Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ47 ዓመት ያስቆጠረው ሕንፃ እንዲፈርስ መታሸጉ ቅሬታ ፈጠረ

47 ዓመት ያስቆጠረው ሕንፃ እንዲፈርስ መታሸጉ ቅሬታ ፈጠረ

ቀን:

‹‹ባለይዞታ ለሆኑት በሕጉ መሠረት አስፈላጊውን አድርገናል›› የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ

በተለምዶ አሜሪካ ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከታላቁ አንዋር መስጊድ (ወደ ተክለ ሃይማኖት በሚወስደው መንገድ በስተግራ በኩል) ፊት ለፊት የሚገኘውና ከተሠራ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገረው፣ ባለአምስት ፎቅ መዲና ሕንፃ እንዲፈርስ በድንገት መታሸጉን ባለይዞታዎቹ ተቃወሙ፡፡

ንብረትነቱ የሐጂ ኡመር ኢማም የሆነውና በ1957 ዓ.ም. ተጀምሮ በ1961 ዓ.ም. እንደተጠናቀቀ የተገለጸው መዲና ሕንፃ፣ በ1967 ዓ.ም. የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ሲታወጅ 85 በመቶ የሚሆነው በአዋጅ መወረሱ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕንፃውን የገነቡትና በአሁኑ ጊዜ 89 ዓመታቸው መሆኑን የሚናገሩት ሐጂ ኡመር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ልጆቻቸውን ያሳደጉበትንና አሁንም ልጆቻቸው ሠርተው የሚተዳደሩበት ሕንፃ ያለምንም ማስጠንቀቂያ መታሸጉን ተቃውመዋል፡፡ ሕንፃው ደረጃውን በጠበቀ ብረት የተገነባ በመሆኑ አፍርሶ ከእሱ የተሻለ ሕንፃ ይገነባል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸው፣ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ማስጠንቀቂያም ሆነ ተገቢው ካሳ ሳይሰጣቸው በድንገት ‹‹ውጡ›› ተብሎ መታሸጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

ከ70 ዓመታት በላይ በንግድ ሥራ ተሰማርተው ሲሠሩ አስፈላጊውን የመንግሥት ግብር በመክፈልና ሕግና ደንብ አክብረው ሲሠሩ መኖራቸውን የገለጹት ሐጂ ኡመር፣ ማን እንደጻፈው በማይታወቅ ወረቀት ‹‹ታሽጓል›› ብሎ በንብረት ላይ የንግድ ሱቅን ማሸግ ተገቢ አለመሆኑን፣ ሌሎች ነጋዴዎችም ተረጋግተውና በመንግሥት ላይ እምነት ኖሯቸው እንዳይሠሩ ስለሚያደርግ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥበት አሳስበዋል፡፡

ልማትን እንደማይቃወሙ የሚናገሩት ሐጂ ኡመር፣ ሕንፃው መፍረስ ካለበት በሕጉና በአግባቡ ሊሆን ይገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ዓለምገና ዳለቲ አካባቢ ተወልደው በ1937 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን የገለጹት ሐጂ ኡመር፣ ትምህርት ባይኖራቸውም የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን በመሥራት ባገኙት ሀብት ያነፁትን መዲና ሕንፃን መንግሥት እውነት ለልማት ከፈለገው፣ አስፈላጊውን ካሳና ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ሐጂ ኡመር ባቀረቡት ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የካሳ ክፍያና መልሶ ማቋቋም ንዑስ የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ኤልያስ ተስፋዬ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አሜሪካ ግቢና አካባቢውን መልሶ ማልማት የተጀመረው በ2006 ዓ.ም. መሆኑን የገለጹት አቶ ኤልያስ፣ ሁሉም ነገር የተጀመረው አስፈላጊው ማጣራት ከተካሄደና ለባለይዞታዎች የሚያስፈልገው ካሳና የምትክ ቦታ ከተሰጠ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአካባቢው ያሉ 13 ነጋዴዎች ሕንፃቸው ሳይፈርስ ባለበት እንዲያለሙ ሲጠይቁ፣ በተደረገ ጥናት አምስቱ ብቻ በግል ተይዘው መገኘታቸውን የገለጹት አስተባባሪው፣ መዲና ሕንፃን ጨምሮ ሌሎቹ ሕንፃዎች የመንግሥት ድርሻ ስላለባቸው (በአዋጅ የተወረሱ ክፍሎች ስላሉባቸው) መፍረስ እንዳለባቸው በአስተዳደሩ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ለመዲና ሕንፃ ባለቤት ሐጂ ኡመር የ50 ካሬ ሜትር ቦታ ካሳ 497,296 ብር ታስቦ እንዲወስዱ ሲጠየቁ፣ የቦታው ግምት ትክክል እንዳልሆነ በማመልከታቸው እንደገና በተደረገ ጥናት 318.4 ካሬ ሜትር መሆኑ መረጋገጡን አቶ ኤልያስ ገልጸዋል፡፡

አዲስ በቀረበው ቦታ ግምት ካሳ ተሠርቶ 623,823 ብርና 150 ካሬ ሜትር ቦታ እዚያው አሜሪካ ግቢ ውስጥ ከሌሎች ጋር ግድግዳቸውን አገናኝተው እንዲያለሙ እንደተፈቀደላቸው አስረድተው፣ እሳቸውም በደንብ ተረድተው መስማማታቸውንም አክለዋል፡፡

በድንገት የታሸገው ለምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ኤልያስ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዳያጡ በሚል እንዲቆይ መደረጉን ገለጹ፡፡ አሁን ነዋሪዎቹ በመልቀቃቸውና ባለሱቆቹ እንዲለቁ ሲጠየቁ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው እንዲታሸግ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በአግባቡና ልማቱ በሚፈቅደው ሁኔታ ከመስተናገዳቸው ባለፈ፣ እነሱን የሚጎዳ ወይም ቅር የሚያሰኝ ነገር በክፍለ ከተማውም ሆነ በመንግሥት በኩል እንዳልተደረገ አቶ ኤልያስ ጠቁመዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...