጂ ወገኖች ቁጥር 2.9 ሚሊዮን ነበር፡፡ በተመሳሳይ ዓመት የተረጂዎች ቁጥር በነሐሴ ወር 4.5 ሚሊዮን ከፍ አለ፡፡ እነዚያን እየረዳን ቆየን፡፡ በዚያን ጊዜ የለጋሾች ድርሻ ቀዝቃዛና 55 በመቶ ነበር፡፡ ከሚፈለገው 45 በመቶ የቀነሰ ነበር፡፡ ለየት የሚያደርገውና መንግሥት ትልቅ ነገር ወስዷል የምንለው፣ አስከፊ ነገር ቢመጣ ቁጥሩ ስንት ሊሆን ይችላል በሚል አርቆ በማሰብ አስቀድሞ መዘጋጀቱ ነው፡፡ መጀመርያ ያደረግነው ለእርጥበት ዕቀባ ሥራና ለማካካሻ ዘር ለክልሎች ገንዘብ ላክን፡፡ የእርጥበት ዕቀባ ሥራና ማካካሻ ዘር ካለ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ዘርቶ ማካካስ ይቻላል፡፡ ጥራጥሬዎችን ጨምሮ ብዙ እህል ገዝተናል፡፡ ከዚያ ባሻገርም አልሚ ምግብ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን በማነቃቃት አልሚ ምግብ እንዲያቀርቡ አድርገናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ለዜጎቻችን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተደረጉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አልሚ ምግብ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ተመርጠው እንዲያመርቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ የተመረጡት እንዴት ነው?

አቶ ምትኩ፡- ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና እኛ የምንሠራው በጋራ ነው፡፡ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በማኅበር ተደራጅተዋል፡፡ የማኅበር አባላትና ባለሀብቶቹ የተካተቱበት የጋራ ኮሚቴ አለ፡፡ በዚህ ኮሚቴ አማካይነት ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተነጋግረንና የማምረት አቅማቸው ተገምግሞ አልሚ ምግቡን እንዲያመርቱ ተመርጠዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ ጨረታዎች ከሚደረጉበት መደበኛ አሠራር ለየት ባለ ሁኔታ ውስን ጨረታ እንዲሆን ይወሰናል፡፡ በዚህ ጊዜ የተለያዩ አሻጥሮች ይሠራሉ፡፡ ማለትም እህሎች ለተረጂዎች ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የሚሸጡበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ አስቸኳይነቱ ለሙስና የተጋለጠ ያደርጋዋል፡፡ በግልጽነት የመሥራቱና የተጠቀሱት ብልሹ አሠራሮችን ከመከላከል አንፃር የተሠራ ነገር አለ?

አቶ ምትኩ፡- የስንዴ ግዥ የምንፈጽመው በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ በኩል ነው፡፡ አወዳድሮ ነው የሚገዛው፡፡ እስካሁን የመንግሥትን የግዥ መመርያ ጠብቆ እየገዛ ነው፡፡ አልሚ ምግቦችንም በሚመለከት አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ችሎታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባትና ሁሉም የማምረት አቅማቸውን ገልጸው ነው የተሰጣቸው፡፡ የመሸጫ ዋጋውም ስለሚታወቅ በዋጋው መሠረት ነው እየተገዛ ያለው፡፡ የበቆሎ ግዥም ከኅብረት ሥራ ዩኒየኖችን በኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በኩል በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት እየገዛን ነው፡፡ ምንም ዓይነት ወደሌላ የሚከት ነገር የለም፡፡ በግልጽ አሠራር ነው የሚከናወነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ባለድርሻዎች በዕርዳታው ላይ ሲሳተፉ የማስተባበር ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ማጓጓዝ ቢቻልም በቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎችን የመምረጥ ችግር፣ ለታለመለት ቦታ በሰዓቱ አለመድረስና ችግሩ በደረሰበት አካባቢ ለመድረስ የሚያስችል መንገድ አለመኖር የመሳሰሉት ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ አሁን ዕርዳታው በምን ሁኔታ እየተካሄደ ነው?

አቶ ምትኩ፡- ሥራው የሚመራው በብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው የሚመራው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ነው፡፡ ኮሚቴው የሚመለከታቸውን ሁሉንም ያጠቃልላል፡፡ በብሔራዊ ኮሚቴው ሥር የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቴክኒክ ኮሚቴ አለ፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው ዳይሬክቶሬቶችን የያዘ ነው፡፡ በክልልም በተመሳሳይ አለ፡፡ ሁሉም ክልሎች የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ አላቸው፡፡ በቴክኒክ ኮሚቴው ሥር የጤና፣ የትምህርትና የውኃ ግብረ ኃይሎች አሉ፡፡ በእነዚህ ውስጥ ለጋሾችም አሉበት፡፡ ስለዚህ ለዕርዳታ የተዘጋጀው ሀብት ለሌላ የሚውልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴው በየሳምንቱ እየተገናኘ እያንዳንዱን ነገር ይገመግማል፡፡ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውሳኔ ይወስናል፡፡ ክልሎችም በየሳምንቱ ዓርብ ሪፖርት ይልካሉ፡፡ ተናበን ስለምንሠራ አንድም ነገር ያላግባብ የሚሾልክበት ሁኔታ የለም፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች አሉ፡፡ በእነዚህም ላይም ተባብረው የሚሠሩ አሉ፡፡ ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ግዥ የሚፈጽመው የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ የዘይት ግዥ ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ ጨረታው ተሰርዟል፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይታችሁ የምትወስኑት ከሆነ ለምን ተሰረዘ?

አቶ ምትኩ፡- ስንዴ ከአገር ውስጥ አንገዛም፡፡ ምክንያቱም አገር ውስጥ ያለው የዋጋ ውድነት የበለጠ ያንረዋል፡፡ በቆሎ ግን በቂ ምርት ስላለን እንገዛለን፡፡ ዘይት ለመግዛት አስበን የነበረው የአገር ውስጥ ዋጋን እንዳያንር ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን በቂ ምርት መኖሩን ስናረጋግጥ፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ማውጣት ለምን አስፈለገ?›› ብለን ጨረታውን ሰረዝን፡፡ ራሳችን ገምግመን ነው ያስቀረነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለድንገተኛ አደጋ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደታሰበውና እንደተፈለገው ቀና ላይሆን ይችላል፡፡ ያጋጠሟችሁ ተግዳሮቶች አሉ? ካሉ ምንድናቸው?

አቶ ምትኩ፡- ይኼ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ማታ፣ ቅዳሜንና እሑድን ጨምሮ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የሰውን ሕይወት ማዳንና ያለውን ችግር መከላከል ስለሆነ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት ችግር አንዱ ተግዳሮት ነበር፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም የመንገድ ችግር አለ፡፡ ትራንስፖርት በማይገባበት አካባቢ የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ የማዳረስ ሁኔታ አለ፡፡

ሪፖርተር፡-  መንገድ የሌለባቸውን ቦታዎች መጥቀስ እንችላለን?

አቶ ምትኩ፡- ቦታው ይኼ ይኼ ተብሎ መጥቀሱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ስንሄድ የአቅርቦትም ችግር አለ፡፡ በምንፈልገው ልክ ፈጥነን ለመሄድ የሀብት ችግር አለ፡፡ የሰው ኃይል ችግር ፈታኝ ነው፡፡ ፈጥኖ አሰባስቦ ከሌላው ዕርዳታ ጋር አቀናጅቶ የመውሰድ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ባቡሩ በቅርቡ ሥራ ስለሚጀምር እስከ ማዕከላዊ መጋዘን ድረስ ለማጓጓዝ ይቀል ይሆናል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴርን የብሔራዊ ኮሚቴው አባል ያደረግነው ትራንስፖርትን ከማስተባበርና ከማቅረብ አኳያ ፋይዳ ይኖረዋል ከሚል ነው፡፡ ማዕከላዊ መጋዘኖች ድሬዳዋ፣ መቐለ፣ አዳማና ሌሎችም ቦታዎችም አሉን፡፡

ምሕረት አስቻለው እና ታምሩ ጽጌ

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ...