በሙሉቀን ካሳ
ይድረስ ለተከበርከው ለኃያሉ ዓባይ፣ ባያሌው እንዴት አለህ? እኔ አንተ መብራት ሆነህ ትመጣለህ ከሚል ናፍቆት በስተቀር ክፉንም ደጉንም እያሳለፍኩ አለሁ፡፡ ለመሆኑ አንተ ማነህ እንዳትለኝ፡፡ እኔ ይህንን ደብዳቤ የጻፍኩልህ የአገርህ ልጅ አዋሽ ነኝ፡፡ አዎ አዋሽ ወንዝ፣ ለሀገር ልጅ የመድረስ፣ አንዲት ጠብታ ውሃ ወደውጪ የማላፈስ፣ አዋሽ አንጀት አድርስ ነኝ፡፡ እንደዚህ ስልህ መቼም ጎረርክብኝ እንዳማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለራስ አብዝቶ ማውራት በሰውኛ ብቻም ሳይሆን በኛ በወንዝኛም እንደጉራ ይቆጠራል ብዬ ነው፡፡
ዓባይ አንተን ለጦቢያ ሊድሩህ መሆኑን ሰማሁና ከነገ ዛሬ እጽፍልሃለሁ ስል ይሄው የትዳር ጎጆህ የተቀለሰበት 7ኛ ዓመትህን ሊከበር ነው፡፡ እንኳን ደስ አለህ! ደስ ብሎኛል ደስ ይበልህ! ከዛሬ ነገ እፅፍልሃለሁ፣ ደስታየን እገልፅልሃለሁ እያልኩ መሠረተ ድንጋይ ከተጣለበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ አልሞላ ብሎኝ እስከዛሬ ደስታዬን ሳልገልፅ ቆየሁ፡፡ አትቀየመኝ ወዳጄ ዓባይ! ዛሬ ግን ተሳክቶልኛል፡፡ 7ኛ ዓመት ደስታዬን ምክንያት በማድረግ ስላንተ አንዳንድ ያሉኝን መረጃዎች እኔ አዋሽ ልጽፍልህ ወድጃለሁና ልብ ብለህ አድምጠኝ፡፡ በዚያውም ስላንተ ያለኝን ዕውቀቴን ምን ያህል እንደሆነ ትረዳለህ፡፡
ዓባይ አንተ በርካታ ስሞች እንዳሉህ ይነግራል፡፡ የጥንት ግብፆች “ኡር” በማለት ሲጠሩህ ትርጉሙም ጥቁር ማለት ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ከአገራችን ምድር ይዘኸው ከምትሄደው አፈር የተነሳ እንደሰጡህ አያጠራጥርም፡፡ ሌላው “ናይል” ትባላለህ፡፡ ይሄም በካም፣ በዓረብ፣ በዕብራይሥጥ ቋንቋ የወንዝ ሸለቆ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ፈለገ ግዮን ተብለህም ትጠራለህ፡፡ ፈለግ ማለት በግእዝ ወንዝ ማለት ነው፡፡
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ዓባይ እያለ ይጠራሃል፡፡ አፈታሪኩ እንደሚያስረዳው ከሆነ በጥንት ወቅት አንድ ሕፃን ስንጥር እንጨት ይዞ መሬት ጫር ጫር ሲያደርግ ውኃው ቡልቅ ቡልቅ እያለ መፍለቅ ይጀምራል፡፡ ብላቴናውም ወደአባቱ ዞር ይልና “አባ እይ ” ብሎ ውኃ መፍለቁን ሲነግረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ ከልጁ አንደበት የወጡት ቃላት ተጣምረው “አባይ” እንደ ተባልክ ይነገራል፡፡ መቼም ይህ ስላንተ ያለኝ ዕውቀቴ ሳይገርምህ አልቀረም፡፡ እኔ አዋሽ ስለ አገሬ ወንዞች ጠንቅቄ የማውቅ፣ እንደዚህ ንቁ ነኝ፡፡
የተከበርከው ታላቁ ዓባይ መነሻህና መፈጠሪያ ቦታህ ሲታይ ነጩ ዓባይ ከኡጋንዳ ቪክቶርያ ሐይቅ ሲነሳ፣ ይሄውም 13% የውኃ ፍሰትህን ይሸፍናል፡፡ የኛው ጥቁር አባይ ደግሞ ከምሥራቅ ጎጃም እንጮቄ ተራራ ስር ግሽ ዓባይ ሰቀላ ወረዳ ተነስተህ በጣና ሐይቅ የምትሄድ ሲሆን ይህም 87% የዓባይ ውኃን ትይዛለህ፡፡ ሱዳን ካርቱም ላይ ስትደርስ ተቀላቅለህ ትጓዛለህ፡፡ አቋርጠህም የምትሄዳቸው አገሮች ታንዛኒያ በከፊል፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ዛየር፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ ባብዛኛው፣ በመጠኑ ኤርትራና ምላው ግብፅ ታካልላለህ፡፡ ጠቅላላ ርዝመትህም ከ6825 ኪ.ሜ በላይ ነው፡፡ ይሄውም ከዓለም ረዥሙ ወንዝ አስብሎሀል፡፡ ከ1840 ሜትር ከፍታ በላይ ካላት ሀገረ ኢትዮጵያ ምድር እየተምዘገዘክ ወደ 340 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ወዳላት ግብፅ እተወረወርክ እብስ ትላለህ፡፡
ለዚህ እኮ ነው “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፣ ኢትዮጵያን አስርቦ ግብፅን ያበላል” የተባልከው፡፡ ምን ይሄ ብቻ “የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው፣ የላጭን ልጅ ቅማል በላው” እየተባለ የሚተረተው ለኔ ለአዋሽ ሳይሆን ላንተ ለዓባይ ነው፡፡ በእውነት እንደዚህስ እየተባሉ ከመኖር በቅርቡ ያውጣህ! አሜን በል አንተ! ምርቃቴ እንዲህ ቀላል እንዳይመስልህ መሬት ጠብ አይልም ፤ በቅርቡ ነው የሚደርስህ፡፡
እንግዲህ ዓባይ በዓመትም 52.62 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ ወደ ግብፅ ትፈሳለህ፡፡ ግብፅም 97% የውኃ ፍላጎቷን የምታሟሏው በአንተ ነው፡፡ 69.64% የመሬት ክፍሏን በአንተው መስኖ ታለማለች፡፡ ከ43 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የሚይዝ ማረፊያ ግድብ ሠርታልሃለች፡፡ ግብፆች ብዙውን ጊዜ የውኃ ቆጣሪ አይጠቀሙም፤ የተረፈው ሲፈስ ይውላል፡፡ በመስኖም አብዛኛውን የሚያለሙት ሩዝና ሸንኮራ አገዳ ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች ደግሞ ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዓመትም ከአስዋን ግድብ እስከ 10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚደርስ ትተናለህ፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ቤትህ የተሠራው እልም ያለ በረሃ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ሲተርፋቸው በዓመት እስከ 48 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚደርስ ውኃን ወደ ተረሸን የበረሃ ጫካና ሜዲትራኒያን ውቅያኖስ ይለቁሀል፡፡
ይህ ታድያ የአንተን የቤኒሻንጉል ጉሙዙን ጉባ ላይ ያለውን፣ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚይዘውን ቤትህን ሁለት ዓመት እንኳን ሳይሞላህ አይሞላውም ብለህ ታሰባለህ? አየህልኝ አይደል ከርታታው ወገኔ ዓባይ፣ ግብፅ ባንተ ምንያህል የተጫወተችብህ እንደሆነ? ይህንን የውኃ አጠቃቀሟን ሳታስተካክል ታዲያ
“ዓባይ የኔ ስጦታ ነው ማነው የሚነካው
ዓባይ ከተነካ ይመጣል እልኬ
እትቱ በረደኝ ዓባይን አትንኩብኝ፣” የምትለው፡፡ ይልቅ የሚበጀው በአንተ ጉዳይ ላይ “ተማክረው የፈሱት ፈስ አይገማም” አንደተባለው ከኢትዮጵያ ጋር ተመካክሮ በጋራ መጠቀም ነው፡፡ አሁን ላይ ከመመካከር ያለፈ ነገር ዋጋ እንደሌለው ያወቀች ይመስላል፡፡
ወዳጄ ዓባይ ሆይ ወደኛው ጉዳይ መለስ ልበልና ኢትዮጵያ ካሏት 12 ትላልቅ ወንዞች አንተን ጨምሮ 9 ድንበር ተሻጋሪ ናችሁ፡፡ 30% የመሬት የቆዳ ስፋት በአንተ ዙሪያ ቢሆንም እስካሁን የተጠቀመችው በፊንጫአ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ነው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ባንተ ላይ እስካሁን አለመጠቀሟ እንደምክንያት የሚነሳው፣ ዝናብ ተኮር የግብርና ምርት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ባንተ ጉዳይ ገንዘብ መከልከልና የግብፅ የውስጥ ለውስጥ አሻጥርና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ይህም ማለት ኢትዮጵያ ማልማት ከነበረባት መሬት እስካሁን 5% ብቻ ነው የተጠቀመችብህ ማለት ነው፡፡ እኔ አዋሽ ግን በዓመት 4.63 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ እያፈሰስሁ አለሁ፡፡ አንዲትም ውኃ ሳትባክን የደቡቡንና የምሥራቁን ክፍል እየተሸከረከርኩ በልማት አጥለቀልቀዋለሁ፡፡ አሳውን፣ የመስኖ አገዳ ምርቱን ፣ ሽንኩርቱን፣ ካሮቱን፣ በቆሎውን ወዘተ. ኧረ ምኑቅጡ፡፡ ብቻ ምን አለፋህ በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ በመቀመጫው በኩል ያለውን ቀዳዳ ወትፎ የሚበላው እኔ የምሰጠውን ምርት ነው ማለት ትችላለህ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው “በእጅ ያለወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል” ብለው ነው መሰለኝ እንዳንተ በተረት፣ በዘፈን፣ ሲያመሰግኑኝ አልሰማም፡፡
‹‹ነቢይ በአገሩ አይከበርም›› እንደተባለው ነው መሰለኝ በአገሬ የሚሠራ አይመሰገንባትም፡፡ በቅርቡ እንኳን ትልቁን የተንዳሆ የሽንኮራ አገዳ ምርት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ ኧረ እንዲያውም በግማሽ ምርት እየሰጠሁ ነው፡፡ እድሌ ሆኖ አነድ አፋሽ ይመስል ምስጋናው የልፋቴን ያህል አልሆነም፡፡ ግዴለም እኔ አዋሽ የምመሰገንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ወደአንተ ልመለስ፡፡
ዓባይ! እስካሁን ድረስ 7 የተፋሰስህ አገሮች አንተን በጋራ ለመጠቀም ተፈራርመውብሃል፡፡ ከግብፅ ማንገራገር በስተቀር ሁሉም በጋራ ለመጠቀም አምነዋል፡፡ መሠረተ ድንጋይ የተጣለበትና ግድቡ ቤትህ የተጀመረበትን 7ኛ ዓመትህን ይሄው በተለያዩ ዝግጅቶችና ቦንድ በመግዛት እየተከበረ ነው፡፡ በእውነት በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ቤትህም 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚይዝ ሰምቻለሁ፡፡ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ 6450 ከፍ ብሏል፡፡ ጠቅላላ ስፋትህ ከ1680 ስኩዌር ሜትር በላይ ሲሆን የግምብህም ውፍረት 130 ሜትር፣ የርዝመትህ ከፍታ ደግሞ 145 ሜትር ይደርሳል፡፡ በቅርቡም ካሉ 16 ተርባይኖች ሁለቱ መብራት እንደሚያመነጩ ተነግሯል፡፡ ይሄ እንግዲህ ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 7ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጥሃል፡፡ ትልቁ ሰው ሠራሽ ሐይቅም ትሆናለህ፡፡ በየወሩም በርካቶች ይጎበኙሃል፡፡
ተገንብተህም ስታልቅ 6450 ሜጋባይት የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በመቶሺ የሚቆጠር የዓሳ ምርት፣ የባህር ትራንስፖርት፣ ለቱሪዝም፣ አልፎም ተርፎም ለመስኖ እንደምትውል አውቃለሁ፡፡ ከጦቢያም አልፈህ አጎራባች አገሮችን በመብራት እንደምታጥለቀልቅ፣ እየጠበቁህ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ደስ ይላል! የቤኒሻንጉልና ጉሙዝ ጉባ ወረዳ ቤትህ በአሁኑ ሰአት ከ64% እንደተሠራ ባለፈው በረዶ አዘል የጣለው ዝናብ አደረሰኝ፡፡ በጣም የገረመኝ የሕዝቡ መነሳሳት ነው፡፡ ከ84 ቢሊዮን በር ወጪህም 30% የሚሆነው ከሕዝብ ከተዋጣ ገንዘብና የቦንድ ሽያጭ እየተሰበበ ያለ መሆኑ አስደንቆኛል፡፡ ስላንተ የምሰማው ዜና ሁሉ አስደስቶኛል፤ በእውነት በጣም ነው የቀናሁብህ፡፡ ይሄን ስልህ መንፈሳዊ ቅናት ነው፡፡ እኔ አዋሽ ምቀኝነት አላውቅም፡፡
ዓባይ! እንግዲህ አንተም ተመከር “አንተ ትንሽ አዋሽ እኔን ልትመከር” ብለህ አትናቀኝ፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለ አገር የለም፡፡ ስለዚህ ቅምጥህን፤ ውሽማህን ግብፅን ተውና ጦቢያን አግብተህ ተቀመጥ፡፡ ግብፅ ከሠራችልህ አስዋን ቤትህ የኢትዮጵያ ይበልጣል፡፡ ሲያሻት ወደበረሃ እየለቀቀችህ ስትፈስ ከምትኖር ረጋ ሰከን በል፡፡ ዕድሜ ብዙ ያስተምራል እኮ፤ አንተም ተማር፡፡ ጦቢያ እስከዛሬ ጥገቷን፣ ወተቷን፣ ለም አፈሯን ልጆቿን እየቦጠቦጥህ ስትወስድ ውሽማህን ግብፅን ስታበላት ዝም ነው ያለችህ፡፡ ይቺ ምስኪን! አንጀቷን አስራ ከመቀመጥ በስተቀር መች በክፉ ዓይኗ አየችህ?
ከእንግዲህ በኋላ ግን አንተም ስምህ አይጥፋ፡፡ እስከመቼ ድረስ “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ትባላለህ? እስከ መቼ ድረስ በየጊዜው እየሞላህ “ዓባይዬ ሞላልሽ፣ ሞላልሽ ፍቅሬ የትላግኝሽ” እየተባልክ የሚዋደዱ ሰዎችን ታስናፍቃለህ? ተው! ደግም አይደል ተው! ከእንግዲህ ጉባ ላይ ቤትህ እየተሠራ ነው፡፡ በቅርቡም ተሠርቶ ሲያልቅ ሕዝቡ ድል አድርጎ ደግሶ፣ አልብሶ “ብሮወሸባዬ” ፣ “ብሮወሸባ” ብሎ ይድርሃል፡፡ አንተም በተራህ መበራት ሆነህ ድረስለት፤ ለዚህ ምስኪን ሕዝብ፡፡ ላቡን ጠብ አድርጎ እየሠራህ ላለው ሕዝብ ድረሰለት፡፡
ደግሞ ጦቢያ ደግ ናት፡፡ ጉባ ላይ አረፍ ብለህ የጫጉላ ሽርሽር አርገህ፣ የያዘከውን ለም አፈር አራግፈህ፣ ለልጆቿ ትንሽ ጥሪት ካስቀመጥህ በኋላ ትለቅሃለች ፡፡ እዛች ውሽሚትህ ግብፅ ጋር መሄድ ትችላለህ፡፡ አየህ እንዲህ አይነት ሚስት ይገኛል ወይ? አይገኝም፡፡ ቢገኝማ ስንቱ ቆሞ ባልቀረ፡፡
ዓባይ ደግሞ የቤትህ ግድብ ሲሠራ የኔ የአዋሽ ገንዘብ እንዳለበት እንዳትረሳ፡፡ ምክንያቱም በኔ ባለሙት ብር ነው ሕዝቡ ላንተ እያዋጣ ያለው፡፡ ቦንድ እየገዛ ያለው፡፡ አይዞህ ለመክፈል እንዳታስብ የኔም የአዋሽ ሆነ የአንተ ጥረት ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት ነው፡፡ ግባችን ዓላማችን ታላቂቷን ኢትዮጵያን መገንባት ነው፡፡
በል እንግዲህ ወዳጄ ዓባይ ሰላም ሁንልኝ፡፡ እንደኔ እንደ አዋሽ ኢትዮጵያን በቅርቡ እንደምትጠቅም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ግማሴህ ጥሩ ነው፤ ፍጻሜውን ያሳምረው፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚሁ እፅፍልሃለሁ፡፡ ፍሬህን ለማየት ያብቃኝ፡፡
የአንተው የቅርብ ወዳጅህ አዋሽ፣ የልብ አድራሽ፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡