የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ዓርብ መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ አገሪቱ ወደ ቀውስ እንድትገባና አገራዊ ህልውናን የመፈታተን ጠንቅ ያጋጠመበት አንዱ ምክንያት፣ የሥልጣን ፍላጎት ለጥቅም ቡድኖች መፈጠርና መሻኮት የተመቸ ሁኔታ በመፍጠሩ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩ ልዩ ችግሮች ሲያጋጥሙት እንደነበር፣ እነዚህ ችግሮችም ሳይፈቱ በመቆየታቸው ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ሲጋለጥ እንደቆየ ጠቁሟል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከልም አንደኛው መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ በርካታ ያልተከናወኑ ሥራዎች እንደነበሩ በመግለጫው ተገልጿል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እያስመረመረና በሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዳይኖር ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሙስና እየተበራከተና የሕዝብን ተጠቃሚነት ክፉኛ ሲጎዳው መቆየቱን የምክር ቤቱ መግለጫ አስረድቷል፡፡ በሙስና ሳቢያም ሕዝብ ፈጣን አገልግሎት እንዳያገኝ፣ የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ዴሞክራሲ እንዲዳከም ምክንያት መሆኑን መግለጫው አስረድቷል፡፡ ችግሩ በጊዜ ባለመፈታቱ የተነሳም የለውጥ ጉዞውን አደጋ ላይ እንደጣለና አገራዊ ህልውናን እየተፈታተነ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኢሕአዴግ እነዚህን ችግሮች በአፋጣኝ እንዳያስተካክል ካደረጉት ምክንያቶች መካከልም በድርጅቱ ውስጥ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ መዳከም፣ ሥልጣንን የግል ጥቅም ማሳደጃ መሣሪያ አድርጎ መመልከትና የመጠቀም ዝንባሌ ሲስፋፋ በመቆየቱ እንደሆነ መግለጫው አስታውሷል፡፡ በአመራሩ ውስጥ የሚንፀባረቁ የትምክህትና የጠባብነት አመለካከቶች መግነን፣ የድርጅቱንና የአገሪቱን ህልውና ክፉኛ እንደተፈታተነ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
እነዚህ ችግሮችም የከፍተኛ አመራሩ ድክመቶች መሆናቸውን ምክር ቤቱ እንደገመገመና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለተፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ዕርምጃም እንደሚወሰድ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በመግለጫው ከተካተቱት መካከል ሌላው ጉዳይ በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የተመለከተ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ ደረጃ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያሻክሩ ግጭቶች እየተስፋፉ ሲመጡ መቆየታቸውን መግለጫው አስታውሷል፡፡ የተከሰቱ ግጭቶችም በአገሪቱ ሕዝብ ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉ በመግለጫው ተካቷል፡፡ የእርስ በርስ መጠራጠሮችና አንድን ማኅበረሰብ ነጥሎ የማጥላላት ዝንባሌ መታየቱን ምክር ቤቱ እንደገመገመ አስታውቋል፡፡
ከአገሪቱ የዕድገት ደረጃዎች ጋር ያልተጣጣሙ የአሠራር ክፍተቶች መኖራቸው፣ እነዚህን ክፍተቶች ደግሞ በአግባቡና በጊዜ ባለመደፈናቸው ሳቢያ የቅሬታ ምንጭ እንደሆኑና ግጭቶች እንደተከሰቱ ተብራርቷል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሠርቶ የመኖር መብቱ እንዲከበርና ተግባራዊ እንዲሆን ኢሕአዴግ እንደሚሠራ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
ኢሕአዴግ ለፓርቲው አመራሮችና አባላት፣ ለአገሪቱ ሕዝቦች፣ ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች፣ ለወጣቶች፣ ለሴቶች፣ ለባለሀብቶችና ለንግዱ ማኅበረሰብ፣ ለምሁራን፣ ለአጋር ድርጅቶች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመከላከያ ሠራዊትና ለፀጥታ አካላት መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ በተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ላይም የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፍ ምክር ቤቱ መጠየቁ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡