ቀደም ባሉት ጊዜያት የሴት ልጅ አደባባይ ወጥታ ራሷን መግለጽ አልያም ከቤት ውስጥ ሥራ ውጪ በመደበኛ ሥራ ተሰማርታ የቤተሰቧን ገቢ መደገፍ ማኅበረሰቡ በቀላሉ የሚቀበለው አልነበረም ነበር፡፡ ትምህርት ቤት መግባትም ከባድ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ቤተሰቦቿን መንከባከብ እንደ ግዴታዋ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ለውጦች ቢኖሩም ይህ ሥር የሰደደው አመለካከት ዛሬም በተለያየ መንገድ ሲንፀባረቅ ይስተዋላል፡፡
መማር ቅንጦት በነበረበት ዘመን እንችላለን በሚል ስሜት ተምረው ራሳቸውን መግለጽ የቻሉ፣ ለሌላውም አርዓያ የሆኑ ጥቂት ሴቶች ታይተዋል፡፡ ብዙ ሴቶች በማይደፍሩት የበረራ ኢንደስትሪ ፋና ወጊ የሆኑት የ54 ዓመቷ ወይዘሮ አሰገደች አሰፋን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ማኅበረሰቡ የሴት ልጅ ኃላፊነት ናቸው ብሎ ከሚያስቀምጣቸው ነገሮች በተለየ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ድርጊቶች ይሳተፋሉ፡፡ በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በዋና፣ በዒላማ ተኩስ፣ በፈረስ ጉግስና ጉዞዎች በማድረግ ይታወቁ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ጓደኞቻቸውም ወንዶች ነበሩ፡፡
በአንድ ወቅት ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር እየተጫወቱ ሳለ አንደኛው ጓደኛቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሁሉም ክፍት የሆነ አዲስ የበረራ ትምህርት ቤት መክፈቱን ነገራቸው፡፡ ወ/ሮ አሰገደችም እንደዋዛ ሰምተው አላለፉትም፡፡ ትምህርት ቤቱን ተቀላቀሉ፡፡ ብዙዎቹ ወንዶች በድፍረታቸው ተገረሙ፡፡ ትምህርቱን ያገባድዳሉ የሚል እምነትም አልነበራቸውም፡፡ በትምህርት ቤቱ ብቸኛ ሴት ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የተፈራው ሳይሆን ቀርቶ ትምህርታቸውን ጨርሰው የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት ፓይለት ለመሆን በቁ፡፡ በወቅቱ የነበሩ የተለያዩ ጋዜጦችም ስለ ስኬታቸው ጻፉ፡፡ ዝናቸውን የሰሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ቤተ መንግሥት አስጠርተው ልዩ ልዩ ሽልማቶችና ማበረታቻዎች አበርክተውላቸው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በበረራው መስክ ስማቸውን ካስጠሩ ሌሎች ሴቶች መካከል ካፒቴን አምሳለ ጓሉም ይጠቀሳሉ፡፡ በ1969 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ የተወለዱት ካፒቴኗ ፓይለት የመሆን ጉጉት ያደረባቸው ልጅ ሳሉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅትም ሕልማቸውን ዕውን የሚያደርጉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዓመት የአርክቴክቸር ተማሪ ሳሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው የትምህርት ዕድል ተሳታፊ ለመሆን ተወዳደሩ፡፡ ይሁን እንጂ አልቀናቸውም፡፡ ‹‹እውነት ለመናገር ፈተናውን ግማሽ በግማሽ አልሠራሁትም ነበር፤›› ሲሉ በፈተናው ያስመዘገቡት ውጤት አነስተኛ በመሆኑ ዕድሉን ሳያገኙ መቅረታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም ደግመው ተወዳደሩ፡፡ ካለፈው ስህተታቸው ተምረው ስለነበር ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ትምህርት ቤቱን ተቀላቀሉ፡፡
በ1994 ዓ.ም. የበረራ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ስድስተኛዋ ኢትዮጵያዊ ሴት ፓይለት ለመሆን ቻሉ፡፡ ‹‹ሥራውን ማግኘት ሳይሆን በሥራው ትልቅ ቦታ መድረሴ ያስደስተኛል፤›› የሚሉት ካፒቴኗ በፓይለትነት ሙያ ለስምንት ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ የካፒቴንነት ማዕረግ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ በትምህርት ላይ ሳሉ ያደረጉት የመጀመርያ በረራ ከአዕምሯቸው እንደማይጠፋ የሚናገሩት ካፒቴን አምሳለ የካፒቴንነት ማዕረጋቸውን እንዳገኙ በቦምባርዴር አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ጎንደር በረራ አድርገዋል፡፡
‹‹በማንኛውም ሥራ ላይ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ዋናው ግን ችግር አይመጣም ማለት ሳይሆን ችግሮቹን ተጋፍጦ መወጣት ነው፤›› በማለት ንጋት ላይ መነሳት እንዲሁም ሌሊት እንቅልፍ ማጣት ለሙያው የሚከፍሉት መስዕዋትነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሁኔታው በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ፈተና ቢሆንም ካፒቴን አምሳለ ከባለቤታቸው ጋር በመረዳዳት ሥራቸው በኑሯቸው ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡
አየር መንገዱ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. መዳረሻውን ባንኮክ ያደረገው በሴቶች የተመራ በረራ ላይም የቡድን መሪ የነበሩት ካፒቴን አምሳለ ነበሩ፡፡ በርካቶችም በረራው በሰላም በመጠናቀቁ አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ ‹‹የባለፈው ሥራ ለየት የሚያደርገው በሴቶች ብቻ መሠራቱ እንጂ መሥፈርቱ እንደ ሁሉም በረራ ዓይነት ነው፤›› በማለት ሴት በመሆናቸው የተለየ መሥፈርት እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ በሴቶች በተመራ በረራው ከካፒቴን አምሳለ ጎን የነበረችው ረዳት አብራሪ ሰላም ተስፋዬ ነበረች፡፡ የ27 ዓመቷ ሰላም እንደ ካፒቴን አምሳለ ሁሉ ፓይለት የመሆን ፍላጎት ያደረባት ልጅ እያለች ነበር፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሳለችም አየር መንገዱ ባወጣው የትምህርት ዕድል ለመካተት ተመዝግባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቁመቷ በማጠሩ ፈተናውን ሳታልፍ ቀረች፡፡ ነገር ግን በዚህ ተስፋ አልቆረጠችም ከወራት በኋላ በድጋሚ ተወዳድራ አለፈች፡፡ የፓይለትነት ትምህርቷን በማጠናቀቅም ቦይንግ 767 እና ቦይንግ 757 አውሮፕላኖች ላይ ረዳት አብራሪ ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ በሴቶች የተመራው በረራም አስደሳች እንደነበር ገልጻለች፡፡
ወደ ባንኮክ ያደረጉት በረራ ተጠናቆ መመለሳቸውን የሚገልጹ የተለያዩ ፎቶግራፎች በአየር መንገዱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ተለጥፈው ነበር፡፡ ከፎቶግራፎቹ ሥር የተለያዩ የአድናቆት አስተያየቶች ሰፍረዋል፡፡ በረራው የተዋወቀበትና የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሴቶች ትልልቅ ስኬት እንደ ልዩና ሴቶች የማይችሉትን ቻሉ ዓይነት አንድምታ አለው የሚል አስተያየት የሰጡም ጥቂት አልነበሩም፡፡ ሴቶች ከወንዶች እኩል መሥራት እንደሚችሉ፣ የሙያ ብቃታቸውም ከሴትነት አንፃር ሳይሆን ሙያው ከሚፈልገው ብቃት አንፃር መታየት እንዳለበት የሚያመለክቱ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል፡፡