Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

“በኢትዮጵያ የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ እያደገ ይሄዳል የሚል ተስፋ አለኝ”

መታሰቢያ ሰለሞን (ዶክተር) ባዮሜዲካል ኢንጂነር

ዶክተር መታሰቢያ ሰለሞን በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ ነች፡፡ ተወልዳ ያደገችው፣ የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው አዲስ አበባ በሚገኘው ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ነው፡፡ የመሰናዶ ትምህርት መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን አልፋ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋኩልቲ ብትመደብም፣ የተመደበችበትን ትምህርት ሳትጀምር በትውልድ ኢትዮጵያውያን በዜግነት ደግሞ አሜሪካውያን ከሆኑትና ቴክሳስ ዳላስ ውስጥ ከሚኖሩት እናትና አባቷ ዘንድ አቀናች፡፡ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ ገብታ በባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን፣ እንዲሁም ሴንት ሉዊስ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በዚሁ ሙያ የፒኤችዲ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ የሁለተኛ ዲግሪዋን ሳትሰራ በቀጥታ ሦስተኛ ዲግሪ የሠራችው የመጀመሪያ ዲግሪዋን እየሰራች ሪሰርችና ቱተር ታስተምር ስለነበር የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መውሰድ ስላልነበረባት ነው፡፡ ለወላጆቿ ብቸኛ ልጅና የ32 ዓመት ወጣት የሆነችው ዶ/ር መታሰቢያ፣ ከባዮሜዲካል ኢንተርናሽናል ባገኘችው ፊሉውሺፕ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አንድ ዓመት ከስምንት ወር ያህል በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ አገልግላለች፡፡ ተልዕኮዋንም አጠናቅቃ ወደመጣችበት ተመልሳለች፡፡ ከመሄዷ ቀደም ብሎ ታደሰ ገብረማርያም በባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ እና በአገልግሎቷ ዙሪያ አነጋግሯታል፡፡

ሪፖርተር፡- ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግን ብታብራሪልን?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ባዮሎጂን፣ ኢንጂነሪንግን፣ ማትስንና ፊዚክስን ተጠቅሞ ለሕክምና የሚውል ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ የተለያዩ አካሄዶች አሉት፡፡ ኢንስትሩሜንቴሽን፣ ኢሜጂንግ፣ ዲጂታል አፕሊኬሽን፣ ቲሹ ኢንጂነሪንግና ኮምፒቲሽልናል ይባላሉ፡፡ እኔ የጨረስኩት ዲጂታል አፕሊኬሽንና ኢንስትሩሜንቴሽን ነው፡፡ በመሆኑም ከኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ብዙ ኮርስ ወስጃለሁ፡፡ ፒኤችዲዬንም የሠራሁት ለካንሰር ምርመራ አገልግሎት በሚያግዝ ማሽን ላይ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመጣሁበት ወቅት የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ይሰጥ እንደነበር በማወቄ ካሪኩለም ሰርቼያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ስለመሰጠቱ መረጃ ስላልነበረኝ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ተመድቤም ሰርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት መሰጠቱን ካወቅሽ በኋላ ለዚሁ ዩኒቨርሲቲ ምን ያደረግሽው አስተዋጽኦ አለ?

ዶ/ር መታሰቢያ፡-  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ትምህርቱ መሰጠቱን ካወኩ በኋላ ለሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አራት ኮርሶችን ሰጥቼያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ ያደረግሽው አስተዋፅኦ ምንድን ነው?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- በኮሌጁ ቆይታዬ ወቅት ኮርስ ከመስጠት በተጨማሪ፣ ለሠራተኞች የተወሰነ ሥልጠና መስጠት፣ ወርክሾፑን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል ፕላን ማውጣትና የተወሰነ ሥልጠና መስጠት፣ የሕክምና መሣሪያዎች ሲበላሹ እንዴት መፈተሽ እንዳለባቸው ለባለሙያዎች ማሳየት፣ የሆስፒታሉ የሕክምና ማሽኖች ያሉበትን ደረጃና ብዛታቸውን መዝግቦ መያዝና ተመሳሳይ አገልግሎቶች ይገኙባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ባየሽው ከባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የቱ ነው?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- ሆስፒታል ውስጥ እንዳየሁት ከሆነ አሁን የሚያስፈልገው ክሊኒካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ችግሮችም እንዳሉ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ካየኋቸው ችግሮች መካከል አንዱና ዋንኛው ጠንከር ያለ ማኔጅመንት አለመኖሩ ነው፡፡ ዕቃዎች ከመበላሸታቸው በፊት እንዴት ነው ማኔጅ የሚደረጉት? ከመበላሸታቸው በፊት በየጊዜው እየታዩ እድሳትና ቁጥጥር ይደርጋል ወይ? የሚሉት አሠራሮች ተገቢው መልስ ያልተሰጣቸውና ችላ የተባሉ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ሰው ሳይሰለጥን ማሽኑ በቅድሚያ ተገዝቶ መምጣቱ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አግባብ ባልሆነ መንገድ ማሽኑ ጥቅም ላይ ስለሚውል ወዲያው ተበላሽቶ የሚቀመጠው ብዙ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ማንኛውም ሆስፒታል የማኔጅመንትና የቴክኒካል ሥልጠና የወሰደ ባለሙያ ያስፈልገዋል፡፡ ካለው ክፍተት አንፃር ያበረከትኩት አስተዋጽኦ ጥቂት ቢሆንም፣ በቆይታዬ የሚጠቅመኝን ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራሽ ያጋጠመሽ ችግር ምንድነው?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ሲባል ማሽኖችን መጠገን ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ በውስጡ ብዙ ዘርፎች እንዳሉት በሆስፒታሉ ማኅበረሰብ ዘንድ ገና አልሰረፀም፡፡ እንደመጣሁ ማሽኖችን እንድጠግን፣ እንዳስተካክል እጠየቅ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የተማርኩትና ፒኤችዲዬን የሰራሁት ለካንሰር የሚሆን ማሽን ዲዛይን በመሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሎች ትልቁ ችግራቸው ሲቲስካን፣ የኤክስሬይ ማሽንና ሌሎችም ወሳኝ ማሽኖች መበላሸት ነው፡፡ ከተበላሸ ሳይጠገን ለረዥም ጊዜ ይቀመጣል፡፡ ምናልባትም ለዚህ ይሆን ጠግኝልን የሚል ጥያቄ የሚቀርብልሽ?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- አዎ፡፡ እሱ ነው፡፡ ፒኤችዲ ያለው ሰው ሁሉ ሁሉንም ያውቃል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ፒኤችዲ አለው ማለት በአንድ ነገር ላይ አተኩሮ ሙያውን አሳድጓል ማለት እንጂ ሁሉንም ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ የሁሉንም ዘርፍ ንድፈ ሐሳብ ላስተምር እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ዕቃው ሲበላሽ ከአምራቹና ከአስመጪው ኩባንያ ስልጠና የወሰደ ባለሙያ ነው መጠገን ያለበት፡፡ በተረፈ ይህ ዓይነቱን ሥልጠና ያልወሰደ ሰው መክፈትና መፈተሽ የለበትም፡፡  

ሪፖርተር፡- በዚህ ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አልተወያየሽም?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- ውይይት አድርገናል፡፡ እየሠራንም ያለነው ይህንኑ ነው፡፡ ከአስመጪዎች ጋር በተፈጠረው ግንኙነት የተነሳ ባለሙያዎች ሰልጥነው ሲቲስካንና ሌሎችንም መሳሪያዎች እየጠገኑ ነው፡፡ አሁን አሁን አካሄዱና አሠራሩ እየተለወጠና እያደገ ነው፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትም በዚህ ዘርፍ ስልጠና እየሰጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ቆይታሽ በሕክምናው ዘርፍ ያስደሰተሽና ያሳዘነሽ ነገር ምንድነው?

ዶ/ር መታሰቢያ፡- ከአስደሰቱኝና ከተደነቅኩባቸው የሕክምና ዘርፎች መካከል አንዱና ዋንኛው አገሪቱ የእናቶችንና የሕጻናት ሞትን ለመቀነስ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በአርአያነት የሚታይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ በፊት በጥቁር አንበሳና በአንድ የግል ሆስፒታል ብቻ የነበረው የኩላሊት ማጠቢያ (ዲያሊስስ) በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ ጨምሮ ጨምሯል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅም ይህ ዓይነቱን አገልግሎት መጀመሩ ያስደስታል፡፡ በተለይ ኮሌጁን ለማስፋፋትና የልቀት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ) ለማድረግ፣ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ለማቋቋም የሚታየው ጥረት ሁሉ ከጠበኩት በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የኮሌጁ ተማሪዎችም ለመሥራትና ለማወቅ የሚያሳዩት ፍላጎት እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግን ባለው ጥሪትና አቅም ማቋቋም ይቻላል፡፡ ከጊዜ በኋላ ደግሞ እየተጠናከረና እየሰፋ ይሄዳል፡፡ እኔና ጓደኞቼ  አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ የተማርነው የመጀመሪያ ተማሪዎች ሆነን ነው፡፡ ካሪኩለሙንም ያስተካከሉት ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንስቶ እየታየ ያለውን ክፍተት አቅምን ባገናዘበ መልኩ ደረጃ በደረጃ እየሸፈኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ቀስ በቀስ ክፍተቶች እየተሞሉ ዘርፉ ከትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብዬ አምናለሁ፡፡ በቆይታዬ ወቅት በጣም ያስደነገጠኝ ነገር ቢኖር የካንሰር በሽታ በዝቶ ማየቴ ነው፡፡ ብዙ የካንሰር በሽተኞች አሉ፡፡ በሽታው በመጀመሪያ ሲመጣ ስለማይታወቅ፣ ግንዛቤም ስለሌለ ዘግይተው ነው ወደሕክምና ተቋም የሚሄዱት፡፡ በሽታው ደግሞ በአብዛኛው ጎልቶ የሚታየው ወጣቱ ላይ ነው፡፡ በተለይ ወጣት ሴቶች ላይ፡፡ የጡትና የማኅፀን በር ካንሰር በጣም ተንሰራፍቷል፡፡ የአንጀት ካንሰርም በዝቷል ተብያለሁ፡፡ ሕክምና ተቋም ሲመጡ ደግሞ ለሕክምና ስድስት ወር፣ አንድ ዓመት ቀጠሮ ይጠብቃሉ፡፡ ይህም የበሽታውን የመግደል አቅም ያፋጥነዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከፍተኛ የሆነ የካንሰር ማዕከል ለማቋቋም አስቧል፡፡ ይህ ተግባራዊ ከሆነ ችግሩ በመጠኑም ቢሆን ይቀረፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን መገናኛ ብዙኃን ለዚህ በሽታ ትኩረት አለመስጠታቸው ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ዙሪያ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡  

ሪፖርተር፡- የካንሰር መንስዔው ምንድነው? በተለይ አንቺ የፒኤችዲ ዲግሪሽን የሰራሽው በካንሰር ማሽን ዙሪያ ነው፡፡ እስቲ ስለ ማሽኑ ትንሽ ማብራሪያ ብታደርጊልን?

ዶ/ር መታሰቢያ፡-  የካንሰር መንስዔዎች በርካታ ናቸው፡፡ አንዱና ሁሉም የሚያውቀው የአኗኗራችን ሁኔታ መለወጥ ነው፡፡ አገሪቱ እያደገች ሕዝቦቿም ከድህነት እየተላቀቁ መሆኑን ዓለም መስክሯል፡፡ በዚህም ተነሳ የአመጋገባችን መሻሻል፣ ለብዙ ነገር ተጋላጭ መሆናችን ሁሉ መንስዔ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የሰራሁት የሊንፍሎድ ካንሰር የሚለይ ወይም መኖሩን የሚያሳይ ማሽን ነው፡፡ ይህም ማለት ከመነሻ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን የካንሰር ዕድገት የሚያሳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፊሉውሺፕሽን ጨርሰሻል፡፡ በቀጣይ ምን አስበሻል?

ዶ/ር መታሰቢያ፡-  የማስተርስ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፋቸውን እንዲጨርሱ እንደ አድቫይዘር ሆኜ እንድሰራ፣ ከተቻለ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ እየመጣሁ ኮርስ መስጠት የምችልበት ሁኔታ የሚፈጠርበትን መንገድ ለማመቻቸት እጥራለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከምቀመጥ ይልቅ እዛው አሜሪካ ተቀምጨ ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለስኩ ባገለግል የበለጠ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እችላለሁ፡፡ እዚህ ያለውን እንቅስቃሴ በበጀትና በሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሟላት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኜ ከምንቀሳቀስ ይልቅ አሜሪካ ሆኜ ጥረት ባደረግ የተሻለ ይሆናል፡፡ ዕርዳታ ለማፈላለግና በመስኩ የሰለጠኑ ባለሙያዎችንና  ምሁራንን ለመመልመል መንገዱ ቀላል የሚሆነው አሜሪካ ብሆን ነው፡፡ በተቻለኝ ሁሉ ኢትዮጵያን በተማርኩበት ዘርፍ ለማገልገል እጥራለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...