Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር በቀሉ ኩባንያ በሱዳን የ120 ሚሊዮን ብር የሽያጭ ማዕከል ሊገነባ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዋው ፕራይም ሐውስ ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ በሱዳን ጠቅላላ የግንባታና የፊኒሺንግ ዕቃዎች የሽያጭ ማዕከል በ120 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በአገር ውስጥም ከጥቂት ወራት በኋላ የተለያዩ የሽያጭ ማዕከላትን በ150 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ ገልጿል፡፡ 85 በመቶ የሚሆነው ምርትም በተቋሙ እንደሚመረት የገለጹት የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማይ ዓለማየሁ፣ 15 በመቶ የሚሆነው አቅርቦት አገር ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች አምራቾች እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ምርቶችን በበቂ ማቅረብ ለማስቻልም የማምረት አቅማችንን እያሳደግን እንገኛለን፡፡ በገበያ ውስጥ ተፈላጊ የሆኑና የተመረጡ የኮንስትራክሽንና ፊኒሺንግ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ለማምረት በገላን ከተማ 10,000 ካሬ ሜትር የማምረቻ ቦታ ተረክበን በግንባታ ሒደት ላይ እንገኛለን፤›› ያሉት አቶ ግርማይ ኃይሉ የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡

‹‹ድርጅታችን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ስትራቴጂ ነድፎ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጥበትን የተደራጀ አሠራር ለመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ ነው፤›› ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ ኩባንያው በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የገነባውን የመጀመሪያ ማስፋፊያ የሽያጭ ማዕከሉንም ኅዳር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በይፋ አስመርቋል፡፡ ‹‹ዋው ሁሉም በአንድ ላይ›› የተሰኘው የሽያጭ ማዕከሉ በ10 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ 120 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ዓመታዊ ሽያጩም 150 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህንንም በመጪው አምስት ዓመታት ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር እንደሚያደርስ አቶ ግርማይ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የንግድ ማዕከሉ በውስጡ ሁሉንም ዓይነት የኮንስትራክሽንና የፊኒሺንግ ዕቃዎች፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ለሆቴልና ለመዝናኛ ተቋማት የተሟላ አቅርቦት፣ እንዲሁም የፕላን ሥራና የቤት ውስጥ ዲዛይን መሥራትን ጨምሮ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የችርቻሮ፣ የጅምላ፣ የጨረታ፣ የዱቤ፣ የሙሉ ፓኬጅ ሽያጭ፣ እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ ለሆኑ ከውጭ አገር ዕቃ የማስመጣት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ገበያውን ከተቀላቀለ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ዋው ፕራይም ሐውስ ሰርቪስ ምርቶችን ለሽያጭ የሚያቀርብበት የቦታ እጥረት እንዳለበት የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ የተገነባው የሽያጭ ማዕከሉ የገበያ ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ ኩባንያው ያለበትን የተደራሽነት ችግር ለመቀነስም ከስድስት ወራት በኋላ በባህር ዳር፣ በሐዋሳና በመቀሌ ተመሳሳይ የሽያጭ ማዕከሎች በ150 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመገንባት አቅዷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች