Sunday, June 4, 2023

በራስ አቅም ለተረጂዎች ዕርዳታ ማድረስና ፈተናው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ብዙዎችን በተለይ በወሎ ኮረምና ደቡብ ትግራይ ለሕልፈት ባበቃው የ1977 ዓ.ም. ረሃብ ለዕርዳታ ፈላጊዎች እህል በማድረስ ረገድ ትልቁ ችግር ትራንስፖርት ነበር፡፡ ለተጐጂዎች የሚሆን የዕርዳታ እህል በአሰብ ወደብ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ፣ ድርቅ ወደነበረባቸው ቦታዎች ለማድረስ መንገድ አለመኖሩ በእጅጉ ፈታኝ እንደነበር መንግሥትን ጨምሮ ዕርዳታ በማድረሱ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ድርቅም ወደ ተጎዱ የአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የዕርዳታ እህል በማድረስ እንቅስቃሴ የትራንስፖርት ችግር መኖሩን የመንግሥት፣ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅት፣ ሌሎችም የተመድ ኤጀንሲዎችና በጎ አድራጐት ድርጅቶች ተሳትፎ ውስን ሲሆን፣ በገንዘብ ድጋፍም ሆነ መሬት ላይ ወርዶ ከማስተባበርም አንፃር፣ ለተጐጂዎች ዕርዳታ በማድረስ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው መንግሥት መሆኑንም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ተመሳሳይ አጋጣሚዎች በገንዘብም ሆነ በማስተባበር የዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር፡፡ በወቅታዊው የዓለም አቀፍ ሁኔታ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ መለወጥ፣ እንዲሁም በመንግሥት መዋቅር የታዩ ለውጦች ለድርቁ ምላሽ በመስጠት ረገድ በተዋናዮች ሚና ላይ ለውጥ ማስከተሉ ይስተዋላል፡፡ በዚህ መሠረት ዛሬ መንግሥት በራሱ አቅም ለችግሩ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ዕርዳታ የመስጠት እንቅስቃሴው በተጠቀሰው ለውጥ ውስጥ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ችግሮችስ አሉ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

የዓለም አቀፍ ተቋማት ልብና ገንዘብ ያለው የመካከለኛው ምሥራቅ የስደት ቀውስ ላይ መሆን፣ ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታ ቢያሻውም መንግሥት በራሱ ምላሽ መስጠት እችላለሁ ያለበት ጊዜ መሆኑና ሌሎችም ለውጦች ከግንዛቤ ሲገቡ ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች ማንሳት የግድ ይላል፡፡

አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከመጠባበቂያ ክምችት ወጥቶ ስንዴ ለተረጂዎች እንዲከፋፈል ሲደረግ 222,000 ቶን ደግሞ ጂቡቲ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በተሰጠ አቅጣጫ፣ እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ፍላጐት ተጨማሪ 405,000 ቶን ስንዴ ለመግዛት ከአቅራቢ የአውሮፓ ኩባንያዎች ጋር ውል እየተፈጸመ መሆኑን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የግዥ ሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በትረ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ድርቅ ላለ ድንገተኛ አደጋ የሚሰጥ ምላሽ በተፈጥሮው በብዙ መልኩ ለሙስና ይጋለጣል፡፡ በዚህም ነገሮች እንደታሰበው ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ መድረስ ያለባቸው ነገሮችም መድረስ ባለባቸው መጠን ለተጠቃሚዎች ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ ከሚኖረው ጥድፊያ አንፃር ጨረታዎች ውስን እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ እህል ከማዕከላዊ መጋዘን ወጥቶ ረዥም ርቀት ሲጓጓዝና በመጨረሻም ሲከፋፈል በየደረጃው ሙስና የሚፈጸምበት ክፍተት መኖሩ በቀደሙት ጊዜያት ታይቶ እንደነበር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ዋስትና ትምህርት ክፍልን ሥርዓተ ትምህርት የቀረፁትና በትምህርት ክፍሉ ያስተማሩት ዶ/ር አበጀ ብርሃኑ ይገልጻሉ፡፡

የስንዴ ግዥ ጨረታው እንዴት ነበር? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሰለሞን ካለው አጣዳፊ ሁኔታ አንፃር 35 እና 45 ቀናት አለመጠበቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቢሆንም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ልዩ ፈቃድ በመጠየቅ ውስን ጨረታ እንዲሆን መደረጉንና በዚህ መንገድ አሥር ኩባንያዎች ተመርጠው ስድስቱ አሸናፊ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ኩባንያዎቹም አቅምና ዋጋቸው ከግንዛቤ ገብቶ ከመቶ ሺሕ ቶን ጀምሮ ለእያንዳንዳቸው እስከ ሦስት መቶ ሺሕ ቶን መሰጠቱን ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሆነው ከፍትሐዊነትና ከግልጽ አሠራር አንፃር መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ አገሮች ላይ በደረሱ ድንገተኛ አደጋዎች  የዕርዳታ እህል ከውጭ ሲገዛ፣ ወይም በልገሳ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የእህል ደረጃውን የጠበቀ አለመሆን ወይም የአስገቢው አገር ሕግ የማይፈቅደው ዓይነት ምርት (ለምሳሌ ዘረ ልውጥ) በመሆን ችግሮች የተፈጠሩበት አጋጣሚ አለ፡፡

በአጣዳፊ ሁኔታ ስንዴ በመገዛቱ ጥራትን በማስመልከት ለአቶ ሰለሞን ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ጨረታዎች ውስን ቢሆኑም መሥፈርቶቹ ቀደም ሲልም ግዥ የሚፈጸምባቸው መሆናቸውን፣ እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ያሉ ተቋማት በእንቅስቃሴው ተሳታፊ መሆን በዚህ ረገድ ችግር እንዳይኖር እንደሚያደርግ ያስረዳሉ፡፡ የተመረጡት ኩባንያዎች ከዚህ በፊትም የሚታወቁና አብረው የሠሩ መሆናቸውም አንድ መተማመኛ ነው ይላሉ፡፡

በመንግሥት በድርቁ የምላሽ እንቅስቃሴ ትልቅ ማነቆ ይሆናል ተብሎ የተፈራው የሎጂስቲክስ ጉዳይ (ወደብ ላይ ሊፈጠር የሚችል መጨናነቅና ትራንስፖርት) ነው፡፡ ወደብ ላይ ሊኖር የሚችልን መጨናነቅ ለማስቀረት የታዘዘው እህል በክፍል በክፍል በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲገባ እንደሚደረግ አቶ ሰለሞን ሲገልጹ፣ ሊያጋጥም የሚችለውን የትራንስፖርት ችግር ለማስቀረት የባቡር ትራንስፖርትንና የግል ትራንስፖርት ኩባንያዎችን አቅም የመጠቀም ጥረት እንደሚኖር አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ከትራንስፖርት ባሻገር መጀመሪያ የእህል ግዥ ጨረታ ሲወጣ ታሳቢ የተደረገው የተረጂዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ተደርጐ መሆኑ፣ በተወሰኑ ቦታዎች የአቅርቦት እጥረት አስከትሎ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደገና የቁጥሩ መጨመርና 8.2 ሚሊዮን መድረሱን ታሳቢ ያደረገ የግዥ ትዕዛዝ በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ዕርምጃ መወሰዱን፣ በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሥራዎች በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ አስተባባሪ አቶ ምትኩ ካሳ ገልጸዋል፡፡

የዕርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር በሚመለከት በዓለም አቀፍ ተቋማትና በመንግሥት መካከል ልዩነት ቢኖርም፣ ተቋማቱ ዕርዳታ በማድረስ ረገድ በውስን ደረጃም ቢሆን እየተንቀሳቀሱ መሆኑ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ተገልጿል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት የዓለም ባንክ በመንግሥት የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በኩል ስንዴ እንዲገዛለት ፍላጐት ማሳየቱን ከአቶ ሰለሞን ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቢሆንም ተቋሙ የድርጅቱ አሠራር ምን ያህል ግልጽ ነው የሚለውን ማጤን ፈልጓል፡፡ በሌላ በኩል አቶ ምትኩ ደግሞ ቃል የመግባትና መሰል እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እስካሁን በተጨባጭ ያደረጉት ነገር እንደሌለ በመግለጽ ዕርዳታ በማድረስ ከፍተኛውን እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው መንግሥት ነው የሚለውን የአቶ ጌታቸውን ሐሳብ ያጠናክራሉ፡፡

መንግሥት በእንቅስቃሴው ውስጥ በገንዘብና ሥራዎችን በማስተባበር ትልቁን ድርሻ ሲይዝ፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የመንግሥት ተቋማት የመናበብና ተቀናጅቶ የመሥራት ነገር ሊተኮርበት እንደሚገባ ይነገራል፡፡ የእህል ግዥ የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ዘይት ለመግዛት ከሦስት ሳምንት በፊት ጨረታ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ የተሰረዘው በአገር ውስጥ በቂ ምርት በመኖሩ ከውጭ ማስገባት አስፈላጊ አይደለም ተብሎ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ የእንቅስቃሴውን የተቀናጀ መሆን ከጥያቄ ውስጥ አይከትም ወይ? የሚል ጥያቄ ለአቶ ምትኩ ተነስቶ ነበር፡፡

ስንዴ ከአገር ውሰጥ ያልተገዛው ያለውን የዋጋ ውድነት የበለጠ ላለማናር ሲሆን፣ በቂ ምርት በመኖሩ በቆሎ ግን በአገር ውስጥ እንዲገዛ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡ በተመሳሳይ የዋጋ ንረትን ያስከትላል በሚል ሥጋት መጀመሪያ ዘይትም ከውጭ እንዲገዛ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ በቂ ምርት መኖሩ ሲረጋገጥ ጨረታው ሊሰረዝ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ኩባንያዎች አልሚ ምግብ እንዲያመርቱ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ በዚህ ሁኔታ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ተሳትፎ እንዲቀናጅና አሠራሮችም ግልጽ እንዲሆኑ ንግድ ሚኒስቴር፣ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ እንዲሁም የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የተወከሉበት ኮሚቴ መኖሩን መረዳት ተችሏል፡፡

ለዚህ ዓይነቱ ድንገተኛ አደጋ በሚሰጥ ምላሽ የዕርምጃዎች ውጤታማነትና የታለመላቸውን ግብ አለመምታት፣ ተጠቃሚዎችን በአግባቡ አለመለየት፣ ዕርዳታዎች ከተከፋፈሉ በኋላ በአግባቡ ለውጦችን አለመገምገም፣ እንዲሁም የዕርዳታ ጥገኝነትን የመፍጠር አዝማሚያ እንደ ትልቅ ችግር ይነሳሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደግሞ ከታች እስከ ላይ ቀደም ሲል በተዘረጉ የመንግሥት መዋቅሮች፣ እንዲሁም ለአፋጣኝ ምላሽ ሲባል በሚፈጠሩ ጊዜያዊ አሠራሮች ላይ የሚንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዕርዳታ ይደርስ ዘንድ ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎች የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮች እንቅስቃሴውን መሸከም ይችላሉ ወይ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች መታየት እንደሚኖርባቸው ዶ/ር አበጀ ይናገራሉ፡፡ የክልሎች የምግብ ዋስትና ቢሮዎች አቅምም ከዚሁ አንፃር የሚታይ ነው፡፡

መንግሥት ለችግሩ ምላሽ የሰጠበት መንገድ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ በየጊዜው የሚከሰት ድርቅን ከመከላከል አንፃር ለሁልጊዜም ሊኖሩ ይገባሉ የሚሏቸውን መዋቅሮች ይጠቅሳሉ ዶ/ር አበጀ፡፡ ‹‹በፌደራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን ክልሎችም የራሳቸው የመጠባበቂያ እህል ክምችት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከመንግሥት ከሚያገኙት በጀት ለዚሁ ብለው የሚያውሉት ገንዘብ መኖር አለበት፤›› በማለት እንደዚህኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዕርዳታ ዓይን ሌላ ቦታ (የመካከለኛው ምሥራቅ የስደት ቀውስ) ሆኖ፣ መንግሥት ከሞላ ጐደል ዕርዳታ የመስጠቱን ሥራ በራሱ አቅም ሲሠራ ሸክሙ ሙሉ በሙሉ እሱ ላይ እንዳይወድቅ ያስችል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ገበሬዎች በተለይም ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች በብድርና ቁጠባ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረገው ሁሉ፣ የምግብ ኢንሹራንስ እንዲኖራቸው ሥርዓት መዘርጋት ቀጣይነት ያለው መፍትሔ ከመፈለግ አንፃር ወሳኝ ዕርምጃ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ይህን አስተያየት ታሳቢ በማድረግ ለአቶ ምትኩ መንግሥት ለድርቁ አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱ አዎንታዊ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ የዚህ ዓይነቱን አደጋ ተፅዕኖ ከመቆጣጠር አንፃር የተሠሩ ሥራዎች ምን ያህል ጠንካራ ነበሩ? የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የተለያዩ ሥራዎች ቢሠሩም የእዚህ ዓይነቱን ለአደጋ ተጋላጭነት ማቆም የሚቻለው በዘላቂ ልማት ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡     

መንግሥት በቀጣይም ለተጎጂዎች ዕርዳታ የማድረስ እንቅስቃሴውን ከሞላ ጎደል የራሱን አቅም ታሳቢ አድርጎ እያቀደ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከሆነ መንግሥት ከገንዘብና ከመዋቅር አንፃርም ይህን መሸከም የሚችል አቅም እንዳለው መፈተሽ እንዳለበት የሚያሳስቡ አሉ፡፡ በተመሳሳይ ለዕርዳታ የሚውለው ሀብት ያለብክነት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የሚያስችል አሠራር እየተከተለ መሆኑን፣ የአገር ውስጥ ሀብትን (የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንቅስቃሴን እንደ አንድ ግብዓት ዓይቶ ማስተባበር እንደሚያስፈልገው አስተያየታቸውን የሚሰነዝሩ አሉ፡፡

    

ምሕረት አስቻለው እና ታምሩ ጽጌ

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -