Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት ይከበር!

ሕዝብ ስለአገሩ አጠቃላይ ሁኔታዎች መረጃ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ሕዝብ የአገሩን የዕለት ሁኔታ (ውሎና አዳርን በተመለከተ) ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ቢኖርበትም፣ በአሁኑ ጊዜ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ከምንጩ በማግኘት ለማሠራጨት ከፍተኛ የሆነ ችግር አለ፡፡ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት የመረጃ ፍሰት ባለመኖሩ ምክንያት የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት እየተከበረ አይደለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ሙስናና የፍትሕ መስተጓጎል እየተበራከተ ነው፡፡ ግልጽና ለሕዝብ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ለመገንባትም መሰናክሉ በዝቷል፡፡ ይህ ችግር ፈጣን መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የፕሬስ ነፃነት ተደንግጓል፡፡ ዜጎችም የዚህ ነፃነት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ዋስትና ተሰጥቷል፡፡ ይህንን የሚያስፈጽመው የፕሬስና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ከነችግሮቹም ቢሆን በ2000 ዓ.ም. ወጥቷል፡፡ በተለይ ከፕሬስ ጋር ተደባልቆ የወጣውን መረጃ ነፃነት ተግባራዊ ለማድረግ፣ አሁንም ከስምንት ዓመታት በኋላ በዝግጅት ላይ ያሉ ጉዳዮች አሉ መባሉ ትልቅ የአገር ድክመት ነው፡፡ ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው፣ ዛሬም መረጃ የማግኘት መብትን እየተጋፉ ነው፡፡ የፕሬስና የመረጃ ነፃነት አዋጁ ሲወጣ መንግሥታዊ ተቋማት የመረጃ ቋት (Data Base) ለማዘጋጀት የሦስት ዓመታት ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይህ ሥራ በ2003 ዓ.ም. ተጠናቆ አዋጁ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ይውላል ቢባልም፣ አሁንም ከአምስት ዓመታት በኋላ ብዙዎቹ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የተደራጀ መረጃ የላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ እየተጎዳ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥታዊ ተቋማት ለሚዲያ ተገቢውን መረጃ እንዲሰጡ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ ለሚዲያ  በአግባቡ መረጃ የሚሰጡ ተቋማት ያሉትን ያህል ችግር ያለባቸው መኖራቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከተፈለገ የመንግሥት በር ክፍት መሆን አለበት ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ለሕዝቡ ተስፋ የሰነቀው ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል፣ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ዘንድ ሰርፆ ባለመግባቱ የመረጃ ድርቅ ተፈጥሯል፡፡ የመረጃ ድርቅ ባለበት ደግሞ የሚኖረው ውዥንብር ብቻ ነው፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት መረጃ የመስጠት ባህል በሌለበት አገር ውስጥ፣ ድርቅን የመሰሉ አደገኛ ችግሮች ሲያጋጥሙ መረጃው አዝጋሚ ይሆናል፡፡ ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት አለው ሲባል፣ የዚያኑ ያህል የመረጃ ምንጮቹ መብዛት አለባቸው፡፡ ከአንድ አቅጣጫ የሚንቆረቆር መረጃን አለ ከማለት ይልቅ ዝም ማለት ይቀላል፡፡ አማራጭ ተብለው ከሚጠቀሱ የመረጃ ምንጮች መካከል አንዱ የግሉ ሚዲያ ነው፡፡ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ብዙዎቹ የመንግሥት ተቋማት በራቸው ለግሉ ሚዲያ ክፍት አይደለም፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት ከሆኑት በስተቀር ለግሉ ሚዲያ መረጃ ለመስጠት ያለው ፍላጎት ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ የግሉን ሚዲያ እንደ ጠላት ከሚያዩት ጀምሮ ፋይዳው የማይገባቸው ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የግሉ ሚዲያ የመረጃ ደሃ እየሆነ፣ ሕዝብም መረጃ የማግኘት መብቱ ተደፍጥጧል ማለት ይቻላል፡፡

የአንድ ሚዲያ ዘገባ ትክክለኛ፣ ተዓማኒ፣ ሚዛናዊና ወቅታዊ እንዲሆን ሲፈለግ የሚመለከታቸው አካላት ትብብር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ በእጃቸው ላይ ያለ መረጃን አንቀው የሚይዙ መንግሥታዊ ተቋማት ትብብር ሲጠፋ በመረጃ አሰባሰብ፣ ጥንቅርና አዘጋገብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጠራል፡፡ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባ እንዲኖር ሲፈለግ የሁሉም ወገኖች ኃላፊነትና ተሳትፎ መኖር የግድ ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት ሳይወጡ በወጡ ዘገባዎች ላይ ጣት መቀሰርና ማስፈራራት የብዙዎቹ ተቋማት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ የሕዝብን መረጃ የማግኘት መብት እየተጋፉ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳይኖር ማድረግ በቃህ መባል አለበት፡፡

መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ለሕዝቡ በቂ መረጃ ለማድረስ፣ ሚዲያ የማይተካ ሚና አለው ሲል ተደምጧል፡፡ ይህ በተግባር ታይቶ የግሉን ሚዲያ ቢያካትት መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም ዜጎች ትክክለኛ መረጃ በማግኘት በመንግሥት አሠራሮች ላይ ለሚያነሱዋቸው ቅሬታዎችና አስተያየቶች ጥሩ ግብዓት ይሆናል፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን የሚፈለገው የመረጃ ፍሰት በአግባቡ ይከናወናል ወይ የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ምላሽ የሚሆነው ደግሞ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት እንቢተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የተደራጀ የመረጃ ቋት ስለሌላቸው ፈጣን ምላሽ ማግኘት አይቻልም፡፡ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችንና ሰነዶችን የያዙ የሥራ ኃላፊዎች በሥልጠናና በስብሰባ ሰበብ አይገኙም፡፡ በየተቋማቱ የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች  በአብዛኛው የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎች ተረድተው ምላሽ የመስጠት አቅማቸው ውስን ነው፡፡ ብዙዎቹ እንኳን መረጃን አደራጅተው ሊያሠራጩ ቀርቶ ተቋማቶቻቸውን አያውቋቸውም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ከባቢ ውስጥ ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ እንዴት ይረጋገጥ?

በሥራ ላይ ባለው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ የሕዝብ ጥቅምን የሚነኩ በመንግሥት እጅ ያሉ መረጃዎች ሳይዘገዩና ገደብ ሳይደረግባቸው ለሕዝብ መቅረብ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ እዚህ ላይ ምንም እንኳ አሻሚና ሰፊ ትርጉም የሚሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች አዋጁ ውስጥ ቢካተቱም፣ መንግሥት ከብሔራዊ ደኅንነትና ከሕዝብ ጥቅም ጋር በተገናኘ ገደብ ሊደረግ እንደሚችል ቢደነግግም፣ ነገር ግን በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች ያለምንም ክልከላ ወቅታቸውን ጠብቀው መቅረብ አለባቸው ተብሎ በማያሻማ ሁኔታ ተብራርቷል፡፡ እንግዲህ ይህ መብት ነው ራሳቸውን ባነገሡ ግለሰቦች እየተደፈጠጠ ያለው፡፡ መረጃዎች ሳይዛቡ በትክክል እንዲቀርቡ መንግሥታዊ ተቋማት በራቸውን ክፍት ማድረግ ከሌለባቸው ማን ነው የሚወቀሰው? ማን ነው የሚከሰሰው? ይኼ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ መረጃን በማዛባት ተብሎ የግሉ ሚዲያ ለብቻው ሲቀጠቀጥ ግን ማንም አይሰማውም፡፡ የግብር ከፋዩ ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብትም ይጣሳል፡፡ ይኼ አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል፡፡

የመረጃ ነፃነት አዋጁን የሚቃረኑ በርካታ ተግባራት በአደባባይ ይታያሉ፡፡ ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር የሚጋጩ ተግባራት ደግሞ የመረጃ ፍሰቱን ገድበውታል፡፡ መንግሥት ይህንን የግልጽነትና የተጠያቂነት ጠላት የሆነ አሠራር ከሥር መሠረቱ ሊንደው ይገባል፡፡ ለሕዝብ መድረስ ያለበት መረጃ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይሠራጭ፡፡ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በግልጽ መግለጫ ይስጡ፡፡ በራቸው ክፍት ይሁን፡፡ የፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግ፣ የፍርድ ቤቶችና የመሳሰሉት አሠራርን የሚመለከት መረጃ ግልጽ ይደረግ፡፡ ፓርላማው የመረጃ ነፃነት አዋጁ በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምር የሚመለከታቸውን ሁሉ ያስገድድ፡፡ ሕዝብ የትኛውንም ዓይነት የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ኃላፊነቱን መወጣት ካቃተው ስለግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት ይከበር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...