Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ወድቋል የሚባለው ነገር ውሸት ነው››

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ

የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ዙሪያ በሳምንቱ አጋማሽ የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በማዘጋጀት በተለይ ከከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ጋር መክሯል፡፡ የውይይት መድረኩ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ በመጀመሪያው የዕቅድና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ለማሳየት፣ እንዲሁም ሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማመላከትም ያለመ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መድረኩ በዘርፉ ጠንካራና ደካማ ጐኖች ላይ ውይይት የተደረገበት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ናቸው፡፡ በመድረኩ ጣልቃና ማጠቃለያ ወቅት አቶ ተክለወልድ ከጋዜጠኞች ጋር አጭር ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ቆይታቸው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ዳዊት ታዬ በጋራ የተሰጠውን ቃለ ምልልስና በተለይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ በማጠናቀር እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- በፋይናንስ ዘርፉ በኢንሹራንስና በባንኮች ውስጥ በባለቤትነት መሳተፍ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለአክሲዮን ከሆኑ በኋላ በአጋጣሚ ዜግነታቸውን ቢቀይሩ የእነዚህ ባለአክሲዮኖች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? በዚሁ ዙሪያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ ቢኖርም እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር ምንድን ነው መደረግ ያለበት?

አቶ ተክለወልድ፡- ነገሩን በሁለት ዓይነት መንገድ መመልከት ይቻላል፡፡ አንደኛ የፋይናንስ ዘርፉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ በአዋጁ መሠረት ሕገወጥ ነው ማለት ነው፡፡ ሕገወጥ ከሆኑ እንዴት መስተናገድ አለባቸው የሚለውን ከእኛ ውጭ የሚመለከተው አካል የሚያየው ነው፡፡ በእኛ በኩል ሰነዶችን ይዘን ለዓቃቤ ሕግ ከመስጠት ውጭ ሌላ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ግን አክሲዮናቸውን ወደሌላ ያስተላለፉ ካሉና የተላለፈለት ሰው ኢትዮጵያዊ ከሆነ፣ በሕጉ መሠረት ቦርዱ፣ የሚመለታቸውና አክሲዮን የገዛበት ባንክ ሆነው ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ አስፀድቀን ለውልና ማስረጃ ቀርቦ የተላለፈላቸው ባለአክሲዮን ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- በሕጉ አንድ ባለአክሲዮን ዜግነቱን ቢቀይር እንዲህ ማድረግ አለበት የሚል አለ?

አቶ ተክለወልድ፡- በዋናነት ለኢትዮጵያውያን ተብሎ ነው የተቀመጠው፡፡ እኔ የሕግ ባለሙያ አይደለሁም ግን አንድ ሰው ኢትዮጵያዊነቱን ከመቀየሩ በፊት የሌላ አገር ዜጋ እሆናለሁ ብሎ ካሰበ አስቀድሞ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያገኘውን ነገር በሙሉ መተው አለበት፡፡ የሌላ አገር ዜጋ እሆናለሁ ብሎ ማመልከቻ ከማቅረቡ በፊት ኢትዮጵያዊነት የሚያስገኘውን ነገር በሙሉ መተው አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በባንኮችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች አክሲዮን ካለው የሌላ አገር ዜጋ ለመሆን ሲያስብ ይህንን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ነበረበት ማለት ነው፡፡ አንድ ሁለት ተብሎ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም አንድ ሰው ዜግነቱን ከቀየረ ወዲያውኑ ያለውን አክሲዮን አስተላልፎ ወደሌላ አገር መሄድ አለበት ማለት ነው፡፡

አንዳንዶቹ እኮ ዜግነቴን ቀይሬያለሁና ምንም ማድረግ ስለማልችል፣ ለልጄ ሰጥቻለሁ፡፡ ለእከሌ ሰጥቻለሁ ያሉ እኮ አሉ፡፡ ያኔ እኮ ምንም አላደረግንም ነበር፡፡ በራሳቸው መንገድ ኢትዮጵያዊ የሚያገኘውን ጥቅም ማግኘት የለብኝም ያለኝን ግን ለእከሌ አስተላልፌያለሁ ባሉበት ጊዜ ያስተላለፍንላቸው ብዙ አሉ፡፡

የአሁን ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ፡፡ ቅድም እንዳልኩት ከማድረጉ በፊት ማስተላለፍ የነበረበት ቢሆንም በመሃል ግን ዜግነቱን ሲቀይርም ተቀብለን አስተላልፈን ነበር፡፡ የአሁኑን ግን ልዩ የሚያደርገው ጥቆማ መጥቶ ባንኮቹ ሲፈተሹና አቅርቡ ሲባሉ በድብቅ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው ተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሕገወጥነቱን ወደ ላይ ከፍ የሚያደርገው ይሄ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ምን ማድረግ ነበረበት? እከሌ የተባለ ሰው ኢትዮጵያዊ ሳይሆን በሕገወጥ መንገድ ባለአክሲዮን ሆኖ ተቀምጧልና እንድታውቁት ተብሎ ሲላክ፣ እንደ ብሔራዊ ባንክ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ልንወስድ አንችልም፡፡ ሕገወጥ ከሆነ ወደ ሕግ ይሄዳል እንጂ ወደ ብሔራዊ ባንክ አይሄድም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሕጉ የፈለገውን ያድርግ፣ በእኛ በኩል ግን ይህ ነገር ሕገወጥ ነው በማለት ለሚመለከተው አካል ያቀረብነው፡፡

ጥያቄ፡- በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በተለይ በፋይናንስ ዘርፉ የተገኘው ዓበይት ስኬት ምንድን ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከፍተኛ ስኬት አድርገን የምንወስደው የኢኮኖሚ ዕድገቱን ነው፡፡ ባለሁለት አኃዝ ዕድገት መገኘቱ ትልቅ ዕድገት ነው፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ የተገኘው ዕድገት ከ5.2 በመቶ ባልበለጠበትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች በበዙበት ወቅት ላይ ሆነን በአምስት ዓመት ውስጥ በአማካይ 10.1 በመቶ ማደጋችን ትልቁና ዋናው ስኬት ነው ልንል እንችላለን፡፡ ከዚህ ባሻገር ዕድገቱ ያመጣቸው ብዙ ውጤቶች አሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. ከድህነት በታች (በቀን 1.25 ዶላር ማግኘት የማይችለው) የነበረው ሕዝባችን ቁጥር 29.6 ከመቶ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ግን 22 ከመቶ ደርሷል፡፡ ይህም ማለት ወደ አምስትና ስድስት ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝባችን በቀን አንድ ጊዜ መብላት ይቸገር ከነበረበት እንዲወጣ ማድረግ ተችሏል፡፡  

በዚህ ረገድ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ መንግሥታችን የሚከተለው ደሃ ተኮር የበጀት አተገባበርን ስለነበር በየዓመቱ 70 በመቶ የሚሆነው በጀታችን ለግብርና፣ ለውኃ መስኖ፣ ለትምህርት፣ ለመንገድና ለጤና በመዋሉና ሕዝባችንም ተጠቃሚ በመሆኑ ድህንነቱ በጣም ወርዷል፡፡  

በሁለተኛ ደረጃ የፋይናንስ ዕድገት ልማቱም ከፍተኛ ስለነበር እስከታች በመውረድ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በ2002 ዓ.ም. 680 የነበረው የባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 2,868 ደርሷል፡፡ ተጠቃሚውም ከ4.6 ሚሊዮን ወደ 16.6 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶቹም 4.3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጐች ቁጠባና ብድር መስጠት ችለዋል፡፡

ስለዚህ የባንክ አገልግሎትን ይጠቀም የነበረው ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ወደ 21 ሚሊዮን በማድረስ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ አድርገናል፡፡ 82 ቢሊዮን ብር የነበረው የብድር አገልግሎት ወደ 376 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ብድር አዲስ ሥራ ፈጥሯል፡፡ የአገራችንን ሀብት በፍትሐዊነት ተጠቃሚ መሆን ተችሏል፡፡ ሥራ አጥነት ቀንሷል፡፡

ጥያቄ፡- የባንክ ዘርፉን ለማጠናከር የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ባንኮች ካፒታላችሁን አሳድጉ ተብለዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለውን ሒደት ያብራሩልን?

አቶ ተክለወልድ፡- ኢኮኖሚው ማደግ ካለበት ኢንቨስትመንቱ ከአጠቃላይ ምርት ድርሻው ከ35 እስከ 40 ከመቶ መድረስ አለበት፡፡ ኢንቨስት የምናደርገው ከአጠቃላይ ምርቱ ከ35 እስከ 40 ከመቶ መድረስ አለበት፡፡ ይህንን መጠን ኢንቨስት ለማድረግ ደግሞ ገንዘብ ፋይናንስ የሚያደርግ አካል ሊኖር ይገባል፡፡ ስለዚህ ኢንቨስት ለማድረግ የአገር ውስጥ ቁጠባ እጅግ በጣም ወሳኝነት አለው፡፡ ስለሆነም የአገር ውስጥ ቁጠባን በሚገባ ለማሰባሰብ በመቻላችን ብዙ ዓይነት ፕሮግራሞችን በመንደፍ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የባንኮችን ቅርንጫፎችን ከአራት እጥፍ በላይ ከማሳደግ በተጨማሪ የህዳሴ ግድብ ቦንድ፣ የቤት ቁጠባ ልማት ፕሮግራም፣ የግለሰቦች የመድን ዋስትና፣ የመንግሥት ሠራተኞች ዋስትናና ሌሎች ሰፊ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ የመንግሥት ቁጠባ ትልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ ቁጠባችንን ከአጠቃላይ ምርት ወደ 22.5 በመቶ አካባቢ ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ በቁጠባና በኢንቨስትመንቱ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ ቀሪው ከ45 እስከ 50 በመቶ ያለውን ኢንቨስትመንቱን የሸፈነው ከውጭ በተገኘ ብድር ነው፡፡ ስለዚህ በውጭ አገር ብድር ሁልጊዜ ኢንቨስትመንቱን ማስቀጠል ከፍተኛ አደጋ አለው፡፡ ይህንን ለማጥበብ ቢሠራም ከዚህም በኋላ በዚሁ አካባቢ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ ዋናው ነገር ዕድገት መኖር አለበት፡፡ ዕድገት ሲኖር ነው ቁጠባ የሚሰበሰበው፡፡ መጀመሪያ ዕድገቱን ማፋጠን  አለብን፡፡ ሁለተኛ በዕድገቱ የተገኘውን ገንዘብ ሰው እንዲቆጥበው ለማድረግ ተደራሽነቱን ማስፋት አለብን፡፡ በዚህ ረገድ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሁን ያሉትን የባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር በእጥፍ እናሳድጋለን ብለናል፡፡ ሌላው ደግሞ በኅብረተሰቡ አካባቢ ያሉት ማይክሮ ፋይናንሶች አሁን ያላቸው ቅርንጫፎች ብዛት ከ1,600 የማይበልጥ ነው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግን የማይክሮ ፋይናንሶች ቅርንጫፎችን የማሳደግ ሥራ ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉት 20 ሺሕ ቀበሌዎች አሥርሺው ውስጥ የማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፎች ይከፈታሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

ጥያቄ፡- ከፍተኛ ገንዘብ የማሰባሰብ ዕቅድ አለ፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ለየትኞቹ ትኩረት ይሰጣል?

አቶ ተክለወልድ፡- ይህንን ሁሉ ገንዘብ ስናሰባስብ አንዱና ዋናው የዕድገታችን አስቀጣይ ነገር ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከዚህ በፊት እናደርግ የነበረው በአብዛኛው በመንግሥት መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ ያጋደለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ማጋደሉም ተገቢ ነበር፡፡ መሠረተ ልማት ካልተስፋፋ ምንም ነገር የለም፡፡ አሁን ግን ሁሉንም ነገር ሚዛናዊ በማድረግ በአብዛኛው ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ትኩረት ይሰጣል፡፡ በቀጣዩ አምስት ዓመትም የታሰበው ይህ ነው፡፡ የግል ኢንቨስትመንቱ በዋናነት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ በሚገባ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ከልማት ባንክ የረዥም ጊዜ ብድር የሚያገኙበትና ከግል ባንኮች የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ማግኘት የሚችሉት ዓይነት አካሄድ እያደራጀን ነው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ወይም በሌሎች ዘርፎች የግል ዘርፉን የማበረታታቱ ሥራ ይጠናከራል፡፡ የምናበረታታውም ለእሱ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚያችን መሠረቱ ከዚህ በኋላ የግል ዘርፉ መሆን እንዳለበትና የሥራ ፈጣሪውም እሱ መሆን እንዳለበት ስለሚታመን ነው፡፡ የሥራ ስምሪቱም ከእሱ ጋር መገናኘት ያለበት ስለሆነ ከዚህ በኋላ የመሠረተ ልማት ሥራውን መንግሥት እያጠቃለለ ሲሄድ የሚሰበሰበው ሀብት በሙሉ ወደግሉ ዘርፍ ሄዶ የግሉ ዘርፍ ብዙ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ማበረታቻ ያልናቸውንም ነገሮች አስቀምጠናል፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ወይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሚባሉት ሁሉ በተለየ ሁኔታ ይታያሉ፡፡ ብድር ከውጭ ባለሀብቶች በተለየ ሁኔታ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሰጥና ሌሎችም ነገሮች ሲሰጡ እነሱን ማሳደጉ አስፈላጊ ስለሆነ ይህንን የምናደርግበት መንገድ ይመቻቻል፡፡ በጥቃቅንና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል ያሉት ደግሞ እያደጉ ሲሄዱ ወደ ኢንዱስትሪ ወይም የኢንዱስትሪ ባለሀብት ሊሆኑ የሚገባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ ባለፈው ዓመት ብዙ የተሠራ ቢሆንም፣ አሁንም ክፍተቶች ታይተዋል፡፡ ስለዚህ ልማት ባንክ እነዚህን ኢንተርፕራይዞችም በተለየ ሁኔታ እንዲያስተናግድ በአዲስ መዋቅሩ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሁለት ክንፎች ይኖሩታል፡፡

ባንኩ መካከለኛ፣ ከፍተኛውን፣ የጥቃቅንና አነስተኛዎቹን ሁሉ የሚደገፍበትን አሠራር አመቻችተን ጨርሰናል፡፡ በዚህ አዲስ አሠራር መሠረት አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች አዲስ አበባ ሳይመጡ በሁሉም ዞኖችና ትላልቅ ወረዳዎች በኩል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ175 በላይ ቅርንጫፎቹ በሚገኙበት በኩል ለእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ብቻ ብድር የሚያቀርብበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ይህም የብድር አሰጣጥ ከሊዝ ፋይናንሲንግ ጋር ተቆራኝቶ የሚሰጥበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ስለዚህ ጥቃቅኖችም ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችም በአጠቃላይ የግሉ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራበታል ብለን እናምናለን፡፡      

ጥያቄ፡- በአሁኑ ወቅት እየተነሳ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ብዙ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየገጠመን ነው ይላሉ፡፡ ባለሀብቶች ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ይግቡ ሲባል የውጭ ምንዛሪ የግድ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት? በውጭ ምንዛሪ እጦት የተዘጉ ማምረቻዎች እንዳሉም እየተነገረ ነው?

አቶ ተክለወልድ፡- የውጭ የምንዛሪ ችግር አለ ወይም የለም የሚለው ብዙም የሚያከራክረን አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምንጩ መታየት አለበት፡፡ ያንን ምንጭ ደግሞ ለማን? ለምን? እንዴት? ይከፋፈላል የሚለውም ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋና ምንጩ የኤክስፖርት ዘርፉ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኤክስፖርቱን ማሳደግ የሞት ሽረት ነው ብለናል፡፡ ኤክስፖርቱን ለማሳደግ ከግብርና በተለየ ሁኔታ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው የተባለለትን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኩል ኤክስፖርት ተደርጎ ብዙ የውጭ ምንዛሪ እንዲመጣ ከማስቻልና ምርታማነቱን ከማምጣት አንፃር የሚታይ ነው፡፡

ስለዚህ ኤክስፖርቱን ለማሳደግ ሥራዎች ገና እየተሠሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከኤክስፖርት የሚመጣው ገንዘብ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው የአገልግሎት ኤክስፖርት ከዕቃ ኤክስፖርት ያልተናነሰ አንዳንዴም እኩል የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ ዘርፍ ነው፡፡ ከቱሪዝም፣ ከአየር መንገድ ከመሳሰሉት የሚገኘው የአገልግሎት ዘርፍ ገቢው ሁለተኛ ምንጭ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከግል ኃዋላ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጐች፣ ትውልደ ኢትዮያዊያንና ሌሎችም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሳይቀሩ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገራችን ይልካሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እንዲያውም ከኤክስፖርት ገቢ ይልቅ እጥፍ ሊደርስ ትንሽ የቀረበው ነው ማለት ይቻላል፡፡

አራተኛው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ የመንግሥት ኃዋላ የሚባለው ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት በዕርዳታ የሚያገኛቸው ገንዘቦች ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ይዘው የሚመጡት ገንዘብ ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዘርፍ በአሁኑ ጊዜ በ40 እና 50 በመቶ እያደገ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተጠቃሎ የሚሠራውን ሁሉ ፋይናንስ ስለሚያደርግ ብድር አለ ማለት ነው፡፡ ብድሩም በሁለት ዓይነት መልኩ ይታያል፡፡ ቀጥተኛ የመንግሥት ብድርና የልማት ድርጅቶች ብድር ተብሎ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪው ከዚህ ሁሉ የሚሰበሰብ ነው፡፡ከዚህ ሁሉ የተሰበሰበ ገንዘብ ለማኑፋክቸሪንጉ፣ ንግድ ላይ ለተሰማራውና ለሁሉም የሚተላለፍ ነው፡፡ ይህ ሲደረግ አንዳንዴ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ሲታይ ሚዛናዊ ይሆናል፡፡ ተመጣጣኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ በመጀመሪያው ሦስት ወር ወይም እስከ ታኅሳስ ባለው ጊዜ ሲታይ የውጭ ምንዛሪ በብዛት የማይመጣበት ወቅት ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ጊዜ መንገጫገጮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን በሦስተኛውና በአራተኛው ሩብ ዓመትም በዚያው ሁኔታ ይቀጥላል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ብድሮች ሳይፈረሙ ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ ብድሩ በተፈራረሙበት ጊዜ ልክ እንጂ እኛ ስለፈለግን ዛሬውኑ አይመጣም፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣውም በራሱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነው፡፡ የግል ኃዋላ የምንለው ራሱ በዓል ሲደርስ ታኅሳስ መጨረሻ አካባቢ ወይም ጥር፣ የጥምቀት በዓል ሲደርስ የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም የእስልምና ተከታዮች በዓላት ወቅት ሊመጣ ይችላል፡፡ እንደዚህ እየሆነ የሚመጣበት ራሱን የቻለ ጊዜያት አሉት፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ሲታሰብ እንዲህ ያሉ ነገሮችንም ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ሰው ዛሬውኑ የጠየቀውን ካላገኘሁ ከማለት በስተቀር ያን ያህል ችግር የለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፍሰቱ ላይ የኤክስፖርቱ ቀዝቀዝ ማለት ያሳየው ለውጥ አለ፡፡ ቀዝቀዝ ስላለ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ የለም የሚል አስተሳሰብ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስላለ ነው፡፡ ከኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ለወጪ ንግድ ከምንከፍለው ሃያ በመቶውን ብቻ ነው የሚሸፍነው፡፡ ሰማንያ ከመቶው በሌላ በኩል በሚመጣ የውጭ ምንዛሪ የሚሸፈን ነው፡፡ ሰው ግን ኤክስፖርቱ ትንሽ ቀዝቀዝ አለ ከተባለ የውጭ ምንዛሪ የለም ይላል፡፡ የዚህ ዓይነት ግምታዊ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ አንድ የኢንዱስትሪ አምራች ይህ ወሬ በመኖሩ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠይቀውን የስድስት ወር አድርጐ ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ የለም ተብሎ ስለሚመራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሲታይ በሦስት ወር ውስጥ ለገቢ ዕቃዎች የከፈልነው 4.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር በንጽጽር ሲታይ በ12.6 ከመቶ አድጓል፡፡ በአንፃሩ ወጪ ንግዱ እንዲያውም ከአምናው ቀንሷል፡፡ ስለዚህ ለገቢ ዕቃዎች ግዥ የዋለው የውጭ ምንዛሪ የተገኘው ከኤክስፖርት ገቢው ብቻ ሳይሆን ከሌላው የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ነው፡፡ የመረጃ ጥንቅሩና እያወጣን ያለነው ገንዘብ ሲታይ የውጭ ምንዛሪ ችግር መኖሩን አያሳይም፡፡ የማንክደው ነገር ቢኖር ኢኮኖሚው እጅግ በጣም እየሰፋና እያደገ ስለሚሄድ የውጭ ምንዛሪ ፍላጐቱ ከምንጠብቀው በላይ እየሰፋ መምጣቱን ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ችግር የለም ማለት አንችልም፡፡ እኔ በማስበው መልክ ካየን ግን ያስተላለፍነው ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ ከአምናውም የበለጠ ነው፡፡ ነገር ግን የአምራቾች በተለየ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ብዙ ቦታ መንገራገጮች አሉ፡፡ በመንግሥት ባንኮች አካባቢም እንዲህ ያሉት ነገሮች ይታያሉ፡፡ ማየት ያለብን ግን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የ46 በመቶ ድርሻ የያዘው የአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ነው፡፡ አምራቹ ኢንዱስትሪና ሌሎችም ተደማምረው አምስት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከአጠቃላይ የሥራ ስምሪት አኳያ ከግብርና ቀጥሎ 19 በመቶ ሕዝብ ያሰማራው የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ዶላር ይፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰው እያደበላለቀ ልማታዊ አይደለም የሚባል ነገር ስላለ ይህ መስተካከል አለበት፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያለው 46 ከመቶ ካልተንቀሳቀሰ ግብር የሚባል ነገር የለም፡፡ የመንግሥት ግብር የሚባለው 95 በመቶ ወይም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ከዚህ ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ብድሩም የውጭ ምንዛሪውም ለእነሱ ሊሰጥ ይገባል፡፡ የሆነ ችግር ካለ ለአንዱ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አስተካክለን የምንሄድበት ሁኔታም ስላለ፣ አንዳንድ ጊዜ ጩኸቱና ወሬው ወደ አንዱ አጋድሎ ሌላው ዝም ስላለ ችግር ያለበት ዓይነት ተደርጐ ስለሚታይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ብሔራዊ ባንክ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ማለት አምራቹን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዘርፍ ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን፣ ግብርናውን፣ አገልግሎቱን፣ ንግዱንና ሌሎቹን እያየ ሁሉም በተመጣጠነ ሁኔታ ብድር እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ለኢኮኖሚው ባለው ድርሻ ልክ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኝ የምናደርግበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው መስጠት አለብንና መታየት ካለበት እናያለን የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

ጥያቄ፡- የውጭ ምንዛሪ ክምችትና አሰጣጡ ላይ የሚነሱ ሌሎችም ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የዶላር ክምችት በጣም ቀንሷልና ለዚህ ነው የውጭ ምንዛሪ ያጠረው የሚሉ አሉ፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ አገልግሎት አሰጣጡም ላይ የውጭ ምንዛሪ የሚጠየቁ አካላት የውጭ ምንዛሪ ከሚፈቅደው አካል ሙስና በሚባል ደረጃ በመቶኛ አስቡልን የሚል ጥያቄ እየተነሳብን ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ፋብሪካዎች ደግሞ ጥሬ ዕቃ ማስመጣት አቅቶን ዘግተናል ብለው እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ ለምሳሌ ቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲያነሳ ችግሩ ከፍ ብሏል ማለት አንችልም ወይ?

አቶ ተክለወልድ፡- ይሄንንም ከአቅጣጫው ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ አንደኛ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ወድቋል የሚባለው ነገር ውሸት ነው፡፡ በዋናነት መጀመሪያ የብሔራዊ ባንክም የግል ባንኮችም የውጭ ምንዛሪ ለሌላ አካል ሲያቀርቡ ቀይዋ መስመር ሳትነካ ነው፡፡ ስለዚህ ከውጭ ምንዛሪ ክምችት ጋር የተያያዘ ነገር የለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አሁንም ለ2.1 ወራት የገቢ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚያስችል ነው፡፡ በተያዘለት መንገድ እየሄደ ስለሆነ ከውጭ ምንዛሪ ክምችት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ በእርግጥ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ካስቀመጥነው ግብ በላይ ከሆነ ብሔራዊ ባንክም እንደገና ለባንኮችና ለሌሎችም የውጭ ምንዛሪ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን በተባለው ዓይነት ሁኔታ ከብሔራዊ ባንክ የሚመጡ ገንዘቦችም ሲኖሩ ለባንኮችና በተለይ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ለሚባሉት ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅና ለሜጋ ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ በቀጥታ እየተላለፈ ባለበት ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ችግር አለ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁለተኛ ባንኮቹ የውጭ ምንዛሪ ሲጠየቁ እንደሌላው አካል ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የጉቦና ሌላም ዓይነት ነገር ውስጥ ሁሉ ተገብቷል የሚሉ ነገሮችን እንሰማለን፡፡ የአንዳንዶቹ ጋዜጦች ላይ ይወጣል፡፡ ሁለት ሦስት ብር ኮምሽን እየተወሰደ ነው የሚል ነገር አለ፡፡ የብሔራዊ ባንክ ዋናው ሥራ ባንኮችን መቆጣጠርና ክትትል ማድረግ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን ብሔራዊ ባንክ እነዚህን ሥራዎች የሚሠራው በሰነድና በሰነድ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ አለው፡፡ ደንብ አለ፡፡ መመርያ አለ፡፡ ይሄንን ወደ ንግድ ባንኮቹ አስተላልፏል፡፡ ባንኮችም ይህንን መሠረት በማድረግ የራሳቸው ፖሊሲ አላቸው፡፡ ደንብ አላቸው፡፡ የራሳቸው መመርያ አላቸው፡፡ በተቀመጠው መሠረት ብሔራዊ ባንክም በሳምንት፣ በየቀኑ ለምሳሌ የትላንትናው የውጭ ምንዛሪ መጠን ብሔራዊ ባንክ ዛሬ አራት ሰዓት ላይ ይቀርባል፡፡ ሁልጊዜ ምን ያህል ገንዘብ አለ? ምን ያህል ሰጥተሃል? በእጅህ ምን ያህል አለ? ነው የሚባለው፡፡ ሌሎችም በዚያው ዓይነት መልክ ተመላሽ የሚባሉ በየሳምንቱና በየቀኑ የሚቀርቡ አሉ፡፡ ይሄንን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ተንትኖ ያያል፡፡ ከዚያ በኋላ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበውንና የባንኮቹን ሰነዶች ይመረምራል፡፡ የተጻፈው አንድ ነው? አይደለም? የሚለውን ደግሞ በመስክ ላይ ምርመራ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በመመርያዎችና በእነዚህ መሠረት ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ ነገሮች ምርመራ ያካሂዳል፡፡ በዚህ ምዘና መሠረት የመጣ ችግር ካለ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ግድፈቶች ከተገኙ አስፈላጊ የሆነውን ዕርምጃ ይወስዳል ማለት ነው፡፡ ልዩ ምርምራም ያደርጋል፡፡ ከሕዝብ የሚመጣ ጥያቄ ካለ በዚያው መሠረት ሄዶና ምርመራ አድርጐ ችግሮች ካሉ እንዲስተካከሉ ያደርጋል፡፡ ይሄ ወደ ሙስናና ወደ ሌሎች ነገሮች ሲመጣ እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ መልካም አስተዳደር ማስፈንና ሙስናም የኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋን ከማጥፋት አንፃር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ያሉበትና በሚዲያም እየሰማን ያለነው ነገር አለ፡፡ የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ነው ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚው እስካልተቀየረ ድረስ የፋይናንስ ዘርፉም ከዚህ የፀዳ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ዙሪያ ይወራል፡፡ እንደ አገር እንደሚባለው ሁሉ በደላሎችና ባንክ ውስጥ ባሉ የተጨማለቁ ሰዎች የሚደረግ ሙስና ካለ ያው ሁሉም ሰው እየተናገረ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ እንደ ሁልጊዜው ምርመራ ያደርጋል፡፡ ሆኖም ሙስና የሚታወቀው በወረቀት ላይ ተቀምጦ ስላይደለ ብሔራዊ ባንክ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በመንግሥት በኩል በሰፊው በዕቅድ በተያዘው መሠረት የፋይናንስ ዘርፉ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ እኛም ደሴት አይደለንምና በሌሎች ላይ የተነሱት የመልካም አስተዳደርና የሙስና ጉዳዮች በሙሉ እኛም ጋር ቢንፀባረቁ እኔን አይገርመኝም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ብቻም ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በሙሉ አንድ ላይ ሆነን በጋራ ማስተካከል ካለብን ማስተካከል አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከኢንቨስተሮቹ ጋር ያለው ችግርና እየተጮኸ ያለበት ጉዳይም ቢኖር አሁን ባልኩት መሠረት መፈታት ያለበት፡፡ ሁሉም ጋ ማድረስ የግድ ነው፡፡ ሁሉም በመጣው የገንዘብ ፍሰት መሠረት ስለሆነ የሚሰጠው በተለይ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ለሆኑት ዘርፎች የግል ባንኮችን ምንም ማድረግ ስለማንችል የመንግሥት ባንኮች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቅድሚያ እንዲሰጡ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ ይህ ትንሽ የተወለጋገደ ከሆነ የምናየው ነገር ይሆናል ማለት ነው፡፡       

ጥያቄ፡- የባንኮች ማቋቋሚያ ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር ደርሷል እየተባለ ነው፡፡ ዋጋን ከማረጋጋት አንፃር ግሽበትን በነጠላ አኃዝ ማቆየት ተችሏል ወይ? ከዚያ ወደ ሁለት አኃዝ አድጓል፡፡ የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ ደግሞ የምግብ ዋጋ ይጨምራል የሚል ሥጋት ስላለ ይሄንን ከመቆጣጠር አንፃር ብሔራዊ ባንክ ምን ዓይነት ዕርምጃ ይወስዳል?

አቶ ተክለወልድ፡- የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አኃዝ እናወርዳለን ብለን አስቀምጠናል፡፡ በዋናነት የገንዘብ ፖሊሲ ተልዕኮ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሽከረከረውን ገንዘብ መቆጣጠር ነው፡፡ ግሽበትን ለመግታት የሚያስችል ፖሊሲ ይዘን ሄደናል፡፡ ሁለተኛው ዋጋ ንረት ከፍተኛ ሆኖ የሚታየው የምግብ ዋጋ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ የምግብ ዋጋ በምን ዓይነት ሁኔታ ወጣ? እውነትም በአገሪቱ ምርት የለም ወይ? ተብሎ ነው የሚጀመረውና ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ግብርና በ6.6 በመቶ አድጓል፡፡ የተከሰተው ድርቅ እያለም በዚሁ መጠን አድጓል፡፡ አሁን ግን እየታየ ያለው የምግብ ዋጋ መውጣት ነው፡፡ የምግብ ዋጋ መውጣቱን ዘርዘር አድርገን ስናይ የምግብ ዋጋ የወጣው በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ነው፡፡ የሌላው አልወጣም፡፡ ኦሮሚያ ደግሞ ብዙ የሚመረትበት ክልል ነው፡፡ ዋጋው ለምን ወጣ? የሚለውን ማየት ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ ሕዝቡና አርሶ አደሩ ጋር ብዙ ገንዘብም ስላለ ገበያ ላይ ምርቱን ላለማውጣት ድርቅ መጥቷልና የምርቱ ዋጋው ይወደድ ይሆናል በሚል ምርቶችን ገበያ ከማውጣት ይልቅ የማቆየት ሁኔታ ያለ ይመስላል፡፡ ብዙ ጥናት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሚያ ከሁሉም በላይ ጥሩ የሚያመርት፣ ትርፍ የሚያመርት አካባቢ ሆኖ እያለ የምግብ ዋጋ ከፍ ማለቱ የሌላውንም ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሌላው የእሱ ተቀጽላ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ነው ትልቅ የሆነው፡፡ የአዲስ አበባን ብቻ የምግብ ዋጋ ስናይ ሃያ ሁለት በመቶ ነው ያደገው፡፡ የኦሮሚያ በአሥራ ስምንት በመቶ አድጓል፡፡

ጥያቄ፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ማሳደግ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማሳደግ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል፡፡ ለውጭ ምንዛሪው ግኝት አንዱ ምንጭ የወጪ ንግድ ነው፡፡ የወጪ ንግድ ገቢው አሁንም አዝጋሚ በመሆኑ ከወጪ ንግድ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ካልተገኘ እንዴት ማኑፋክቸሪንጉን ማሳደግ ይቻላል? ከዚህ አንፃር ምን አማራጭ ተቀምጧል? ምንስ ታስቧል?

አቶ ተክለወልድ፡- የማኑፋክቸሪንግን ልማት ማምጣት ማለት ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ነው ብለን አስቀምጠናል፡፡ ስለዚህ ይህንን ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ማኑፋክቸሪንግ ላይ መሥራት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡ ይህ የተባለው በራሱ ስለሚለወጥ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይዞ ስለሚወጣ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ሊፈታልን ይችላል በሚል ነው፡፡ ከወጪ ንግድ ይህንን ያህል የውጭ ምንዛሪ እናገኛለን ስንል፣ ለማኑፋክቸሪንግ ባስቀመጥነው ልክ በ24 በመቶ እያደገ ሲመጣ ነው ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ማኑፋክቸሪንጉ ለዚያኛው ውጤት ሳይሆን ምክንያት ነው፡፡ ኤክስፖርትን ለማሳደግ ማኑፋክቸሪንግ ማደግ አለበት፡፡ ይህ ዘርፍ ካደገ በአብዛኛው ኤክስፖርት መር ማኑፋክቸሪንግ ብለን እየደገፍን ስለሆነ  ለኤክስፖርት የሚሆኑ ዕቃዎችን የሚያመርት ነውና የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ማለት ነው፡፡ ይህ ተመልሶ ሌሎች ማኑፋክቸሪንግ ዕቃዎችን እንዲገዙ ያደርግና የብዜት ውጤቱ እየተስፋፋ ይሄዳል የሚል ነው ግምቱ፡፡ ስለዚህ ለማኑፋክቸሪንግ ዕድገቱ ከመነሻው ለካፒታል ዕቃውም ሆነ ለጥሬ ዕቃው የውጭ ምንዛሪ ማስፈለጉ ትክክል ነው፡፡ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ስለሆነ ነው ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ ሲመደብ ማኑፋክቸሪንግ ቅድሚያ ማግኘት ያለበት ከማኑፋክቸሪንግም እንደ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ያሉ ብዙ የሰው ኃይል ለሚፈልጉ ዘርፎች ቅድሚያ መሰጠት አለበት ብለን እየሠራንበት ነው፡፡ ስለዚህ ሌላ የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበትን መንገድ ሰፋ እናደርጋለን፡፡    

ጥያቄ፡- የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከፍ ለማድረግ ሌላ አማራጭ አለ ሲባል ሊጠቀስ የሚችል ምን አለ?

አቶ ተክለወልድ፡- ኤክስፖርቱ አንዱ ነው፡፡  

ጥያቄ፡- ከኤክስፖርቱ ሌላ?

አቶ ተክለወልድ፡- ቀደም ብዬ ከጠቀስኩት ውስጥ አንዱ ብድር ነው፡፡ ከብድር ሌላ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሲገባ ብድር ይዞ እንዲመጣ ይፈቀድለታል፡፡ ይህ አንዱ ነው፡፡ የአገር ውስጥ አምራች ሆኖ ኤክስፖርት የሚያደርግ ከሆነም ከውጭ ብድር እንዲያገኝ ይፈቀድለታል፡፡ ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት የሚያመርት ፋብሪካ ካለም ከውጭ በውጭ ምንዛሪ እንዲበደር ይፈቀድለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጩት ባለሦስትና አራት ኮከብ ሆቴሎች እኮ በውጭ ምንዛሪ ሊበደሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ የሚያመነጩት ገንዘብ ይህንን ሊከፍል ይገባዋል፡፡ ከሌላ ባንክ ወስደው ከሌሎች ጋር ተሻምተው መውሰድ የለባቸውም እንጂ ይህ በር ለእነሱ በተለየ ሁኔታ ክፍት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ መንግሥት ተበድሮም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያመጣውን ለእነሱ በቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ከውጭ እንዲበደሩ ኤክስፖርት መር ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ከሆነ በሩ ክፍት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች