Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከበሻሻ እስከ አራት ኪሎ

ከበሻሻ እስከ አራት ኪሎ

ቀን:

ማክሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት እኩለ ሌሊት እየተቃረበ እያለ የተሰማው ሰበር ዜና በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ያነጋገረ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ ተተኪያቸው ማን ይሆን የሚለው በመላ አገሪቱ ዋነኛ መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በተለይ ማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ተተኪውን የግንባሩን ሊቀመንበር ለመምረጥ ስብሰባ የተቀመጠው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለአንድ ሳምንት በመቆየቱ፣ በርካቶች በመላ ምቶችና በሴራ ንድፈ ሐሳቦች እንዲጨናነቁ አድርጓቸዋል፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ ለትንተና እስከሚያስቸግር ድረስ የተለያዩ መረጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመሰማታቸው፣ የተተኪው ማንነት ብዙዎችን ቢያሳስብ አይገርምም ነበር፡፡ ሰዎች በአካል ተገናኝተው ከሚለዋወጡት ሐሳብ ጀምሮ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የነበረው ውዝግብና ግራ መጋባት የተተኪው ማንነት ላይ ያነጣጠረም ነበር፡፡ ሰበር ዜናው ከተሰማ በኋላ ግን በርካታ ግምቶችና ትንተናዎች ፉርሽ ቢሆኑም፣ ውጤቱን በተለያዩ ስሜቶች በሚጠበቁት ዘንድ ግን መገረምን ፈጥሯል፡፡ የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እንዲሆኑ መመረጣቸው ይፋ ከሆነ በኋላ፣ በኢሕአዴግ አሠራር መሠረት ሦስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑበት የፓርላማ ሥነ ሥርዓት ብቻ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ናቸው? የት ተወለዱ? የት አደጉ?  እዚህ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ያለውን የሕይወት ታሪካቸውን ከቤተሰቦቻቸውና በቅርበት ከሚያውቋቸው ጋር በትውልድ ሥፍራቸው በመገኘት በዳዊት እንደሻውና በዳዊት ቶሎሳ የተጠናቀረውን ዘገባ ይመልከቱ፡፡ 

ከበሻሻ እስከ አራት ኪሎ

 

- Advertisement -

ልክ እንደ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ከተሞች በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን በምትገኘው የገጠር ከተማ በሻሻ ኑሮ የሰከነና የተረጋጋ ነው፡፡ ከ6,000 በላይ ለሆኑ ነዋሪዎቿ መጠለያ የሆነችው የበሻሻ ከተማ፣ በአገሪቱ እየተካሄደ ካለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ርቃ የምትገኝ ትመስላለች፡፡

የበሻሻ ከተማ ላለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የብዙኃኑን ሕይወት ቀጥፎ የበርካቶችን ንብረት ባወደመው ብጥብጥና ተቃውሞ ብዙም የተነካች አትመስልም፡፡ ሕይወት እንደ ወትሮ ቀጥሏል፡፡ ንግዱም እንደ ጦፈ ነው፡፡ ከሌሎች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተለየ ሰዎች በእርጋታ ወጥተው ቡናቸውን ሸጠው ይመለሳሉ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኘው በሻሻ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና የአገሪቱንም ሆነ የወጪ ንግዱን በዋናነት በሚያንቀሳቅሱት ቡናና ጫት የታደለች ናት፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ማኅበረሰብ ከእነዚህ ምርቶች በሚያገኘው ገቢ ነው የሚተዳደረው፡፡

በበሻሻ ወጣቶች ቀጣዩ ሀብታም የቡና ነጋዴ ለመሆን፣ መኪና ለመግዛትና ከአዲስ አበባ 497 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አጋሮ ከተማ ወጥተው ሌላ ንግድ ለመጀመር ያልማሉ፡፡

የበሻሻ ነዋሪዎች በአብዛኛው ሙስሊም ሲሆኑ፣ ልጆችም ቁርዓን እየቀሩ ያድጋሉ፡፡ ምንም እንኳን የክርስቲያንና የሙስሊም ማኅበረሰቡ ክፍሎች ተጋብተውና ተዋልደው የኖሩ ቢሆንም፣ በከተማዋ አሳዛኝ ክስተት ማጋጠሙ አይዘነጋም፡፡

በሻሻ በቡና ንግድ የታወቀች ብትሆንም ብዙዎች የሚያስታውሱት በሙስሊሙና በክርስቲያን ማኅበረሰቡ መካከል በጥቅምት 1999 ዓ.ም. ተፈጥሮ የነበረው ግጭት፣ የዚህችን ትንሽ የገጠር ከተማ ስም በተደጋጋሚ እንዲጠራ አድርጓል፡፡ በተለይ በአክራሪ ሙስሊሞች አነሳሽነት በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ በተቃጣ ጥቃት በርካቶች መሞታቸው አስከፊ ትዝታ ነው፡፡

በጊዜው የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን ካረጋጋ በኋላ ለዘመናት አብረው ከመኖር በላይ በሰላም የሚኖሩ፣ በድንገት ወደ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የገቡትን የአካባቢውን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ለማስታረቅ ዕቅድ ይነደፋል፡፡

በዚህን ጊዜ ነው ታዲያ ከስምንት ዓመታት በፊት የፌዴራል መንግሥት የዕርቀ ሰላሙ አስፈጻሚ በማድረግ፣ የ34 ዓመቱን አፍቃሬ ቴክኖሎጂ የሆኑትን ወጣት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከውጤት ጋር እንዲመለሱ ወደ አካባቢው የላከው፡፡

ይህም አጋጣሚ በወቅቱ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ወጣቱን ዓብይ፣ በተወለዱበት ሥፍራ አስታራቂ ሆነው በመሄድ ባስመዘገቡት አርኪ ውጤት ትኩረት ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡

‹‹በወቅቱ ከተደረገው ዕርቅ በኋላ በሁለቱ ማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ግጭት ቀርቶ በጠላትነት መተያየት የሚባል ነገር እንኳን የለም፤›› ሲሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዩ የ76 ዓመት አዛውንቱ አቶ ብርሃኑ ኃብተ ማርያም ጉዳዩን ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ በተፈጸመው ጥቃት ተጋላጭ የነበሩት አቶ ብርሃኑ በዕድል እንደተረፉም ይናገራሉ፡፡

‹‹ዓብይ ነበር የዕርቁ ዋነኛ ተዋናይ፤›› ሲሉ የሚናገሩት ደግሞ፣ ኢማሙ አብዱልከሪም መሐመድ ናቸው፡፡

በእርግጥም ይኼ ክስተት ነበር ዓብይ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናት የሠሩበትን ርዕስ እንዲመርጡ ያነሳሳቸው፡፡ ‹‹የማኅበረሰብ ካፒታልና በኢትዮጵያ በባህላዊ መንገድ ግጭቶችን ለመፍታት ያለው ሚና በጅማ ዞን በነበረ ሃይማኖታዊ ግጭት›› የሚል ነበር የጥናታቸው ርዕስ፡፡

ዓብይ አህመድ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ከፈነዳ በኋላ ስለተወለዱ በልጅነታቸው ‹አብዮት› በሚል መጠሪያ ነበር የሚታወቁት፡፡ በርካታ ቁጥር ካለው ቤተሰብ የተገኙት ዓብይ፣ አራት ሚስቶች ላሉዋቸው አባታቸው 13ኛ ልጅ ናቸው፡፡ ዓብይ በአካባቢያቸው የተከበሩ ሽማግሌ የሆኑትና ለበሻሻ ክሊኒኮች እንዲገነቡና የስልክ አገልግሎት ይገባ ዘንድ፣ የቡና ተክል መሬታቸውን ለመስጠት ያላቅማሙት የአህመድ አባ ፊጣ ወይም አባ ደብስ አባ ፊጣ ልጅ ናቸው፡፡

አባ ደብስ አባ ፊጣ ለአካባቢያቸው እጅግ ብዙ አስተዋፅኦዎችን ማድረጋቸውን፣ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አውቃቸዋለሁ የሚሉትን አቶ ብርሃኑን ጨምሮ በርካታ የበሻሻ ነዋሪዎች ይመሰክራሉ፡፡

የዓብይ እናት ወ/ሮ ትዝታ ወልዴ ይባላሉ፡፡ ከቡራዩ የተገኙት ወ/ሮ ትዝታ ለዓብይ አባት አራተኛ ሚስት ሲሆኑ፣ ስድስት ልጆች ወልደዋል፡፡ ዓብይ ደግሞ የመጨረሻ ልጅ ናቸው፡፡

‹‹ልጅ እያለ ቁርዓን ሲቀራ እጅግ ጎበዝ ነበር፣›› ሲሉ አቶ አህመድ ስለልጃቸው ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ሁሌም ቢሆን መማር፣ ማጥናትና ከታላላቆቹ ጋር መዋልን የሚወድ ነበር፤›› ይላሉ፡፡

ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን ዓብይ ትምህርታቸውን በበሻሻ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይከታተሉ ነበር፡፡ በሻሻ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ፣ 17 ኪሎ ሜትር ወደምትርቀው አጋሮ ከተማ ሄደው ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ከበሻሻ እስከ አራት ኪሎ

 

‹‹ዓብይ ወጣት እያለ ለጓደኞቹ ምሳሌ መሆን የሚወድ ነበር፣ እንዲያጠኑና እንዲማሩ ይገፋፋቸው ነበር፤›› ሲሉ ታላቅ እህታቸው ወ/ሮ ጥሩዬ አህመድ ያስታውሳሉ፡፡

ቡና በመሸጥ ሀብታም መሆንን ከሚያልሙት ጓደኞቻቸው ዓብይ ልዩ እንደነበሩ እህታቸው ያወሳሉ፡፡ ጓደኞቻቸው ሁሉ እንደሚሉት በትምህርት ነፃ አውጭነት በፅኑ ያምኑ የነበሩት ወጣቱ ዓብይ፣ ወደ ፖለቲካው የተቀላቀሉት በለጋ ዕድሜያቸው ነበር፡፡ ወቅቱ አገሪቱ ከደርግ አገዛዝ ተላቃ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መራሹ መንግሥት ሥልጣን ለመያዝ ዋዜማ ላይ ነበር፡፡

ለ17 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት የተሰላቹ የፖለቲካ ኃይሎችም፣ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን በጠረጴዛ ዙርያ የተቀመጡበት ወቅት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እንደ ኸርማን ኮኸን ያሉ ታዋቂ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አገሪቱ ውስጥ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማምጣት የሚደረገውን ውይይት ከጀርባ ሆነው ይደግፉ ነበር፡፡

በወቅቱ በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን በዋናነት ይወያዩ የነበሩት አሁን ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነበሩ፡፡

ሆኖም በኦሮሚያ ክልል ሰፊ ተቀባናይነት ከነበረው ኦነግ ጋር የሚደረገው ድርድር ፍሬያማ መሆን ሳይችል ሲቀር፣ እንደ ኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ያለ አማራጭ ኦሮሚያን የሚወክል ድርጅት እንዲሆን ተቋቋመ፡፡

የወቅቱ ምስክር ሆነው ያለፉ ሰዎች ልክ እንደ ሌላዎቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ አሁን ከ37,000 በላይ ነዋሪዎች ያሉባት አጋሮ ውስጥም ኦነግ ከፍተኛ ድጋፍ ነበረው ይላሉ፡፡

በዚህ ወቅት የዓብይን ቤተሰብ ቀጥተኛ ተጠቂ ያደረገ ክስተት ይፈጠራል፡፡ የዓብይ አባት ከታላቅ ልጃቸው ከአቶ ከድር አህመድ ጋር ተይዘው ይታሰራሉ፡፡ ይሁንና አባትየው ሲፈቱ አቶ ከድር ግን ይገደላል፡፡ ግድያው በፖለቲካ ቂም ተነሳስተው ሌሎች ወገኖች የፈጸሙት ድርጊት እንደሆነም ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ይናገራሉ፡፡ በጊዜው አጋሮ ለኦነግ ፅኑ መሠረቱም ነበረች፡፡

‹‹የወንድሙ መገደል ለዓብይ ሕይወት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብዬ አስባለሁ፤›› ሲል የዓብይ የልጅነት ጓደኛ አቶ ሚፍታህ ሁዲን አባ ጀበል ይናገራል፡፡ ‹‹ወጣቶች ስለነበርን አንድ ማታ ዓብይ ጠርቶኝ ትግሉን እንቀላቀል አለኝ፡፡ እውነት ለመናገር የሚለውን ለመረዳት ለእኔ እጅግ ከባድ ነበር፤››  ብሏል፡፡ ከዚያ በኋላ ዓብይ በ1982 ዓ.ም. ደርግ ከመውደቁ ከጥቂት ወራት አስቀድሞ በ15 ዓመታቸው ኦሕዴድን መቀላቀላቸውን  በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ድምፃዊ ጌትሽ ማሞ ከዓብይ ጋር ከልጅነት ጀምረው የሚተዋወቁ ሲሆን፣ ኦሕዴድን አብረው እንደተቀላቀሉ ይናገራል፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ በጣም ወጣቶች ነበርን፡፡ እኔ፣ ዓብይና አንድ ቆሚጣስ እያልን የምንጠራው ሾፌር ነበርን፤›› ሲል ቢፍቱ ኦሮሚያ የሚባለው የኦሕዴድ የሙዚቃ ቡድን አባል የነበረው ጌትሽ ያስታውሳል፡፡ ‹‹ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ጋርም እጅግ ቅርብ ነበርን፤›› የሚለው ጌትሽ፣ ዓብይ ያኔ የሬዲዮ ቴክኒሻን እንደነበሩ ያስረዳል፡፡

በፖለቲካውና በውትድርናው ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት ዓብይ ወደ ሩዋንዳ የዘመተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ሠራዊት አባል ሆነው ተልከዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ በሩዋንዳ ከ1985 ዓ.ም. እስከ 1987 ዓ.ም. ሲዘልቅ በ1987 ዓ.ም. የተመለሱት ዓብይ፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከተሠለፉት የሠራዊቱ አባላት መካከል በሬዲዮ ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያነት ነበሩበት፡፡

በውትድርናው ዓለም እስከ 2000 ዓ.ም. የቆዩት ዓብይ፣ የሻለቅነት ማዕረግ እስከ ማግኘት ደርሰዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ አባል ሆነው ሲቀርቡ አጭር የሕይወት ታሪካቸው ላይ ይኼ ማዕረግ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ዘገባዎች ደግሞ ሌተና ኮሎኔል መድረሳቸው ይነገራል፡፡

በ2000 ዓ.ም. ነበር የአገሪቱን የሳይበር ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለመው የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተቋቋመው፡፡ ባላቸው የሬዲዮ ግንኙነትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እውቀት ዓብይ ከመሥራቾቹ አንደኛው እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በኤጀንሲው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሠሩት ዓብይ፣ የለውጥ ኃይል እደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡

እስከ 2002 ዓ.ም. ዓብይ በኤጀንሲው የቆዩ ሲሆን፣ በመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት በተጠባባቂ ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ በ2002 ምርጫም ተሳትፈው አጋሮ ወረዳን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ተመርጠዋል፡፡ከበሻሻ እስከ አራት ኪሎ

 

ዓብይ ለአጋሮ ወረዳ ዕድገት ኢንቨስተሮችን በማሰባሰብ አስተዋፅኦ ያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ በሸራተን ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ጭምር እንዲዘጋጅ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በተመረጡባቸው በእነዚህ ጊዜያት በሻሻ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተሠራ ሲሆን፣ አጋሮ ደግሞ ሆስፒታል አግኝታለች፡፡

‹‹ብዙ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች ፈጽሟል፤›› ሲሉ በአጋሮ ኢንቨስተርና የሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ደበላ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ጅማና አጋሮን ለሚያገናኘው መንገድ ቃል ቢገባም እስካሁን አልተሳካም፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ መታዘብ እንደቻለው ምንም እንኳን አካባቢው በግብርና ምርቶችና በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ቢሆንም፣ ምቹ የሆኑ መንገዶች ባለመኖራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ ሰዎችን ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ‹‹አካባቢው ደካማ የመንገዶችና የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ስላለው ችግሮች ይገጥሙናል፤›› ሲሉ የጎማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሬይስ ዓሊ ይናገራሉ፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲገባለት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቢከፍልም፣ ሰባት ዓመታት ሙሉ በጥበቃ ላይ መሆኑም ይነገራል፡፡

ምንም እንኳን ዓብይ ለቴክኖሎጂ ፍላጎትና ቅርበት ቢኖራቸውም፣ በእነዚህ ጊዜያት ከሌሎቹ የምክር ቤት አባላት በተለየ ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን አብጠልጥለው በማንበብ፣ የተድበሰበሱ ሪፖርቶችን በመተቸትና የሰላ አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡

ከዚህ በመቀጠል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉት ዶ/ር ዓብይ፣ ከሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተሾሙ፡፡

በሚኒስቴሩ ለአንድ ዓመት ያህል ቢቆዩም፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲን እንደገና በማዋቀር በሚኒስቴሩ ሥር በማድረግ የኤሮ ስፔስ ኢንስቲትዩት ብለው ሰይመውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዶ/ር ዓብይ ሚኒስቴሩን በፖለቲካ ብቻ ከሚነዳ ተቋምነት ወደ ምርምር ማዕከልነት አሳድገውታል የሚሉ አሉ፡፡

ዓቢይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዋሲሁን ዓለማየሁ፣ ‹‹ዓብይ ለትምህርት ያላቸው አመለካከትና ቆራጥነት ውስጤ የቀረ ማንነታቸው ነው፤›› በማለት ያስታውሷቸዋል፡፡

አቶ ዋሲሁን እንደሚሉት በአገሪቱ ለመንግሥት ሠራተኞች የሚሰጥ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሽፕ) እንዲኖር በማድረግ፣ ሠራተኞች መማር የሚችሉበትን ዕድል ያመቻቹ ናቸው፡፡ ‹‹ሁሌም ቢሆን እንድንማርና ራሳችንን እንድናሳድግ ያበረታቱን ነበር፤›› ይላሉ አቶ ዋሲሁን፡፡

በዓብይ አህመድ በተጀመረው የትምህርት ዕድል መሠረት 1,500 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች፣ በተለያዩ አገሮች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ይላሉ፡፡ አቶ ዋሲሁን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በውጭ ቋንቋዎች ክፍል ትምህርት ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ ‹‹እኔ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቴን ስጀምር ከ3.5 በታች ካመጣሁ ደስተኛ እንደማይሆኑ ገልጸውልኝ ነበር፤›› ሲሉ አቶ ዋሲሁን ያስታውሳሉ፡፡

ዶ/ር ዓብይ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲሄዱ አቶ ዋሲሁንም ተከትለዋቸው በሚኒስቴሩ በሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርነት ተሾሙ፡፡ ‹‹በእርሳቸው አበረታችነት ተነሳስቼ 3.7 ነጥብ አምጥቼ ተመረቅሁ፤›› ይላሉ አቶ ዋሲሁን፡፡

ይሁንና የዶ/ር ዓብይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቆይታ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው መጠነ ሰፊ ተቃውሞና ብጥብጥ ምክንያት በአጭሩ ተቋጨ፡፡ በርካታ የኦሕዴድ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ወደ ክልል ሲሄዱ፣ እርሳቸውም ክልሉን ለማረጋጋት ወደ እዚያው አቀኑ፡፡

ዶ/ር ዓብይ ከሌሎች የኦሕዴድ አባላት ጋር በመተባበር በክልሉ ተንሰራፍቶ የነበረውን ተቃውሞና አመፅ ማርገብ ችለዋልም ይባልላቸዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች አሁን ኦሕዴድ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የሕዝብ ተቀባይነት ማግኘት ችሏል ይላሉ፡፡

ዶ/ር ዓብይ ከሚኒስትርነታቸው ከለቀቁ በኋላ የኦሮሚያ ክልል የከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ከሠሩ በኋላ፣ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድን በመተካት የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊም በመሆን አገልግለዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በተካሄደ የኦሕዴድ ምክር ቤት ምርጫም፣ ዶ/ር ዓብይ የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆን አቶ ለማ መገርሳን በመተካት ተመርጠዋል፡፡

ምንም እንኳን በስኬቶቻቸው የሚመሠገኑ ቢሆኑም፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲፀድቅ በምክር ቤቱ ሳይገኙ በመቅረታቸው በእጅጉ ሲተቹ ነበር፡፡ ይህም በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተንፀባርቆ ነበር፡፡

የ42 ዓመቱ ዓብይ በጋብቻ የተሳሰሩት ከወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይና ወ/ሮ ዝናሽ የተገናኙት ዓብይ ውትድርና ውስጥ በነበሩበት ወቅት ሲሆን፣ ወ/ሮ ዝናሽ የወታደራዊ የሙዚቃ ቡድን አባል ነበሩ፡፡ ዶ/ር ዓብይና ወ/ሮ ዝናሽ ሦስት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

ዶ/ር ዓብይን በቅርበት የሚያውቋቸው ለስፖርትና ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትኩረት የሚሰጡ እንደሆኑና ወደ ጂምናዝየሞች በመሄድ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ያወሳሉ፡፡ በብዛትም በአዲስ አበባ በቦዲ ዋይዝ ዌልነስና ፊትነስ ሴንተር፣ ቀጥሎም በጥላ ኸልዝ ክበብ ስፖርት ይሠሩ እንደነበር ማወቅ ተችሏል፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በመሆን የተመረጡት ዶ/ር ዓብይ፣ አቶ ኃይለ ማርያምን በመተካት ሦስተኛው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፡፡

ዶ/ር ዓብይ በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት የተከፋፈለውን ሕዝብ ወደ አንድ በማምጣት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ትልቁ የቤት ሥራ ይሆንባቸዋል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ዶ/ር ዓብይ የሚሄዱበት የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ተመስገን ብርሃኑ አንዱ ናቸው፡፡

መጋቢ ተመስገን ተቋማቸውን ሳይወክሉ በግላቸው ስለ ዶ/ር ዓብይ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ዶ/ር ዓብይ እግዚአብሔርን የሚወድ ቅንና ትሁት ሰው ሲሆን፣ ባገኘው ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል መማር የሚወድና ዕድል ሲያገኝም ቃሉን የሚያስተምር ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዶ/ር ዓብይ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ከመሆኑ በፊት የመንግሥት ሥልጣን ላይ የቆየ ነው፤›› የሚሉት መጋቢ ተመስገን፣ ‹‹ልዩ ትኩረት የማይፈልግና በሥልጣኑም የማይኩራራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከእዚያም በላይ ሕዝቡንና አገሩን የሚወድና ከበላይም ሆነ ከበታቹ ካሉ ሰዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የማይቸገር ነው፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣና ሰላም እንዲመጣ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ሁሉም ቤተ ክርስቲያኖች ሲፀልዩ ነበር ያሉት መጋቢ ተመስገን፣ አሁን እግዚብሔር ፀሎታቸውን ሰምቷል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ መጋቢው አክለውም ዶ/ር ዓብይ ብቻቸውን ለአገሪቱ ሰላም ማምጣት ስለማይችሉ፣ አብረዋቸው ያሉት ባለሥልጣናት በአንድነትና በመግባባት እንዲሠሩ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በዳዊት እንደሻውና በዳዊት ቶሎሳ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...