Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት የተጠረጠሩት የሸካ ዞን አስተዳዳሪና ሌሎች ሹማምንት ተከሰሱ

የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት የተጠረጠሩት የሸካ ዞን አስተዳዳሪና ሌሎች ሹማምንት ተከሰሱ

ቀን:

– በጦርነቱ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውና ንብረት መውደሙ ተገልጿል

በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ይዞታቸው ለኢንቨስተር በመሰጠቱ ምክንያት ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ በማቅረባቸው ‹‹ለሕግ ተገዢ አይደሉም›› በማለትና በሽፍታነት በመፈረጅ፣ በሸኮዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ሸካዎችን በማስታጠቅና የእርስ በርስ ጦርነት በማነሳሳት የተጠረጠሩ፣ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ 12 ተሿሚዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የደቡብ ክልል መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተዘዋዋሪ አንደኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ የሸኮ ብሔር ተወላጆችና የየኪ ወረዳ ፃኑ ቀበሌ ጉፍታ ንዑስ መንደር ነዋሪዎች ይዞታ ለኢንቨስተር ተሰጥቷል፡፡ ነዋሪዎቹ ለረዥም ዓመታት ምትክ ቦታና የንብረት ግምት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በመቀበል ምላሽ መስጠት ያልፈለጉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝመራ አንደሞና የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ‹‹ለሕግ ተገዢ አይደሉም›› በማለትና በወንጀለኛነትና በሽፍታነት በመወንጀል፣ በዞኑ ፖሊሶች ተይዘው እንዲታሰሩ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕጋዊ መብታቸውን በመጠየቃቸው ወንጀለኞች የሚል ስያሜ በመስጠት ነዋሪዎቹን በመተባበር በማሰርና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ያደረጉት ተጠርጣሪዎች የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝመራ አንደሞ፣ በዞኑ የደኢሕዴን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፣ የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሻረው፣ የየኪ ወረዳ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምሳሉ ከሴቶ፣ የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ሻሎ አድሎና ሌሎችንም ተጠርጣሪዎች ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከ30 በላይ የፖሊስ አባላትን መሣሪያ በማስታጠቅ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ፃኑ ቀበሌ ጉፍታ ንዑስ መንደር በመሄድ የሸኮ ብሔር ተወላጆችን ከበው መያዛቸውን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ያልተያዙት የአካባቢው ነዋሪዎች በሁኔታው በመደናገጥና በመረበሽ ንብረታቸውንና ቤታቸውን ጥለው አጎራባች ወደሆነው ጋምቤላ ክልል ዶንቻዬ ቀበሌ መሰደዳቸውንም ያስረዳል፡፡

የሸኮ ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ትተው ሲሰደዱ ተጠርጣሪዎቹ ‹‹አካባቢውን ተቆጣጥረነዋል›› በማለት አካባቢው ላይ ባንዲራ መትከላቸውንና ተመልሰው ሲመጡ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ንዑስ የፖሊስ ጣቢያ መክፈታቸውም ተገልጿል፡፡ በአካባቢው ምሽጎችን ቆፍረው ለውጊያ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

ድንገት በተፈጠረባቸው ወረራ ወደ አጎራባች ክልል የተሰደዱት ሸኮዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ሕገወጥ ድብደባና እስር በተጠርጣሪዎቹ ሲፈጸምባቸው ቆይቶ፣ ድርጊቱ ወደ እርስ በርስ ግጭት ተቀይሮ በሸኮዎችና በሸካ ብሔረሰቦች መካከል ጦርነት እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በሸኮዎችና በሸካ ተወላጆች መካከል በተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ስማቸው የታወቁ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ማረጋገጡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ስማቸውን ማወቅና መለየት ያልተቻለ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ባቀረበው ክስ ላይም ገልጿል፡፡ ከሰባት የሚበልጡ ነዋሪዎችም ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና የገቡበት እንዳልታወቀም አክሏል፡፡ ጦርነቱ ከእነሱ አልፎ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እንዲስፋፋና በዞኑ የፀጥታ ችግር እንዲሰፍን ምክንያት መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ ‹‹ወደዳችሁም ጠላችሁም የዞኑና የወረዳው ቁልፍ ያለው በእኛ እጅ ነው›› በማለት በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል የተነሳው ግጭት ወደ ቴፒ ከተማ አስፋፍተዋል፡፡ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. የቴፒ ከተማ ፖሊስ አባላት የሆኑ አምስት ፖሊሶች ወደ ጫካ ገብተው በነበሩ የሸኮ ተወላጆች እንዲገደሉ ማድረጋቸውንና ግጭቱ እስካሁን እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውን፣ በሕዝብ ደኅንነትና ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተላቸውንና የእርስ በርስ ጦርነት የማነሳሳት ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ሕግና ሥርዓትን ተከትለው ኅብረተሰቡን ማገልገል ሲገባቸው፣ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ ሆን ብለውና አስበው በሕገወጥ ተግባራት በመሰማራት በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ጉዳይ የሚያየው በተዘዋዋሪ ችሎት ቢሆንም፣ የሚቀጥለው ችሎት መቼ እንደሚሰየም አልታወቀም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...