Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየከበደው ጥላ

የከበደው ጥላ

ቀን:

የትምህርት ጊዜው ተጠናቆ ወደ የቤታቸው ሊበታተኑ ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተዋል፡፡ እንደሌሎቹ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በርካታ ተማሪም ሆነ የመማሪያ ክፍሎች የሌሉት ይህ ትምህርት ቤት ሃያ ሁለት ማዞሪያ ከጌታሁን በሻህ ሕንፃ ወረድ ብሎ ነው የሚገኘው፡፡ ተማሪዎቹም በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም መማር የማይችሉ ‹‹የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት›› ያለባቸው እንደ ሕይወት (ስሟ ተቀይሯል) ያሉ የሚማሩበት ነው፡፡

      ቀልጣፋና ተግባቢዋ ሕይወት ያገኘችውን ሁሉ በትህትና ጎንበስ ቀና ብላ ሰላምታ መስጠት ትወዳለች፡፡ የለበሰችው ረዘም ያለ የድሮ ፋሽን ሽንሽን ቀሚስና ከላይ ጣል ያደረገችው መደረቢያ ክምክም ተደርጎ ከተበጠረው አፍሮ ፀጉሯ ጋር የራሷን የተለየ ዘዬ (ስታይል) ፈጥሮላታል፡፡ አጠቃላይ ሁኔታዋና ያላት በራስ መተማመን በክፍሉ ውስጥ የተሰባሰቡ ተማሪዎችን የምትገራ ጠንካራ መምህር ያስመስላታል፡፡ ነገሩ እንዴት ነው የሚሉት ቀላል ጥያቄ ለመመለስ ስትደነጋገር ነው፡፡

      ሕይወት ዕድሜዋ ስንት እንደሆነ አታውቅም፡፡ እንዲህ ያሉ መልሳቸውን የማታውቃቸውን ጥያቄዎች የምትመልስላት አስተማሪዋ ነች፡፡ 30 ዓመት እንደሞላት አስተማሪዋ ነገረቻት፡፡ ነገር ግን ገና ጽሑፍ በመማር ላይ የምትገኘው ሕይወት 30 ከቁጥር በዘለለ ምኗም አይደል፡፡ ለሚያዩዋት ትልቅ ትምሰል እንጂ የአሥር ዓመት ታዳጊ ያለውን ያህል ብስለት እንኳ የላትም፡፡ የኖረችባቸው 30 ዓመታት በውጣ ውረድ የተሞሉ ቢሆኑም አንዳቸውም ብልጥ አላደረጓትም፡፡ ሌላው ቢቀር እየተጠቋቆሙ የሚሳለቁባትን እንኳ እንድትሸሽና እንድትጠላቸው አልገፋትም፡፡ ሁሉም ተቀባብሎ እንደሚያሳድገው ድክ ድክ እንደሚል ሕፃን አዕምሮዋ ንፁህ ነው፡፡

- Advertisement -

      አምርራ የምትጠላው ሰው ቢኖር ከትምህርት ቤት ስትመለስ ከመንገድ ጎትቶ ቤቱ አስገብቶ የደፈራትን ሰው ብቻ ነው፡፡ ሕይወት እንዲህ ያለ ግፍ የፈጸመባት ግለሰብ የምታውቀው የሠፈር ሰው እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ሰው ሲመጣበት ለቀቀኝ፡፡ ከዚያም ሮጬ ከግቢው ወጣሁ፤›› ትላለች እርግጠኛ መሆን እያቃታት፡፡ ስለዚህ ክፉ አጋጣሚ ስትናገር ሁሉ ነገር ድንግርግር ይላታል፡፡ አብራው ብዙ የኖረች ያህል ይሰማታል፣ ወዲያው ደግሞ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብቻ አፍኖ እንደያዛት ትናገራለች፡፡

      የምትናገረውን አታውቅም ብሎ በሚያምን ማኅበረሰብ ውስጥ የሕይወት እርግጠኝነት የራቀው ንግግር ዋጋ የለውም፡፡ ‹‹ምንድነው የምትለው?›› ብሎ ጆሮ የሚሰጣትም ከስንት አንድ ነው፡፡ ልብ የሚሏት መምህሮቿ እንዲሁም መሰል ጓደኞቿ ናቸው፡፡ መደፈሯን ስትነግራቸው ያላመኗት እናቷ አስመርምረዋታል፡፡ ነገር ግን ውጤቱ በትክክል መደፈሯን የሚያረጋግጥ ቢሆንም ግለሰቡ አልተከሰሰም፡፡ ‹‹ፖሊስ አልነበረማ ስደፈር፡፡ ስለዚህ አልታሰረም፡፡ አሁን ሌላ ሴት ጠልፏል፤›› አለች ሕይወት ክብሯን አዋርዶ በነፃነት እንዲኖር የተፈቀደለትን ግለሰብ ነገር ስታነሳ፡፡

      ጊዜ ጊዜን እየተካ ወራት ተቆጠሩ፡፡ ሕይወትም ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ወደ ትምህርት ገበታዋ ተመለሰች፡፡ የሕይወት ሆድ ግን እየገፋ ሄደ፡፡ ይሁንና ማንም ግን ልብ አላለውም፡፡ ሕይወት እንኳን በአካሏ ላይ የተፈጠረው እንግዳ ነገር ምን መሆኑን አላወቀችም፣ እንዲያውም ልብ አላለችውም ነበር፡፡ አንዳንድ ጓደኞቿ ግን ሆዷን እየነኩ ይቺ ልጅ እርጉዝ ነች እያሉ አንድ ያጠፋቸው ነገር እንዳለ ሁሉ ለአስተማሪ ይነግሩባት ነበር፡፡ እርግዝና ምን መሆኑን የማታውቀው ሕይወት ግን አብራቸው ከመሳቅ በዘለለ ምንም አትልም ነበር፡፡

      ‹‹ቲቸር ይቺ ልጅ እርጉዝ ነች ሲሉን አንድ ቀን እስኪ ብለን አየናት፣ እውነትም አርግዛለች፡፡ የሚገርመው ቤተሰቦቿ አያውቁም ነበር፡፡ እኛ ነን ጠርተን የነገርናቸው እርግዝናዋ ገፍቶ ስለነበር ማስወጣት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እናቷ ይወለድ አለች፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ አዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ወ/ሮ የሸዋጌጥ ክብሩ ናቸው፡፡

      ሕይወት ከማንኛውም ሰው ባልተለየ መልኩ የምታያት ልጇ ከተወለደች ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ያልበሰለ አዕምሮ ያላት ሕይወት ግን እናትነት ምን እንደሆነ የምታውቀው የላትም፡፡ ልጅሽ ነች ሲሏት ሰምታ ልጅ አለኝ ትላለች፡፡ አነጋገሯ ግን ልጅ የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለበት ሰው ሳይሆን አሻንጉሊት እንደተገዛላት ሕፃን ነበር፡፡ ለነገሩ እሷም ሆነ ልጇን የማሳደግ ኃላፊነቱን ወስደው አብረው በድህነት የሚቸገሩት   ወላጆቿ ናቸው፡፡

      የሕይወት ወላጆች ካዛንችስ አካባቢ ከሚገኘው ሠፈሯ ተነስታ  22 ማዞሪያ ከጌታሁን በሻህ ሕንፃ ወረድ ብሎ ወደ ሚገኘው ትምህርት ቤቷ የምትሄድበት የታክሲ የመክፈል አቅም እንኳ ያላቸው አይደሉም፡፡ ትምህርት ቤቷ እስክትደርስ መንገዱ ከሥጋት ነፃ አይደለም፡፡ እየተጠቋቆሙ ከሚስቁባት፣ ለምን አየንሽ ብለው ከሚያባርሯት ውጪ ለዱላም የሚጋበዙ ብዙ ናቸው፡፡ ጭር ባለ ሰዓት  መንገድ ላይ ስትንቀሳቀስ የሚያገኟት ደግሞ ሴትነቷን ሽተው ዳግምኛ ክብሯን ሊያዋርዱ ይቃጣቸዋል፡፡

      ሌላዋ የ32 ዓመቷ መዓዛ (ስሟ ተቀይሯል) ነች፡፡ እሷም እንዲሁ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት አለባት፡፡ እንደ ሕይወት ሁሉ ሕይወቷ በፈተና የተሞላ እንቅስቃሴዋ ሁሉ በሥጋት የታጀበ ነው፡፡ የምትኖረው መገናኛ ሾላ አካባቢ ነው፡፡ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች የምታስበው መዓዛ በምን አጋጣሚ ወደ ማኅበሩ እንደመጣች ስትናገር ‹‹የፀሐይ ብርሃን አንፀባረቀብኝና ታመምኩ፡፡ ከዚያ ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ ፀበልም ሞከርን እምቢ ሲል ወደዚህ አመጡኝ፤›› አለች፤ ስላለችበት ሁኔታ አድበስብሰው የነገሯትን እውነት ስትናገር፡፡

      ምንም እንኳ ራሷን ችላ መንቀሳቀስ የሚከብዳት ባይሆንም የምትወጣውና የምትገባው በወንድሟ ወይም በእህቷ አጀብ ነው፡፡ አለዚያ ግን በሰላም ገብቶ መውጣት ከባድ ይሆናል፡፡ የከፋ ነገር ባያጋጥማት እንኳ የሚሰድባት፣ የሚያራሩጣት አይጠፋም፡፡ ስቀውባት የሚያሸማቅቋትም ብዙ ናቸው፡፡ ከሾላ እስከ 22 የምታደርገው ጉዞ በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማቋረጥ ያህል ከባድ ነው፡፡ ወንድምና እህቶች ግን ለሷ እንደ ቪዛ ናቸው፡፡ እጇን ይዘው ያደርሷታል፣ ይወስዷታል፡፡ ከእነሱ ጋር ስትሆን የት ነው የምትሄጂው ብሎ በየመንገዱ አስቁሞ የሚያፋጥጣት፣ ጥፊ ከዚህ ብሎ የሚያባርራት፣ የሚመታትም ሆነ ሴትነቷን ሊጠቀምበት ፈልጎ የሚጎነትላት አይኖርም፡፡

      አብዝተው የሚጨነቁላት በአንድ ወቅት የተፈጠረን ክፍተት ያስከተለው መዘዝ ነው፡፡ መዓዛ ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ብላ ነበር ከቤት የወጣችው፡፡ አንዱ ጠጋ ብሎ ነይ ብሎ መዓዛን አስከትሎ ወደ አንድ ቤት አመራ፡፡ መንገደኛ አያስጥላት ነገር መዓዛ ድረሱልኝ አላለችም፡፡ ሌላው ቢቀር አደጋ ያጋጥመኝ ይሆናል ብላ አልሠጋችም፡፡ ‹‹በሬ ከአራጁ ይውላል›› እንዲሉ ነይ ብሎ እጇን ሲይዝ ያልበሰለ አዕምሮዋ ምንም ሥጋት አላጫረባትምና ተከተለችው፡፡ ያለባትን የአዕምሮ ዕድገት ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ግለሰቡ መዓዛን ደፈራት፡፡ መደፈሯን ያወቁት ቤተሰቦቿ ነገሩን ዓይተው አላለፉም፡፡ ለሚመለከተው አካል አመልክተው ነበር፡፡ ይሁንና የመዓዛ ቃል ለምስክርነት የማይበቃ ነበረና የትም ሳይደርስ ተድበስብሶ ቀረ፡፡

      ተደፍራ የወለደቻት ሴት ልጇን የሚያሳድጉላት ታላቅ እህትና ወንድሟ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመዓዛ ልጅ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ የእናቷ ተደፍሮ እሷን መውለድ ምን ዓይነት የሥነ ልቦና ችግር ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በጉያዋ ሸሽጋ ልታሳድጋት የሚገባት እናቷ ከሷ የበለጠ ድጋፍ የምትሻና በማንኛውም ቅጽበት ህልውናዋ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ማወቋ የሚፈጥርባት ጭንቀትም በዚሁ መጠን አሳሳቢ ነው፡፡

      የአዕምሮው ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕፃናት፣ ታዳጊዎች፣ ወጣት፣ አዋቂና አዛውንት ሳይል ተመሳሳይ በደል፣ ጾታዊ ትንኮሳ ይደርስባቸዋል፡፡ ከባዱ ነገር የደረሰባቸውን ችግር ለመግለጽ ሲቸገሩ፣ ከገለጹም በኋላ የሚያምናቸው ሲጠፋ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር የሰደደው ‹‹የሚናገሩትን አያውቁም›› የሚል የተሳሳተ እምነት ሀቁን ቢናገሩም ጆሮ እንዳያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በጨዋታ መሀል እከሌ እንዲህ አደረገኝ ሲሉ አልያም ያደረጋቸውን በድርጊት ቢገልጹ ልብ የሚላቸው ባለመኖሩ በዝምታ ውስጥ ስንት ዓይነት ግፍ የዋሉ በነፃነት እንዲኖሩ ሆኗል፡፡

      ‹‹አፌን እንደዚህ በእጁ አፍኖ ወደ ጫካ ወስዶ ደፈረኝ፤›› አለች የተፈጸመባትን ድርጊት አኳኋን በድርጊት እየገለጸች፤ ንግግር ትንሽ ይከብዳታል፡፡ ሰዎች እንዳልተረዷት ስታውቅ ደጋግማ ይገልጽልኛል በምትለው ነገር ሁሉ ለመግለጽ ትሞክራለች፡፡ እንዳላመኗት ሲገባት ተስፋ እንደመቁረጥ ብላ ትቀመጣለች፡፡ መልሰው ሲጠይቋት ያንኑ ትደግምላቸዋለች፡፡ ከመሰል ጓደኞቿ ጋር በንግግር ለመግባባት ግን አትቸገርም፡፡ ማለት የፈለገችውን እንደ ራሷ ሆነው ይገልጹላታል፡፡ መደፈሯን ግን እነሱም አምነው አልተቀበሏትም፡፡ ስትደፈር የደረሰላት ምስክር የላትም፣ አልያም እንደሌሎች ጓደኞቿ አላረገዘችም፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የ23 ዓመቷ ሙሉእመቤት ተደፍሬያለሁ ስትል የምትሰጠው ቃል እንኳንስ በሕግ ፊት በጓደኞቿ ዘንድም ምሉዕነት የጎደለው የማያስተማምን ቃል ነው፡፡

የምትኖረው ደምበል አካባቢ ሲሆን፣ እሷም እንደ ሌሎች ጓደኞቿ 22 ማዞሪያ ወደሚገኘው ትምህርት ቤቷ ምትማርበት ድረስ የምትሄደው በእግሯ ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ጾታዊ ትንኮሳና ሌሎች በደሎች በመንገዷ ሁሉ ያጋጥማታል፡፡ የጓደኞቿ ትልቁ ሥጋታቸው ግን መደፈር ስለሆነ ሌሎች አያስጨንቋቸውም፡፡ የመደፈር አደጋ ያጋጠማት ምሽት ላይ ወደ ቤቷ እያመራች ነበር፡፡ ብቻዋን ስትንቀሳቀስ ያገኛት አንዱ ከመንገድ ዘወር ወዳለ አካባቢ ጎትቶ እንደወሰዳት፣ ልትጮህ ስትል አፏን አፍኖ እንደደፈራት ትናገራለች፡፡ ያን ዕለት ወደ ቤቷ የደረሰችው እኩለ ሌሊት አካባቢ እንደሆነ፣ መንገድ ላይ ያገኟት ሰዎች የታክሲ ከፍለው ወደ ቤቷ እንዳሳፈሯት ሁሉ ትናገራለች፡፡ የምትለው ምን ያህል እውነት እንደሆነ ያረጋገጠ ግን የለም፡፡ ‹‹ተደፈርኩኝ ትላለች፤›› እያሉ በጥርጣሬ ዓይን ያዩዋታል፡፡

      የኢትዮጵያ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር ቅጥር ውስጥ 110 ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ተማሪዎች መካከል አሥሩ መደፈራቸውን፣ ከነሱም ስድስቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ ሦስቱ ለደፈራቸው መውለዳቸውን፣ አራቱ ደግሞ በግብረሰዶማውያን የተደፈሩ ታዳጊ ወንዶች መሆናቸውን የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሸዋጌጥ ክብረት ይናገራሉ፡፡

ከተመሠረተ 23 ዓመታትን ያስቆጠረው ማኅበሩ በወላጆች የተመሠረተ ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ቅርንጫፍ ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹የኛ ልጆች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሸዋጌጥ፣ ከአባሎቻቸው መካከል ጥቂት የማይባሉ የተደፈሩ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ መደፈራቸው በእርግዝና ወይም በሌላ አጋጣሚ ያልታወቀላቸው ተደፍረው ዝም የሚሉ እንዳሉም ‹‹ሌሉቹ አለመደፈራቸውን በምንም ማወቅ አይቻልም፡፡ የነዚህ የታወቀውም ከጊዜ በኋላ አንዳንድ ምልክቶች ሲያሳዩ ነው፡፡ ቀርበን ብናናግራቸው የተደፈሩ ብዙ እንዳሉ ማወቅ ይቻልል፤›› ይላሉ፡

በጎረቤትና በቤተሰብ አባል ሲያልፍም ቤት ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት በሚቆዩ እንግዶች እየተደፈሩ ለሥነ ልቦና ቀውስና ለተለያዩ የጤና ችግሮች የሚጋለጡ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ብዙ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የኛ ልጆች እንደሌሎቹ ስሜት ያላቸው፣ የሚከፉና የሚያዝኑ አይመስላቸውም፤›› ይላሉ፡፡ ሕፃናት ወንዶችን ወደ ዘዋራ ቦታ ወስደው የሚደፍሩ ግብረ ሰዶማውያንም በዚሁ መጠን ናቸው፡፡

‹‹አንዱን ታዳጊ በላዳ ታክሲ አሳፍረው ሩቅ ቦታ ወስደው ተፈራርቀው ደፈሩት፡፡ ቀልጣፋ የነበረው ልጅ በዚህ ምክንያት በደረሰበት የሥነ ልቦና ቀውስ ከሌሎች መነጠል አበዛ፣ ዝምታን መርጦ በሐሳብ መተከዝ፣ ሰው መሸሽ መደናገጥና መደናበር ሲያበዛ ክትትል ማድረግ ጀመርን፡፡ ቀርበን ማውራት ስንጀምር ሁሉንም ነገረን፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሸዋጌጥ መሰል አጋጣሚዎች በብዛት እንደሚያጋጠሙ ይናገራሉ፡፡ የደረሰባቸውን በአንደበታቸው መግለጽ ቢያቅታቸው በሥዕል ወይም በእንቅስቃሴ የሚገልጹ መኖራቸውን ወላጆች ልጆቻቸውን አተኩረው ማድመጥና መከታተል እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

ያለባቸውን ውስንነትና የሰውን አለመኖር ተገን አድርገው ግፍ የሚውሉባቸውን ሕግ ፊት ማቅረብ አስቸጋሪ ሲሆን፣ እነዚህም ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙት ግልጽ ነው፡፡

‹‹ወላጆች ልጄ ተደፈረ፣ ተደፈረች ብለው ለመክሰስ ብዙ ጊዜ ያንገራግራሉ፡፡ ከአንዳንዶች በቀር አደባብሰው የሚያልፉ ብዙ ናቸው፡፡ ክስ ከተመሠረተ በኋላም የሚያቋርጡ ብዙ አሉ፡፡ ተከሳሾች ብዙ ጊዜ በሽምግልና ለመጨረስ የሚያደርጉት ጥረት ይሳካል፤›› ይላሉ፡፡ ይህም በተጠቂዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እንዳይቀጡ የሚያደርግና ለሌሎችም መቀጣጫ እንዳይሆን ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡

‹‹እቺን ጠጣ፣ እችን ቅመስ እያሉ ልጆቹን ሱሰኛ የሚያደርጉ ሰዎችም አሉ፡፡ በዚህ መልኩ ለከባድ የአልኮልና የሲጋራ ሱስ የተጋለጠ ታዳጊ እኛ ጋር አለ፤›› በማለት ማኅበረሰቡ ለእነዚህ ታዳጊዎች በአንድ ወገን መልካም በሌላ ወገን ደግሞ አሉታዊ ነገር እያስተማረ እንደሚገኝ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...