Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሙዚቀኞች የቤት ሥራችንን እየሠራን አይደለም›› ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ

‹‹ሙዚቀኞች የቤት ሥራችንን እየሠራን አይደለም›› ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ

ቀን:

አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ድምጻዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ ወደ ሙዚቃ የገባችው በግምት የሃያ ዓመት ወጣት ሳለች ነው፡፡ እንግሊዝኛ ዘፈኖችን በማቀንቀን ሙዚቃ የጀመረችው ድምፃዊቷ፣ ሁለት አልበሞች ለቃለች፡፡ ፀደንያ በቅርቡ በኦል አፍሪካ ሚውዚክ አዋርድስ (አፍሪማ) ምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ ድምፃዊት ተብላ ተሸልማለች፡፡ ሦስተኛ አልበሟም በቅርቡ እንደሚለቀቅ ይጠበቃል፡፡ ስለ ሽልማቱ፣ አዲሱ አልበሟና አጠቃላይ ሥራዎቿ ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪማ የሙዚቃ ውድድር በምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ ድምጻዊት ዘርፍ አሸንፈሻል፡፡ ሽልማቱ ላንቺ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለሽ ታምኛለሽ?

ፀደንያ፡- ሙዚቃ ወይም ማንኛውንም ነገር ይዞ ውድድር ላይ መቅረብ፣ ሕዝቡን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውንና ማንነቱንም ወክሎ መቅረብም ነው፡፡ በተለይ ሙዚቃ ይህንን ያንፀባርቃል፡፡ ብዙ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አንዱ ስለ ሙዚቃችን ማንነት ምንነት መታወቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሙዚቃ በአፍሪካም ሆነ በዓለም እንድትታወቅ ያደርጋል፡፡ ቋንቋችንም ይታወቃል፡፡ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ለመተዋወቅ መንገድ ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ውድድሮች ላይ መሳተፍ በጥበቡ ያሉ ሰዎችንም ያስተዋውቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓመታት በፊት በኮራ ውድድር ላይም አሸናፊ ነበርሽ፤ መሰል ውድድሮች ላይም በጣም ትሳተፊያለሽ እንዴት ነው?

ፀደንያ፡- እንደ ኢትዮጵያዊ፣ ሙዚቃ ውስጥ እንዳለ ሙያተኛም ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ አገር ውስጥ መሥራቱ እንዳለ ሆኖ ከፍ ባለ ደረጃ ሙዚቃዬን ይዞ መውጣት አቅሜንም መለኪያ ነው፡፡ እስከዛሬ አግዶ ቁጭ ያደረገን ምንድነው የሚለው ጥያቄም አለ፡፡ እየተንቀሳቀስን ያለነው በኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ ያኔ ኮራ ከተሸለምኩ በኋላ በመሀል ዝግጅቱ ሲመጣ ሲቋረጥ ስለነበር ብዙም አልተሳተፍኩም፡፡ አፍሪማ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አንድ አካል ነው፡፡ ናይጄሪያ ለሦስት ዓመት ጨረታውን አሸንፋ እዛ ይካሄዳል፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት፣ የአገሪቱ ባህልና ቱሪዝምና ባለሀብቶችም የሚሳተፉበት ትልቅ ዝግጅት ነው፡፡ የአፍሪማን አዘጋጆች በሆነ አጋጣሚ ተዋውቄአቸው ነበር፡፡ በነሱ አነሳሽነት ባለፈው ዓመት ተወዳደርኩ፡፡ ዕጩ የነበርኩት ቪዲዮ ሳልክ በኦዲዮ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ዓመትም ተነሳሽነቱ ነበረኝ፡፡ ራስን በተወሰነ ደረጃ ገፋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ፍላጎት ስላለኝ ነው የማደርገው፡፡ ራሴን ማሳወቅ አለብኝ፤ አቅሜንም መግፋት አለብኝ፡፡ እኔን ስጠቅም ደግሞ ሙዚቃዬ፣ ባህሌንም ያሳውቃል፡፡ ኃላፊነት እንዳለብኝ ስለሚሰማኝ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ላይ መሳተፍ በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሙዚቃ አንፃር በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ተደማጭነት ውስን እንደሆነ ይነገራል፡፡ በስፋት ከሚደመጡ የምዕራብ አፍሪካን ሙዚቃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ትያለሽ?

ፀደንያ፡- ቅኝ ግዛት እንደ ጥሩ ነገር ባይወሰድም በፈረንሳይ ስር ለነበሩ የተወሰኑ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ሙዚቃቸው እንዲታወቅ በተወሰነ ደረጃ ረድቷል፡፡ ፈረንሳዮቹ ረዥም ጊዜ እዛ ከመቆየታቸውም አንፃር ሙዚቃቸውን በደንብ ያውቁታል፤ ተዋህዷቸዋል፡፡ ግንኙነቱም ስላለ ፌስቲቫል ላይ ይሳተፋሉ፡፡ በአገራቸው ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በፈረንሳይኛም ይዘፍናሉ፡፡ እኛ ጋ ያለው ባህል ዝግት ያለ ነው፡፡ በራሳችን ነገር ብቻ ነው የምንኖረው፡፡ የውጭ ነገር ብዙም እንዲመጣብን አንፈልግም፡፡ የራሳችንን ለማውጣትም ብዙ ግድ የለንም፡፡ ልምዱም የለንም፡፡ ብዙም ለውጥ አንወድም፡፡ ለውጥ ላይ ያለን አቋም አነስተኛ ነው፡፡ ዘመኑ ተቀይሯል፡፡ ሥልጣኔውም እንደሚታየው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሩጫና በሌሎችም ነገሮች እየታወቀች ነው፡፡ ሙዚቀኞች ግን የቤት ሥራችንን እየሠራን አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ የእኛ ድክመት ይመስለኛል፡፡ ሙዚቃው ወጣ እንዲል ብዙ አልገፋነውም፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ለማድረግ ከባድ ነገር አይጠይቅም፡፡ ፍላጎትና ጥረት እንጂ የተለየ ታሪክ የለውም፡፡ አንድ የስልክ ጥሪ ወይም ክሊክ ማድረግ ነው፡፡ ፌስቡክ የማይጠቀም፣ ኢሜይል የማይላላክ የለም፡፡ ስንፍና ይዞን ካልሆነ ፍላጎትና ጥረት ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ ብዙ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮች በኤምቲቪ አፍሪካና ቻናል ኦ ላይ አያለሁ፡፡ ለምሳሌ የዚህ ዓመት ኤምቲቪ አፍሪካ አዋርድ ላይ ከነበሩት 90 በመቶ የሚሆኑ ሙዚቀኞች አፍሪማ ላይ ነበሩ፡፡ ትንሽ ጎርጎር አድርጎ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ ፍላጎቱና ጥረቱ ካለ ቢያንስ በሁለት ዓመታት ይኼ ነገር ይለወጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ውድድሮች ለውጥ ያመጣሉ ብለሽ ታምኛለሽ?

ፀደንያ፡- ያመጣሉ፡፡ አምና የተሳተፍኩት፣ ዕጩ የሆንኩትም እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ በዚህ ዓመት ኃላፊነቱን ወስጄ ብዙ ዘፈኖች ልኬ ነበር፡፡ ዕጩ የሆነው አራት ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኞች ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ሔለን በርሔ፣ አቤል ሙሉጌታና እኔ ነበርን፡፡ እኔና ሔለን በአንድ ዘርፍ ነበር የምንወዳደረው፡፡ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሌሎችም ተሳትፈው ብዙ ዕጩ እንደማይ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ሦስተኛ አልበምሽ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ከቀደሙት ጋር እንዴት ታነጻጽሪዋለሽ?

ፀደንያ፡- ማነጻጸሩ ይከብዳል፡፡ የፈጠራ ሥራ እንደ ዕድሜ፣ አመለካከት፣ ዕውቀትና ሁኔታዎች ይቀያየራል፡፡ በመጀመሪያው አልበሜ ላይ ያለው በሁለተኛው የለም፡፡ በሁለተኛው አልበሜ ላይ የነበረው ሦስተኛው ላይ አይገኝም፡፡ አሁንም ፍቅር ላይ ነው የማጠነጥነው፡፡ የበለጠ ላይቭ መሣሪያዎችን ተጠቅሜአለሁ፡፡ የተወሰኑ ሙዚቃዎች ላይ ባህላዊ መሣሪያዎችም ተጠቅሜያለሁ፡፡ ትንሽ ዝግ ያሉ፣ ፈጠን ያሉም ሥራዎች አሉት፡፡

ሪፖርተር፡- በአልበሙ ከድምጻዊነት በተጨማሪ በምን ተሳትፈሻል? ገበያ ላይ የሚውለውስ መቼ ነው?

ፀደንያ፡- ዜማ በብዛት ሠርቻለሁ፡፡ ሙዚቃውን አሬንጅ ያደረገው አቤል ጳውሎስ ነው፡፡ ወጪውን በሙሉ እኔ ሸፍኜ ነው የምሠራው፡፡ ፕሮዲውሰር ነኝ ማለት ይቻላል፡፡ እየተነጋገርን፣ እየተመካከርን ነው የተሠራው፡፡ አብዛኛውን ዜማ እኔ ስለሠራሁ፣ ግጥምም ሳስገጥም በዚህ ላይ ብትገጥሙልኝ እያልኩ ሐሳብ ስለምሰጥ አልበሙ ስሜቴ ተንፀባርቆበታል፡፡ አልበሙ ለገና መውጣት አለበት፡፡ እኔ ራሱ ናፍቆኛል፡፡ ከተጠናቀቀ ቆይቷል፡፡ የቀረው ህትመት ብቻ ነው፡፡ ስፖንሰር ነበር ያዘገየው፡፡ አሁን ትንሽ ተስፋ አለ፡፡ ስፖንሰር ተገኘም አልተገኘም ግን ይወጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃዎችሽ ምን ዓይነት መልዕክት ማስተላለፍ ትፈልጊያለሽ?

ፀደንያ፡- ደስ የሚለኝ ፍቅር ነክ ጉዳይ ላይ መስራት ነው፡፡ ፍቅር ላይ ሆኖ ቀናነትን፣ ጥንካሬን፣ ልስላሴን የሚያሳዩ ዘፈኖች መሥራት እመርጣለሁ፡፡ አሉታዊ የሆኑትን መቸገር፣ መበደልና መሰቃየት ባላሳይና ደስ የሚል፣ ሰላማዊ ስሜት የሚፈጥር ሐሳብ ባንፀባርቅ እመርጣለሁ፡፡ ቃላት ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ የፈለገ አሪፍ ሐሳብ ቢሆን የሚገለፅበት ቋንቋ ይወስነዋል፡፡ ሲሰማ የሚያስደስት ነገር መሥራት ነው የምፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ካሉት ሥራዎችሽ መካከል በኤችአይቪ ኤድስ፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ያተኮሩት ይጠቀሳሉ፡፡ ማኅበራዊ መልዕክት ባላቸው ሙዚቃዎች ላይ በተደጋጋሚ ለመሳተፍ የሚያነሳሳሽ ምንድነው? ለማኅበረሰቡስ ምን አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል?

ፀደንያ፡- ስለ ማኅበራዊ ጉዳዮች መልዕክት ለማስተላለፍ ሙዚቃ በጣም ቀላሉ መንገድ ነው፡፡ ከሥነ ጽሑፍ፣ ከቴአትርና ከፊልም በቀረበ መልኩ እያዝናኑ በቀላሉ መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ የጥበብ ሰው ከማዝናናት ባሻገር እነዚህ ላይ መሳተፍ አለበት፡፡ ሐሳቦችን እያነሱ መልዕክት ማስተላለፍ እንደ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቴ መስሎ ስለሚሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡ ‹‹እሹሩሩ እማማ›› በማኅበረሰቡ ዘንድ አወንታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ‹‹ማለባበስ ይቅር›› ከታቀደለት ዓላማ የወጣበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ዘፈኑ በጣም ተወድዶ መጨፈርያም ሆኖ ነበር፡፡ እኔን ታዋቂ አድርጎኛል፡፡ አንዳንዶች ግን የሙዚቃው ቪዲዮ ላይ ለምን ይወቀጣል? ለምን ሰፌድ ይቀባበላሉ? ብለው ይጠይቁኝ ነበር፡፡ መልዕክቱን መረዳታቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ግጥሙ ኤችአይቪ የሚል ነገር የለውም፡፡ አናለባብስ፣ እንረዳዳ የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ያለመ ነው፡፡ ስለ እናቶች እንዲሁም ሕፃናትን ስለመመገብ የሠራናቸውን ሰው አሪፍ ነው የሚለው ከመልዕክቱ ተነስቶ ነበር፡፡ እነሱ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡ አንዳንዴ የአድማጩን ምላሽ መገመት አይቻልም፡፡ ‹‹መላ መላ›› በጣም ዝነኛ ነበር፡፡ ዘሪቱን ታዋቂ አድርጓል፡፡ ማስተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት ግን ሁሉም አድማጭ አላገኘውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሐረገወይን አሰፋ ጋር በጥምረት በሚዘጋጀው የሬዲዮ ዝግጅት ‹‹ዜማ ፍቅር›› ስለፍቅር ግንኙነቶች ምክር ትሰጣላችሁ፤ የፍቅር ግንኙነቶችን ታድገናል ብለሽ ትምኛለሽ?

ፀደንያ፡- ዝግጅቱ ቀለል ባለ መልኩ የሚቀርብ ነው፡፡ ምክሩ ከራሳችን ተሞክሮ ወይም ከምንሰማው ተሞክሮ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ቀን በቀን የማይገኙ ነገር ግን ቀላልና በፍጥነት ሊተገበሩ የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ሚስቴን አስቀየምኳት፣ ባሌ አኮረፈኝ ሌላም የሚሉ ይደውላሉ፡፡ ምክር ከሰጠን በኋላ ብዙዎቹ ይታረቃሉ፡፡ ደውለው ታርቀናል ይሉናል፡፡ የሚደውሉልን ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቤተሰብ ስለሚፈሩ፣ የሚያዋራቸው ስለሌለም ግራ ይገባቸዋል፡፡ ቀለል ያሉ፣ ጠንከር ያሉም የምንናገራቸው ነገሮች አሉ፡፡ የግል ስልክ ወስደው የሚያዋሩን ሰዎችም አሉ፡፡ ያን ያህል በትምህርት የበለፀገ ምክር አልነበረም የምንሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሽ የሙዚቃ ዝንባሌ ነበረሽ?

ፀደንያ፡- አልነበረኝም፡፡ የጀመርኩት አሥራ ሁለተኛ ክፍል ጨርሼ የቴክኒክ ኮሌጅ ከገባሁ በኋላ ነው፡፡ ከዛ በፊት ቤተሰብም ስለማይፈቅድ ለመወሰን ሃያ እስኪሞላኝ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ በእርግጥ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ስማር፣ የመዝሙርና ሃይማኖት ክፍለ ጊዜ ላይ በደንብ ስለሚያዘምሩን ደስ ይለኛል፡፡ ያ ግን የሙዚቃ ፍቅር መስሎኝ አያውቅም፡፡ በሙዚቃ መግፋት እንደምፈልግ ያወቅኩት ማመዛዘን ስችልና ቤተሰቤን መጋፈጥ እንደምችል የገባኝ ወቅት ነው፡፡ በሙዚቃ ከቤተሰብ ጋር ተጣልቻለሁ፡፡ አባቴ ደስ ያለው ኮራ ከተሸለምኩ በኋላ ነው፡፡ ፎከስ የሚል የእንግሊዝኛ ፕሮግራም ላይ ኢንተርቪው ሰጥቶ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቀኛ ለመሆን የወሰንሽበት አጋጣሚ እንዴት ነበር?

ፀደንያ፡- በመጀመርያ መሆን የማልፈልገውን ነገር አውቃለሁ፡፡ ‹‹ዘጠና ሥራዎች›› የሚባለውን ነገር ላለመሥራት የወሰንኩት ገና 12ኛ ክፍል እያለሁ ነው፡፡ ተቀጥሮ በመሥራትና በሌላም ራሴን ላየው አልቻልኩም፡፡ ያደረኩት አስፈሪው ነገር 12ኛ ክፍል አለማጥናቴ ነው፡፡ ኮሌጅ ወይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት አልፈልግም ነበር፡፡ ከዛ በኋላ አባቴን ለማስደሰት ቴክኒክ ኮሌጅ ገባሁ፡፡ ሙዚቃ ስሰማ የሚሰማኝ ደስታ አለ፡፡ የሚያስደስተኝን ማድረግ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ አባቴ በጣም የተማረ ሰው ነበር፡፡ በሕይወቱ ግን ደስተኛ አልነበረም፡፡ ከት ብሎ ሲስቅ ያየሁት እንኳን ጥቂት ቀን ነው፡፡ ሙሉ አቅሙን በሰጠው ነገር ደስተኛ እንዳልነበር አይቻለሁ፡፡ የሞተው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፡፡ እኔ ሕይወቴን ደስተኛ ሆኜ ማሳለፍ ስለምፈልግ የምወደውን ሙዚቃ መረጥኩ፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያ ዕርምጃሽ ምን ነበር?

ፀደንያ፡- ሜጋ ክሪኤቲቭ አርት ሴንተር ከመባሉ በፊት ደብረ ያሬድ ይባል ነበር፡፡ እዛ ኦዲሽን አደረግኩ፡፡ ሰኞ ተፈትኜ ዓርብ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ሜጋ እያለሁ ክለቦች እሠራ ነበር፡፡ የተወሰነ ዓመት ከሠራሁ በኋላ መስማማት ስላልቻልን ወጣሁ፡፡ ማታ አትሥሩ ይባል ነበር፡፡ እኔ አመፀኛ ነኝ፡፡  ቀን ሜጋ ማታ ክለብ እሠራ ነበር፡፡ ሳይፈቀድልኝም ውጪ እሄድ ነበርና በስተመጨረሻ ተባረርኩኝ፡፡ በክለብ ሥራ ስለተቋቋምኩኝ የሜጋን ደመወዝ የምወስደው ከቀናት በኋላ ነበር፡፡ ከወጣሁ በኋላ ቡፌ ዳላጋር፣ ኮፊ ሐውስ፣ ላየን ክለብ፣ ማክሲስና ፋየር ሐውስ በሚባሉ ክለቦች ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎች ክለብ መሥራት በተለይ ለሴቶች ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፤ አንቺስ እንዴት አገኘሽው?

ፀደንያ፡- ያን ያህል ዓመት ስሠራ ሳይመቸኝ ቀርቶ አያውቅም፡፡ ራሴን የምጠብቅበት መንገድ ነበር፡፡ ያን ያህል አልጠጣም፤ መጠጣት ካለብኝም ከሥራ በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ነው፡፡ ወንዳ ወንድም ስለነበርኩኝ ማንም የሚናገረኝ አልነበረም፡፡ ፊቴ ሁሌ እንደተኮሳተረ ነው፡፡ ብዙም ፊት ስለማልሰጥ አልደፈርም፡፡ ልመታቸው የምችል የሚመስላቸው ሰዎችም ነበሩ፡፡ ስስ መስሎ መታየት ነው ለአደጋ የሚያጋልጠው፡፡ በብዛት ክለብ የሚሠሩት ወንዶች ሆነው እኔ ብቻ ሴት ነበርኩ፡፡ ጥቃት ደርሶብኝ ግን አያውቅም፡፡ የአምስት ወር እርጉዝ ከሆንኩ በኋላና ከወለድኩ ከሁለት ዓመት በኋላ ክለብ መሥራት አቆምኩ፡፡ ከዛ በኋላ በጊዜ ተጀምረው በጊዜ የሚያልቁ ሥራዎች ላይ ማተኮር ጀመርኩ፡፡ ሁሌ ኮንሠርት ስለማይሠራ ክለብ ከሕዝብ ጋር የምገናኝበት መንገድ ነው፡፡ እንደ ማማስ ኪችን አነስ ያሉ ቤቶች ከታዳሚ ጋር በቅርበት ለመገናኘት ያስችላሉ፡፡ በዚህ መንገድ ከሕዝቡ ጋር ቢያንስ በሳምንት አንዴ ካልተገናኙ መራራቅ ይመጣል፡፡ እንደድሮው ብዙ ክለብ ባልሠራም በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ቀን እሠራለሁ፡፡ በሌሎች አገሮች በጣም ትልልቅ ሙዚቀኞች የሚጫወቱባቸው አነስ ያሉ ዝነኛ ቤቶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃ የጀመርሽው በእንግሊዝኛ ዘፈኖች ነበር፤ አሁንም በሙዚቃዎችሽ የእንግሊዝኛ ስንኞች ታክያለሽ፤ ተደማጭነቴን ያሰፋዋል ብለሽ ታምኛለሽ?

ፀደንያ፡- ምናልባት ያሰፋው ይሆናል፡፡ የማደርገው ግን ደስ ስለሚለኝ ነው፡፡ እደመጣለሁ ብዬ ሳይሆን በወቅቱ በፈጠረብኝ ስሜት ነው የምመራው፡፡ አዲሱ አልበሜ ላይ አንድ ሙሉ የእንግሊዝኛ ዘፈን አለኝ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባልደረባ የነበረው ተፈራ ‹‹ካምፕፋየር ኦን ማይ ቤድ ሳይድ›› የሚል ግጥም አሳየኝ፡፡ ለዘፈን አይደለም ቢለኝም ሙጥኝ ብዬ ወሰድኩት፡፡ ኬ አለን ጋር ሔጄ ዘፈን አድርግልኝ አልኩት፡፡ ዜማውና አሬንጅመንቱን ሠራልኝና ጥሩ አር ኤንድ ቢ ዘፈን ሆነ፡፡ ሙዚቃ በስሌት ሳይሆን በስሜት የሚሠራ ነው፡፡ የመጀመርያው ስሜት ደግሞ ሁልጊዜም ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃን እንዴት ትገልጭዋለሽ?

ፀደንያ፡- ለእኔ ሙዚቃ ነፃነቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሕይወትሽ ከገጠሙሽ ነገሮች ሙዚቃዬ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል የምትይው ሁነት አለ?

ፀደንያ፡- አሁን አሁን ፈጠራዬ ጨምሯል፡፡ ከምን ጋር ተያይዟል ብባል አላውቅም፡፡ ራሴን የመግፋት፣ ነገሮችን የመገንዘብ፣ ፍላጎቴን የማወቅ ይሁን የሌላ ባላውቅም ከ‹‹ሕመሜ›› በኋላ ፈጠራዬ ጨምሯል፡፡ ከዛም በፊት ሦስተኛ አልበሜን ልሠራ ሳስብ ዜማ መሥራት አለብኝ አልኩ፡፡ የተወሰኑ ዜማዎች ሠራሁ ግን አልጣሙኝም፡፡ አንድ፣ ሁለት እያልኩ ስቀጥል ግን ቀላል ሆነ፡፡ የ‹‹ሕመሜ›› ግጥም እጄ የገባው ድንገት ነበር፡፡ ከሠራሁት በኋላ በጣም ደስ ስላለኝ ሰው ደስ ይበለው ብዬ ለቀቅኩት፡፡ ስኬታማም ሆነ፡፡ ሰውም ሰምቶ ሲወደው ዜማ መሥራት አለብኝ አልኩ፡፡ ከዛ በኋላ ወሰንኩኝና ዜማ መሥራት ቀጠልኩ፡፡ የ‹‹ሀረየት›› ፊልም ማጀቢያ ‹‹የፍቅር ግርማ››ና ሌሎችንም ብዙ ዜማዎች ሠራሁ፡፡ ሌሎች ዜማዎቼ የምቀይራቸው ባይሆኑም ‹‹ሕመሜ›› እንደፈጠረብኝ ዓይነት ስሜት አይሰጡኝም፡፡ አዲሱ አልበሜ ላይ የአንድ ዘፈን ሙሉ ዜማ የሌላ ሰው ነው፡፡ የሁለት ዘፈን ዜማ በጥምረት ሠርቻለሁ፡፡ የቀሩትን ዜማዎች የሠራኋቸው እኔ ነኝ፡፡ አሁን ፈጠራዬን እየፈተሽኩ ያለሁበት ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃ ሕይወትሽ የገጠመሽ ትልቁ ፈተና ምንድነው?

ፀደንያ፡- ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም አልበም መልቀቅ ራስ ምታት እየሆነ ነው፡፡ ሕገወጥ ሥርጭቱ ቁጥጥር የለውም፡፡ አልበም ሽያጭ እስከዚህም ነው፡፡ በፍላሽ ይወሰዳል፡፡ ሬድዮ ዝም ብሎ ያጫውታል፡፡ የአዕምሮአዊ ንብረት መብትና የሮያሊቲ ክፍያ ገና አልተከበረም፡፡ ኢንዱስትሪውን ለማቆየት ያክል እየሠራን፣ መስዋዕትነት እየከፈልን ነው ያለነው፡፡ አልበም መልቀቅ ፈታኝ ስለሆነ ነው ሁላችንም ቆይተን አልበም የምናወጣው፡፡ መክሰር አለ፡፡ ገንዘብ የሚገኝባቸውን መንገዶች ማስተካከል አለ፡፡ ስፖንሰር ማፈላለግም አለ፡፡ እንደሚታየው ብዙ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ግን ሙዚቃ ውስጥ የሚገቡበት መንገድ ግልጽ አይደለም፡፡ አካሄዱም ልክ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ያንን ዕድል አያገኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሁኔታ አልበም መልቀቅ ያሠጋሻል?

ፀደንያ፡- ያው በኮንሠርት፣ በቱር ይገኛል፡፡ አልበሙ የግድ መውጣት አለበት፡፡ ብዙ ሰውም መቼ ነው የሚወጣው እያለ እየጠየቀ ነው፡፡ ለውጥ የሚመጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብዬ አስባለሁ፡፡ ዘፈን ከወጣ በኋላ በማንኛውም ቦታ ጥቅም ላይ ሲውል ሙዚቀኛው ገቢ የሚያገኝበት ሕግ አለ፡፡ ሕጉን የማስከበር ሒደት እየተሠራ ነው፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ያንን ሕግ የሚተገብረው ኮሌክቲቭ ማኔጅመንት ሶሳይቲ ይመሠረታል፡፡ በዲጄዎች፣ ለማስታወቂያ፣ ለፊልም፣ በመገናኛ ብዙኃንና በሌላ አገርም ሙዚቃው ቢጫወት ይከፈላል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ሙዚቃዎቻችን ይጫወታሉ፡፡ እንዴት ሲዲው እንደሚሸጥ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ይሸጣል፡፡ ኮሌክቲቭ ማኔጅመንት ሶሳይቲ ሲቋቋም ነገሮች እየተስተካከሉ ይሄዳሉ፡፡ እኛም የውጪ አገር ሙዚቃዎችን ስናጫውት እንከፍላለን፡፡ ቢያንስ አልበም ሽያጭ ላይ ብቻ አይተኮርም፡፡ ነጠላ ዜማም ቢወጣ ዘፈኑ በተጫወተ ቁጥር ይከፈላል፡፡ ያኔ የሙዚቃ አልበም ብቻ ሳይሆን ነጠላ ዜማ መሥራትም ራሱን የቻለ ገቢ የሚመጣበት መንገድ ይፈጠራል፡፡ ኢንዱስትሪውንም የበለጠ ያነቃቃዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አገር ውስጥ ወይም ውጭ ከነበሩሽ መድረኮች በጣም ደምቄበታለሁ ብለሽ የምትጠቅሽው የቱን ነው?

ፀደንያ፡- ውጪ ከተሳተፍኩባቸው ፌስቲቫሎች ዘጠና በመቶው የተሳካ ነው፡፡ በወርልድ ሚውዚክ ሪከርድስ በአማርኛ የተሠሩ ሙዚቃዎች የያዘውን አልበም ለማስተዋወቅ ከዓለም ክፍሎች ወደከፊሉ ተጉዘናል፡፡ ኮንሠርቶቹ በአጠቃላይ ስኬታማ ነበሩ፡፡ በደንብ የደመቅንበት፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በደንብ ያስተዋወቅንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ መዝፈን ብቻ ሳይሆን ወርክሾፖችም እንሰጥ ነበር፡፡ ያ ቅፅበት እኔም የደመቅኩበት ነው፡፡ ወቅቱ ልምድ ያዳበርኩበት፣ የአገሪቱን ሙዚቃ ያስተዋወቅኩበትም ነበር፡፡ በዛ ሁለትና ሦስት ዓመት ፕሮፌሽናል ሥራ እንዴት መሠራት እንዳለበት አይተናል፡፡ የመጀመርያው አልበም ሪከርድ የተደረገው እንግሊዝ አገር ነበር፡፡ ስለ ፐርፎርማንስ፣ መድረክ አያያዝ በየዕለቱ ነበር የምንማረው፡፡ በሙዚቃም ሆነ በምንም ሥራ ሁሌ ትምህርት አለ፡፡ በዛ ተሞክሮ ከሌላ ሙዚቀኞች ጋር መሥራት፣ ዓለም አቀፍ መድረክና ዓለም አቀፍ ሚዲያ ብዙ አያስደነግጠኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በጣም ትንሹና ትልቁ ክፍያሽ ስንት ነው?

ፀደንያ፡- ሜጋ ስሠራ 150 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡ እሱም መድረክ ስሠራ ነው፡፡ እንደኔ ደስተኛ ግን አልነበረም፡፡ ያኔ የነበረውን ደስታና ተስፋ መናገር አልችልም፡፡ በልጅነት ሳይሰማኝ ብዙ ነገር አሳልፌአለሁ፡፡ በ90 ብር ተከራይቼ የምኖርበት ትንሽ የጭቃ ቤት ነበር፡፡ ለእኔ እንደ ቤተ መንግሥት ነበር፡፡ የምንኖርበት እኔና ወንድሜ ነበርን፡፡ የዛ ቤት ፎቶ ቢኖረኝ ከየት ተነስቼ የት እንደደረስኩ ያሳይ ይሆናል፡፡ ከፍ ሲል እንደመድረኩ ከ30,000 እስከ 150,000 ብር ድረስ ተከፍሎኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያዝናናሻል?

ፀደንያ፡- ከመውለዴ በፊት በሳምንት አራት ቀን፣ ለሁለት ሰዓት ጂም እሠራ ነበር፡፡ ከወለድኩ በኋላ ልጆቹ ራሳቸው ሥራ ሆነዋል፡፡ ልጆቼ መንታ ናቸው፡፡ አሁን ትምህርት ቤትም ስለገቡ ወደ ስፖርት መመለስ እፈልጋለሁ፡፡ ስፖርት ውጥረት ማራገፊያም ነው፡፡ ፊልም ማየት፣ ከልጆቼ ጋር መሳቅ መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ራሴን ለማስደሰት ያን ያህል ብዙ ነገር አያስፈልገኝም፡፡ በሕይወቴ እየተደሰትኩ ስለሆነ ተጨማሪ ነገር ባይኖርም ግድ የለም፡፡ አንድ ዜማ ሠርቼ የሚፈጠርብኝ ደስታ ያረካኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ አልበምሽ ይወጣል በተያያዘስ ያቀድሻቸው ነገሮች አሉ?

ፀደንያ፡- ኅዳር 16 የምሥጋና ኮክቴል አለኝ፡፡ በውድድር ሒደቱ ላይ ብቻዬን አልነበርኩም፡፡ ሚዲያዎች ዘፈን በመልቀቅ፣ ምረጡ በማለትና ኢንተርቪው በማድረግ ተባብረዋል፡፡ ሌሎችም ብዙ የተባበሩኝ ስላሉ ለማመስገን የተዘጋጀ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...