ወዳጆቼ እንዴት ሰነበታችሁ? እኔ እዚህ በደስታ እየተብነሸነሽኩ እገኛለሁ፡፡ ይህንን የእኔን ደስታ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ እንዲገኝ እሻለሁ፡፡ የባሻዬ ልጅ እንዲያውም፣ ‹‹እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይ እንደ ባህል ሊያከብረው የሚገባው ቀን ነው በማለት ሲናገር አድምጬዋለሁ፤›› የባሻዬ ልጅ በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ በየፌስቡኩ ላይ ቢቻል ሁሉም ሰው ‹ፕሮፋይል ፒክቸሩን› በመቀየር ይህንን አገራዊ ባህል ሊያከብረው ይገባል እያለ ነበር፡፡ አክሎም፣ ‹‹መቼም ጫማ ቀየርኩ፣ ሸሚዝ ቀየርኩ፣ ቤት ቀየርኩ… እያሉ ፌስቡክ ገጻቸው ላይ ሲለጥፉ የነበሩ በሙሉ ዛሬ ደግሞ አገር መሪን የሚያህል ነገር ስትቀይር ወይም አዲስ መሪ ሲመጣልን፣ ያውም ያለምንም የደም መፋሰስ፣ ያውም ያለ ዘር አድልኦ ይኼንን እንደ በዓል ማክበር ይጠበቃል፤›› አለ፡፡
ባሻዬ በደስታ የሚያደርጉትን አሳጥቷቸው፣ ‹‹ይህ ትንሳዔ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከትንሳዔ በፊት ልናከብረው የሚገባ ትንሳዔ፡፡ የጥይት ድምፅ ሳንሰማ እንደዚህ ዓይነቱ የሽግግር ወቅት ላይ በመድረሳችን፣ ይህንን ዓለም በማየቴ ከዚህ በላይ የሚያስደስተኝ አንዳችም ነገር የለም፡፡ አሁን ብሞትም አይቆጨኝም፤›› አሉ፡፡ ባሻዬ የደስታቸው ብዛት እንደ ጦር የሚፈሩትን ሞት እንኳን እንዲደፍሩት አድርጓቸዋል፡፡
ባሻዬ ሁልጊዜም ቢሆን የሚያቆስላቸው ነገር አፍሪካውያን መሪዎች ወደ ሥልጣን የሚመጡበት መንገድ ነው፡፡ እንዲያውም አብዛኞቹን መሪዎች፣ ‹‹እነዚህ የደም መንገደኞች!›› እያሉ ሲራገሙ የታላቋ ኢትዮጵያ መሪ በሰላም ወንበሩን ለቆ ሌላኛው መሪ ወደ ሥልጣን መምጣቱ እጅግ እያስፈነጠዛቸው ነው፡፡ ‹‹ብሞትም አይቆጨኝ! ለዘመናት ስጠማው የነበረውን ነገር በሠለጠኑት አገሮች ዓይቼ ስቀናበት የነበረውን ነገር አገሬ ላይ ማቆጥቆጥ መጀመሩን ስመለከት፣ ከዚህ በላይ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም፤›› ይላሉ፡፡ ባሻዬ የፀሎት ርዕሳቸው ሳይቀር ተቀይሮ አዲሱ ፀሎታቸው ‹‹ባሪያህን አሰናብተኝ›› የሚል ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ልጃቸው በፀሎታቸው ባይስማማም፡፡
‹‹አባቴ ገና ምኑን አይተህ ነው ሞት የተመኘኸው? ይህ እኮ ሁልጊዜ ልናያት የምናስባት የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ጅማሮ ነው፡፡ ገና ባንተ ዕድሜ ልታያቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ሁልጊዜም የሚያሳምምህ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተሰገሰገው ሙስና አክትሞለት ሳታይ አትሞትም፡፡ ዘረኝነት ከምድራችን ላይ ተወግዶ ሕዝቦቿ ሁሉ የሚኮሩባትና የሚመኩባት አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያ ተመሥርታ ሳታይ አትሞትም፡፡ የአንድ ወገን የበላይነትና የሌላው የበታችነት የሚታይበት አሠራር ተወግዶ ኢትዮጵያ የሚል ሰንደቅ በአየሩ ላይ ብሎም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ሳታይ አትሞትም…›› እያለ አባቱን ሲያነቃቃ ቆየ፡፡
እኔም ደላላው አምበርብር ምንተስኖት የባሻዬ ልጅ በሳል ምክር ነክቶኛል፡፡ ስለዚህ ይህንን የአቋም መግለጫ እንዳወጣ ሆኛለሁ፡፡ አዲስ መሪ በሰላማዊ መንገድ ከመመረጡ ማግሥት እነዚህን ነገሮች ሳላይ አልሞትም የሚል የአቋም መግለጫዬን በመላው የደላሎች ማኅበር ስም እገልጻለሁ፡፡ ዘረኝነት ተወግዶ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ የሚውለበልብላትን ኢትዮጵያ ሳላይ አልሞትም፡፡ ለሚመጣው ትውልድ ፍቅርን፣ ሰላምንና መቻቻል አውርሰን ልጆቻችን በፍቅር ሲኖሩ ሳላይ አልሞትም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ፈለገበት የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋውሮ ያለምንም ገደብ ሲሠራ፣ ሲያገባ፣ ሲወልድ፣ ሀብት ሲያከማች ሳላይ አልሞትም፡፡ የደላሎች ማኅበር ካወጣው የአቋም መግለጫ ውስጥ ጥቂቱን ብቻ መርጬ ወደ እናንተ እንዳደረስኩ ልብ በሉልኝ፡፡
በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ ምን ማለት እንደሆነ ባይገባኝም እንደዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ፔሲሚስቶች›› ናቸው እያለ ሲቃጠል ነበር፡፡ እኔም ትንሽ እንዲያብራራልኝ ወሰወስኩት፡፡ ‹‹እነዚህ መልካም ነገርን ለማየት ዓይኖቻቸው የታወሩባቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ለጥ ካለ ሜዳ ላይ ገደል የሚመለከቱ፣ ፍጹም ከተረጋጋ ሰላም ውስጥ ጦርነትን የሚያነፈንፉ፣ ከብርትኳን ዛፍ ላይ ኮምጣጤ የሚያወርዱ አመፅና ክፋት ብቻ የሚታያቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ይሰውረን ማለት ነው፡፡ ከውኃ ውስጥ እሳትን የሚመለከቱ ፍጡሮች ናቸው፡፡ እኛ የምንፈልገው ከደረቅ ምድረ በዳ ውስጥ ለምለም ኢትዮጵያን የሚመለከትን ዓይናማ የሆነውን ነው፡፡ አይጣልባችሁ እነዚህ ሰዎች ከኤደን ውስጥ ደረቅ ምድረ በዳ የሚመለከቱ ፍጡሮች ናቸው፤›› ብሎ የባሻዬ ልጅ አጫውቶኛል፡፡
ወዳጄ በእኔ ዕድሜ እንኳን ወደ አራት መሪዎችን ተመለከትኩ እኮ፡፡ ይህ አፍሪካ ውስጥ የማይታሰብ ጉዳይ ነበር፡፡ አንድ ሰው ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሥልጣን በማይለቅባት አኅጉር፣ ይህንን በማየቴ ምን እፈልጋለሁ? መቼም የትኛው ባለመረጋጋት ውስጥ ያለው አገር ሁኔታ ለእኛ ምሳሌ መሆን ባይችልም ብልህ ከሰነፍ ይማራል እንዲሉ የእነሱን አገር ውጥንቅጥ በምንም መንገድ አገሬ ላይ እንዳላሁ ከባሻዬ ጋር አብሬ በፀሎት ተግቻለሁ፡፡
የባሻዬ ልጅ ሥልጣናቸውን ያስረከቡትን ጠቅላይ ሚኒስትር አመሥግኖ መጨረስ አልቻለም፡፡ ‹‹ምክንያቱ ደግሞ ለዚህች አገር ሰላም፣ መረጋጋትና ብልፅግና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይ ደግሞ በሁሉም ረገድ ሥልጣን ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እሳቸው በነበራቸው ኃላፊነት ያደረጉት ነገር ሊመሠገን የሚገባው ነው፡፡ በሰላምና በፈቃደኝነት ሥልጣናቸውን ከመልቀቅ የበለጠ አንድ ታላቅ መሪ ከዚህ የበለጠ ውለታ ለአገሩ ምን ሊውል ይችላል?›› በማለት ሲያሞጋግሳቸው ነበር፡፡
የባሻዬ ልጅ አክሎም፣ ሁልጊዜም ቢሆን ወደፊት መንደርደርን ስናስብ የኋላችንን እየናድን መሆን የለበትም፡፡ የቀድሞው መሪ ያልነበሩ ያህል መቆጠር የለባቸውም፡፡ ይልቁንም እንደ ኢትዮጵያ ባለውለታ ሊቆጠሩ ይገባቸዋል፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ለአገራቸው ከመሥራት አንድም ቀን ቦዝነው ስለማያውቁ፡፡ ስለዚህ አዲስ ለመገንባት ስንነሳ የቀደመውን ማፍረስ ወይም እንዳልነበረ መቁጠር አሁን ለምንገነባው ግንባታ ምንም ዓይነት ጥቅም ስለሌለው፣ በተመሠረቱ ነገሮች ላይ ደግመን ሌላ አንመሠርት፣ ይህም ማባከን ነውና፡፡ ያለፉት መሪዎቻችንን ጥረትና መልካምነት ላይ ውኃ አንቸልስበት…›› የሚል የደላሎች ማኅበር ካወጣው የአቋም መግለጫ የማይተናነስ ነገር ሲገልጽ ካደመጥኩት ውስጥ ነው ጥቂቱን ወደ እናንተ ያደረስኩት፡፡
ከዚህ በመቀጠል እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እንዲሁም ወደ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ባሻዬና የባሻዬ ልጅ፣ ታማኙን ውሻዬን ጨምሮ፣ እነሆ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያለንን ታላቅ ፍቅርና አክብሮች ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ በርካታ ኃላፊነቶች በጫንቃዎ ላይ እንደሚወድቁ በማመን የተቻለዎትን ሁሉ ጥረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ጊዜዎትን እንዲያጠፉልን፡፡ ሙስናን በተቻለዎት አቅም ሁሉ ከኢትዮጵያ እንዲሸኙልንና በየመሥሪያ ቤቱ ማግኘት የሚገባንን አገልግሎት ኢትዮጵያውያን ስለሆንን ብቻ በደስታ እንድናገኝ ያድርጉ፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን እንድንጠላ ካደረጉን አንዳንድ አሠራሮች ገላግሉን፡፡ ሙሰኞችን ወደ ፍርድ መንበር ላኩልን፡፡
የቀድሞው ጠቀላይ ሚኒስትር የጀመሩትን የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ አደራ ጨርሱልን፡፡ እልቅ ብሎልን የሚሸጠውን ያህል ኃይል ሸጠን በሚቀርልን እኛም በመብራት እንንበሽበሽ፡፡ የመብራት ጋርደን ሠርተን እንደሰት፡፡ ከምናበራት አምፖል አልፈን በመብራት ወደ ምንዘንጥበት ዘመን አሻግሩን፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊነታችን አኩሩን፡፡ ሞት ይርሳኝ በተለይ የስደትን ጉዳይ የተማረውም ያልተማረውም እኮ ነው እያስመረረ ያለው፡፡ የተማረው መማሩን እየረገመ፣ ያልተማረውም አለመማሩን እየረገመ ይህችን አገር እየረገመ እንዲኖር ያደረገውን አሳዛኝ አስተሳሰብ ድራሹን አጥፉልን፡፡
ዛሬ የደስታችን ቀን ነው፡፡ ችግር ውስጥ ስንወድቅ ብቻ በየሚዲያው ላይ የሚጥዱን ዛሬ ይቁረጣቸው፡፡ እኛም ዘመን መጥቶልን መሣሪያ አስቀምጠን ማውራትና መግባባት ጀምረናል፡፡ እንዲያው እኔ ደላላው አምበርብር ምንተስኖት ከተማውን ዞር ዞር ብዬ ስመለከተው ሁሉም ሰው ፊት ላይ ያነበብኩት ደስታ የሚያስገርም ነው፡፡ ትንሹ፣ ትልቁ፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ እናቱ ከገበያ እንደተመለሰችለት ሕፃን እየቦረቀ ነው የሚገኘው፡፡ አዲሱ መሪ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደተቀበላቸው መገንዘብ ችያለሁ፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይም በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ክቡር ሆይ የተቃናና የተሳካ ዘመን እንዲሆንልዎት ቤተሰባዊ ምኞታችን ነው፡፡ እስከ ዛሬ ላዩት ዘርፈ ብዙ ችግር ምነው እኔን በላከኝ እያሉ መቆየትዎትን እንጠራጠራለን፡፡ ይኸው አሁን ተልከዋል ታላቅ ዓላማን አንግበው፡፡ ይኸው እንደ ሙሴ በትሩ በእጅዎት ይገኛል፡፡ እባክዎትን በድፍረት ባህሩን ይክፈሉልን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእርስዎ ላይ ታላቅ እምነት አሳድሯል፡፡ እንዲያኮሩን እንማፀናለን፡፡ የእኛ ናቸው ብለን እንድንመካብዎት እንዲያደርጉን እንማፀናለን፡፡ ሺሕ ዓመት ለማንኖረው ፍርኃትን አስወግደው ወሳኝ ውሳኔዎችን በመስጠት ልቡ ተንጠልጥሎበት ያለውን ኢትዮጵያዊ እንዲያሳርፉልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ባሻዬ ደግሞ እንዲህ በማለት ነበር የተነሳሱት፡፡ ‹‹እናቴ ኢትዮጵያ እንኳን ደስ ያለሽ፡፡ አሁን ማቅሽን ቀደሽ ከአመድ ላይ ተነስተሽ የምትቦርቂበትና የምትስቂበት ሰዓት ደርሷል፡፡ ሐዘን ምሬትሽ ተወግዶልሻል፡፡ እንባሽም ይታበስልሽ ዘንድ ንፁህ ጨርቅ ተዘጋጅቶልሻል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እንሂድ የሚባልባት ዘመን እነሆ በደጅ ነው፡፡ በምድር ዙሪያ ያሉ ሰዎች እኛ ዘንድ ያለው ሰላም፣ መረጋጋትና ብልፅግና ማርኳቸው፣ የተወለዱበትን ትተው፣ እንዲሁም ምሬት አንገሽግሿቸው አገራቸውን ጥለው የወጡ ሁሉ በአገራቸው እየተፈጠረ ያለውን ብልፅግናና አንድነት ተመልክተው ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ ‹‹ኑ ወደ ኢትዮጵያ እንሂድ›› የሚሉበት ዘመን እነሆ ይጀመር…›› በማለት፣ የኢትዮጵያ እውነተኛው ህዳሴ አሁን ገና ነው የጀመረው በማለት በርካታ ነጥቦችን አስቀምጠው አብራሩ፡፡
እኔም አምበርብር ምንተስኖት የባሻዬን ሐሳብ ደግሞ ወደዚያች ሰላም እንደ ዥረት ወደሚንቆረቆርባት፣ ብልፅግና የእያንዳንዱ ግለሰብ ዕጣ ፈንታ ወደሆነባት፣ መቻቻልና መቀባበል የእያንዳንዱ ግለሰብ መታወቂያ ወደሆነባት፣ ዘረኝነት ዘሩ ወደ ጠፋባት፣ ሙሰኝነት ደብዛ ቢስ ወደሆነባት፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ ወደሚከበርባት ወደ ታላቂቷ ኢትዮጵያ እንሂድ ወደሚባልበት ዘመን እንኳን ደህና መጡ… እያልኩ የዛሬን ልሰናበት! መልካም ሰንበት!