Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊምግብ እንደ መድኃኒት

ምግብ እንደ መድኃኒት

ቀን:

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ ሕመምተኞችን ለመፈወስ ከሚደረገው የሕክምና ሥራ በተጓዳኝ ሕመምን በተመጣጠን ምግብ አማካይነት ለማዳን የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ሕክምናን ‹‹ኒውትሪሽን ቴራፒ›› በማለት ይጠሩታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ‹‹ምግብዎ መድኃኒቶዎ ይሁን›› የሚል ብሂልም ተፈጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ ምንነት፣ ይዘትና ጥቅምን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ጠለቅ አድርጎ ያውቀዋል ለማለት እንደሚከብድ ይነገራል፡፡ በተለይም በሕክምና ደረጃ ተግባራዊ የማድረግ  ነገር ለጭላንጭል ያህል የራቀ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ቢሆን የተመጣጠነ ምግብ እንዲበላ የሚሰማው ሥጋ ሲያገኝ ነው ይላሉ፡፡

በሕክምና ዓለምም ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው መድኃኒት ከማዘዝ በስተቀር የተመጣጠነ ምግብ ሕክምና ወይም ኒውትሪሽን ቴራፒ (ሕክምና) ሲሰጡ ብዙም አልተለመደም፡፡ ይኼንንም ባደረባቸው ሕመም ሆስፒታል ተኝተው ለሚታከሙ የሚቀርበውን የምግብ ዝርዝር ዓይቶ መናገር ይቻላል፡፡ ከሕክምናው ጎን ለጎን ለፈውስ የሚረዳቸውን የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት ጋር በተያያዘ ትልቅ ክፍተት እንዳለ ነው የሚነገረው፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኒውትሪሽን ባለሙያዋ ወይዘሪት ይርጋለም መንግሥቱ ይኼንን አስመልክተው እንደገለጹት፣ እስካሁን ድረስ በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ ሜኖ የለም፡፡ ለሁሉም የበሽታ ዓይነት የሚዘጋጅላቸው አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ምግብ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በተለየ ሁኔታ አንድ ታካሚ በሐኪም የታዘዘለትን ምግብ እንዲዘጋጅለት ይደረጋል፡፡

ይኼ ዓይነቱን የምግብ አቀራረብ በማስቀረት ወጥ የሆነ፣ ደረጃውን የጠበቀና ከሕክምናው ጋር ተያያዥነት ያለው ምግብ ለማቅረብ እንዲቻል አዲስ አበባን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች በተመረጡ 22 ጠቅላላ ሆስፒታሎች ውስጥ የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ ተሞክሮ በበጀት ዕጦት የተነሳ መስተጓጐሉን የገለጹት ባለሙያዎች፣ ጥናቱ በጀት ከተያዘለትና አስፈላጊው ነገር ሁሉ ከተሟላላት በኋላ በቀጣዩ ዓመት በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል፡፡

በጥናቱ ከተካተቱት መካከል ግን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተመጣጠነ ምግብ ሕክምና (ኒውትሪሽን ቴራፒ) አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት በማከናወን ላይ እንደሆነ የሚገልጽ ሪፖርት እንደደረሳቸውም ወይዘሪቷ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ግርማ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የኒውትሪሽን መምህርና ባለሙያ ሲሆኑ ወይዘሪት ብዙሐረግ ተካ ደግሞ የዚሁ ኮሌጅ የኒውትሪሽን ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያ ኮሌጁ እስካሁን ድረስ ባካሄደው እንቅስቃሴ የኒውትሪሽን ቴራፒ ዩኒት አቋቁሟል፡፡ አሁን ለጊዜው ሁለት ኒውትሪኒስቶች ተመድበዋል፡፡ ለኒውትሪሽን ሕክምና የሚውሉ ግብአቶችን እያደራጀና ሌሎች አገሮች በኒውትሪሽን የሚያክሙባቸውን የተለያዩ መስፈርቶችን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህም ሌላ ለኒውትሪሽን የሚያስፈልጉ የምግብ መገልገያ ዕቃዎች በሚገባ ተደራጅተው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከሚገኙት ዘመናዊ የወጥ ቤት ዕቃዎች መካከል አንዱ ምግብ የሚበስልበትን፣ የሚቀቀልበትንና የሚፈላበትን ዘመናዊ መሣሪያዎች የመገጣጠሙ ሥራ ተጠናቋል፡፡

በኒውትሪሽን ቴራፒ ዩኒት ለሚመድቡ የሕክምና ባለሙያዎችና ለወጥ ቤት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ለስኳርና ለልብ ታካሚዎች፣ በተለይም የኩላሊት ንቅለ ተከላና ዲያሊሰስ እጥበት ለሚያስፈልጋቸው ሕሙማን ሊቀርብላቸው የሚገባውን ምግብ የሚያመላክት መመሪያና ሜኖ ከተዘጋጀ በኋላ ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን የኒውትሪሸን ቴራፒ ሕክምና በሙከራ ደረጃ እንደሚጀመር ከባለሙያዎቹ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የውጭ አገሩን የኒውትሪሽን ቴራፒ አገልግሎት በአካል ተገኝተን ተሞክሮ የመቅሰም ዕድል ባያጋጥመንም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃን፣ በየጊዜው በተደጋጋሚ እየተሻሻሉ የሚወጡት የዓለም አቀፍ የኒውትሪሽን ሕክምና ጆርናሎችና ሪፖርቶችን የመዳሰስ አጋጣሚዎች ወይም ዕድሎች አሉ፤›› ብለዋል አቶ ተስፋዬ፡፡

ኮሌጁ የኒውትሪሽን ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መንቀሳቀሱ አዲስ ነገር መሆኑ፣ ይኼ ዓይነቱ አገልግሎት በሌሎች የመንግሥት ሕክምና ተቋማት እስከዛሬ አለመሞከሩን እንዳረጋገጡ ወይዘሪት ብዙሐረግ ጠቁመው፣ ቴራፒው የሚሰጠው ተኝተው ለሚታከሙ ብቻ ሳይሆን በተመላላሽ የሚታከሙ ሕሙማንም እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በቤታቸውም የዚህኑ ዓይነት ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስችላቸውን የማማከር (ካውንስሊንግ) ፕሮግራም እንደሚጀመርም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...