Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአሜሪካን ያገለለው የኢራንና የሩሲያ ግንኙነት

አሜሪካን ያገለለው የኢራንና የሩሲያ ግንኙነት

ቀን:

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኢራንና የሩሲያን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሰኞ ኅዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢራን ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ከኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሚኒ ጋር ለ90 ደቂቃዎች የዘለቀ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ውይይቱም በሶሪያ ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡

በሶሪያ ለአራት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነትና አገሪቷ የአሸባሪዎች መፈንጫ መሆኗን ተከትሎ፣ አሜሪካና ምዕራባውያኑ በሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ በሥልጣን የመቆየት አጀንዳ ላይ ከሩሲያና ከኢራን የተለየ አቋም አላቸው፡፡ ሩሲያና ኢራን አል አሳድ በሥልጣን መቆየት አለባቸው ሲሉ፣ ምዕራባውያኑና አሜሪካ ደግሞ መወገድ አለባቸው የሚል አቋም አላቸው፡፡

የሽብር ጥቃቱ እያየለና እየተለዋወጠ የመጣውን አይኤስ ለማጥፋት አገሮቹ ተመሳሳይ አቋም ቢኖራቸውም፣ በሶሪያ ላይ ያላቸው የፖለቲካ ልዩነት እርስ በርስ እንዲፈራረጁ አድርጓቸዋል፡፡ በፑቲን የኢራን ጉብኝት ወቅት የተስተዋለውም ይኼው ነው፡፡

ፋይናንሻል ታይምስ እንደ ዘገበው፣ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሜሪካ የሶሪያን ፕሬዚዳንት ለማስወገድ መብት የላትም፣ የዋሽንግተን ፖሊሲም ለመካከለኛው ምሥራቅ ሥጋት ሆኗል ብለዋል፡፡

አያቶላህ እንደሚሉት፣ ‹‹አሜሪካ በሶሪያ የበላይነት አግኝታ ለመቆየት የረዥም ጊዜ ዕቅድ አላት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በምዕራብ እስያ ያጣችውን የበላይነት በመካከለኛው ምሥራቅ ለማካካስ ነው፡፡ አካሄዱ ለሁሉም ሕዝቦች በተለይም ለኢራንና ሩሲያ ሥጋት ነው፡፡››

ፑቲን ከስምንት ዓመታት በኋላ ኢራንን ሲጎበኙ፣ ሩሲያ በሶሪያ ላይ ያላትን አቋም አያቶላህ አሞግሠዋል፡፡ አይኤስን ለመዋጋት ሞስኮ በሶሪያ ያላትን ጣልቃ ገብነት በይፋ ደግፈዋል፡፡

ኢራንና ሩሲያ ስትራቴጂካዊ የትብብር ማዕቀፍ ባይኖራቸውም፣ ኢራን የኑክሌር ማብላያ ተቋማቷን በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከ20 ሺሕ ወደ 6,104 ለመቀነስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር እንድትስማማ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የተጣለባት ዕግድ እንዲነሳላት በተደረሰው ስምምነት ሩሲያ ዋና ሚና ነበራት፡፡ ኢራን የሶሪያ ቀኝ እጅ ስትሆን፣ ሩሲያ ከሶሪያ ጋር ባላት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት መሠረት የአል አሳድን መንግሥት ትደግፋለች፡፡

ከ97 በመቶ በላይ የሺአ ሙስሊሞች ላሉባት ኢራን አጋር የሆነችው ሶሪያ፣ በአሁኑ ጊዜ የሱኒ እምነት ያራምዳሉ ተብለው በሚፈረጁት የኢስላሚክ ስቴት ቡድኖች መናኸሪያ መሆኗ ለኢራን ሥጋት ነው፡፡ በመሆኑም ኢራንና ሩሲያን አስተሳስሮ የሚያቆያቸው የጋራ አጀንዳ አላቸው፡፡ የተለያዩ ሚዲያዎች ኢራንና ሩሲያን የሰሞኑ ውይይታቸውና በሶሪያ ላይ ያላቸው አንድ ዓይነት አቋም ለረዥም ጊዜ አይዘልቅም ብለው ቢዘግቡም፣ አያቶላህ ሩሲያ የዩክሬንን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላትን ፖሊሲ ‹‹መልካም›› ሲሉ አድንቀዋል፡፡

የኢራን የፖለቲካ ተንታኝ ግን ሶሪያን በተመለከተ ሁለቱ አገሮች ያላቸው ትብብር ለረዥም ጊዜ ይቀጥላል ወይ? የሚለውን በጥያቄ ያነሱታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሞስኮ የቴህራን ጠላት ከሆነችው እስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላላት ነው፡፡ በሌላም በኩል በቀጣናው የኢራን ተቀናቃኝ የሆነችውን ሳዑዲ ዓረቢያ በደማስቆ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከእስራኤል ጋር በማደራደሩ ረገድ ሩሲያ ሚና ስለነበራትም ነው፡፡

ሞስኮ በሶሪያ ላይ በሚኖራት የረዥም ጊዜ ዕቅድ ከኢራን ጋር አብራ ትቀጥላለች ወይ? የሚለው ጥያቄም ተነስቷል፡፡ ሩሲያ በአሁኑ ጊዜ ለአሳድ የወገነች ቢሆንም፣ በሶሪያ ሰላም ከሰፈነ በኋላ አሳድ ከሥልጣን እንዲወርዱ፤ ምዕራባውያን በሩሲያ በኩል የሚያነሱትን የዩክሬን ጉዳይ እንደ ማደራደሪያ አድርጋ ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ትንታኔም አለ፡፡

እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ‹‹ኢራን ሁሌም የምንተማመንባት አጋር ናት፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹ሩሲያ እንደ ሌሎች አገሮች ለአጋሮቿ በፊት ለፊት ጓደኛ እየመሰለች፣ በኋላ በር ሸፍጥ አትሠራም፤›› ሲሉም አሜሪካን ጎሸም አድርገዋል፡፡

ኢራን ሩሲያ በሶሪያ የምታካሂደውን አይኤስ ተቃዋሚዎችን መምታቷን ትደግፋለች፡፡ የኢራን ወታደሮች፣ የሊባኖስ ሚሊሺያና የፖለቲካ ፓርቲ የሆነው ሒዝቦላህ ተዋጊዎችም ፕሬዚዳንት አሳድን በእግረኛ ጦር የሚደግፉ ናቸው፡፡ ሩሲያ ደግሞ በእግረኛ ውጊያ ሳይሆን በአየር ድብደባ አሳድን ትረዳለች፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ፣ ፑቲን ኢራንን በጎበኙበት ዕለት የሳዑዲ ዓረቢያንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣናትን በአቡዳቢ አነጋግረው ነበር፡፡ አጀንዳውም በሶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውን ዕቅድ እንዲደግፉ ነው፡፡ በሶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የተቸረውን ዕቅድ ሩሲያና ኢራን ከወር በፊት መደገፋቸውን አሳውቀዋል፡፡

የጋዝ ላኪ አገሮች ፎረም በኢራን መካሄድን አስመልክቶ በቴህራን የተገኙት ፑቲን፣ እንደ አሜሪካና አጋሮቿ ፕሬዚዳንት አሳድን ለመጣል ለሚዋጉ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ከሚያደርጉት የዮርዳኖስ ንጉሥ ጋር ይምክራሉ ተብሏል፡፡

ክሬምሊን በተለይ የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን በግብፅ ሲናይ በረሃ ከተከሰከሰ በኋላ በፈረንሣይ በአይኤስ የሽብር ጥቃት ከደረሰና አይኤስን ለማጥፋት የብዙ አገሮችን በር እያንኳኳች ነው፡፡ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንዶም፣ አይኤስን በመምታቱ ዙሪያ ለመምከር ሰሞኑን ወደ ሞስኮ እንደሚያመሩ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡

አሜሪካና አጋሮቿ በሶሪያ ጉዳይ ከኢራንና ከሩሲያ ተቃርነው የቆሙ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ‹‹በሶሪያ ሽብርተኞችን ለመዋጋት የአሳድን መንግሥት ማጠናከር ነው፡፡ ሰላም ከሰፈነ በኋላ ቀሪው ሥራ የሶሪያ መንግሥት ይሆናል፤›› ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡ ኢራንም የሐሳቡ ደጋፊ ናት፡፡ አያቶላህ እንደሚሉት፣ የሶሪያን መንግሥት የመቀየር ሥራ የሶሪያውያን እንጂ የአሜሪካ አይደለም፡፡ ሩሲያ አሜሪካ እየፈጠረች ያለውን ጫና ተቋቁማ እየሠራች መሆኗን አሞግሰው፣ ‹‹አሜሪካ እምነት የሚጣልባት አይደለችም›› ሲሉ አሜሪካንን አጣጥለዋል፡፡ ‹‹ከኑክሌር ድርድር ውጪ በሶሪያ ጉዳይም ሆነ በሌሎች አጀንዳዎች ከአሜሪካ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አይኖረንም፤›› ሲሉም ለኢራን ሚዲያዎች ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን ከኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሩሃኒ ጋር ውይይት ማድረጋቸውም ኢራንና ሩሲያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የጀመሩትን ጥረት ለማጠናከር ያግዛል፡፡ የኢራን ፕሬዚዳንት ሩሃኒም፣ ‹‹ሽብርን በመዋጋቱ በኩል ሩሲያና ኢራን አንዳንድ አገሮች ለታይታ እንደሚያወሩት ሳይሆን በተግባር አብረው ይሠራሉ፤›› ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...