ባለፈው ዓመት የካቲት አጋማሽ ላይ በጉለሌ ቦታኒክ ጋርደን ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከስድስት ቶን በላይ የሚሆን የዝሆን ጥርስ በተቃጠለበት ወቅት፣ ከባቢ አየር ውስጥ የተጨመረውን ካርቦን በመምጠጥ የሚያካክሱ 90 ሺሕ የዛፍ ችግኞች ዘንድሮ እንደሚተከሉ፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባሥልጣን የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ዝውውር ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር አስታወቁ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ዳንኤል ጳውሎስ እንደገለጹት፣ ችግኞቹ የሚተከሉት በቅጥር ጊቢው በሚገኘው 30 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ ችግኞችን የማፍላትና ቦታውን ለተከላ የማመቻቸት ሥራ በመከናወን ላይ ነው፡፡
የዝሆን ጥርሱን በማቃጠል ለማስወገድ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ጊዜ ከቃጠሎው የሚወጣው ካርቦን በኢንቫይሮመንት ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚረዱ ሦስት ዘዴዎች በአማራጭነት ቀርበው ነበር፡፡
አንደኛው ዘዴ ካርቦኑን የሚመጡ የዛፍ ችግኞችን መትከል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጥርሱን በመፍጨት እንዲወገዱ ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው ዘዴ ግን በቃጠሎው ሳቢያ ወደ ከባቢ አየር የተጨመረውን ካርቦን ለማካካስ፣ በአደስ አበባ የሚገኙ የግል ተሽከርካሪዎች በሙሉ ለሦስት ወይም አራት ቀናት ቆመው በምትካቸው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችና ታክሲዎች ብቻ እንዲንቀሳቀሱ የሚል ነው፡፡
ከተጠቀሱትም ዘዴዎች መካከል የመጀመሪያው ዘዴ ተቀባይነትን በማግኘት በተያዘው በጀት ዓመት 90ሺሕ የዛፍ ችግኞች እንደሚተከሉ አቶ ዳንዴል ተናግረዋል፡፡ የዝሆን ጥርሱ በተቃጠለበት ወቅት፣ 79 የሚጠጉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን፣ ይህም ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የዝሆን ልማትና ጥበቃ ሥራ የገንዘብ ዕርዳታ ለማድረግ ቃል እንዲገቡ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በገቡትም ቃል መሠረት የሚለግሱት ገንዘብ እየተሰበሰበና በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሒሳብ ቁጥር ገቢ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ገቢ የተደረገውን መጠን በተመለከተ አሁን ላይ የተሟላ መረጃ ለመስጠት ገና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዝሆን ጥርሱ እንዲቃጠል ያደረገችው ሕልውናቸው በአስጊ ደረጃ ላይ በሚገኙ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ዓለም አቀፍ ንግድ ስምምነት መሠረት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 187 አገራት የተቀበሉት ስምምነት፣ የዝሆን ጥርስ ለንግድ እንዳይውል ይከለክላል፡፡