Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሉሲ ኢንሹራንስ ብሔራዊ ባንክን ያስቀመጠውን የካፒታል መጠን አሟላሁ አለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – አዋሽ ኢንሹራንስ የተጣራ ትርፉ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን አስታወቀ

  ሉሲ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል መጠን ማሳካቱን አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ለጠቅላላ መድን ሽፋን  ዝቅተኛው የመድን ድርጅቶች የተከፈለ ካፒታል መጠን 60 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ሉሲ ኢንሹራንስ ይህንን መጠን 75 ሚሊዮን ብር ማድረሱን ቅዳሜ፣ ህዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በደሳለኝ ሆቴል ባደረገው የባለአክሲዮኖች 5ኛ መደበኛና 4ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አስታውቋል፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ ካቻምና ባወጣው መመርያ መሠረት አዲስ የሚቋቋሙ መድን ድርጅቶች የተከፈለ ዝቅተኛው ካፒታላቸው ከሰባት ሚሊዮን ብር ወደ 75 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል ማዘዙ ይታወሳል፡፡

  ኩባንያው አቻምና ያስመዘገበው የተከፈለ ካፒታል 15 ሚሊዮን ብር እንደነበረ የገለጹት የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባይነህ ከበደ፣ ‹‹የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁለት ታላላቅ ስኬቶች የተለየ ዓመት ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ ኩባንያው ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡንም አክለዋል፡፡

  እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኩባንያው አዲስ እንደመሆኑ የሁለትና የሦስት ዓመታት ኪሳራ ሊያስመዘግብ ይችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው ወዲያው ወደ ገበያ በመግባት ተወዳዳሪ ለመሆን በመብቃቱ ትርፋማ ሊሆን ችሏል፡፡

  ሉሲ ኢንሹራንስ የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ ካሰባሰባቸው 17 ኩባንያዎች አንዱ ለመሆን የበቃው በቅርቡ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው በጠቅላላው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 5.2 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፣ 57 ሚሊዮኑን ሉሲ ኢንሹራንስ በማስመዝገብ 0.4 በመቶ የነበረውን የገበያ ድርሻውን ወደ 1.1 በመቶ ማሳደግ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በ2006 የበጀት ዓመት 55.1 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ካስመዘገበው የ42,663,064.40 ብር ገቢ አኳያ የ14,343,836 ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡

  ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 4,610 ፖሊሲዎች በተለያዩ የዋስትና ዓይነቶች የሸጠ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው 3,144 መጠን ጋር ሲነጻጸር የ1,466 ብልጫ አሳይቷል፡፡ ለተለያዩ የዋስትና ዓይነቶችም 14,828,171,361.40 ብር የዋስትና ሽፋን ሰጥቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለሠራተኛ ጉዳት ካሳ የተከፈለው 5.3 ቢሊዮን ብር አብላጫውን ይዟል፡፡ ለሞተር 2.4 ቢሊዮን ብር፣ ለማሪን 1.8 ቢሊዮን ብር፣ ለገንዘብ ዋስትና አንድ ቢሊዮን ብር፣ ለጠቅላላ አደጋ ግማሽ ቢሊዮን ብር፣ ለእሳትና ተዛማጅ አደጋዎች 1.6 ቢሊዮን ብር የመድን ሽፋን መስጠቱ ተገልጿል፡፡ ኢንሹራንሱ 40,143,352.99 ብር የተጣራ የአረቦን ገቢ ሲያገኝ፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ13,251,535 ብር ዕድገት እንዳስመዘገበ ተገልጿል፡፡

  የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከኢንሹራንስ ቢዝነስ ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ዕድገቱ ለኢንዱስትሪው የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የመድን ሽፋን በመስጠት ገበያውን እንደሚያሰፋ፣ ዘርፉም ተደራሽነቱን በመጨመር እንደሚንቀሳቀስም ገልጸዋል፡፡      

  በሌላ በኩል አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ባለፈው በጀት ዓመት የተጣራ ትርፉ 64.3 ሚሊዮን ብር መድረሱን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው እንዳስታወቀው በጠቅላላ መድን ሥራ ያስመዘገበው የአረቦን ገቢ 44.3 ሚሊዮን ሲሆን፣ በሕይወት መድን 40 ሚሊዮን ብር አረቦን ለመሰብሰብ ችሏል፡፡

  ኩባንያው በጠቅላላ መድንና በሕይወት መድን ዘርፍ ከግል የመድን ኩባንያዎች የበለጠውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ የቻለበት ዓመት እንዳሳለፈ ገልጾ፣ ይህም ሆኖ ለካሳ ክፍያ 189.5 ሚሊዮን ብር ማዋሉን ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በአዲስ አበባ ከኡራኤል ወደ ቦሌ በሚወስደው አካባቢ ባለሰባት ፎቅ ሕንፃ ከመግዛት በተጨማሪ በቃሊቲ አካባቢ ሌላ ሕንፃ ለመሥራት የሚያስችለውን ቦታ መግዛቱንም አስታውቋል፡፡ በጠቅላላው በአሁኑ ወቅት 39 ያህል ቅርንጫፎችን እያንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉን 118 ሚሊዮን ብር ያደረሰው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በአሁኑ ወቅት ከ448 በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች