የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2008 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት፣ በመንግሥት ላይ ከ172.6 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው በተጠረጠሩ አካላት ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ምርመራው እየተካሄደ ካለባቸው አካላት መካከል ጥቂት ግለሰቦች ከክፍለ ከተማና ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር፣ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በድርጅት ስም የተከራዩትን ቤት በሁከት ይወገድልኝ ጥያቄ ካርታ በማውጣት፣ 6,263 ካሬ ሜትር (ግምቱ ከ78.6 ሚሊዮን ብር በላይ) የሆነ ቦታን የግል በማድረግ ከተፈጸመ ወንጀል ጋር የተያያዘው ይገኝበታል፡፡
በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሕንፃ ግንባታ ሥራዎች፣ የማሽነሪ ግዥና ተከላ ሥራ ከሕግና ከመመርያ ውጪ በመፈጸሙ፣ በመንግሥት ላይ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱ በተሰጠ ጥቆማ ኮሚሽኑ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲም እንደዚሁ የኤችአይቪ መመርመሪያ መሣሪያ ግዥ ላይ ከሕግ ውጪ የተወሰኑ አቅራቢዎችን በማሳተፍና ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ፣ በመንግሥት ላይ የ20 ሚሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ አምስት የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ላይ ኮሚሽኑ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡
እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 እየተሠራ ላለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለ 11 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ የማሽነሪና የግንባታ ዕቃ ማስቀመጫ ቦታ ለኮንስትራክሽን ድርጅቱ በሊዝ መሰጠት ሲገባው በነፃ በመፈቀዱ፣ መንግሥት ከሊዝ ማግኘት የሚገባውን 22 ሚሊዮን ብር በማጣቱ ጉዳዩ በኮሚሽኑ እየተመረመረ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከመካነ ሰላም – ግንደ ወይን በሚገነባ መንገድ ሥራ ላይ ሲጂጂሲ ከተባለ የቻይና ድርጅት ጋር ከተደረገው የኮንትራት ስምምነት ውጪ፣ ያላግባብ 12 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል በሚል በቀረበ ጥቆማ ላይ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ እያካሄደ ከሚገኝባቸው ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡
የምርመራውና የማስረጃ ማሰባሰቡ ሥራ እንደተጠናቀቀ ክስ እንደሚመሠረትና ጥፋተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ፣ ኮሚሽኑ ንብረት የማስመለሱን ተግባር እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡