በውብሸት አየለ ጌጤ
1. መግቢያ
ይህ ጽሑፍ በ1966 ዓ.ም. በየካቲቱ የኢትዮጵያ አብዮት ምክንያት በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩትን ባለሥልጣኖች ሥራቸውንና አገራቸውን በቅን ልቦናና በትክክል የማከናወን ግዴታቸውን በመዘንጋት ያላግባብ በሥልጣናቸው የተጠቀሙና ታማኝነት የጎደላቸውን፣ እንዲሁም በዳኝነትና በአስተዳደር በደል ያደረሱ ካሉ፤ ተለይተው እንዲታወቁና በሕግ እንዲቀጡ ለማድረግ፣ በዚህ ምርመራና ውጤትም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሰፋ ለማመቻቸት፣ በመጨረሻም በመንግሥት ባለሥልጣኖችም ላይ ሊኖር የሚገባውን ታማኝነት ለማረጋገጥ እንዲቻል የሚል ግብ ይዞ በአዋጅ ቁጥር 326/66 ሰኔ 8 ቀን 1966 ዓ.ም. የተቋቋመው መርማሪ ኮሚስዮን ተግባሩን በትክክል ተወጥቶ እንደሆነ መመርመር ነው።
ጽሑፉ አተኩሮ የመረመረውም ኮሚስዮኑ እንዲቋቋም ንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ከሰጡበት ከመጋቢት 16 ቀን 1966 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሚሲዮኑ ተመርማሪዎቹ እንዲከሰሱ የሚያዘውን ውሳኔውንና ዝርዝር ምርመራዎችን ለልዩ ጦር ፍርድ ቤት ጽሕፈት ቤት እስካስረከበበት እስከ ኅዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም. እና ተመርማሪዎቹ ከሕግ ውጭ እስከ ተገደሉበት እስከ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ነው።
በተጨማሪም ኮሚስዮኑ በራሱ አነሳሽነት በ1965 ዓ.ም. ከወሎ ረሃብና ዕልቂት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የመረመራቸውን ባለሥልጣናት በአዋጅ ቁጥር 326/66 ድንጋጌ መሠረት ሥራውን መፈጸም አለመፈጸሙን አገናዝቦ ትዝብቱን አስፍሯል።
በመጨረሻም ኮሚሲዮኑ በሕግ የተደነገገውን የሥራ ዘመኑን ከተቋቋመበት አዋጅ አንፃር እንዴትና መቼ እንዳጠናቀቀ ይመለከታል።
2. የአመሠራረቱ ታሪካዊ ምክንያትና አባላቱ
በ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ምክንያት የካቲት 20 ቀን 1966 ዓ.ም. የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ ለንጉሠ ነገሥቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ከሥልጣኑ ወረደ። በምትኩ ንጉሠ ነገሥቱ በጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን የሚመራ አዲስ ካቢኔ እንዲቋቋም አዘዙ።
ሕዝቡ የደረሰበትን በደል ምክንያት አድርጎ የጀመረውን አመፅ በአዲሱ ካቢኔም አላቋረጠም። ይህንን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለማብረድ፣ እግረ መንገዱንም ሕገወጥ በሆነ መንገድ የበለፀጉ የመንግሥት ባለሥልጣኖችም ካሉ የሚመረምር አንድ ጊዚያዊ መርማሪ ድርጅት ማቋቋም ያስፈልጋል ተብሎ በልጅ እንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ ታመነ።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ ንጉሠ ነገሥቱም መጋቢት 16 ቀን 1966 ዓ.ም. “የመንግሥት ሥራ በሐቀኝነት፣ በታማኝነትና በትጋት መሠራት ስላለበት ኃላፊነት የተቀበሉ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሁሉ ይህን መንፈስ ተከትለው ሥራቸውን በጥንቃቄ ማከናወን የሚገባቸው መሆኑን በመገንዘብ ንፁኁን የመንግሥት ባለሥልጣን ከጥፋተኛው መለየት፣ የመንግሥት ስም ለማስከበርና አጥፊ ሆኖ የተገኘው ወደ ፍርድ ሸንጎ እንዲመራ ለማድረግ ታስቦ ባለፈው ጊዜ የነበሩትና አሁን በሥራ ላይ ያሉት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሕገወጥ በሆነ መንገድ ያፈሩት ሀብትና ያባከኑት የመንግሥት ንብረት ቢኖር ተገቢውን ሕጋዊ ምርመራ ተከትሎ የሚያጣራ አንድ ኮሚሲዮን እንዲቋቋም” ብለው ንጉሣዊ ትዕዛዝ ሰጡ።
በትዕዛዙም መሠረት መጋቢት 19 ቀን 1966 ዓ.ም. ንፁሁን የመንግሥት ባለሥልጣን ከጥፋተኛው በመለየት፣ ጥፋተኛውን የሚያስቀጣ፣ የመንግሥትን ስም የሚያስከብር፣ በልጅ እንዳልካቸው መንግሥት የተሾሙ ሰባት አባላትን የያዘ መርማሪ ኮሚሲዮን ተቋቋመ። አባላቱም አቶ ኅሩይ ጥበቡ፣ አቶ አበበ በንቲ፣ ፊታውራሪ ታደሰ ማርቆስ፣ ኮሎኔል ኃይለ ማርያም አረዶ፣ አቶ መዋዕለ መብራቱ፣ ሻለቃ ሽመልስ መታፈርያና አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ ናቸው።
እነዚህ ሰባት አባላት ለኮሚሲዮኑ ሕጋዊ አቋም የሚሰጠውን ረቂቅ ሕግ በስምንት ቀን አዘጋጅተው መጋቢት 27 ቀን 1966 ዓ.ም. ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስረከቡ። አራት የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ይህን የሕግ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀረቡ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤቱም በቀረበው የሕግ ረቂቅ ላይ ከመከረበት በኋላ ሚያዝያ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ለፓርላማ አስተላለፈ። ፓርላማውም በቀረበለት የኮሚስዮን ማቋቋሚያ ረቂቅ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከመከረ በኋላ ተመርማሪው ወገን፣ ሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በመሆኑ ምርመራው ወገናዊ እንዳይሆን፣ ሥራውም በነፃነት እንዲሠራ መርማሪዎቹን ይህ አካል ሊመርጥ አይገባም የሚል ጥብቅ አቋም ወሰደ። በዚህም ምክንያት አስቀድመው በሥራ አስፈጻሚው ተመርጠው ረቂቅ ሕጉን የአዘጋጁት ሰባት ሰዎች ሰኔ 7 ቀን 1966 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋ ቀርበው ተሰናበቱ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ፓርላማው በቀረበለት ረቂቅ ላይ ዋና ዋና የተባሉ ሦስት ለውጦች አደረገ።
የመጀመርያው የፓርላማው ትኩረት፣ የአባላት አመራረጥና ብዛት ነበር። በዚህም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተረቀቀው ሕግ አባላቱን አሥራ አንድ እንዲሆን ሲል ያቀረበውን ሐሳብ ፓርላማው አሥራ አምስት ይሁን ሲል ለወጠው። ሁለተኛው ዓብይ ቁም ነገር በኮሚሲዮኑ አባላት የኅብረተሰብ ውክልና ላይም ፓርላማው የተለየ አቋም ያዘ። በዚሁ መሠረትም ስድስት ሰዎች ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከኅብረተሰቡ ይመርጣል የሚል ድንጋጌ በአንቀጹ በማስፈር፣ የኮሚሲዮኑን 40 በመቶ አባላት የመምረጡን መብት ፓርላማው ለራሱ ወሰደ። እንዲሁም መለዮ ለባሹ በኮሚሲዮኑ ውስጥ ልክ እንደ ፓርላማው ስድስት አባላት ይኑሩት በማለት ሌላውን 40 በመቶ የኮሚሲዮኑን አባላት ድርሻ ለመለዮ ለባሹ ሰጠ። ቀሪውን ሦስት አባላት ማለትም 20 በመቶ የሚሆነውን ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አንድ፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ከኢትዮጵያውያኑ መሀል አንድ፣ ከዋናው ኦዲተር ሠራተኛ አንድ፣ እንዲመደቡ ደነገገ። ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከኅብረተሰቡ መርጦ የኮሚሲዮኑ አባል ያደረጋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶክተር በረከት ሀብተሥላሴ፣ አምባሳደር ዘነበ ኃይሌ፣ አቶ መዋዕለ መብራቱ ጉግሳ፣ አቶ ጅሃድ አባቆያስ ቃዲና አቶ አሰፋ ሊበን ናቸው። አምባሳደር ዘነበ ኃይሌ ምርጫውን ባለመቀበላቸው በምትካቸው አቶ ባሮ ቱምሳ ተመረጡ። አቶ አሰፋ ሊበን በየትኛውም የኮሚስዮኑ ቃለ ጉባዔዎቹን በያዙት መዝገብም ሆነ በሪፖርቱ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ አይገኝም። ከዚህ የተረዳሁት ይህን ኃላፊነት ያልተቀበሉና ሥራውንም ያልሠሩ መሆኑን ነው።
በአዋጅ ቁጥር 326/66 ንዑስ አንቀ3 (2) ላይ በዝርዝር ከተቀመጡት የጦር ክፍሎች ተመድበው የኮሚስዮኑ አባል የሆኑት ኮማንደር ለማ ጉተማ ደበል፣ ሌተና ኮሎኔል ነጋሽ ወልደ ሚካኤል አብዲ፣ ሌተና ኮሎኔል ጌታሁን ዳምጤ ገብረየስ፣ ሻለቃ ዓለማየሁ ሥዩም ወልደ ማርያም፣ ሻለቃ ምትኩ ደምሴ በየነና ሻለቃ ሰላም ኅሩይ ገሜ ናቸው።
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ዶክተር መኮንን ወልደ አምላክ ወልደ አረጋዊ ከኦዲተር መሥሪያ ቤት አቶ ጌታቸው ደስታ ወልደ ሚካኤል፣ ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አቶ ሁሴን እስማኤል የኮሚሲዮኑ አባል ሆኑ።
እንቅስቃሴውን ሕዝባዊ መልክ የሰጡትን ሠራተኞችንና ማኅበራቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ተማሪዎችን ይህ አዋጅ የመርማሪ ኮሚስዮኑ አባል አላደረጋቸውም። እንዲሁም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ መምህራንንና የመምህራን ማኅበርን ዝቅተኛ በሆነ ቁጥር በኮሚሲዮን እንዲወከሉ የኮሚሲዮኑ መቋቋሚያ አዋጅ ደንግጓል።
በሌላ በኩል ድንጋጌው 40 በመቶ የኮሚሲዮኑን አባላት ከመለዮ ለባሹ ማድረጉ የሚያስገነዝበው፣ የወቅቱ ፓርላማ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሠራተኛው፣ ከመምህራኑ፣ ከሌሎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ከተማሪዎች የመለዮ ለባሹን አቅም አጉልቶ በማየት፣ የጦሩን ክፍል የጉዳዩ ባለቤት እንዳደረገው ይታያል።
ሦስተኛ ፓርላማው በሥራ ላይ ያሉት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሕገወጥ በሆነ መንገድ ያፈሩት ሀብትና ያባከኑት የመንግሥት ንብረት ቢኖር፣ መመርመር ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም የአስተዳደርና የዳኝነት በደልንም ኮሚስዮኑ የሚመረምረው ሌላው ዓብይ ጉዳይ፣ እንዲሆን በመደንገግ የምርመራውን አድማስ አሰፋው።
በመጨረሻም በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ፊርማ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በነበረው ፓርላማ ውሳኔ ሰኔ 8 ቀን 1966 ዓ.ም. የመርማሪ ኮሚሲዮን በአዋጅ ቁጥር 326/66 የተቋቋመ መሆኑን የሚገልጸው አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ወጣ።
የየካቲት ሕዝባዊ አመፅን ለማብረድ ወይም አቅጣጫውን ለማስቀየር የተጠነሰሰው መርማሪ ኮሚስዮን የማቋቋም ጉዳይ ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እጅ ወጥቶ ፓርላማ ሲደርስ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሕዝባዊ ጉልበት ያገኘ አስመስሎታል።
ይህም የፓርላማው ድካም ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት “አሥራ አምስት ከሚሆኑት የኮሚሲዮኑ አባላት ውስጥ በትክክለኛነታቸውና በኅሊናቸው ንፅህና ብርቅ የሆኑ ሰዎች” ይዞም ይሁን ሳይዝ የተቋቋመ ስለመሆኑ የሚታይ እንዲሆን ዕርምጃውን ሁሉ በትኩረት ለመታዘብ ታሪክ ምዕራፉን ሁሉ ክፍት አድርጎ ጠበቀው።
ኮሚሲዮኑ ሐምሌ 9 ቀን 1966 ዓ.ም. ከአሥራ አምስት አባላቱ መካከል ዘጠኙ በመጀመርያ ቀርበው “ኮሚሲዮኑን የፖለቲካ መሣሪያ ላለማድረግ፣ ብሔራዊና ሰብአዊ መብቶችን ለመጠበቅ፣ ሥራቸውን በትክክለኝነት፣ በታማኝነት ያለ አድልዎ ለማከናወን” የሚል ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥራውን ጀመሩ። ቃለ መሃላውም የተፈጸመው የጽሕፈት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በነበሩት በአቶ ሰለሞን ገብረ ማርያም አስተናጋጅነት ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ቀርበው ነበር። ቃለ መሃላውም ከላይ እንደተገለጸው የኮሚስዮኑ አባላት ኮሚስዮኑን የፖለቲካ መሣሪያ እንዳያደርጉት አጥብቆ ይከለክላል፤ ብሔራዊና ሰብአዊ መብቶችን አባላቱ እንዲጠብቁ ያስገድዳል፤ ሥራቸውን በትክክለኝነት በታማኝነትና ያለአድልዎ እንዲያከናውኑ እንደሚጠበቅ ከአዋጁ ድንጋጌ መረዳት ይቻላል።
እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ሁኔታዎች አጉልቶ የያዘው የቃለ መሃላው ድንጋጌና ንጉሠ ነገሥቱ ፊት የተፈጸመው የቃለ መሃላው ሥርዓት “በትክክለኛነታቸውና በኅሊናቸው ንጽህና ብርቅ” የሆኑትን የኮሚስዮኑ አባላት አቅም ማጎልበት ይጠበቅበታል።
ኮሚስዮኑ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ሊቀመንበር አድርጎ ከመረጠ በኋላ አዋጁን በማጥናት ምርመራውን የሚያከናውንበት የምርመራ ሥነ ሥርዓት አዘጋጀ።
ኮሚሲዮኑ ጽሕፈት ቤቱን በበላይነት የሚመሩ በአዋጁ አንቀጽ 4 (1) መሠረት ዋና ጸሐፊ የሕግ ትምህርትና ዕውቀት ያላቸውን አቶ ሰይፉ ተክለ ማርያም ሀብቴን መድቧል። እንዲሁም ኮሚስዮኑ አሥራ አምስት ሠራተኞች ነበሩት፡፡ በተጨማሪም አሥራ አራት የዕድገት በኅብረት ዘማቾችም ተመድበውለት ነበር።
3. የኮሚስዮኑ ምርመራና ውሳኔው
ኮሚስዮኑ በራሱ አነሳሽነት ወይም ከማንኛውም ሰው በሚቀርብ አቤቱታ ምርመራ መጀመር እንደሚችል አዋጁ ደንግጓል። ሥራውንም የጀመረው ከወሎ ረሃብና ዕልቂት ጋር በተያያዘ የተፈጸመ የአስተዳደር በደልን የተመለከተ ነበር። ኮሚስዮኑ አብዛኛውን ምርመራ ያካሄደው አዲስ አበባ ከሚገኘው ጽሕፈት ቤት ነበር።
ኮሚስዮኑ በራሱ አነሳሽነት ከጀመረው የ1965 ዓ.ም. ከወሎ ረሃብና ዕልቂት ጋር ጉዳያቸው የተያያዘውን የባለሥልጣኖችን ምርመራ ሲያካሂድ 138 ፋይሎችን፣ 87 ባለሥልጣኖችን አስቀርቦ መርምሯል። ምርመራውን ከአጠናቀቀም በኋላ እነማን መከሰስ እንዳለባቸው ወሰነ። በዚሁ ውሳኔም በግልጽ የታየው ተመርማሪዎቹ ከሦስት ወር እስከ አሥር ዓመት ብቻ በእስር የሚያቆይ ክስ በ1949 ዓ.ም. በወጣው ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 412 እና ቁጥር 509 እንዲመሠረት ያዘዘ መሆኑ ነው።
በዚህ ዕልቂት ምክንያት በኃላፊነት ሊጠየቁ ይገባል ያላቸው 35 የቀድሞ ባለሥልጣኖች ናቸው። ከእነሱም ውስጥ ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ሃያ ስድስቱ ሚኒስትሮች፣ አንድ የክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ፣ ሦስት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ሁለት ምክትል ሚኒስትሮችና አንድ ሥራ አስክያጅ ናቸው።
የኮሚስዮኑ ውሳኔ ሁለት ገጽታ ያለው ነው። አንደኛው ገጽታ ባለሥልጣኑ በግሉ የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጣም በሚል በግሉ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። ሁለተኛው የውሳኔው ሌላው ገጽታ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን የሚመለከት ነው። ኮሚስዮኑ የምክር ቤትን ኃላፊነት አምስት መልክ ሰጥቶ፣ ምክር ቤቱ ላልተወጣው ኃላፊነት የወቅቱን የምክር ቤት አባላት ተጠያቂ የሚያደርግ ነው።
በዚሁ መሠረት በ1965 ዓ.ም. በወሎ ለደረሰው ዕልቂት በያዙት የመንግሥት ኃላፊነት መሠረት ተገቢውን አላደረጉም፡፡ በሚገባም ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፣ በማለት በግል ሊከሰሱ ይገባል ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።
ይህ ውሳኔ ያረፈባቸው ባለሥልጣኖች የክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ ክቡር ደጃዝማች ሰለሞን አብርሃ፣ የእህል እጥረት አጥኚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ክቡር ደጃዝማች ለገሰ በዙ፣ ክቡር አቶ ሙላቱ ደበበና አቶ ጌታቸው በቀለ፣ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚእ፣ አቶ አበበ አንዱዓለም፣ አቶ ንጉሤ ሀብተወልድና ክቡር አቶ ተገኝ የተሻወርቅ፣ ከእርሻ ሚኒስቴር ክቡር አቶ አበበ ረታ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድና አቶ አብተው ዮሐንስ ናቸው።
የውሳኔው ሌላው ገጽታ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን የሚመለከተው ነው። ኮምሲዮኑ በዚሁ በ1965 ዓ.ም. በወሎ ለደረሰው አስከፊ ረሃብና መዘዙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕዝቡን ከደረሰበት አደጋ ሊታደገው ሲገባ ይህን የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጣም ሲል ወስኗል። ምክር ቤቱ የአልተወጣቸው ኃላፊነቶችም አምስት መልክ ያላቸው ጭብጦች መሆናቸውን በግልጽ ውሳኔው ላይ አስፍሯል።
የመጀመርያው ከኅዳር 28 ቀን 1961 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 18 ቀን 1964 ዓ.ም. ድረስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የረሃቡን ችግር ለማቃለል የሚያስችል ፕላን አውጥቶና ድርጅት አቋቁሞ ባለመሥራቱ በዚህ ወቅት የምክር ቤቱ አባል የነበሩ ሁሉ በኃላፊነት ተጠያቂ ናቸው የሚል ነው።
በዚህ ውሳኔ መሠረት በጋራ ሊከሰሱ ይገባል ሲል ውሳኔውን ያሳረፈባቸው፣ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ ተፈራ ወርቅ ኪዳነወልድ፣ ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳ፣ ክቡር አቶ አበበ ረታ፣ ክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ፣ ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሀብተወልድ፣ ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ክቡር ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል፣ ክቡር ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት፣ ክቡር ቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት፣ ክቡር አቶ ታደሰ ያዕቆብ፣ ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ፣ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ሻለቃ አሰፋ ለማ፣ ክቡር ዶ/ር ሥዩም ሐረጎት፣ ክቡር አቶ በለጠ ገብረ ፃድቅ፣ ክቡር ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ፣ ክቡር አቶ ሣላ ሂኒት፣ ክቡር ደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ፣ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ክቡር አቶ ከተማ አበበ፣ ክቡር አቶ ሰይፉ ማኅተመ ሥላሴ፣ ክቡር ፊታውራሪ አበበ ገብሬ፣ ክቡር አቶ ሙላቱ ደበበ፣ ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚእ እና ክቡር አቶ በላይ ዓባይ ናቸው።
ሁለተኛው ውሳኔ ያረፈበት ጭብጥ የወሎ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ የነበሩ በ1958 ዓ.ም. የነበረውን ረሃብ ምክንያት አድርገው በክፍለ ሀገሩ የእህል ጎተራ እንዲሠራና ሕዝቡ በፍቃዱ እህሉን አጠራቅሞ በችግር ቀን ራሱን እንዲረዳ ሐሳብ አቅርበው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሐሳቡን ተቀብለው እንዲጠና አዘዙ።
በትዕዛዙ መሠረትም ጥናቱ ተከናወነ። ምክር ቤቱም ሊነጋገርበት አጀንዳ አድርጎ ያዘው። ለሁለት ዓመት ይህ ጥናት የምክር ቤቱ አጀንዳ ሆኖ ከቆየ በኋላ ከአጀንደነት እንዲሰረዝ ተደረገ። በዚህ ምክንያት በጊዜው የነበሩት የምክር ቤቱ አባላት እንዲከሰሱ ወሰነ።
በዚህ ውሳኔ መሠረት በጋራ ሊከሰሱ ይገባል ሲል ውሳኔውን ያሳረፈባቸው፣ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ወልድ፣ ክቡር አቶ አበበ ረታ፣ ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ክቡር ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል፣ ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ፣ ሻለቃ አሰፋ ለማ፣ ዶ/ር ሥዩም ሐረጎት፣ ክቡር አቶ በለጠ ገብረ ፃድቅ፣ ክቡር አቶ ሣላ ሂኒትና ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እግዚእ ናቸው።
ሦስተኛው ውሳኔ ያረፈበት ጭብጥ በ1964 ዓ.ም. በራያና ቆቦ አውራጃ ላይ ከደረሰው ድርቅ ጋር የተያያዘ ነው። የተራበውም ሕዝብ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ ነበር። ለተራበው ሕዝብ በወቅቱ ምክር ቤቱ ስድሳ ሺሕ ኩንታል ተጠይቆ ሳለ የላከው ሁለት ሺሕ ኩንታል ብቻ በመሆኑ፣ በጊዜው የነበሩ አባላት በሙሉ ሊከሰሱ ይገባል ሲል ወሰነ።
በዚህ ውሳኔ መሠረት በጋራ ሊከሰሱ ይገባል ሲል ውሳኔውን ያሳረፈባቸው፣ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ ክቡር አቶ አበበ ረታ፣ ክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ፣ ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሀብተ ወልድ፣ ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ክቡር አቶ ታደሰ ያዕቆብ፣ ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ፣ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ክቡር ዶ/ር ሥዩም ሐረጎት፣ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ፣ ክቡር አቶ ሣላ ሂኒት፣ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ክቡር አቶ ከተማ አበበ፣ ክቡር አቶ ሙላቱ ደበበና ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረእግዚ ናቸው።
አራተኛው ውሳኔ ያረፈበት ጭብጥ በ1964 ዓ.ም. የክረምቱ ወራት ድርቅ በወሎና በትግራይ ነበር። በዚህ ምክንያት በ1965 ዓ.ም. በእነዚህ ሁለት ክፍላተ ሀገር ረሃቡ ተባብሶ በተለይ የወሎ ሕዝብ በእግሩ እየተሰደደ በጥርና በየካቲት ወራት በአዲስ አበባ አካባቢ መታየት ጀመረ። ይህ ሁኔታ ችግሩ እየተባባሰ ከባድ ዕልቂትን እስከሚያመጣ ድረስ በቂና አስቸኳይ ዕርምጃ ምክር ቤቱ አልወሰደም። በመሆኑም በዚህ ወቅት የነበሩት የምክር ቤቱ አባላት ሁሉ በኃላፊነት ተጠያቂ ናቸው ሲል ወሰነ።
በዚህ ውሳኔ መሠረት በጋራ ሊከሰሱ ይገባል ሲል ውሳኔውን ያሳረፈባቸው፣ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ ክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ፣ ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተ ወልድ፣ ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ክቡር አቶ ታደሰ ያዕቆብ፣ ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ፣ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ዶ/ር ሥዩም ሐረጎት፣ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ፣ ክቡር አቶ ሣላ ሂኒት፣ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ክቡር አቶ ሰይፉ ማኅተመ ሥላሴ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ክቡር አቶ ከተማ አበበ፣ ክቡር አቶ ሙላቱ ደበበ፣ ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረእግዚእ፣ ክቡር አቶ በላይ ዓባይና ክቡር ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም ናቸው።
አምስተኛውና የመጨረሻው ጭብጥ በወሎ ክፍለ ሀገር በደረሰው ድርቅ ምክንያት በሕዝቡ ላይ የችጋርና የረሃብ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ከመጋቢት 27 ቀን 1965 ዓ.ም. ጀምሮ ከተረዱ በኋላ ለችግረኞቹ እህል የሚገኝበትንና እንዲሁም የሚጓጓዝበትን ዘዴ ምክር ቤቱ የሚገባ ዕርምጃ አልወሰደም። በመሆኑም በዚህ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት የነበሩት ሁሉ በኃላፊነት ተጠያቂ ናቸው ሲል ወሰነ።
በዚህ ውሳኔ መሠረት በጋራ ሊከሰሱ ይገባል ሲል ውሳኔውን ያሳረፈባቸው ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ፣ ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሀብተወልድ፣ ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ክቡር አቶ ታደሰ ያዕቆብ፣ ክቡር አቶ ማሞ ታደሰ፣ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ዶ/ር ሥዩም ሐረጎት፣ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ፣ ክቡር አቶ ሣላ ሂኒት፣ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ክቡር አቶ ሰይፉ ማህተመ ሥላሴ፣ ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ክቡር አቶ ከተማ አበበ፣ ክቡር አቶ ሙላቱ ደበበ፣ ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገብረእግዚእ፣ ክቡር አቶ በላይ ዓባይና ክቡር ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም ናቸው። ይቀጥላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡