– ድርቁ ተጠናክሮ ከቀጠለ በዕቅዱ መሠረት ግዥ ላይፈጸም ይችላል
መንግሥት ለ2008 ምርት ዘመን ካቀደው አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ፣ 443 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ግዥ ፈጸመ፡፡ በሁለተኛ ዙር የወጣው 309 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የጨረታ ውጤት በሚቀጥለው ሳምንት መጀመርያ ውሳኔ ያገኛል፡፡
የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የክልሎችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በምርት ዘመኑ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ አስታውቆ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት በመጀመርያው ዙር ጨረታ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ጨረታ ቢያወጣም፣ በተለይ ዩርያ ለማቅረብ የተወዳደሩ ኩባንያዎች ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርት ባለማሟላታቸው 157 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ግዥ ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡
በሁለተኛው ዙር ጨረታ ይህ ተካቶ 309 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም ጨረታ ወጥቷል፡፡ ጨረታው ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የተከፈተ ሲሆን፣ አሥር ዓለም አቀፍ አቅራቢዎች ተወዳድረዋል፡፡
ጨረታውን ያወጣው የግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ፣ የጨረታውን ውጤት ገምግሞ ለብሔራዊ ማዳበሪያ ግዥ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
ብሔራዊ ማዳበሪያ ግዥ ኮሚቴ በግብርና ሚኒስቴር የሚመራ ሲሆን፣ በኮሚቴው ውስጥ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ይገኙበታል፡፡
ይህ ኮሚቴ በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ተሰብስቦ ከገመገመ በኋላ፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጡበታል ተብሏል፡፡
በወጣው ሁለተኛ ዙር ጨረታ 228 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ዩርያ፣ ቀሪው 81 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ኤንፒኤስ ነው፡፡ ይህን ማዳበሪያ ለማቅረብ የተወዳደሩ ኩባንያዎች ለዩርያ በአንድ ቶን 300 ዶላር፣ ለኤንፒኤስ 400 ዶላር ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ግዥው በኮሚቴው ከታመነበት ለምርት ዘመኑ 752 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባት ይጀምራል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ በየነ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዳበሪያውን በአዲሱ ባቡር ወደ አገር ለማስገባት ታቅዷል፡፡
ከስድስት ወራት በኋላ በይፋ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውና በአሁኑ ወቅት የሙከራ ሥራ የጀመረው ባቡር እስከ ወለንጪቲ (መርመርሳ) ድረስ ያጓጉዛል፡፡ አቶ በየነ እንደገለጹት፣ የኢንተርፕራይዙ የባለሙያዎች ቡድን ሰሞኑን በሥፍራው ተገኝቶ ቅኝት አካሂዷል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች መንግሥት አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለመግዛት ቢያቅድም፣ የተከሰተው ድርቅ የእርሻ ሥራን የማስተጓጎል አቅም ያለው በመሆኑ ዕቅዱን እንደገና ሊያጤነው ይችላል ይላሉ፡፡
ምክንያቱም የኤልኒኖ ክስተት በአገሪቱ ያስከተለው ድርቅ ከ30 ዓመታት በፊት በ1977 ዓ.ም. ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተመሳሳይነት ያለውና ጠንካራም በመሆኑ፣ በእርሻ ሥራ ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ የጎላ ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡
የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው እስካሁን የሰጠው እስከ ጥር ድረስ ያለውን ትንበያ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የኤልኒኖ ክስተት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
‹‹በቀጣይ የበልግ ትንበያ የምናወጣ ቢሆንም ከአራት ወራት በላይ ያለውን የአየር ሁኔታ ለመተንበይ ያስቸግራል፤›› በማለት አቶ ዱላ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኤልኒኖ ክስተት ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ የእርሻ ሥራ በሰፊው ማካሄድ ላይ እንቅፋት ስለሚሆን ማዳበሪያ በብዛት መግዛት አስፈላጊ ላይሆን ይችላል በማለት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች መንግሥት በዕቅዱ መሠረት አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዥ መፈጸም አዋጭ ላይሆንለት እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል፡፡