ቅዳሜ ኅዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም. የሕፃናት ታላቁ ሩጫ በአዲስ አበባ ተከናውኗል:: በኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ማዕከል በተካሄደው የሕፃናት አንድ ኪሎ ሜትር ሩጫ ከ11 ዓመት በታች፣ ከስምንት ዓመት በታች፣ እንዲሁም ሕፃናት አካል ጉዳተኞች በሚል ዘርፍ 4,000 ሕፃናት ተሳታፊ ሆነዋል:: በዕለቱ ከቤተሰቦቻቸው የተጠፋፉ ታዳጊ ሕፃናት የጠፉ ሕፃናት በሚቆሙበት ሥፍራ ሆነው ወላጆቸውን ሲጠባበቁ ይታያሉ:: (ፎቶ ቴዎድሮስ ክብካብ)
* * *
ሩሲያ ለፈረንሳይ የውሻ ስጦታ ላከች
የፓሪሱን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የፈረንሳይ ፖሊስ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ፍተሻ ባደረገበት ወቅት ከአሸባሪዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ለተገደለው ዲዝል መታሰቢያ የፈረንሳይ ፖሊስ አነፍናፊ ውሻ ምትክ እንዲሆን ሩሲያ ለፈረንሳይ ውሻ መላኳን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ ለፈረንሳይ የላከችውና ደርቢያና የተሰኘው ውሻ ዲዝልን የሚተካም ይሆናል፡፡ የሩሲያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቭላድሚር ኮሎኮልቴዝ ለፈረንሳዩ አቻቸው በጻፉት ደብዳቤ ስጦታው ‹‹በዚህ ፈታኝ ቀን ከፈረንሳይ ፖሊስ ጐን መሆናችንን የማስረገጥ ምልክት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፈረንሳዩ ውሻ ዲዝል የተገደለው ጥቃቱን ተከትሎ ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ ፖሊስ የጥቃቱ አቀነባባሪ ነው የተባለው የ28 ዓመቱ አብዱልሀሚድ አባውድ የነበረበትን አፓርትመንት ሰብሮ ሲገባ በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ነው፡፡
* * *
የስምንት ዓመት ሕፃን ማሪዋና ይዛ ተገኘች
በአሜሪካ ኦሪዮ በአንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነች የስምንት ዓመት ሕፃን ማሪዋና ይዛ መገኘቷን ዩኤስ ቱዴይ ዘግቧል፡፡
ሕፃኗ የትምህርት ቤቱ ሠራተኛ የሆነ ሰው እንደደረሰባት ወዲያው በእጇ ይዛ የነበረውን ማሪዋና የመፀዳጃ ቤት የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ጥላለች፡፡ በዘገባው እንደተመለከተው ሕፃኗ ማሪዋናውን ማጨስ ፈልጋ የነበረ ቢሆንም እንዴት ማጨስ እንዳለባት እንኳን አታውቅም ነበር፡፡
ሕፃኗ ማሪዋናውን እንዴት እንዳገኘችው ማወቅ አልተቻለም፡፡ ይህን ፖሊስ እያጣራ የሚገኝ ሲሆን፣ ሕፃኗም ለጊዜው በሕፃናት ጥበቃ ማዕከል ውስጥ እንድትገባ ተደርጓል፡፡
ይህኛው አጋጣሚ አስገራሚ ተደርጐ ቢታይም በአካባቢው ብዙ ሕፃናት በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
* * *
የአስቀያሚዎች ውድድር ውጤት ረብሻ አስነሳ
በዚምባብዌ ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው የአስቀያሚ ወንዶች ውድድር ሚሊተን ሴሬ የተባለ የ42 ዓመት ጎልማሳ ማሸነፉ ረብሻ ማስነሳቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ረብሻው የተቀሰቀሰው የቀድሞ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ዊሊያም ማስቬና ደጋፊዎቹ አሸናፊው በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን በሚያስችል ደረጃ አስቀያሚ አይደለም በማለታቸው ነው፡፡ ‹‹እኔ በተፈጥሮ አስቀያሚ ነኝ እሱ ግን አይደለም፤›› ብሏል የቀድሞው አሸናፊ፡፡
የውድድሩ ውጤት ይፋ መሆንን ተከትሎ የዳኞችን ውሳኔ አንቀበልም ያሉት የቀድሞ አሸናፊ ደጋፊዎች ሚስተር ሴሬ ውድድሩን ለማሸነፍ የማይችል ‹‹ቆንጆ›› ነው ብለዋል፡፡ ሌላ ተወዳዳሪም ውጤቱን እንደማይቀበል ‹‹ለማሸነፍ ጥርሳችንን ማውለቅ አለብን ወይ?›› በማለት ገልጿል፡፡
ምንም እንኳ ከተወዳዳሪዎች ከደጋፊዎችም የተቃውሞ አስተያየት ቢሰነዘርበት የ428 ዶላር ሽልማት ያገኘው አሸናፊ አስተያየቶቹን ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ ‹‹እኔ ከእነሱ የበለጠ አስቀያሚ መሆኔን አምነው መቀበል አለባቸው፤›› ያለው ሚስተር ሴሬ በትምህርት ቤቶችና በሌሎችም ቦታዎች እየተዘዋወረ አስቀያሚነቱን እያሳየ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የቴሌቪዥን ኮንትራት ማግኘትም ተስፋ አለው፡፡
* * *
ጉግል ሉሲን ዘከረ
ጉግል የሉሲ 41ኛ ዓመትን በድረ ገጹ ዘከረ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1974 ከአፋር ሀዳር የተገኘውን 3.2 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረው የሉሲ አጽም መገኘት 41ኛ ዓመት ማክሰኞ ህዳር 14 ቀን 2008 በጉግል ድረ ገጽ ተዘከረ፡፡
ከ41 ዓመታት በፊት የሉሲን አጽም ያገኙት ሳይንቲስቶች ዶናልድ ጆንሰንና ቶም ግሬይ ነበሩ፡፡
የሉሲ አጽም መገኘት በሰው ልጆች ዕድገት አዝጋሚ ለውጥና በሰው ልጆች አመጣጥ ጥናት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡