Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የድርቅ ተጎጂ ወገኖችን ለመታደግ ፈጣንና የተቀናጀ ርብርብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው!

  የዘንድሮ ድርቅ ባለፉት 30 ዓመታት ከታዩት በሙሉ የከፋ ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 8.2 ሚሊዮን የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊዎች ሲኖሩ፣ ይህ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት በዚህ ድርቅ ረሃብ እንደማይከሰትና እንደ 1977 ዓ.ም. ድርቅ የከፋ ችግር እንደማይኖር በተደጋጋሚ ማረጋገጫ ቢሰጥም፣ አሁን በቀጥታ የድርቁ ተጎጂ የሆኑ ወገኖችን ለመታደግ ግን ፈጣንና የተቀናጀ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ ድርቅ ሲከሰት በአየር ንብረቱ ምክንያት    የተራዘሙ ደረቅ ወራት ስለሚኖሩ፣ የዝናብ እጥረቱም የተራዘመ ይሆናል፡፡ የዕርዳታ አቅርቦቱ ፍጥነት ከሌለው ተጎጂዎች ለምግብና ለውኃ እጥረት ይጋለጣሉ፡፡ ዕርዳታ ዘግይቶ ቢደርስ እንኳን ለማገገም አይችሉም፡፡ ከችግሩ አንፃር ዋና ዋና ጉዳዮችን እንመልከት፡፡

  1. የዕርዳታ ምግብ አቅርቦት ፍትሐዊ ይሁን

  የዕርዳታ ምግብ አቅርቦት በባህሪው ውስብስብ ነው፡፡ ውስብስብ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው፣ በዕቅድ የማይመራ የዕርዳታ ምግብ ዕደላ ተጎጂዎችን ሊያፈናቅል ይችላል፡፡ አቅርቦቱ ፍትሐዊ ካልሆነ ተረጂዎች ምግብ ፍለጋ ወደ ሌላ አካባቢ ስለሚያማትሩ መፈናቀልን ያስከትላል፡፡ የዕርዳታ አቅርቦቱ ፍትሐዊ ሲሆን ተጎጂዎች እንኳን ቀዬአቸውን መኖሪያ ቤታቸውን አይለቁም፡፡ የዕርዳታ ምግብ በአግባቡ ካልተሠራጨ ግን ዜጎች ይፈናቀላሉ፡፡ በአገሪቱ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ከመፍጠሩም በላይ፣ ድርቁ ወደ ረሃብ ተለውጦ ዜጎችን ለሕልፈት ይዳርጋል፡፡ ስለዚህም ፍትሐዊ የዕርዳታ ሥርጭት እንዲኖር በዕቅድ የሚመራ አሠራር መዘርጋት ከምንም ነገር ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡

        የዕርዳታ ምግብ ሥርጭት በተቻለ መጠን ዜጎች ከመጎዳታቸው በፊት መደረግ አለበት፡፡ የዕርዳታ ምግብ ሥርጭት ዕቅድ ሲወጣ የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለት ዕርዳታው የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከችግራቸው በቶሎ አገግመው ወደ እርሻ ሥራቸው የሚመልሳቸው መሆን አለበት፡፡ የዕርዳታ ምግብ በዘላቂነት የሚቀጥል ባለመሆኑ፣ ዜጎች በፍጥነት በማገገም ተመልሰው ራሳቸውን በምግብ እንዲችሉ ጠብሰቅ ያለ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ በምግብ ዕጥረት የተጎዱ ሕፃናት ሕይወታቸውን ከማትረፍ አልፎ ቀድሞ ወደነበሩበት  በመመለስ፣ አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ጠንካራ ቁጥጥርና ግምገማ መካሄድ አለበት፡፡ የዕርዳታ ምግብ ሥርጭት ፈጣንና ፍትሐዊ ሲሆን፣ የተጋረጠውን አደጋ በብቃት መቋቋም ይቻላል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ከሰፈነ ግን አደጋው ከሚታሰበው በላይ ይሆናል፡፡

  1. ወረርሽኝ እንዳይከሰት 

  በድርቅ ወቅት ከሚከሰቱ ችግሮች መካከል አንደኛው የጤና ጉዳይ ነው፡፡ በምግብ እጥረት በሚፈጠረው ጉዳት ምክንያት የሕፃናትና የአዋቂዎች ጤና በእጅጉ ከመቃወሱም በላይ፣ በንፅህና ጉድለት ሳቢያ የተለያዩ ዓይነት ወረርሽኞች ይከሰታሉ፡፡ በሕፃናት ላይ የቫይታሚኖች እጥረት የተለያዩ በሽታዎችን በማስከተል ሕይወታቸውን ለአደጋ ይዳርጋሉ፡፡ ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶችም እንዲሁ ይጎዳሉ፡፡ የድርቅ ተጎጂዎች በተገቢው ጊዜ ተገቢውን ዕርዳታ ካላገኙና አካባቢያቸው ንፅህና ከጎደለው ወረርሽኝ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ይፈጥራል፡፡ በምግብ የተጎዱ ሰዎች ሰውነታቸው በሽታዎችን የመቋቋም ችሎታው ደካማ ስለሚሆን ወባና መሰል በሽታዎች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ኪሳራ ያደርሳሉ፡፡

        በዚህ አሳሳቢ ወቅት ከምግብ በተጨማሪ ውኃ፣ መድኃኒትና የተለያዩ ቁሳቁሶች የተጎጂዎችን ጤና ለመጠበቅ ከመርዳታቸውም በላይ፣ ድንገት ተላላፊ በሽታዎች ወይም ኢንፌክሽኖች ቢከሰቱ ለመከላከል ያስችላሉ፡፡ ከሰዎች በተጨማሪ እንስሳት በቂ መኖ፣ ውኃና መድኃኒት ካላገኙ ከፍተኛ ጉዳት ሊያጋጥም ስለሚችል የማያቋርጥ ክትትል ያስፈልጋል፡፡ በድርቅ ወቅት ከሚከሰቱ በሽታዎች ለማገገም ያለው ዕድል በጣም የተመናመነ ስለሚሆን፣ በተቻለ መጠን ማናቸውንም ዓይነት እንቅስቃሴዎችን ማፍጠን ያስፈልጋል፡፡ በምግብ  እጦት ላይ በሽታ ሲጨመር ውጤቱ ምን እንደሚሆን ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡ የጤና ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ ወረርሽኝ እንዳይነሳ ጥረቱ ይጠናከር፡፡

  1. አስተማማኝ የሆነ የምላሽ ሥርዓት መዘርጋት

  ድርቅ በመጣ ቁጥር ለአደጋ የሚያጋልጡ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የመረጃ ክፍተት ነው፡፡ በድርቅ ወቅት ምን ያህል ወገኖች ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና የድርቁ የአስከፊነት መጠን ሳይታወቅ ሲቀር፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ ላይም ሆነ በምላሽ አሰጣጡ ላይ ያለውን ችግር ያሳያል፡፡ አስተማማኝ የሆነ የምላሽ ሥርዓት ሊኖር የሚችለው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ ጠንካራ ሲሆን ነው፡፡ የትኞቹ አካባቢዎች በድርቁ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት፣ ኤልኒኖ የተባለው የአየር ንብረት ክስተት መጀመሪያ በታየበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሚደረገው ፈጣንና የተቀናጀ ምላሽ የመስጠት አቅም የዜጎችን ሕይወት ከማትረፉም በላይ፣ የድርቁን መጠንና የአሳሳቢነት ደረጃ ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ በዚህ ደረጃ መንቀሳቀስ ሲቻል ሕይወት አድን እንቅስቃሴው የበለጠ ይጎለብታል፡፡ አሁንም ድርቁ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፣ ዝናብ መቼ ሊመጣ እንደሚችል፣ በእጅ ያለው የዕርዳታ አቅርቦት ለምን ያህል ጊዜ አስተማማኝ እንደሆነ፣ ወዘተ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ቢከሰት እንኳን የምላሹ አቅም በምን ያህል መጎልበት እንደሚገባው ከወዲሁ ካልታወቀ፣ የሕይወት አድን ሥራው አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡ ፍጥነትና ቅንጅት በዚህም መስክ ያስፈልጋል፡፡

  1. የድርቅ ተፅዕኖ መቼ ነው የሚያበቃው?

  ይኼ በቀጥታ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂን የሚመለከት ነው፡፡ አገሪቱ በየአሥር ዓመቱ ከሚመላለሰው ድርቅ መቼ ነው የምትላቀቀው? ድርቅን ለዘለቄታው ሊያስቀሩ የሚችሉ አማራጮች ምንድን ናቸው? ከዚህ በፊት የተከሰቱት ድርቆች በዜጎች ላይ የሞት አደጋ ያስከተሉ ሲሆን፣ በተለይ በ1977 ዓ.ም. የደረሰው ድርቅ ወደ ረሃብ ተቀይሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ማለቃቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት 30 ዓመታት ከታዩት የከፋ ነው ቢባልም፣ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እንኳን ባይገኝ በራሴ እወጣዋለሁ በማለት የመከላከል ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተጓዳኝም ጠብ ጠብ የሚሉ የውጭ ዕርዳታዎችም አሉ፡፡

  ‹አንድም ሕይወት መጥፋት የለበትም› እየተባለ ሲነገር ግን፣ ጥረቱ ፈጣንና የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ቁም ነገር ድርቅ ከዚህች አገር እንዲወገድ ምን ይደረግ? ለዘመናት በዝናብ ጠባቂነት ሥር የሚዳክሩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች እስከ መቼ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላሉ? አገሪቱ ‹የአፍሪካ የውኃ ማማ› የሚለውን ካባ ደርባ እስከ መቼ ድርቅ ይጫወትባታል? በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ ሥፍራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከዝናብ ጠባቂነት ለምን አይላቀቁም? ከተበጣጠሱና ኋላ ቀር የአርሶ አደር ማሳዎች በተጨማሪ፣ ለምን ዘመናዊ ሰፋፊ የግል ሁዳዶች እንዲኖሩ የፖሊሲ ማበረታቻ አይደረግም? ወዘተ ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ፡፡

  በየጊዜው አገሪቱን የሚጎበኟት ድርቅ በተፈጥሮ መዛባት ብቻ የሚመጣ ነው የሚለው አያስኬድም፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ የድርቅ ሰለባ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ መለወጥ ካለበት እንዲለወጥ፣ መሻሻል ያለበት ጉዳይ ካለ እንዲሻሻል መደረግ አለበት፡፡ ለድርቅ ተፅዕኖ ተጋላጭ የሆኑ ታዋቂ የሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ሁሌም ተጎጂ ከሆኑ፣ ድርቅን ተቋቁመው ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ትርፍ አምራች መሆን የሚችሉበት አማራጭ መታየት አለበት፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ መጠነ ሰፊ

  ውኃ፣ ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የአየር ፀባዮች ባሉበት አገር ውስጥ ድርቅ በየጊዜው እየተከሰተ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ችግር ውስጥ የሚወድቁ ከሆነ፣ ወይ የፖሊሲ ካልሆነም የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ይህንንም በጥልቀት ገምግሞ አስቸኳይ የሆነ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ለዚህም ፈጣንና የተቀናጀ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥትም ሆነ ከአገሪቱ ዜጎች የሚጠበቀው የድርቅ ተጎጂዎችን በፈጣንና በተቀናጀ ጥረት መታደግ ነው፡፡ ይህ ጥረት ፍትሐዊ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ደግሞ የመንግሥት አሠራሮች በሙሉ ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡ የዕርዳታ አቅርቦቱም ሆነ የመረጃ ቅብብሎሹ በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው ለተረጂዎች የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እንጂ ወሬ አይደለም፡፡ ድርቁን የፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ ከማድረግ ይልቅ ለወገን መድረስ ይቅደም፡፡ ወገኖቻችን ካገገሙና የድርቁ አደጋ ከተወገደ በኋላ ችግሩን መሠረት አድርጎ መሟገት ይቻላል፡፡ በፖሊሲና በስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ የተሻለ አማራጭ ማቅረብም እንዲሁ፡፡ ድርቁ በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ እያንዣበበ አላስፈላጊ አተካሮ መፍጠር ከቁማር አይለይም፡፡ አሁን ግን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ፈጣንና የተቀናጀ ርብርብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው!  

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አስጠነቀቀ

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ...

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...