የዓለም ባንክ ኅዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ጥናታዊ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለፉት አሥር ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገትና ፍጥነት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ያስችላሉ ያላቸውን ሦስት የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ይፋ አደረገ፡፡
“Ethiopia’s Great Run: The Growth Acceleration and How to Pace It” በሚል ርዕስ ባወጣው ባለ 166 ገጽ ሪፖርት አገሪቱ ላለፉት አሥር ዓመታት አስደናቂ ዕድገት ማስመዝገቧን ይገልጻል፡፡
ላለፉት አሥር ዓመታት በአማካይ በዓመት ያስመዘገበችው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 10.9 በመቶ ከሌሎች ታዳጊ አገሮችና ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የላቀ ነው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂ ልዩ የሚያደርገው በግብርና ልማት ላይ ትኩረት ያደረገና በጠንካራ የመንግሥት የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት የተመራ መሆኑን የዓለም ባንክ ሪፖርት ይገልጻል፡፡
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በርካታ አገሮች የሄዱበትና በኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚመከረው ከግብርና ልማት ወደ ማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪያላይዜሽን መሆኑን የሚያስታውሰው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂ ግን ከዚህ የተለየ ነው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ወሳኝ የሆነውን የማኑፋክቸሪንግና የኢንዱስትሪያላይዜሽን ዘርፍ በመዝለል፣ ከግብርና ወደ ኮንስትራክሽንና የአገልግሎት ዘርፍ መሸጋገሩን ያስረዳል፡፡
አጠቃላይ የዕድገቱ መገለጫዎች መንግሥት በግብርና፣ በኃይል አቅርቦት፣ በትራንስፖርት፣ በኮሙዩኒኬሽንና በማኅበራዊ ዘርፎች ያደረጋቸው ኢንቨስትመንቶች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
ይህ የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን ዕውን ለማድረግ የመከላከያ በጀት እንዲቀንስ መደረጉ፣ የመንግሥት የበጀት ጫና እንዲቀንስ ማድረጉን ይገልጻል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀጣጠል የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1992 ቢሆንም፣ ከ2004 በኋላ ደግሞ ፍጥነቱን ጨምሯል፡፡ በመሆኑም የዕድሜ ጣሪያ መሻሻሉንና የሕፃናትና የእናቶች ሞት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል፤›› በማለት ላርስ ክርስቲያን ሙለር በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስትና የሪፖርቱ አዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
የዚህን አስገራሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ማዕቀፉ ላይ ማሻሻያ ልታደርግ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
የመጀመሪያው የፖሊሲ ማሻሻያ ቀጣይ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ምንጭ የማይዋዥቅ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ፣ በተለይም በፋይናንስ ረገድ በአገር ውስጥ ምንጭ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ሪፖርቱ ምክረ ሐሳቡን ያቀርባል፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የታክስ ገቢን ማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ በዚህ የመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሳተፍ ማበረታታት፣ እንዲሁም የመንግሥት የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ ሪፖርቱ ያስገነዝባል፡፡
ሁለተኛው የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ የግሉን ዘርፍ የፋይናንስ ፍላጐት ማሟላትና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ሦስተኛው የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ደግሞ መዋቅራዊ ማሻሻያ በማድረግ ያልተነኩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕምቅ ሀብቶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን የጅምላ ንግድ ዘርፉን ክፍት ማድረጓን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ያስመዘገበችውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችንም ለምሳሌ የሎጂስቲክስና የፋይናንስ ዘርፎችን ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የዓለም ባንክ ያስቀመጣቸውን የመጀመሪያ ሁለት የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች እንደሚቀበሉ ይገልጻሉ፡፡
የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ በገቢ ግብር ዘርፍ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ተግባራዊ ዕርምጃ ከመጀመራቸውም በላይ አሁን፣ ያለውን የባንኮች የተቀማጭ ሒሳብ ወለድ የማሻሻል ዕቅድ እንዳላቸውም ያስረዳሉ፡፡
የግሉ ዘርፍ የብድር አቅርቦትን በማሟላት ረገድም ሰፊ እንቅስቃሴ በልማት ባንክ በኩል እንደሚደረግ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ የዓለም ባንክም ሆነ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ባንኮች ላይ የተጣለው የ27 በመቶ ግዴታ የቦንድ ግዥ እንዲነሳ የሚቀርቡትን ጥያቄ አይቀበሉትም፡፡ ሦስተኛው ምክረ ሐሳብ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡