- 93 ሔክታር መሬት ከነዋሪዎች ነፃ ሊደረግ ነው
ለፋብሪካ ግንባታዎች ሰፋፊ የቦታ ጥያቄዎችን መቀበል ያቆመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ግንባታ ለማካሄድ ዕቅድ ያላቸው ኩባንያዎች በጋራ የሚስተናገዱበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት 93 ሔክታር መሬት ፈቀደ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታውን በባለቤትነት የሚያካሂደው በቅርቡ የተቋቋመው፣ የአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን ነው፡፡
የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ያብባል አዲስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ የመጀመርያውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ‹‹በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ዲዛይኑን ከሚሠራ አማካሪ ድርጅት ጋር እንፈራረማለን፤›› ሲሉ አቶ ያብባል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገነባው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ገላን በራ አካባቢ ሲሆን፣ የክፍለ ከተማው ከተማ ማደስና መሬት ባንክ ጽሕፈት ቤት ለግንባታው ከተፈቀደው ቦታ ላይ ከሚነሱ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ከተማ ማደስና መሬት ባንክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልዱ ይታገሱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተፈቀደው 93 ሔክታር መሬት ላይ ይነሳሉ ተብለው ከሚገመቱ 60 አባወራዎች ጋር ለመነጋገርና መረጃ ለማሰባሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እያለማ ለኢንቨስተሮች እንዲያቀርብ፣ በ3.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽንን አቋቁሟል፡፡
የከተማው የመሬት ሀብት እያነሰ በመሄዱ ሰፋፊ የቦታ ጥያቄዎችን በተናጠል ከማስተናገድ ይልቅ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ አልምቶ ለኢንቨስተሮች ማቅረብ አማራጭ ተደርጎ መያዙ ታውቋል፡፡
በቅርቡ የፀደቀው የአዲስ አበባ ከተማ አሥረኛው ማስተር ፕላን ባቀረበው ሐሳብ መሠረት በአቃቂ ቃሊቲ፣ በቦሌና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች ሦስት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የመገንባት ዕቅድ አለ፡፡
ነገር ግን ካቢኔው ያፀደቀው አንዱን በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ በአቃቂ ቃሊቲ ፕሮጀክት ላይ ትኩረት ማድረጉን አቶ ያብባል አስረድተዋል፡፡