እነሆ መንገድ። ከመገናኛ ወደ አያት ልንጓዝ ነው። ከጎኔ የቆመ ጎልማሳ “ . . . ባቡር እየጠበቅኩ ነው አልኩሽ እኮ? ምን አስር ጊዜ ትደውይልኛለሽ?” እያለ በስልክ ይደነፋል። ከወዲያ በኩል አንዱ ሲያሽሟጥጠው፣ “አበል ይሰጠው ይመስል ምን ያስጮኸዋል? ተስፋችንን ጥለን በተጠንቀቅ ቆመን በጠበቅናቸው መጓጓዣዎችና መንገዶቻቸው ገድ ቢሆን ይኼኔ ስንት አናይም?” ይላል። ወዲህ ደግሞ ጥላዬን ረግጣ የቆመች ቆፍጣና ሴት፣ “‘ስንት’ ስንት ነው?” ትለኛለች። አንዳንዱ ሰው ሁሉን ነገር ካልተረጎምኩ ሲል ሕይወቱ የህንድ ፊልም መስሎ ቁጭ። “ጎበዝ ይኼን ቢጫ መስመር እባካችሁ አትለፉ። ባቡሩ እኮ በዓይን ስበት አይጓዝም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ነው፤” ይላል ክላሰር በብቱ ወሸቅ አድርጎ የያዘ ነገረ ፈጅ መሳይ። “እናውቃለን…፤” ይላል ጎልማሳው ‘ለምን ተነገረኝ’ ዓይነት ተቆጥቶ። “አውቀንም እናልቃለን…፤” ብሎ ባለክላሰሩ በነገር ተበጥቶ የፈሰሰ ደሙን ሲመለስ ጎልማሳው ዘወር ብሎ እንኳ ሳያየው “አላልቅ ብለን ነው አላቂ ዕቃዎች ያስመረሩን?” አለው።
“ነዳጅ ሳናወጣማ አናልቅም፤” ሴትዮዋ ቀስ ብላ ገባችበት። “ሳይዋጣልንማ እንኳን ከመሬት ውስጥ ከመሬት በላይ ያለውም ቢሆን የትም አያመልጣት፤” ብሎ ጎልማሳው በደም ፍላት መንጠር ጀመረ። “የለም ቂም መያዝ ደግም አይደል። ካልተላቀቅን ልጅ ይወጣልናል ብለህ ነው የእኔ ልጅ?” ጎልማሳውን ቁልቁል እያስተዋሉ አንድ አዛውንት ጠየቁ። “በአገራችን ላይ ቢያቅተን ሰው አገር አያቅተንም አባባ። እዚህ ማበብ ባንችል እዚያ እሾህ ሆነን ሕይወትን መኳል አያቅተንም፡፡ አይሥጉ!” አላቸው። “በስመ አብ ወልድ . . . ! ምነው እሾህነትን አስመኘህ ልጄ? ያውም በሰው አገር?” ቢሉት ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ “ምነው አባት? አበባም እሾህም ያው የግንዱ አካል ናቸው። ደግሞስ ሰው ባገሩ ማበብ ካልታደለ ምን ምርጫ አለውና?” አላቸው። ጽጌረዳም በአቅሟ በሕይወት ተመስላ ይኼን ሁሉ ካነጋገረች ሰው ሠራሹና ሰው ቀባሹ ነገር እንዴት እያነታረከን እንደምንጓዝ አስቡት።
ውረድ እንውረዱ ተጀመረ። መንገዱን ተያይዘነዋለል። ወዲያ ወዘናቸው እንደ አብዛኞቻችን በፀሐይ ግለትና በቫዝሊን ታሽቶ ያልተቅለጠለጠ ቆፍጠን ያሉ ተሳፋሪ ከተቆጣጣሪዎቹ ጋር ይጨቃጨቃሉ። ቀልባችን ተስቧል። “ይኼው ምልክቱ እኮ! ባቡር ውስጥ ሲጋራ ማጨስ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፤” ትላለች ዩኒፎርም ለባሿ። “ተሳስተሻል! ይኼ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ‘አርቴፊሻል’ ሲጋራ ነው። ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም። አውሮፓም ባቡር ውስጥ ማጨስ ክልከል ነው። ይኼ ግን ይፈቀዳል፤” ይሉዋታል። “ገና ለገና በኤሌክትሪክ በሚንቀሳቀስ ባቡር ተሳፈርኩ ብሎ ነው እንዲህ ባለዝና ካልሆንኩ የሚለው?” ይላል ወዲያ ከተጠቀጠቀው ተሳፋሪ መሀል መልኩን የማንለየው። “እንጃ! በዚህ ዓይነትማ በኤሌክትሪክ ኃይል ነው የምንተነፍሰውም ይመጣል። ያን ጊዜ አዳሜ ምን እንደምትሆኚ እንጃ። ለሞባይሎቻችንም አልበቃ እንኳን እኛ ራሳችን በቻርጅ መንቀሳቀስ ጀምረን፤” ትላለች ከፊት ለፊቴ የተቀመጠች ወይዘሮ።
“አሁንስ በምንድነው የምንቀሳቀሰው? የሻይ፣ የማኪያቶ፣ የካርድ እየተባባልን በምንሸጓጉጠው መስሎኝ?” ያ ጎልማሳ ነው ጣልቃ የሚገባው። “በአንዴ ከኮረንቲ ወደ ሻይና ፓስቲ ወሬ ስትወርዱ አይደብራችሁም?” ፀጉሩን ያንጨበረረ ወጣት በድፍረት ጠየቀ። “ሙስና ነው ሻይና ፓስቲ?” አዛውንቱ ገነፈሉበት። “ታዲያ! በቃ ካልተቀባበልን መኖር የምንችል ሰዎች አይደለንም። ይኼን በደንብ እናውቀዋለን። እናንተም እኮ ስታሳድጉን የታዘብነው ብዙ ነገር አለ። ማንም ሰው ቤታችሁ መጥቶ ‘ይህቺን ያዝ!’፣ ‘ቆይ ለመንገድ ሁለት ጎርሰህ ሂድ’፣ ‘አንደኛ ከወጣህ ጫማና ልብስ እገዛልሃለሁ’ እያላችሁ ነው ያሳደጋችሁን። ነገራችን ሁሉ በእከክልኝ ልከክልህ ጥልቅ በሆነ መንገድ የተቆራኘ ነው። ታዲያ ምንድነው ዛሬ ፉከራው? አይገባኝም በበኩሌ፤” ብሎ ወጣቱ እንዳሻው ተናግሮ አበቃ። የአዲሱ ትውልድ ዕይታ፣ ጥልቀቱ፣ አንዳንዴ ለመፍትሔ አልባነት ከማድላቱ የተነሳ እሪታችንን ሰብስቦ በከንቱ ሲበትነው አንገት ያስደፋል። ድሮስ አታካብድ ብሎ ብሂል የት ተወለደና?!
“ፍሬንድ’ በቃ አትከራከራት። ‘በኤሌክትሪክ የሚሠራ አርቴፊሻል ሲጋራ አጫሽ መሆንህን አውቀናል’ ለምን አትሉትም? ይላል ፊት ለፊቴ ሦስተኛ ተደርቦ የተቀመጠ ጎልማሳ፡፡ “ለምን አንተ ራስህ አትለውም? ሰው ማስጠቃትና ማጥቃት በሰው ካልሆነ ደስ አይለንም ማለት ነው?” ፊት ለፊቱ ከአጠገቤ የተቀመጠች ጎልማሳው ላይ አፈጠጠችበት። “‘ፊት ለፊት’ የሚባል አንድ ደህና የቴሌቪዢን ፕሮግራም ቢኖር እሱንም አጠፉት፤” አለ ያ ነገር ነገር የሚለው ጎልማሳ። “ውይ ቆየ እኮ! እነሱም ፊት ነሱን እኛም ጀርባቸውን አጠናን፤” ብሎ ደግሞ ያ ‘ክላሰሩን’ ከአንድ እጁ ወደ ሌላው አሥር ጊዜ የሚቀባበለው ነገረ ፈጅ መለሰ። “ዛሬም የመደብ ትግል ላይ ነን እንዴ?” ብለው ደግሞ ደርባባዋ ሴትዮ ተሳለቁ። “ይኼው ነው ቀዬያችን!” ወጣቶቹ ለትችት ይረባረቡ ጀመር።
“ሰው መሆናችንን አላምን እያልን ፈጣሪ እንኳ ደፍሮ የማይምለውን መሀላ እንምልና በገዛ ምላሳችን በገዛ እግራችን ማንም ሳይነካን ተጠላልፈን መውደቅ ነው። ይኼው ነው ቀያችን!” እያሉ ሲቀባበሉ፣ “ኧረ እናንተ ልጆች ተዉ! የምን ቀዬ አመጣችሁ? ከተማዋ በአሥር ክፍላተ ከተሞች ተቧድና እያያችሁ?” ብለው አዛውንቱ ጠየቁ። “ምን ለውጥ አለው አባት? መቧደን እስካላቆምን ድረስ ሰፍተንም ጠበንም ለውጥ አልታየም፤” አለች የደስ ደስ ያላት ወጣት። “ግለ ሂስ! ‘ለውጥ አልታየም’ ማለት ስለማትችይ በይ ቶሎ መውረጃሽ ሳይደርስ ሂስሽን ዋጪ እያሉ ተሳፋሪዎች ቢያካልቧት፣ “ሃያሲ ሁሉ ተቃዋሚ ከመሰላችሁ እውጣለሁ። አካፋን በማንቆለጳጰስ ግን ‘ሳተላይት’ ማድረግ አይቻልም። ሂስ ስንውጥና ስናስውጥ የኖርንባቸውን ዘመናት ቢያንስ ከፊሎቹን ዓይናችንን የሚያበሩልንን ሀቆች ውጠን ቢሆን ኖሮ ግን ዛሬ የት በደረስን?” ብላ ቦታ ቀየረች። እንግዲህ በእሷ ዓይነት ስንቱ ይሆን የኤሌክትሪክ ባቡር ላይ ሆኖ የሽሽት ባቡር የሚሳፈረው? እስኪ ከተግባባችሁት ሾፌሩን ጠይቁት!
ወዲያ ማዶ ደግሞ የልማት አጋራችን አገር ሰው በሞባይሉ ሙዚቃ ከፈተ። ‘አሸበል ገዳዬ፣ አሃው ገዳዬ’ ስፒከሩ ይነፋነፋል። “ይገርማል! ወገን ተርቦ ሌቱ አልበቃን ብሎ ደግሞ በቀን አስረሽ ምቺው ያምረናል። እንዲያው እኮ!” አዛውንቱ አጉረመረሙ። “ሕይወት እንዲህ ናታ። እንባና ሳቅ እኮ ናት፤” ብሎ ሁሌም መቃረን ነው መሰል የሚቀናው ጎልማሳው መለሰላቸው። “እንዲያ! ምጥ ለእናቷ አስተማረች አሉ። ሰው ምናለበት የኖረውን ብቻ ቢያወራ? እ? አሁን እንባው በእንባዬ ልክ ሳቁ በሳቄ ልክ የተሰፈረ አይመስልም እንዲህ ሲል?” ብለው አዛውንቱ ጎልማሳውን ለወይዘሮዋ አሙላት። “አንዳንዱ እንዲህ ነው። ካልቀባጠረ ይበላዋል፤” ትላቸዋለች ዞራ። “አይገርምሽም ግን? የተቸገሩና የጨነቃቸውን ዝም ጭጭ ያሉ እኮ ብዙ ናቸው፤›› ብለው መልስ ጥበቃ ዓይን ዓይኗን ማየት ሲጀምሩ፣ “የሚያስጠጋስ አለ እንዴ? ይኼኔ ለእርግጫና ለፈንጠዝያ ቢሆን የስፖንሰር መዓት በሰማን ነበር። ለመረዳዳትና ለመተባበር ሲሆን ግን እጆቻችንን መዘርጋት ብንፈልግም ቅሉ ‘ኔትወርኩ’ መቼ እሺ ብሎ?” አለቻቸው። ይኼኔ ያ ጎልማሳ፣ “እህ ልግስናም በ ‘ቴሌ’ ቁጥጥር ሥር ዋለ እንዴ? የት ሄጄ ነው ያልሰማሁት?” እያለ መሀል ጥልቅ ሲል፣ “ምናልባት የአውሮፓ ኳስ ተንታኞችን መሳጭ ሐተታ ለማዳመጥ ከነጥብ ነጥብ ስትባዝን ዓበይት ዜናዎቹ አልፈውህ ይሆናላ፤” ብለው አዛውንቱ ጠቅ አደረጉት። መርዶዎቻችንን ከቅርቦቻችን ሰምተን እንደምናውቅ ሁሉ ወጣቱ አዛውንቱን እንደ ልክ ቆጥሮ አቀረቀረ። የማቀርቀር ‘ታለንት’ እንደሆነ የግላችን!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። በማይክራፎኑ ስለአወጣጥ አገባባችን መመርያ ይዥጎደጎዳል። አንዲት ኮረዳ ከጫጫታው አፈንግጣ “ . . . ስሚ ነገ እኮ ልደቴ ነው!” እያለች ደስታዋን ለወዳጇ ስታበስር እንሰማለን። “ . . . ቀላል እናከብረዋለን? ያውም ሰብሰብ ብለን ልክ እንደ እነ እንትና ለሳምንታት እሺ?! ንገሪያቸው ለሁሉም፤” ትላለች። ጎልማሳው ንቀት ተሞልቶ “እን እንትና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ታግለው ነው። አሁን ይህቺ ዓይን የማትሞላ አንዲት ፍሬ ልጅ ምን አድርጋ ነው?” ብሎ አጠገቡ ወደቆሙት ዘወር ዘወር አለ። ይኼን ጊዜ አንዱ፣ “መታገል ብቻ ነው እንዴ ዋጋ የሚያስከፍለው? አለመታገልም እኮ ዋጋ ያስከፍላል፤” አለው። ጎልማሳው ለመጀመሪያ ጊዜ በትህትና በጥያቄ አንደበቱን አላቀቀ። “እንዴት ማለት?” አለው በመገረም እያየው፡፡
ያኛው መልሶ፣ “በደንብ ካጤንከው ከመታገል ይልቅ አለመታገል ዋጋ ያስከፍላል። እየሰማህ እንዳልሰማ፣ እያየህ እንዳላየ መኖር እኮ እጅ እግር ባያጎልና የሕይወት መስዋዕትነት ባያስከፍል፣ ዘለዓለም ልብ እያደማ ነው የሚኖረው። ታጋይ እኮ በክንዱ፣ በጉልበቱ፣ በድርጊቱ ተመክቶ ወደ ውጭ ይተነፍሳል። አለመታገል ግን ወደ ውስጥ ያስተነፍሳል። ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት አገሩ በአላጋጭና በደም መጣጭ ተሞልቶ እያየህ፣ ለዛሬዋ ቀን እንድንደርስ ስንት ጀግና አገር ወዳድ ታጋዮች የወደቁለትን ቅዱስ ዓላማ ማንም ለግል ጥቅሙ ሲያዞረው እያየህ ‘ዝም’ በጣም ያማል። ስኬቶቻችን በፕሮፓጋንዳ ናዳ ከተለኩ ምን ቀረልን? አሯሯጫችን እኛውና እኛው ብቻ ከሆንን ‘የገባንበትን ሰዓት ተመልከቱ’ እያሉ ዓለምንስ ለምን ሥራ እናስፈታለን? . . . ታዲያ ትውልዱ ያለአቻ ተጋብቶ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተሰቃየ እየኖረ አይደለም ለሳምንታት ለዓመታት ልደቱን ቢያከብር፣ ባይማር፣ ቢቦዝን፣ ተስፋ ቢቆርጥ፣ ቢሰደድ፣ ቢጠጣ፣ ቢቅም፣ ቢያጨስ፣ በነፍሱ ቢነግድ፣ በሥጋው ቢቆምር ይፈረድበታል?” እያለ ተንተክትኮ ሲያበቃ የእኛም ጉዞ አበቃ። ‘የሚንተከተክ ሲበዛ ደግ አይደለም’ ሲባል ብንሰማም፣ በየቦታው ያጋጥመናል፡፡ አማራጭ መፈለግ እያለ የምን መንተክተክ ነው?’ መልካም ጉዞ!